ያለአግባብ የተጋነነ ዋጋ የሚጨምሩና ምርት የሚደብቁ ስግብግብ ነጋዴዎችን በተመለከተ ብዙ ተብሏል። መንግሥት ተገቢውን ቁጥጥር እንዲያደርግ ብዙ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። የምርም ደግሞ መንግሥት ቁጥጥር እያደረገ ነው። ብዙ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል፤ እንደ ጥፋታቸው መጠን የታሰሩ እና ንግድ ቤቶቻቸው የተዘጉባቸው እንዳሉም ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መግለጫ ተመልክተናል። ለስግብግብ ነጋዴዎች ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
ለመሆኑ ግን መንግሥትንስ ማን ይቆጣጠረው? መንግሥት በዚህ በኩልም የሚነሱትን ቅሬታዎች ልብ ማለት አለበት። በነጋዴዎች በኩል የሚጨመሩ ዋጋዎች ብቻ ናቸው ወይ ለዜጋው የኑሮ ውድነት ፈተና የሚሆኑት? በራሱ በመንግሥት (በመንግሥት ተቋማት ማለት ነው) የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎችስ?
በቅርቡ እንደሰማነው የፓስፖርት መመዝገቢያ ክፍያ በድንገት ከሁለት ሺህ ብር ወደ አምስት ሺህ ብር ከፍ ብሏል። ይህ የተነገረው ድንገት ነው። ጭማሪ መደረጉ ካልቀረ በድንገትም ሆነ በረጅም ቀን ልዩነት የለውም ሊባል ይችላል፤ ግን ልዩነት አለው። ለምሳሌ ነገ ለመመዝገብ አስቦ የነበረ ሰው የሚዘጋጀው በሁለት ሺህ ብር ነው። ድንገት ማታ ዜና ሲያይ አምስት ሺህ ብር ሆኗል ሲባል ምን ይሰማዋል? በሁኔታው መገረም ብቻ ሳይሆን ‹‹አይ! ይቺ ሀገር!›› እያለ ይናደዳል ማለት ነው። ለሥነ ልቦና እንኳን ሲባል በረጅም ቀን ማዘጋጀትና በድንገት መንገር ይለያያል። ያልተዘጋጀ ሰው ያላሰበውን ሦስት ሺህ ብር በድንገት ለመክፈል ይገደዳል ማለት ነው።
ፓስፖርት ከሚያወጡ ሰዎች ውስጥ ወደ ውጭ ሀገር ለሥራ መሄድ የሚፈልጉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ደግሞም አብዛኞቹ እንደዚያ አይነት ሆነውም አይተናል። ስለዚህ ለእነዚህ ሰዎች በድንገት ሦስት ሺህ ብር መጨመር አግባብ አይደለም። ሦስት ሺህ ብር ምናልባትም በረጅም ጊዜ አጠራቅመው የሚያገኙት እንጂ ድንገት የሚያገኙት አይሆንም። በተለይም በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ብር በቀላሉ ማግኘት አይችሉም። እንደ ከተማ ቦታ የአገልግሎት ሥራዎች የሉም፤ ብር የሚገኘው ምርት በመሸጥ ነው። ለአንድ ጉዳይ አንድ የእንስሳ አይነት ወይም እህል ይሸጣል። በዚህ ሁኔታ ነው ለአንድ ዓላማ ብር የሚያስቀምጡት።
እነዚህን ዜጎች በተመለከተ ሌላም ችግር አለ። የሚመጡት ሀገር አቋርጠው ሊሆን ይችላል። በሁሉም የሀገራችን ክፍል ኢንተርኔት አለ ማለት አይቻልም። ኢንተርኔት የማይሰራባቸው አካባቢዎች አሉ። ወዲህ ደግሞ ኢንተርኔት ቢሠራ እንኳን በ‹‹ኦንላይን›› ለመመዝገብ የሚያስችል አሠራር የለም። ኢንተርኔት ቤቶች አይኖሩም። በቀላሉ በስልካቸው ለመመዝገብ ደግሞ ልምዱ አይኖራቸውም። ስለዚህ በእነዚህ ምክንያቶች ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ይገደዳሉ።
በ‹‹ኦንላይን›› ወይም በአካል ለመመዝገብ አዲስ አበባ መጥተው እንዳደሩ በድንገት ሦስት ሺህ ብር ተጨምሮ አገኙት እንበል። እነዚህ ሰዎች ሲመጡ የሚያስፈልጉትን ወጪዎች አስልተው ነው የሚሆነው። የተትረፈረፈ ብር አይኖራቸውም። ስለዚህ ተጉላልተው፣ ያወጡት ወጪ ባክኖ ይመለሳሉ ማለት ነው። ምናልባትም የቻሉት ተጨማሪ ገንዘብ አስልከው ሊመዘገቡ ይችላሉ። ቢያንስ ቢያንስ የሁለትና ሦስት ወራት ጊዜ ቢሰጥ ኖሮ፣ ‹‹ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ይህን ያህል ይሆናል…›› ቢባል ግን አስበውበት ይዘጋጁ ነበር ማለት ነው።
ነጋዴዎች የንግድ ግርግር ለመፍጠር እንደ ምክንያት ያደረጉት መንግሥት ያወጣውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የብሔራዊ ባንክ ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ላይ ማሻሻያ በማድረጉ ነው። ከመደረጉ በፊት አስቀድመው የገዙትን ዕቃ ነው ልክ ከጭማሪው በኋላ የተደረገ አስመስለው የሚሸጡት። ይህ ‹‹ስግብግብነት ነው!›› ብለን ወቅሰናል።
ዳሩ ግን መንግሥትም ከማሻሻያው በፊት በተገዙ ዕቃዎች ላይ ታክስ እያደረገ ነው። ባለፈው አርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በሰጡት መግለጫ፤ ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በኋለ ሰነዳቸው በጉምሩክ ተቀባይነት ያገኙ ዕቃዎች በአዲሱ የውጭ የምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት በየዕለቱ በሚኖረው የምንዛሬ ተመን ቀረጥና ታክስ እንዲከፍሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
እነዚህን ዕቃዎች ለማምጣት የሚያስፈልገው ሂደት ከሐምሌ 22 ቀን በፊት ነው የሚጠናቀቅ ሊሆንም ይችላል። ዕቃዎቹም ምናልባትም ቀደም ብለው የተገዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ በአሁኑ የምንዛሪ ተመን ማስከፈል ምን ያህል አግባብ ነው? ትንሽ የእፎይታ ጊዜ መስጠት አይቻልም ነበር ወይ? በዚህ ፍጥነት በአዲሱ የምንዛሬ ተመን ማድረግ በህብረተሰቡ ላይ የኑሮ ውድነትን ማባባስ አይሆንም ወይ? መንግሥት ተጎድቶስ ቢሆን ነጋዴዎችን ለማረጋጋት ሲባል ትንሽ ጊዜ መስጠት አይቻልም ነበር ወይ?
በዚህ አካሄድ ከነጋዴው ይልቅ ሸማቹ ህብረተሰብ የበለጠ ይጎዳል ማለት ነው። ነጋዴው ‹‹ታክስ ተጨምሮብኛል›› በሚል ሰበብ ዋጋ ይጨምራል። ለማትረፍ የሚያስችለውን ደረጃ እስከሚያገኝ ድረስ ይጨምራል። ስለዚህ ታክስ መጨመር በተዘዋዋሪ ሕብረተሰቡ በሚሸምተው ምርት ላይ ዋጋ መጨመር ማለት ነው። ነጋዴውን ‹‹አትጨምር›› ማለት ብቻውን ለውጥ አያመጣም። ምንም እንኳን የድሃ ሀገር መንግሥት መሆኑን ብናውቅም የታክስ ጭማሪ ግን በአግባቡ ቢሆን ነጋዴዎችንም በሙሉ አፍ ለመውቀስ ያመቻል።
በነገራችን ላይ በብዙ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ክፍያ ይከፈላል። ምንም እንኳን ክፍያው ከፍተኛ ነው ባይባልም እነዚህ ክፍያዎች ግን ከግብር ውጭ የሚከፈሉ ናቸው። ነጋዴው ግብር ይከፍላል። የመንግሥት ሠራተኛው የወር ደሞዙን ከታክስ ጋር ይከፍላል። ብዙ የሥራ ዘርፎች ግብር አላቸው። ይህም ሆኖ ግን አንዳንድ አገልግሎቶችን ለማግኘት (ለምሳሌ ከመታወቂያ ጀምሮ) ክፍያዎች አሉ። የአገልግሎት ክፍያዎችን ማስቀረት ባይቻል እንኳን የታክስ ጭማሪ ግን የምርት ውድነትን ያባብሳል።
አንዳንዴ መንግሥትም ራሱ ስግብግብነት ይታይበታል። ለምሳሌ፤ የንባብ ባህል የተዳከመ ነው በሚባልባት ሀገር ውስጥ የወረቀትና የህትመት ሥራ በታክስ ምክንያት እየቆመ ነው፤ መጻሕፍት ማሳተም የማይቻል እየሆነ ነው። መጽሐፉ ከሚሸጥበት ዋጋ የሚታተምበት ዋጋ ሊበልጥ ነው። ሁሉም ነገር ከታክስ ነፃ ይሁን ማለት አይቻልም፤ መንግሥትም ሀገርና ሕዝብን የሚያስተዳድረው በእነዚህ ገቢዎች ነው። ዳሩ ግን መቀነስ እንኳን ቢቀር በየጊዜው መጨመርና አንዳንድ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች ላይ ተገቢውን ቅናሽ አለማድረግ ነጋዴውንም እንዲያጭበረብር ማገዝ ነው።
ልድገመው! መንግሥት ሀገርና ሕዝብ የሚያስተዳድረው ከታክስ ከሚገኝ ገቢ እና ግብር መሆኑን እናውቃለን። ዳሩ ግን የታክስ ጭማሪ ማድረግ ዞሮ ዞሮ የሚያስተዳድረውን ሕዝብ ነው የሚጎዳው፤ ታክስ በጨመረ ቁጥር ነጋዴዎች ዋጋ ይጨምራሉ። ስለዚህ መንግሥት ይህን ነገር ልብ ይበለው! ነጋዴዎችን ብቻ ሳይሆን ራሱንም ይቆጣጠር!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም