አሸንዳ፤ አሸንዳዬ!

የአሸንዳ በዓል በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የሚከበር የልጃገረዶች በዓል ነው። ልክ በመሀል የሀገሪቱ ክፍል እንደሚከበረው የእንስት ኮረዶቹ እንቁጣጣሽ ወይም አበባየሆሽ፣ የኦሮሞዎች ሽኖዬ፣ የጉራጌ ልጃገረዶች በመስቀል መዳረሻ እንደሚያከብሩት አዳብና ዓይነት በዓል ነው።

ተባዕት ብላቴኖች ደግሞ በዚሁ በነሐሴ ወር አጋማሽ ቡሔ ወይም ሆያ ሆዬን ያከብራሉ ይጨፍራሉ። አሸንዳ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ቢከበር እና አከባበሩ ተመሳሳይ ቢሆንም፤ በተለያዩ ስያሜዎች ይጠራል። አሸንዳ በአማራ ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በሚል ስያሜዎች ይጠራል። በትግራይ አሸንዳ፣ በአክሱም ዓይኒ ዋሪ፣ ማሪያ በሚል ስያሜዎች ይጠሩታል።

በዓሉ ስያሜውን ያገኘው፤ ልጃገረዶቹ ወገባቸው ላይ አስረው እንደቀሚስ ከሚያገለድሙት ቄጠማ ነው። በሦስት አቅጣጫ ከላይ እስከ ታች ቦይ የተዘረጋለት ለየት ያለ የቄጠማ ዓይነት ነው። የሚገርመው የአሸንዳ ቄጠማም በቅሎ የሚደርሰው እንደዚሁ በብዛት በነሐሴ አጋማሽ ወቅት በመሆኑ ከበዓሉ ጋር ቀጠሮ ያለው ይመስላል።

‹‹የነሐሴ ወርና የአሸንዳ ጭፈራ ቀጠሮ እንዳለቸው አሸንዳ ሲደራ …›› እንደአጋጣሚው ተመስለን እንድንልም ያምረናል።

ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት አሸንዳ ቃሉ የትግርኛ ሲሆን ፍቺው ርጥብ፣ ገሣ የትግሬ ልጃገረዶች በበዓል ቀን ያሸርቡበታል (ገጽ 144) ሲለው፤ የዊኪዲፒያ ድረ ገፅ ደግሞ ቃሉ በአማርኛ አሸንድየ እንደሚባል ያሳያል። በዓሉ በዋግኽምራ ሻደይ በሚል ስያሜ ይጠራል። ሻደይ በህምጥኛ ቋንቋ ‹‹ለምለም አረንጓዴ›› የሚል ፍቺ አለው።

በእንደርታ እና ተንቤን ዙሪያ በዓሉ አሸንዳ፣ በላስታ ላሊበላ እና ጐንደር አሸንድዬ ሲሉት በአክሱምና ዙሪያዋ ዓይኒ ዋሪ ፣ ዋግ ሕምራ ዞን ሻዳይ ፣በራያ ቆቦ ደግሞ ሶለል በሚል ይጠሩታል። ሰላም ባህለይ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ‹‹Discussions and Findings on Ashenda Festival Describing the Ashenda Festival›› በሚል ርዕስ ባወጣችው ጥናታዊ ጽሑፍ በእንደርታና ክልዕልተ አውላእሎ ወረዳ አሸንዳ ሲባል በአጋሜ ማለትም በአዲግራት ከተማና ዙሪያው ማሪያ በአክሱም ዓይኒ ዋሪ እንደሚባል ጠቅሳለች።

በዋግኽምራ በየዓመቱ ከፍልሰታ ፆም በኋላ በድምቀት የሚከበር የኮረዶች በዓል (ባህላዊ ጨዋታ) ነው። በዓሉ በዋናነት ከነሐሴ 16 እስከ 18 በድምቀት ሲከበር፣ በገጠሩ አካባቢ ደግሞ እስከ ነሐሴ 21 ድረስ ይዘልቃል። አሸንዳ በህምጥኛ ሻደይ ይባላል። ፍቺው ‹‹ለምለም አረንጓዴ›› ማለት ነው። ስያሜው የባህላዊ ጨዋታውና የቅጠሉ መጠሪያ ሆኖ የሚያገልግል ነው። መጠሪያው በክብረ በዓሉ ወቅት ልጃገረዶች በወገባቸው ከሚያስሩት ረዥምና ሥሩ ነጭ ሌላው አካሉ አረንጓዴ ከሆነ ቅጠል መሰል ቄጠማ ነው።

የላስታው አሸንድዬም በየዓመቱ ከነሐሴ 16 እስከ 21 ባሉት ቀናት በድምቀት ይከበራል። በአሸንድዬ ከ12 እስከ 20 ዕድሜ ክልል ያሉ ልጃገረዶች በወገባቸው ላይ ቅጠል እንደ መቀነት አሸርጠው በባህላዊ ዜማና ውዝዋዜ በዓሉን የሚያደምቁበትና ኮረዶቹም የሚደምቁበት ነው።

ከዊኪፒዲያ ድረ ገጽ የተገኘ መረጃ በዚህ በዓል፣ ህጻናት አሸንዳ ከተባለ፣ የነጭ ሽንኩርት ቅጠል የሚመስል ረጅም ሳር የተለያዩ አይነት ጌጦችን በማበጀት፣ እንዲሁም ቀበቶና ቀሚስ በመስራት፣ በየቤቱ በመሄድ

አሸንድየ አሸንድ አበባ

እርግፍ እንደ ወለባ

እያሉ በመዝፈን የሚጨፍሩበት የጨዋታና በዓል አይነት ነው። ያም ሆነ ይህ ግን በአንዳንድ አማራ አካባቢዎች አሸንድዬ ቢባልም ነባር ግጥሙ ግን አሸንዳ በሚል የተጻፉ የዘፈን ግጥሞች ዝቅ ብሎ ያለው ግጥም ማሳያ ነው።

አለቃ ታየ በ1902 ዓ.ም በታተመ የትብብር መጽሐፋቸው፣ አሸንድየ በዓልን አሸንዳ በማለት በራሱ በተክሉ ስም ይጠሩታል ። ይህ በዓል፣ በእርሳቸው ዘመን በሚከተሉት የግጥም ስንኞች ይታጀብ እንደነበር ድረገፁ ያስነብባል፦

አሸንዳ በሉ

አሸንዳ

አሸንዳ ብዬ

አሸንዳ

ለባሌ ብዬ

አሸንዳ

ጎመን ቀቅዬ

አሸንዳ

አረ አረረብኝ

አሸንዳ

እናንተ ሆዬ

አሸንዳ በሉ

በትግርኛም ከላይ የጠቀስነው የሰላም ባህለይ ጽሑፍ

‹‹ አሸንዳ … አሸንዳዋይ ዶ መሲሉኒ

ረሲዐያ ኔረ ይረስዐኒ

አሸንዳዋይ ናይ ዓሚ ናይ ዓሚየ

ተራኺብና ሎሚየ

ክንዲ ምሰሐይ ድራረየ

አሸንዳ መዓረይ…››

ትርጉሙም

አሸንዳ አሸንዳ ይመስለኛል

አሸንዳ ወደኛ እንደረሰ አላወኩምና

እረሳሁኝ

እኔን ይርሳኝ

ዓመት ከጠብቅሁ በኋላ

አሸንዳን አገኘሁት እንደገና።

ምሳና ራት ይቅርብኝ፣

አሸንዳ ማር አለልኝ።

የበዓሉን አዋጭነት በሚያሳይ መልኩ፣ እንዲህ በማለት በዘመኑ የነበሩ የዘመሩ ኮረዶች በሚያገኙት ገንዘብ ወይንም ፍሪዳ፣ ወይንም በግ፣ አለበለዚያ ጠላና እንጀራ ይገዙ እንደነበር በወቅቱ አለቃ ታየ አስፍረዋል።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከላከው ሰነድ የተገኘው መረጃ፣ በዓሉ የአማራና የትግራይ ሕዝቦችን የሚያስተሳስር ባህላዊ ጨዋታ ይለዋል። በበዓሉ ላይ በዋናነት ያላገቡ ልጃገረዶች የሚጫወቱ ቢሆንም በዋግ ኽምራ አካባቢ እናቶች ይጫወቱታል። ከራያ ቆቦ ውጪ በሌሎች አካባቢዎች ሁለት ታዳጊ ወጣቶች እንዲሳተፉ ይፈቀዳል።

የበዓሉ አካባበር የቤተክርስቲያን፣ የመኖሪያ ቤትና የጎዳና ዐውድ አለው። በዓሉን ለማክበር ሲጀመር ልጃገረዶች ተሰብስበው በአጥቢያቸው ከቤተክርስቲያን ደጀ ሰላም ይሳለማሉ ይጸልያሉ። እንኳን ለዚህ በዓል አደረስከን በዓሉን ያማረ የሰመረ አድርግልን፣ ክረምቱን በሰላም አሳልፈን ሲሉ ነው።

በበዓሉ ወቅት ኮረዶች እና ኮበሌዎች ምርጥ በጥልፍ ያጌጠ የተለያዩ ባህላዊ ልብሶችን ይለብሳሉ። ጉብ ጉብ (በብዛት ከወርቅ የሚሠራ የአንገት የጆሮና የፀጉር ጋሻ የመሰለ ጌጥ) አልቦ፣ አምባር፣ የፀጉር ወለባ ኮረዶችና እናቶች የሚያጌጡበት የበዓሉ ማደመቂያ ነው። የአንገት ጌጥና መስቀል፣ በጆሮ ጌጥ ይጊያጋጣሉ። ከነዚህም መካከል ጉባጉብ፣ ወለባ እንዲሁም ልዩ ልዩ የፀጉር ባህላዊ ሹሩባዎችን ይሠራሉ። ከእነዚህም መካከል ግልብጭ፣ እግር ተፈረስ፣ በተለይ ኮረደችና ይህን ማጊያጋጫ በቀላ የማያገኙ ከሆኑ፤ በቅርብ ትዳር ከመሠረተች እንስት በውሰት ይወስዳሉ።

በለበሱት ባህላዊ ቀሚሳቸው ላይ ከወገብ በታች የአሸንዳውን ቄጠማ ዙሪያውን እንደ ጉርድ ቀሚስ አገልድመው የአሸንዳ ባህላዊ ዘፈናቸውን እየዘፈኑ ይጨፍራሉ። ይወዛወዛሉ። ከበሮ ለዘፈኑ ማድመቂያ ሲሆን አሸንዳውም ኮረዶቹ ግራ ቀኝ እያሉ ሲወዛወዙ እንደ ጃን ጥላ ወይም እንደ ክንፍ በሚመስል መልኩ ይዘረጋና ይወዛወዛል። አሸንዳ ቁመቱ ረዘም ያለ መሆኑ ለበዓሉ ተመራጭ ያደረገው ይመስላል። ይህም ለበዓሉ የበለጠ ድምቀትና ውበት የሚሰጥ ነው።

የተወሰነ በዓሉ ከፍልሰታ ጾምና ከማርያም እርገት ጋር የተገናኘ ነው። ማርያም ስታርግ አረንጓዴ ልብስ ለብሳ ስለነበር የሚሉ የሃይማኖት ሰዎች አሉ። በዓሉ የተወሰነ ከሃይማኖት ጋር የተገናኘ ቢመስልም ቅሉ በብዛት ግን ባህላዊ ይዘቱ ሚዛን እንደሚደፋ ሰዎች ይናገራሉ። በቤተክርስቲያንም ወጣቶች በዚሁ ወቅት ‹‹ማርያም ዐረገች ወደ ገነት የሰማይ መላዕክት በደስታ እያጀቧት›› እያሉ ይዘምራሉ።

አሸንዳ ከላይ እንደጠቀስነው በተመድ የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት በዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ነገር ግን ይህን የመሰለ ባህላዊ ቅርስ በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች እንዲከበር ከፖለቲካ ጋር ሊያስተሳስሩት የሚፈልጉ የተለያዩ ፓርቲዎች እጃቸው ከአሸንዳ በዓል ላይ እንዲያነሱ እንጠይቃለን።

ይቤ .ከደጃች ውቤ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You