
የቃላት ጉልላቱና የቀለም ቀንዱ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሕይወታቸው ያለፈው ከዛሬ 75 ዓመት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኔ 24 ቀን 1936 ዓ.ም ነበር።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የተወለዱት በ1864 ዓ.ም መንዝ ተጉለትና ይፋት ውስጥ ከነፋሻማነቱ የተነሳ ቆብ አስጠል በሚል ቅጽል በሚታወቅ ኮረብታማ አካባቢ ልዩ ስሙ እምቢጣጣ በሚባል ስፍራ ነው። አያታቸው መምህር በእውነቱ እጅግ የተማሩ ሊቅ ሲሆኑ፤ ኪዳነ ወልድ ክፍሌን የቁም ጽሕፈት ያስተማሯቸው እርሳቸው ናቸው።
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ 20 ዓመት ሲሆናቸው ወደ እየሩሳሌም በመሄድ የምንኩስና ሕይወት ለመኖር ወሰኑ። በግብጽ አንድ ዓመት ያህል ቆይተው በ1892 እየሩሳሌም ወደሚገኘው የኢትዮጵያውያን ገዳም ገቡ። እየሩሳሌም ሳሉ ለኑሯቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያገኙት ከብዙ የውጭ አገር ሊቃውንት በሚቀርብላቸው ጥያቄ መሠረት የብራና ጽሐፎችን በመገልበጥ ነበር። ሆኖም ለድካማቸው የሚከፈላቸው ገንዘብ አነስተኛ ነበር።
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ አስኬማ (የመነኩሴ ልብስ) የሚለብሱበትን ቀን በጉጉት ሲጠባበቁ ሳለ የሕይወታቸውን ጉዞ ሙሉ በሙሉ የሚቀይር አንድ ነገር ተፈጠረ። ይህም በ1897 መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የተባሉ የኢትዮጵያ ሊቅ ወደ እየሩሳሌም መምጣት ነበር። ክፍለ ጊዮርጊስ ወደ እየሩሳሌም ሲመጡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የ27 ዓመት ወጣት ነበሩ። ሁለቱም የአንድ አካባቢ ተወላጅ መሆናቸውና ከካህናት ቤተሰብ መወለዳቸው ይበልጥ እንዲቀራረቡ አደረጋቸው።
ክፍለ ጊዮርጊስ የኪዳነ ወልድ ክፍሌን ልዩ ተሰጥዎ ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ስለዚህ በዘመናቸው ሙሉ ያካበቱትን እውቀትና ተሞክሮ ለዚህ ትጉህና ንቁ ወጣት ለማውረስ ቆርጠው ተነሱ። ምክንያቱም ሮም ቆይተው ወደ እየሩሳሌም ሲመጡ፤ ጅምር ሥራቸውን ከፍጻሜ የሚያደርስላቸው ሰው በብርቱ ይፈልጉ ነበር።
ክፍለ ጊዮርጊስና ኪዳነ ወልድ ለ11 ዓመታት ያህል በእየሩሳሌም አብረው ኖሩ። መለያየት ግድ የሆነባቸው ክፍለ ጊዮርጊስን ነጣቂው ሞት በ1908 ዓ.ም ሲወስዳቸው ነው። ክፍለ ጊዮርጊስ ጅምር ሥራቸውን ሁሉ በአደራ ያስረከቡት ለኪዳነ ወልድ ክፍሌ ነው። ኪዳነ ወልድ ክፍሌም የተቀበሉትን አደራ ፈጸሙ እንጂ አላሳፈሯቸውም። ይልቁንም የዕብራየሥጥ፣ የሱርስትና የጽርእ /ግሪክ/ ቋንቋዎችን በማጥናት የመምህራቸውን ህልም እውን ለማደረግ ይተጉ ጀመር።
ከመምህራቸው ሞት በኋላ ሌላ 11 ዓመት ተደምሮ ንጉስ ተፈሪ እስከጠሯቸው ጊዜ ድረስ ለ30 ዓመታት ያህል በኢየሩሳሌም ሲኖሩ ቆይተው ወደ አገራቸው ተመለሱ። የተመለሱበት ምክንያትም የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ (በኋላ ቀዳማዊ ዐጼ ኃይለሥላሴ) «ትችል እንደሆነ መጥተህ እዝቅኤልን ተርጉምልኝ» የሚል ደብዳቤ ስለጻፉላቸው ነው።
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትና የሥራውም ትልቅነትና ጥራት እንደሚጠቁመው የግእዝ – አማርኛ መዝገበ ቃላት የአንድ ሰው ሥራ ነው ለማለት አያስደፍርም። ስለዚህ የተጀመረው በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ነው። ኪዳነ ወልድ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላም የመምህራቸውን ጉትጎታ ቸል ሳይሉ ሥራውን በሙሉ ኃይላቸው ቀጠሉ። ሆኖም እርሳቸውም እርጅና ጠላት ሆነባቸው።
ስለዚህም ከዓመት በፊት በአንድ አጋጣሚ የደስታ ተክለ ወልድን የግእዝ ችሎታ ተረድተው ስለነበር አደራውን ከደስታ ሌላ የሚረከብ ሰው እንደሌለ ተገነዘቡ። ደስታንም ጠርተው «አደራውን ተቀበል ሥራውንም ከዳር አድርሰህ ለህትመት አብቃው» አሏቸው።
ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ ደስታ የመጀመሪያውን የግእዝ አማርኛ መዝገበ ቃላት በኪዳነ ወልድ ክፍሌና በክፍለ ጊዮርጊስ ስም በ1948 ዓ.ም አሳተሙ። ኪዳነ ወልድ የሞቱበትን (1934) ዓ.ም እና ደስታ መዝገበ ቃላቱን ያሳተሙበትን ዘመን 1948 ዓ.ም ስናነጻጽር ደስታ የክፍለ ጊዮርጊስንና የኪዳነ ወልድን ህልም እውን ለማድረግ 14 ዓመት መድከማቸውን እንረዳለን። እንግዲህ በመዝገበ ቃላት ሥራው ሦስት ታላላቅ ሰዎች ተሳትፈዋል ማለት ነው።
ይህ መዝገበ ቃላት በኢትዮጵያ ውስጥ የታተመ የመጀመሪያው ትልቁ የግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላት ነው። መዝገበ ቃላቱ ሁለት አብይ ክፍሎች አሉት። የመጀመሪያው ክፍል (ከገጽ 1-191) ስለ ኪዳነ ወልድ ክፍሌና ክፍለ ጊዮርጊስ ሕይወት ይተርካል። 2ኛው ክፍል (ከገጽ 193-908) በአበገደ የፊደል ተራ መሠረት የመዝገበ ቃላቱን ትንተና ይቀጥላል።
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይህን መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ የተሰኘውን መጽሐፍ ሲያዘጋጁ አያሌ መጽሐፍትን አመሳክረዋል። መዝገበ ቃላቱን ለማዘጋጀት በምን ያህል ምንጮች እንደተጠቀሙ ለማወቅ በመጽሐፍ ላይ የዘረዘሯቸውን 64 መጻሕፍት መመልከት ብቻ በቂ ነው።
ኪዳነ ወልድ ይህን ሥራ እንዴት ከዳር ሊያደርሱት እንደቻሉ ደስታ ተክለወልድ ሲገልጹ እንዲህ ይላሉ። «በሥራ ውለው ማታ ነፋስ በመቀበል ጊዜ አንድ ሃሳብ ቢያገኙ በማስታወሻ ለመፃፍ ከውጭ ወደ ቤት ይመለሳሉ። በምሳ ወይም በእራት ጊዜ አንድ ትርጓሜ ቢታሰባቸው ምግቡን ትተው ብድግ ይላሉ።
ሌሊትም ተኝተው ሳሉ አንድ ምስጢር ቢገለጥላቸው ከመኝታቸው ተነስተው መብራት አብርተው ይጽፋሉ። ዛሬ በእጃችን የሚገኘው መዝገበ ቃላት አንድ ለትውልድ የሚያስብ ትጉህና ቅን ሰው ከዕድሜው ከፍሎና ሕይወቱን ሰውቶ ያበረከተልን ውድ ስጦታ ነው።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ እንደሚሉት ይህ መዝገበ ቃላት ጥልቅ ጥናትና ምርምር ተደርጎበታል። «ሥራን መንቀፍ በሥራ ነው እንጂ በቃላት ብቻ መንቀፍ አይበቃም» የሚለውን ብሂል ሲጠቅሱ ለሥራቸው ምን ያህል ትኩረት እንደሰጡ መግለጻቸው ነው።
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላታቸው ውስጥ ብዙ ጊዜ «አያሰኝም» የሚል ቃል ተጠቅመዋል። አያሰኝም በሚሉበት ጊዜ ሁሉ ያሉበትን ምክንያት ገልጸዋል። ይህ የሚያሳየው የሚነቅፉትን ነገር በደፈናው ሳይሆን በምክንያት እንደሚነቅፉ ነው።
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ለሆሄያት ትልቅ ስፍራ ይሰጣሉ። ቃላትን በመደበኛ ሆሄያቸው አለመጻፍ እርሳቸው እንደሚሉት ጸያፍ ብቻ ሳይሆን ግፍ ነው። በሕይወት ዘመናቸው ከአምስት በላይ መጽሐፍ ጽፈዋል። መጽሐፍቱ በጊዜ ቅደም ተከተላቸው 1/ መጽሐፈ ሕዝቅኤል 2/ አበገደ 3/ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግእዝ መዝግበ ቃላት ሐዲስ 4/ መዝገበ ፊደል 5/ ሃይማኖት አበው ቅደም ናቸው።
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ለቋንቋ ብቻ ሳይሆን ለነፃነትም ተጋድለዋል። በዚህም የተነሳ ለእስር የተዳረጉበት ጊዜ ነበር። በተለይ በ1929 ዓ.ም ቀዳማዊ ዐጼ ኃይለሥላሴ ከስደት ወደ አገራቸው ተመልሰው ሲመጡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ነገሩን ያያያዙት ከነፃነት ጋር ነበር። የንጉሰ ነገስቱ ተመልሶ መምጣት ግን ለፋሽስቶች የሚዋጥ ነገር አልነበረም። ለንጉሰ ነገስቱ ቀኝ እጃቸውን የሠጡ ሰዎች በጣልያን ጥርስ ውስጥ ገቡ።
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ በድፍረት የሚናገሩ ሰው ነበሩ። ይህ ይበልጥ በጣልያኖች እንዲጠሉ አደረጋቸው። በመሆኑም ጣልያኖች ወደ ወህኒ ጣሏቸው። ደስታ ተክለ ወልድ እንደገለጹት ፋሽስቶች በጨለማ ውስጥ አስረዋቸው ስለነበር ዓይናቸው ጠፋ። ዓይናቸው ከጠፋ በኋላም በሕይወት እስካሉ ድረስ ቁም ነገር ሰርተው ለማለፍ የተጉ ሰው ነበሩ። ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በአንድ በኩል ለቋንቋ እድገት በሌላ በኩል ለአገር ነፃነት ብርቱ ትግል አድርገዋል። በዚህም ለመጪው ትውልድ ቅርስንና ምሳሌነትን ትተዋል።
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የመጨረሻ የሕይወት ዘመናቸውን ያሳለፉት በችግር ነው። በአንድ ወቅት እንዲያውም የሚበሉትና የሚጠጡት አጥተው የከፋ ስቃይ ላይ ወደቀው ነበር። ችግራቸውን የተረዱት ቀዳማዊ ዐጼ ኃይለስላሴ ቀለብና ድርጎ ይሰፍሩላቸው ነበር።
የቃላት ጉልላቱ ፣ የቀለም ቀንዱ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ እያደር የስኳር በሽታና የጆሮ ህመም ጠናባቸው። ሥራ የጫኗቸው ሹማምት ቸል ባሏቸው ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር በነበሩት ከበደ ሚካኤል ተራዳኢነት በራስ ደስታ ሆስፒታል ሲታከሙ ቆዩ። በመጨረሻም 20 ዓመታት በመንዝ ፣ 30 ዓመታት በእየሩሳሌም እንዲሁም 22 ዓመታት በድሬዳዋና አዲስ አበባ ሲማሩና ሲያስተምሩ ኖረው በተወለዱ በ 72 ዓመታቸው ቅዳሜ ሰኔ 24 ቀን 1936 ዓ.ም አርፈው ደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011
የትናየት ፈሩ