በአዲስ አበባ ከተማ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የተዘጋጀው ዓመታዊው የክለቦች ቅርጫት ኳስ ቻምፒዮና በደማቅ ሁኔታ ተጠናቋል። ውድድሩ በአራት ምድቦች አንድ ዙር የፈጀ ሲሆን በቀጣይ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማካሄድ እንደሚሠራ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የክለቦች እና የተለያዩ ቡድኖች ቅርጫት ኳስ ቻምፒዮና ከመጋቢት ወር ጀምሮ ለ 6 ተከታታይ ወራት በከተማዋ በሚገኙ የማዘውተርያ ሥፍራዎች ሲካሄድ ቆይቶ ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም ፍጻሜውን አግኝቷል። ቻምፒዮናው የዙር ውድድር ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በአንድ ዙር ብቻ እንዲጠናቀቅ መደረጉን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። ለዚህም የጊዜና የበጀት ችግሮች ዋንኞቹ መሆናቸው ተጠቁማል።
በቻምፒዮናው በአራት ምድቦች በአጠቃላይ አርባ ቡድኖች እና አራት መቶ የሚጠጉ ስፖርተኞች (በ 3ኛ ዲቪዚዮን ወንዶች ከ17 ዓመት በታች፣ 2ኛ ዲቪዚዮን ወንዶችና ሴቶች ከ19 ዓመት በታች እንዲሁም በከፍተኛ ዲቪዚዮን) የተሳተፉ ሲሆን አሸናፊ ክለቦችና ቡድኖች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በውድድሩ የታየው ፉክክር ከፍተኛ እንደሆነ የሚጠቅሱት ተጫዋቾችና አሠልጣኞች፤ ከፌዴሬሽኑ እና ከሌሎች አካላት የሚደረግላቸው ድጋፍም የተሻለ መሆኑን ያስረዳሉ። ቅርጫት ኳስ እንደ ሌሎች ስፖርቶች በስፋት ተዘውታሪ ባለመሆኑ ውድድሩ ለስፖርቱ መስፋፋት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። ይሁንና የአሠልጣኞችና የተጫዋቾች አቅም ማነስ እንዲሁም የስፖርት ማዘውተርያ እጥረት በስፋት ይስተዋላል። የበጀት እና ሌሎች ችግሮች ቢኖርበትም በቀጣይ የታዩትን ጉድለቶች በማረም ደረጃውን የጠበቀ የቅርጫት ኳስ ውድድር ለማካሄድ እንደሚሠራ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንደሰን አበበ፣ ክለቦች በውድድሩ ለመሳተፍ ፍላጎት ቢኖራቸውም አስፈላጊ ነገሮችን በጊዜ ከማሟላት አንጻር መዘግየት እንደታየ ይገልጻሉ። በቻምቻዮናው ለመሳተፍ ክለቦች ፈቃድ ወስደው የዓመቱን እድሳት የማጠናቀቅ ግዴታ ቢኖርባቸውም ከዚህ ጋር ተያይዞ ክፍተቶች ተፈጥረው እንደነበር አስታውሰዋል። በአምስት ክለቦች ብቻ ውድድሩን ለማስቀጠል አዳጋች በመሆኑ ቁጥራቸውን ወደ አስራ አራት የማሳደግ ሥራ ማከናወን ተችሏል። በውድድሩ የመሳተፍ ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ ዘጠኝ ክለቦችን የማቋቋም ሥራ በአጭር ጊዜ ማሳካቱም ተገልጿል። ይህም ካለው የማዘውተርያ ሥፍራ እጥረትና ጊዜ አንጻር ማስተካከያዎች ካልተደረጉ ውድድሩን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለማስቀጠል አዳጋች ይሆናል።
የከተማዋ ክለቦች የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግን ካቋቋሙት መካከል ቢሆኑም አሁን ባላቸው አቋም፣ ወደ ሊጉ አድጎ ለመወዳደር የተደራጀ አቅም እንደሌላቸው ኃላፊው አስረድተዋል። ተቋማት ፕሪሚየር ሊግ ላይ የሚሳተፍ ክለብ እንዲይዙ ጥረት እየተደረገ እንደሆነና ፈቃደኝነታቸው ታይቶ፤ በፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፍ ክለብ እንዲኖር የሚሠራም ይሆናል።
ፌዴሬሽኑ የከተማውን ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የቅርጫት ኳስ ክለብን እንዲያቋቋም ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ እንደሆነ ተጠቅሷል። ውድድሩ በሁሉም ምድብ ጥሩ እንቅስቃሴን ማስመልከት የቻሉና የድንቅ ተሰጥኦ ባለቤት የሆኑ ተጫዋቾችን አሳይቷል። የወንዶች ቡድን ተሳትፎ ጥሩ ቢሆንም የሴት ቡድኖች ቁጥር ግን አናሳ እንደሆነና ለሚቀጥለው ዓመት ቁጥሩን ጨምሮ ለመቅረብ ይሠራል።
የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሚሽነር አስናቀ ሙለታ፣ ከዚህ ቀደም በክረምት የታዳጊዎች ሥልጠና የታገዘና ደረጃውን የጠበቀ የክለቦች ውድድር ይካሄድ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህን ለመመለስ የታቀደው ዓላማ በወንዶች በኩል የተሳካ ሲሆን በሴቶችም ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም ክፍተቶች በመኖራቸው ለማረም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በከተማው የቅርጫት ኳስ ላይ የስፖርተኞች ፍላጎትና እንቅስቃሴ የመኖሩን ያክል፣ አመራሩ በተዋረድ እየሠራ ነው ለማለት እንደሚከብድ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል። ሁሉንም ባማከለ ሁኔታ ወደ ታች አውርዶ መሥራትና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል። አብዛኞቹ ስፖርተኞች የውጭ ትምህርት ቤቶች የሚማሩና ስፖርቱን በደንብ የሚያዘወትሩ በመሆኑ አቅም ቢኖራቸውም ከዚህ በላይ መሥራት እንደሚገባም ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሁሉንም ስፖርቶች ያካተተ የጥናት ሰነድ እያዘጋጀ መሆኑን የገለፁት ኮሚሽነር አስናቀ፣ ከተማው የቅርጫት ኳስ ክለብ እንዲኖረው ንግግር መደረጉን ጠቅሰዋል። በዚህም መሠረት ካሉት ቡድኖች ጠንካራ ተጫዋቾችን በመምረጥ አንድ ከተማውን የሚወክል ጠንካራ ክለብ ለማቋቋም እንደሚሰራ አክለዋል።
በከፍተኛ ዲቪዚዮን ወንዶች ምድብ ቻሌንጀርስ የቅርጫት ኳስ ክለብ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሲሆን፣ ቢፎርለ እና አፍሮ ሁፐር ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። በሁለተኛ ዲቪዚዮን ወንዶችም ቻሌንጀርስ የበላይ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ ነገሌ ቦረና እና አሰትማ ተከታዮቹን ደረጃ በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።
በሁለተኛ ዲቪዚዮን ሴቶች የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የወርቅ ተሸላሚ ሲሆን ቻሌንጀርስ የብር፣ ኤቢኤ የቅርጫት ኳስ ቡድን የነሐስ ሜዳሊያን መውሰድ ችሏል። በሶስተኛ ዲቪዚዮን ወንዶች ቻሌንጀርስ የውድድሩ ቻምፒዮን ሲሆን ጉለሌ ክፍለ ከተማ እና ኢን ቡድን ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2016 ዓ.ም