መዋጃ
ጤና ይስጥልኝ ውድ አንባብያን!
ይህ ዓምድ “የሕግና ፍትህ” አምድ ተሰኝቷል። የዓምዱ መሰናዳት ዋነኛ ምክንያቶች ደግሞ ሁለት ናቸው። ሕግ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ወይም የሕብረተሰብ ክፍሎች በጋራ ለመኖር በመሰረቱት ስርዓት ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባ ወይም ሊከተሉት፣ ሊያደርጉት ወይም ሊላበሱት የሚገባ ዝቅተኛው የባህርይ ደረጃ ነው።
ስለዚህ የዚህ ዓምድ ተቀዳሚ ዓይነተኛ ዓላማ በአገራችን የተለያዩ ሕጎች ውስጥ ተደንግገው የሚገኙትን ዝቅተኛ የባህርይ ደረጃዎች ለእናንተ ማስገንዘብ ነው። ሁለተኛው የዓምዱ ዓላማ ደግሞ እናንተ ውድ አንባብያን በየዕለት ተዕለት የግል ሕይወትና ማህበራዊ መስተጋብራችሁ ውስጥ የሚያጋጥሟችሁን የህግ ጉዳዮች በተመለከተ ጥያቄዎቻችሁን በመቀበል ሕጋዊ ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ማገዝ ነው።
ስለዚህ በየሳምንቱ በዚህ ዓምድ የምናቀርብላችሁን የህግ ጉዳዮች በመከታተልና ጥያቄዎቻችሁንም በማቅረብ የሕግ ግንዛቤያችሁን እንደምታሰፉ፣ ሕግ አክባሪና ለሕግ የበላይነት ተቆርቋሪ ዜጎች እንደምትሆኑ እምነቴ የጸና ነው።
በዚህ መነሻም ዓምዱ በየሳምንቱ በናፍቆት የምትጠብቁት እንደሚሆን ተስፋ አለኝ። እናም በተለያዩ ዝርዝር የሕግ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ከማስጨበጥ አስቀድሜ ለዓምዳችን መባቻ ይሆን ዘንድ ለዛሬ ስለ ሕግ እና ፍትህ እንዲሁም ስለ ሕግ የበላይነት ጠቅላላ ጉዳዮች ለዓይን መግለጫ ይሆን ዘንድ ይህን ማብራሪያ እነሆ ብያለሁ።
ሕግ ምንድን ነው?
መቼም ሕግ የሚለው ቃል እንግዳችን አይደለም፤ በየዕለቱ አብዝተን ስንናገረው እና ስንሰማው የምንውል እንጂ። በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት “ሕግ ይከበር! የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ!” የሚሉት ጉዳዮች የሁሉም ነገራችን ማጣፈጫዎች ሆነዋል። ያም ሆኖ አንድ ሰው ሕግ ይከበር፤ የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ በሚል ጥያቄ ሲጠይቅ ወይም ሲደሰኩር በጥቂቱም ቢሆን ሕግ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተረድቶ ሊሆን ይገባዋል።
እናም ሕግ ምንድን ነው? የሕግ የበላይነት ማለትስ? የሚለውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለዚህ ነው እኔም የህግን መሰረታዊ ጉዳዮች ማስገንዘብን የዚህ ዓምድ መባቻ ያደረኩት።
በየትኛውም የዓለም ጥግ የሚኖሩ የሰው ዘሮች ባህላዊም ሆነ ዘመኑን የዋጀ የህግ ስርዓትን ዘርግተው ይኖራሉ። በህግ መኖር፣ ከሕግ ጋር አብሮ መኖር ከሰው ልጅ ስነ ተፈጥሮ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። እርግጥ ነው እንስሳትም በተፈጥሯቸው ሕገ – አራዊት በሚባለው ደመ ነፍሳዊ ስርዓታቸው ይንቀሳቀሳሉ፣ ያድናሉ፣ ይኖራሉ፣ “ጦርነት ይገጥማሉ” ወዘተ።
የሰው ልጅ ደግሞ ከእንስሳት ፍጹም በተለየ መልኩ አገር መስርቶ፣ መንግሥት አቁሞ በዘመናት ቅብብሎሽ ሲወርድ ሲወራረድ ባዳበረው የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሠራሽ ሕግ አልያም የሐይማኖትም ሆነ የሞራል ሕግ ሲመራ ኖሯል፤ ይኖራልም።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን የሕግና የህግ የበላይነት ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዋነኛ የህዝብና የመንግሥት አጀንዳ ስለመሆኑ መናገር ጉንጭ ማልፋት ይሆናል። በዚህ ወሳኝ ወቅት ታዲያ ዜጎችም ሆኑ የመንግሥት አካላት ተስማምተውም ሆነ ሳይስማሙ አጽድቀው በሥራ ላይ ያኖሯቸውን ሕጎች ሊያከብሩ፣ ሊያስከብሩና ሊጠብቋቸው ያስፈልጋል።
ሕጎቹን ሲቀይሯቸውም ሆነ ሲሽሯቸው ባለማክበርና በመጣስ ሳይሆን በሕግ አግባብ መሆን ይኖርበታል። ይህን ለማድረግና ንቃተ ሕግን ለማጎልበት ታዲያ የግንዛቤ ስንቅ መያዝ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ንቃተ ሕግ በዳበረበት ማህበረሰብ ውስጥ የህግ የበላይነት ይሰፍናልና።
እርግጥ ነው ሕግን ማክበርና ለሕግ የበላይነት መገዛት ከንቃተ ሕግም በላይ ነው። የህግ ግንዛቤ መጎልበት ብቻውን መሰረታዊ ጉዳይ አይደለም። ለሰው ልጅ የሕግ ሁሉ ማፍለቂያው ሕሊናው ነው። ዳኝነት በሕሊና ነው። መፋረጃውም መፍረጃውም፣ ሕጉም የህሊና ሚዛን ነው።
ሕግን ማክበር በሕሊና ውስጥ የሚዳብር ራስን የመግዛት ረቂቅ መገለጫ ነው። ራስን መግዛት ደግሞ በምድር ላይ ካሉ ስልጣኖች ሁሉ የሚልቀው ነው። ለሰው ከራሱ በላይ ህግ፣ ከራሱ በላይ ፍርድ ቤት፣ ከራሱ በላይ ዳኛ፣ ከራሱ በላይ አስተማሪ የለውም። ያም ሆኖ በተፈጥሮ የተጎናጸፍነውን ይህንን የሕሊና ጸጋ በአግባቡ እንድንጠቀም በየጊዜው ግንዛቤን ማሳደግ፣ ለሕግ ያለንን የንቃት አድማስ ማስፋት አስፈላጊ ነው።
የህግን ትርጓሜ በተመለከተ እንደብዙ ሌሎች ጉዳዮቻችን ዓለምን በሙሉ የሚያስማማ አንድምታ እስከአሁን አልተገኘም። ያም ሆኖ በተለያዩ ጊዜያት የተነሱ በሕግ ዙሪያ ሃሳብ አፍልቀው የማህበረሰብን አስተሳሰብ የሚቀር ጹ በርካታ ልሂቃን የሚስማ ሙባቸው ትርጓሜዎች አሉ። ከዚህ መነሻ ሕግ የግለሰቦችን ወይም የማህበረሰብን ባህርይ ለመቅረጽ የሚሰናዳ ወይም የሚዘረጋ ስርዓት መሆኑ ብዙሃኑን ያስማማ አንድምታ ነው። በሌላ በኩል ሕግ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ሊኖራቸው የሚገባ መብትና ግዴታን ደንግጎ የሚያስቀምጥ ነው።
አሁን በምንኖርበት ዘመን እሳቤ ሕግ ሲባል ወደ ሕሊናችን ቀድሞ የሚመጣው መንግሥት በሕግ አውጭው አጽድቆ የሚሰጠን ድንጋጌ (አዋጅ፣ ደንብ ወይም መመሪያ) ነው። ይሁንና ቀደም ባሉት ዘመናት የሰው ልጅ ይመራባቸው የነበሩት ዓይነተኛ ሕግጋት የባህል፣ የሞራልና የሐይማኖት (የእምነት) መመሪያዎች ነበሩ።
በእነዚያ ሩቅ ዘመናት የሐይማኖት፣ የባህልና የሞራል መመሪያዎች የሰውን መስተጋብር ለመምራት በተፈጥሮ በራሱ የተቀመጡለት ሕግጋት ተደርገው በጽኑ ይታመኑ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን በጊዜ ሂደት የሰው ልጅ ቀስ በቀስ ከተፈጥሮ ሕግጋት በተጨማሪ ራሱ በሚያወጣቸው ሰው ሠራሽ ሕጎች ወደመመራት ተሸጋገረ። ዛሬ ላይም የግልና የጋራ የሆኑ ባህርያትን በመቅረጽና በመምራት ረገድ ሰው ሠራሽ ሕግ ቀዳሚውን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።
ሰው ሠራሽ ሕግን በተመለከተ ማህበረሰብ ራሱ ሊቀርጽና ሊያዳብረው ይችላል። በሌላ በኩል መንግሥትም በሕግ አውጪው አካል አማካኝነት ሕግ ያወጣል። ግለሰቦችም በአንድ ጉዳይ ላይ ከሌሎች ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር ዙሪያ ሕግን ለራሳቸው ያወጣሉ፤ ይህም ውል ይባላል። ይህ ውል ደግሞ በተዋዋዮቹ መካከል ሕግ ሆኖ ይገዛቸዋል። በአጠቃላይ ሕግ የተጻፈም ይሁን ያልተጻፈ የአንድን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ፣ የታሪክ እና የማህበራዊ አቋሞችን የሚቀርጽ ሁነኛ መሳሪያ ነው ለማለት ይቻላል።
ሕግና ፍትሕ
ሕግና ፍትህ ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ጉዳዮች ናቸው። ፍትሕ ማለት ተገቢ ወይም ትክክል ማለት ነው። ሕግን ከተፈጥሮና ከፈጣሪ ጋር የሚያዛምዱ ልሂቃን ፍትህ የህግ መሰረትና ምንጭ ነው ይላሉ። በሌላ በኩል የሕግን ሰው ሠራሽ ባህርይ አጥብቀው የሚያራምዱ ምሁራን ሕግን ለፍትህ ምንጭና መሰረት አድርገው ያቀርባሉ። ያም ሆነ ይህ ሕግና ፍትህ የማይነጣጠል ግንኙነት ያላቸው መሆኑና ፍትህ የአንድ ውጤታማ ሕግ የተግባር ፍሬ መሆኑ የሚያስማማ ሐቅ ነው።
ፍትህ የሚረጋገጠው ዜጎችና የመንግሥት አካላት እንዲሁም የተለያዩ ቡድኖች ለሕግ በአግባቡ መከበር ዘብ ሲቆሙና ሲያከብሩም ጭምር ነው። ሁሉም ዜጎችና የመንግሥት አካላት ከሕግ በታች መሆን አለባቸው፤ በሕግ መመራት አለባቸው። ይህ ማለት ደግሞ የህግ የበላይነት ማለት ነው።
ስለዚህ በሕግ የበላይነት መከበር ፍትህ በአግባቡ ይረጋገጣል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን መንግሥታት ጠንካራ ጡንቻቸውን በተቀናቃኞቻቸው ላይ ለማሳረፍና ለመግፋት አስበው ብሎም መብቶችን ለማፈንና የአገር ሀብት ለመመዝበር አልመው በፓርላማቸው ሕግ ቢያስጸድቁ በሕግ መግዛት እንጂ የሕግ የበላይነት አለ ሊባል አይቻልም።
ከዚህም ሌላ አንድ ሕግ በራሱ ተገቢነቱ የሚለካው በፍትሐዊነት መነጽር ነው – ለሕግ አንዱ መለኪያው ፍትሕን የማረጋገጥ ዓላማን ያነገበ መሆኑ ነው። ሕግ የሕዝብን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እንዲሁም ታሪካዊ ሳንካዎችን የማረምና የመፍታት ዓላማን ይዞ መውጣት አለበት።
ሕግ ከአወጣጡ ሂደት ጀምሮ አሳታፊና ግልጽ ሆኖ ሊጸድቅ ይገባዋል። ከማህበረሰብ የሞራል መሰረቶች ጋር የተጣጣመ ሆኖ የሚወጣ ሕግ በሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያለው ሆኖ ይዘልቃል። እንዲህ ሲሆን ታዲያ ሕግ የህዝብን ጠቃሚ የሞራል እሴቶች ጠብቆ በማቆየት ረገድ ጉልህ ሚናውን ይጫወታል ማለት ነው። በዚህም ፍትሐዊነትና የህግ የበላይነት ተረጋግጦ ይቀጥላል።
ሕግ ለምን? ያለሕግስ መኖር አንችልምን?
በታሪክ ሰረገላ ተሳፍረን፤ በልሂቃን የአብርሆት መነጽር እየተመራን የጥንቱን ዘመን፣ የጋርዮሹን ስርዓተ ማህበር ለአፍታ እንቃኝ። የያኔውን የሰው ልጅ ኑሮና የህግን ሁኔታ ማየታችን “ሕግ ለምን?” የሚለውን በቅጡ እንድንረዳ ያስችለናል። ይበልጡኑም በአሁኑ ወቅት በአገራችን ያለውን ሁኔታና በዘመኑ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ሕግን አክብሮ የማስከበር ደረጃችንን እንዲሁም እየተጓዝን ያለንበትን መንገድና ፍጻሜውን በደንብ እንድንገነዘበው ያደርገናል።
ቶማስ ሆብስ የተባለው የህግና የማህበራዊ ሳይንስ ሊቅ በደረሰበት የጥናቱ ድምዳሜና ኋላም የእርሱን ፈለግ የተከተሉት ሌሎች ምሁራን እንዳረጋገጡት በጥንት ዘመን የሰው ልጅ በሕግ የማይመራ ነበር። ውሎና አዳሩ ግጭትና ጦርነት ነበር። የሕይወትና የአካል ደህንነት፤ የንብረትም ዋስትና አልነበረም። አገር መስርቶ፣ መንግሥት አቁሞ፣ የሕግ ስርዓትን ሠርቶ መኖር የሚባል ነገር አልነበረም ያኔ።
ግጭት፣ መገዳደል እና ዝርፊያ የዕለት ተዕለት መገለጫዎች ነበሩ። በዚህም የተነሳ አሰቃቂ ግድያዎች፣ ዘግናኝ የአካል ጉዳቶች እና አስከፊ የተፈጥሮ ውድመቶች ተከስተዋል። የሰው ልጅ ሕሊና ከግጭትና ከጦርነት አልፎ እርሻ፣ ንግድ፣ ትምህርት፣ ኪነ ጥበብና ስነ ጥበብን ለማሰብ የተሳነው ነበር። ማምረት፣ ማደግ መመንደግና መበልጸግም አልተቻለውም። መብትና ግዴታ፣ ፍትሕና ርትዕ፣ እውነትና ሃቅ፣ ሕግና መንግሥትም አልነበሩም።
በጊዜ ሂደት ታዲያ ያ የጥንት ሰው ከመካከሉ አንዱን ወይም የተወሰኑትን መርጦ በእነሱ መመራት እንዳለበት አሰበ። አስቦም አልቀረ በመረጠው አካል መመራት ጀመረ። ልሂቃኑ “ማህበራዊ ውል (Social Contract) በሚል በሰየሙት በዚህ ሂደት ውስጥ የመሪውና የተመሪው መብትና ግዴታ፤ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በመደንገጋቸው በህግ የመመራት ዝንባሌ ማቆጥቆጥና መጎልበት ጀመረ። ቀስ በቀስም ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ የሰው ልጅ በሕግ በመመራትና ለህግ የበላይነት በመገዛት ዛሬ የደረሰበት ስልጡን ደረጃ ላይ ደርሷል።
ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው የሰው ልጅ በሕግ መመራት በመጀመሩ በንጽጽር ከትላንት የተሻለ ዛሬ ኖሮታል። ሕግ ከሌለ መሰልጠን፣ ማደግና መበልጸግ አይታሰብም። ሕግ በሌለበትና ኖሮም በማይከበርበት ማህበረሰብ ውስጥ ስርዓት አልበኝነት፣ ግድያና ዘረፋ፤ መገፋፋትና መጠፋፋት የዕለት ተዕለት ክስተቶች ይሆናሉ።
ሕግ በማይከበርበት አገር ውስጥ ሰው ከእንስሳት ብዙም በማይለይበት የህይወት አዙሪት ውስጥ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገን ጎረቤት ሶማልያንና በጣት ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በቅንጡ ሕይወት ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን የሊቢያና የሶርያ ዜጎች አሁናዊ ሰቆቃን መመልከት ይበቃል። ስለዚህ የሰው ልጅ ያለሕግ መኖር አይቻለውም የተባለው የማይታበል ሀቅ ነው።
በአንጻሩ የሕግ የበላይነት ባለበት ማህበረሰብ ውስጥ ሰላም ይሰፍናል፤ ሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብቶች ይከበራሉ፤ የሕይወትና የአካል ደህንነት ይጠበቃል፤ ንብረት ይጠበቃል፤ መገፋፋትና መጠፋፋት አይኖርም፤ ውሎች በአግባቡ ይፈጸማሉ፤ ጉልበተኛና ደካማ አይኖርም፤ አሠሪዎችና ሠራተኞች በየፊናቸው መብታቸው ተከብሮ የኢንደስትሪ ሰላም ይሰፍናል፤ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ይሆናሉ፤ ማህበራዊ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይኖራል፤ ዴሞክራሲ ያብባል፤ ፖለቲካና ስልጣን የሕዝብ ማገልገያ እንጂ መገልገያ አይሆንም፤ ኢንቨስትመንት ይስፋፋል፤ ምርትና ምርታማነት ይጨምራል፤ በፍጻሜውም ዜጎች በደስታና በብልጽግና ይኖራሉ።
ሕግና ኢትዮጵያውያን
ሕግ ለኢትዮጵያውያን እንግዳ አይደለም። እስከ አምስት ሺህ ዘመን የሚዘልቅ የአገርነት፣ የመንግሥትና የሕግ ልምምድ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች ናቸው ኢትዮጵያውያን። የኢትዮጵያውያን የመንግሥት ታሪክና የሕግ አክባሪነት እንዲሁም የጨዋነትና የግብረ ገብነት ተምሳሌትነት በጥንታውያኑ የግሪክ የታሪክ የቀለም ቀንዶች ሳይቀር የተመሰከረ ነው። ኢትዮጵያውያን ዛሬም ድረስ “በሕግ አምላክ” የሚሉ ሕዝቦች ናቸው። “በሕግ ከሄደች በቅሎዬ ያለሕግ የሔደች ዶሮዬ” ብለው በሕግ አግባብ የተወሰነባቸውን አምነው የሚቀበሉና ከሕግ ውጪ የተፈጸመባቸውን ነገር ግን በሕግ ለማረም ቆርጠው የሚነሱ ለሕሊናና ለሕግ መገዛትን የሚያስቀድሙ ሕዝቦች ናቸው።
ኢትዮጵያውያን መርከብ ገንብተው፣ ሳንቲም ቀርጸው ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ሲገበያዩ የነበሩ፤ ያኔ ተቆናጠው የነበረውን የስልጣኔ እርካብ ለትውልድ ቁጭትም ኩራትም እንዲሆን አሻራ ትተው ያለፉ ቀደምት ስልጡን ሕዝቦች ናቸው። ዓለምን በብዙ መልኩ የቀረጹና በተለምዶ “ታላላቅ” የሚባሉትን እምነቶች ገና ከማለዳው ጀምሮ ተቀብለው የዘለቁ ጽኑ ሕዝቦች ናቸው።
“የህግ ምንጭ ፈጣሪ ነው፤ ፈጣሪ ሕግ ሠርቶ ትዕዛዝ ጨምሮ ለሰው ልጆች አስተላለፈው፤ የሰው ልጆችም ከፈጣሪ ቀጥሎ በላያቸው ላይ በሚሾሙት መሪያቸው በሚወጣላቸው ሕግ መመራት ጀመሩ፤ ስለሆነም ሕግና የሰው ልጅ ጥብቅ አብሮነት አላቸው” የሚል አስተምህሮ ያሰፈኑ ሕዝቦች ናቸው። ከዚህ ሌላ ኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊት አገር ናትና ከ80 የሚልቁ ብሔር ብሔረሰቦች ለዘመናት ያዳበሩት የባህልና የልማድ ሕጎችም ባለቤት ናቸው ሕዝቦቿ።
በየዘመኑ የተነሱ መሪዎች ሕዝቡን ሲያስተዳድሩባቸው የነበሩና ለብዙ መቶ ዓመታት የዘለቁ ፈውሰ መንፈሳዊ፣ ስርዓተ መንግሥት እና ፍትሐ ነገስትን የመሳሰሉ የተጻፉ ሕጎችም ነበሩ። በ20ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ የህግ ስርዓቱን ለማዘመንና ከተረኞቹ ስልጡኖች ተርታ ለመሰለፍ በሚል የተለያዩ ጥራዝ ሕጎች (ኮዶች) ወጥተዋል። አስገራሚው ነገር ደግሞ እነዚህ ሕጎች ዛሬም ድረስ በሥራ ላይ ያሉ መሆናቸው ነው። ሕገ መንግሥት በማውጣትም ከአፍሪካ ቀደምት አገር ናት።
እንዲህ ያለ የሺህ ዘመናት ዕድሜ ያስቆጠረ የህግና የመንግሥት ታሪክ ያላት አገር ሕዝቦች ታዲያ በየዘመኑ በፈጠሯቸው ችግሮች የኋሊት መጓዛቸው አልቀረም። በአንድ ወቅት የምድሪቱ የሥልጣኔ ቁንጮ ላይ የነበሩ ሕዝቦች የኋላ ኋላ የድህነት ምሳሌ ሆኑ። አገሪቱም እንደጠፋ በግ በዓለም መድረክ ተዘነጋች። መገፋፋት፣ በፖለቲካና በኃይማኖት ልዩነት መነሾ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ዕጣ ፋንታዋ ሆነ። ‹‹በእንቅርት ላይ…›› እንዲሉ በየጊዜው የሚከሰት ድርቅ የወለደው ረሃብ ሕዝቦቿን አረገፈ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ደግሞ አገሪቱና ሕዝቦቿ ቀድሞ ወደነበሩበት ልዕልና ለመመለስ የሚያስችላቸውን ጭላንጭል ዓይተዋል። አንጻራዊ መረጋጋት፣ ሰላም፣ በመከባበር እና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ አንድነትን በልዩነት ውስጥ ለመፍጠር በጎ መሰረቶች ተጥለዋል።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት በሁሉም የአገራችን ክፍል እየታየ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ሆኗል። የታየው የተስፋ ወጋገን በጭጋግ እየተሸፈነ ነው። የዚህ ሁሉ ዋና መነሻው ደግሞ የሕግ አለመከበር ነው። የመንግሥት አካላት፣ የተለያዩ ቡድኖች እና ሕዝቦችም ጭምር በሕግ ጥላ ስር ከመተዳደር ይልቅ በማፈንገጥ የሕግ የበለይነትን አደጋ ላይ ሲጥሉት ይስተዋላል። ሕግ የማይከበርባቸው አጋጣሚዎች ተበራክተዋል።
መገፋፋት፣ መፈናቀል፣ መጠፋፋት፣ አለመደማመጥ፣ ሁሉም ተናጋሪ መሆን፤ በብሔር ተቧድኖ ጎራ መለየት የኢትዮጵያውያን መገለጫ ከሆነ ሰነባብቷል። አገራዊ ጀግና፣ አገራዊ የጋራ ሃሳብ አጥተናል። በዙሪያው ተቧድነው የተሰባሰቡለትን አንድን ሰው ወይም ቡድን ያለልክ ጀግና አድርጎ ከሰማይ ጥግ መስቀል፤ ሌላኛውን ደግሞ ጭራቅ አድርጎ በመሳል ከእንጦርጦስም በታች አውርዶ በጥልቅ አዘቅት ውስጥ መክተት ብዙዎቹን የተጠናወተ በሽታ ሆኗል።
ራስን ብቻ አዋቂ አድርጎ ሌላውን ባላዋቂነት አኮስሶ መታየት ነግሷል። ምክንያታዊነትና ቅንነት ከብዙዎች የሕሊና ሰሌዳ ተፍቀዋል። አብዛኛውን ዜጋ በተለይም ከተሜውን ወሬ ፈትቶታል። መሪዎቻችን በየዕለቱ ዋነኛ ሥራቸው ምጣኔ ሀብታችን፣ ማህበራዊ ብልጽግናችን፣ ዓለም አቀፍ መስተጋብራችን ወዘተ… ሊሆን ሲገባ ነጋ መሸ ፖለቲካ ሲከኩና ሲሰልቁ እንዲውሉ ተገድደዋል።
የሰሞኑን እጅግ አሳዛኝ ክስተት ብቻ እንደማሳያ ወስደን “እነማን ለምን ፈጸሙት?” የሚለውን ለምርመራና ለጊዜ ብንተወው እንኳን መገዳደል መደማማቱ በራሱ እኛው በእኛው የተፈጸመ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ከሃሳብና ከእስክሪፕቶ ንግግር እንዲሁም ከሕግ ልዕልና ይልቅ ዛሬም ጥይትን መነጋገሪያ ቋንቋችን የማድረግ አባዜ እንዳልተላቀቀን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ይህ እንደ ሕዝብ አንገት የሚያስደፋና አሳፋሪም ነው።
በመሆኑም ሁሉም ዜጋ ቆም ብሎ ሊያስተውል ይገባዋል። ለሚናገረውና ለሚያደርገው እንዲሁም ለሚወስነው ሁሉ ኃላፊነትን መውሰድ አለበት። ለሕሊና ሚዛን፣ ለሞራል ዳኝነት ምርኮኞች መሆን ያስፈልገናል። ይህ የስልጡንነት መለኪያ ነው። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን አንድ ብለን ቆጥረን ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ብቻ በአገሪቱ የፌዴራል ፓርላማ ብቻ ከ1ሺ 100 በላይ አዋጆች ወጥተዋል።
በየክልል ሕግ አውጪ አካላት የወጡ አዋጆችን ክልሎች ይቁጠሯቸው። አዋጆቹን ለማስፈጸም በሚል የወጡት ደንብና መመሪያዎችማ ለቁጥር ያዳግታሉ። ያም ሆኖ እነዚህ ሁሉ ሕጎች እንደታሰቡት በልዩ ልዩ ጉዳዮች የህዝብን ባህርይ ቀርጸው ከሕግ አክባሪዎችና የሕግ የበላይነት ከነገሠባቸው ስልጡን ሕዝቦች ተርታ ሊያሰልፉን አቅም አላገኙም።
ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ሰከን ሊሉ ይገባል። ሕግን ማክበር የመጀመሪያው ግዴታ ነው። በዚህም ወደ ሞራል ልዕልና መጓዝ ያስፈልጋል። የሕሊና ሰው መሆን የግድ ነው። ሕሊናውን የሚያደምጥ ሰው ግብታዊ አይደለም። ከሕግ አስቀድሞ ለሕሊና መገዛት ያስፈልጋል። በሕሊና መገዛት ክፉ ሃሳብ በአዕምሮ እንዳይፈልቅ ያደርጋል። ቢፈልቅ እንኳን ሕሊና ከሕግ በላይ እና ከሕግ አስቀድሞ ክፉ አሳቢውን ሰው ይቀጣዋል።
ምክንያቱም ሕሊና ክፉ ድርጊትን ብቻ ሳይሆን እኩይ ሃሳብንም ያወግዛልና። ስለሆነም በምክንያታዊ ሕሊና መጓዝ ይጠበቅብናል። ሃሳብ አፍላቂዎች፣ ተደማጭና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ መሪዎች፣ ዜጎች በአጠቃላይ ሁሉም የማህበረሰቡ ክፍሎች ሕግን ማክበርና ለሕግ የበላይነት መከበር ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል። የህግ የበላይነት የሰፈነባቸው ጠንካራ የመንግሥትና የማህበረሰብ ተቋማትም መገንባት አለባቸው። ይህ ሲሆን ነው ለትውልድ የሚተርፍ መልካም ታሪክ ሠርቶ ማለፍ የሚቻለው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011
ከገብረ ክርስቶስ