ወጣት በኃይሉ ሰቦቃ ይባላል። የአስኬማ ኢንጂነሪንግ መስራች ነው፤ ድርጅቱ የመኪና ፍሬን ሸራን በሀገር ውስጥ ያመርታል፤ ወጣት በኃይሉ የመኪና ፍሬን ሸራ አካላትን ከተለያዩ የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶች በማምረት ከውጭ የሚመጣውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችል ሥራ ሰርቷል።
ይህን የፈጠራ ሃሳብ የጠነሰሰው ገና በለጋ እድሜው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለ ነው። ወጣቱ በወቅቱ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ጋራዥ ውስጥ ይሰራ ነበር። በዚያም ሰዎች ‹የፍሬን ሸራ ቶሎ አለቀብን፣ ድምጽ እያሰማ ተቸገርን እያሉ ቅሬታ› ሲያሰሙ ያዳምጥ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ ሃሳብ በአእምሮው ተቀርጾ ሲያስላስለው ይቆያል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቆ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ሲገባ ይህን ሃሳቤን ማበልጸግ ያስችለኛል ያለውን የትምህርት ዘርፍ ለመማር ይወሰናል። ከዚያም መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ትምህርትን መማር ይጀምራል። ዩኒቨርሲቲው ይህን ሃሳቡን የሚያጎለበትበት ቦታ እንደሆነ በማመኑ ለረጅም ጊዜ በአእምሮው ተቀርጾ የቆየውን ሃሳቡን በማውጣት የመመረቂያ ጽሑፍ እንዲሆነውም አደረገ። ከዩኒቨርሲቲ ከወጣ በኋላ ጽሑፉን ወደ ተግባር ለመተርጎምና ህልሙ እውን እንዲሆን በማሰብ ወደ ትግበራ ገባ።
በ2014 ዓ.ም የአስኬማ ኢንጂነሪንግን በመመስረት ሥራውን አሃዱ ብሎ ጀመረ። ለዚህም መጀመሪያ የሚያስፈልገውን ብድር በመውሰድ የመኪና ፍሬን ሸራን ከተለያዩ የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶች (ከእንሰሳት አጥንት፣ ከወዳደቁ ቆዳዎች እና ከሴራሚክ ብናኝ) ማምረት ቻለ።
በኃይሉ ወደ ሥራው ሲገባ የገዛቸው ማሽኖች ቢኖሩትም፣ በገበያ ላይ ለተመለከተው ሥራ የሚሆን ማሽን እንደሚያስፈልገው አመነ። ይሁንና እሱ የሚፈልገውን ዓይነት ማሽን ለማግኘት ተቸግሮ እንደቆየም ያስታወሳል። አድርጎ ወደ መስራት ገባ፤ የመካኒክነት ሙያውን ተጠቅሞ ማሽኖቹን በራሱ ልክ ሰራቸው። ‹‹በገበያ ላይ ያገኘኋቸው ማሽኖች ግጥም /ጠበቅ ያሉ አልነበረም፤ ስለዚህ ሙያዬን ተጠቅሜ ለሥራው በሚያመቸኝ መልኩ እንደገና አሻሽዬ ሰርቻለሁ ›› ይላል።
እሱ እንደሚለው፤ ከውጭ የሚመጣውን የመኪና ፍሬን ሸራ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ያለመው ይህ የፈጠራ ሥራ፣ ከፍሬን ሸራ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ዘርፈ ብዙ ችግሮችንም ለመቅረፍ ይረዳል። በመጀመሪያ ደረጃ የፍሬን ሸራ በመገንጠሉ የተነሳ የሚከሰተውን አደጋ ይከላከላል። በሁለተኛ ደረጃ የፍሬን ሸራ ለማምጣት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ያስቀራል። በሦስተኛ ደረጃ ይህ ምርት በሀገር ውስጥ መመረቱ ከኢንዱስትሪ ወጥተው አካባቢን ለብክለት የሚዳርጉ ተረፈ ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ያስችላል።
ፍሬን ማለት መኪናን የሚቆጣጠር የመኪና አካል ነው። ከፍሬን ጋር ተያይዞ ብዙ ጊዜ የሚያገጥመው ችግር ደግሞ የፍሬን ሸራ መገንጠል ነው። የፍሬን ሸራ ሲገነጠል ተሽከርካሪው በምንም ነገር ሊቆም የማይችል በመሆኑ ለከፍተኛ አደጋ ያጋልጣል። መኪናውን ማቆም የሚቻለው ከሆነ ግዑዝ አካል ጋር በማጋጨት ብቻ መሆኑን ገልጿል፤ ስለዚህ የፍሬ ሸራ በጥንቃቄና በተሟላ መልኩ መስራት ይኖርበታል ይላል።
በሀገሪቱ እስካሁን ድረስ የፍሬን ሸራ ምርቶች ከውጭ ብቻ ነበር የሚመጡት፤ በሀገር ውስጥ የሚሰራ ምንም ዓይነት ፍሬን ሸራ አልነበረም›› የሚለው በኃይሉ፤ ምርቱን ሀገር ውስጥ በማምረት መተካት እየተቻለ ከውጭ ለማምጣት ከፍተኛ ወጪ ሲወጣ ኖሯል፤ ምርቱን በሀገር ውስጥ በማምረት ይህን ወጪ ማስቀረት ይቻላል ሲል ያብራራል።
በተጨማሪም የማይፈለጉና የሚጣሉ የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል አካባቢን ከብክለት የሚታደግ መሆኑን አስታውቆ፣ እነዚህን ተረፈ ምርቶች ለሚሰበስቡና ብረት ለሚያቀርቡ ሰዎችም የሥራ እድል እንደሚፈጥር ይናገራል።
እሱ እንዳለው፤ በሀገር ውስጥ የሚመረተው የፍሬን ሸራ ከውጭ ከሚመጣው ጋር ሲነጻጻር በጥራት ይለያል። ከውጭ የሚገባው እይታን ይስባል፤ ሀገር ውስጥ የሚመረተው እይታን በመሳብ በኩል ከውጪ የሚገባውን ያህል ባይሆንም፣ ለየት ያለና ከፍተኛ ጥራት ያለው ነው። ‹‹እኛም ትኩረት አድርገን የሰራነው ረጅም ጊዜ እንዲያገለግልና ጠንካሬ ላይ ነው እንጂ ውበት በመስጠት ረገድ ምንም ኢንቪስት አላደረግንም›› ይላል።
ከውጭ የሚመጣውና በሀገር ውስጥ የሚመረተው ከሚጠቀሙባቸው ግብዓቶች ጀምሮ ልዩነት አላቸው። በውጭ ይህንን ምርት ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውለው ግብዓት የማዕድን ውጤት ነው። ይህ ደግሞ ለሰው ልጆች ከጤና ጋር በተያያዝ የጎንዮሽ ጉዳት እንደሚያስከትል ጥናቶች ያረጋግጣሉ። በሀገር ውስጥ የሚመረተው ፍሬን ሸራ ግብዓቶች ግን ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያስከትሉ በላብራቶሪ ጭምር ተፈትሸው የታዩ ናቸው ሲል ያስረዳል።
ከዋጋ አንጻር ሲታይ በሀገር ውስጡ ምርት ውጭ ከሚመጣው ተመጣጣኝና በሦስት እጥፍ ያነሰ ነው የሚለው ወጣት በኃይሉ፤ ሀገር ውስጥ እንደመመረቱ መጠን ወጪውን የሚሸፈን ከሆነ በቂ ነው በሚል የወጣ ዋጋ መሆኑን ይናገራል። በተጨማሪ ለምርቶቹ የሚያስፈልጉት ግብዓት በቅርበት መገኘታቸውና እነሱን ለማምጣት የሚያስፈልገው ወጪ ብዙ አለመሆኑን ጭምር ከግንዛቤ ያስገባ ተመን የተሰጣቸው መሆኑን ይገልጻል።
ወጣት በኃይሉ እንዳብራራው፤ አብዛኛዎቹ የመኪና እቃዎች ከቻይና የሚመጡት በመሆናቸው የአፍሪካን መልከዓ ምድርና አየር ንብረት ብዙም ከግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ አይደሉም። ይህ ምርት ግን ከአካባቢ ጋር እንዲስማማ ተደርጎ ለእያንዳንዱ መኪና በሚሆን መልኩ የሚሰራ ነው።
ከቻይና የሚመጣው ምርት ቀዝቃዛ ቦታዎችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተሰራ እንጂ የኢትዮጵያ መልከዓ ምድርና አየር ንብረት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ስለማይሰራ ሥራ ላይ ሲውሉ ብዙ አደጋዎችን ሊያስከትሉ። ጥራታቸውም ቢሆን አነስተኛ ነው። እንደ ሀገር ያለው የመግዛት አቅም አነስተኛ በመሆኑ ለሌሎች ሀገራት ከሚላከው ያነሰ ጥራት ያለው ምርት ነው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት።
ለማምረቱ ሥራ የሚያስፈልጉት ግብዓቶች ሁሉ በሀገር ውስጥ ይገኛሉ። ምንም ዓይነት ከውጭ የሚመጣ ግብዓት የለም። ምርቱን ለማምረት የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችና ብረታ ብረት ጥቅም ላይ ይውላሉ። የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶቹን በቀላሉ ማግኘትም ይቻላል። ብረቱንም ቢሆን እዚሁ ካሉ ጋራዦች ማግኘት ይቻላል።
አሁን ላይ ምርቱን አምርቶ በበቂ ሁኔታ ለገበያ ለማቅረብ የመሥሪያ ቦታና የገበያ ትስስር ችግር መኖሩን በተግዳሮትነት የሚያነሳው ወጣት በኃይሉ፤ ምርቱን በሀገር ውስጥ ለማምረት የመሥሪያ ቦታ ጥበት ችግር እንዳለበት አመልክቷል። ምርቱ ገና አለመለመዱም ሌላው ገበያው ሰብሮ ለመውጣት ያለበት ችግር መሆኑንም ጠቁሟል። ብዙ ሰዎች ስላልተረዱት ምርቱን ገዝተው ለመጠቀም ፍላጎቱም የላቸውም፤ ይጠራጠራሉ ሲል ያመለከተው ወጣት በኃይሉ፣ ምርቱን ደፍረው ገዝተው የተጠቀሙ ግን ‹‹ለካ እንዲህ ነው እንዴ፤ እስከ ዛሬም ተሞኝተናል›› በማለት አድናቆትና እየገለጹለት መሆኑን ተናግሯል።
እሱ እንዳለው፤ በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ በቀን 270 ያህል የፍሬን ሸራዎችን የማምረት አቅም ያለው ቢሆንም፣ አሁን ላይ በቀን 30 ያህል ብቻ እያመረተ ነው። ለዚህ ዋንኛው ምክንያቱ ገበያው አለመኖሩ ነው። ገበያው እንደልብ ቢገኝ የማምረቱ አቅም እንዳለው ይገልጻል። ተደራሽነት ማስፋትና የገበያ ትስስር መፍጠር ላይ እምብዛም እንዳልሰራም አመላክቷል።
ድርጅቱ ሥራውን ከጀመረ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል፤ እስካሁን ሦስት ሺ ያህል የፍሬን ሸራዎችን ሸጧል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገበያው ቀደም ሲል ከነበረው ገበያ አንጻር ሲታይ ለውጥ እያሳየ መሆኑን በኃይሉ ጠቅሶ፣ አሁን ምርቱን ብዙዎች እያወቁት መምጣታቸውን ገልጿል። ከዚህም ገበያውም በዚያው ልክ እየጨመረ መምጣቱን መረዳት እንደሚቻል ይገልጻል። ‹‹ እኔ አምኜበት ነው የገባሁት፤ የጊዜ ጉዳይ ሆኖ እስኪለመድ እንጂ ብዙ ሰዎች ሲረዱት ገበያው ይመጣል። የገበያ ችግር ይገጥመናል ብዬ አላሰብም›› ይላል።
ድርጅቱን ከመሰረተ በኋላ ማሽኖች ለመግዛት ብድር ወሰዶ እንደነበር ያስታወሰው ወጣት በኃይሉ፣ አሁን ብድሩን ከመመለስ በዘለለ የኤሌክትሪክ ሞተር መግዛት መቻሉን ይናገራል። አሁን ያለው የገበያ እንቅስቃሴ ቢሆንም መጥፎ የሚባል እንዳልሆነ ተናግሮ፣ ገበያው ላይ በደንብ ቢሰራ ደግሞ ከአቅማችን በላይ ሊሆንና ማምረት የማንችልበት ደረጃ ሊያደርሰን ይችላል ሲል ያስረዳል።
የማምረቱ ሥራ ጥናት ላይ ተመርኮዞ እንደሚካሄድ ተናግሮ፣ ለ20ሺ ኪሎ ሜትር ያህል አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ እየተመረተ መሆኑን ገልጿል። የ3ሺ ኪሎ ሜትር ዋስትና እንደሚሰጥም ይናገራል።
ወጣት በኃይሉ እንደገለጸው፤ ይህ የፈጠራ ሥራ በአእምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ተመዝግቦ የባለቤትነት ማረጋገጫ አግኝቷል። የፈጠራ ውጤቱ በላብራቶሪ ተፈትሾ ማረጋገጫ ስለሚያስፈልገው ይህንን የሚሰጠው የጥራትና ተሰማሚነት ድርጅት የመኪና እቃዎች የላብራቶሪ ውጤት ስታንዳርድ ስለሌለ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአሜሪካ ላብራቶሪ ስታንደርድ መሠረት ሰርቶ የላብራቶሪ ውጤት ስታንደርድ ሰጥቶታል።
የፈጠራ ሥራው በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በተዘጋጀው በብሩህ ኢትዮጵያ የፈጠራ ውድድር ተወዳድሮ አሸናፊ መሆን ችሏል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮሪያ ጋር ባዘጋጀው የኢኖቢዝኬ ኢትዮጵያ ላይ ተወዳድሮ ስልጠናዎችንና ማበረታቻዎችን አግኝቷል። ከተለያዩ ቦታዎች ማበረታቻዎች ማግኘት መቻሉም አስታውቋል።
ድርጅቱ ለስድስት ሰዎች በቋሚነት የሥራ እድል የፈጠረ መሆኑን ጠቅሶ፣ ሥራ በሚበዛበት ሰዓት ደግሞ እስከ 15 ለሚደርሱ ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል እንደሚፈጥር አስታውቋል። በተለይ የቦሎ ሰዓት ሲደርስ ብዙ ጊዜያዊ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ ይገልጻል።
በኃይሉ እንዳብራራው፤ ይህ የፈጠራ ውጤት በላራቦቶሪ ተፈተሾ ያለፈ በመሆኑ አመርቶ ለመጠቀም ምንም ችግር የሚሆንበት ነገር የለም። በቀጣይ የመጀመሪያ ሥራው የሚሆነው ገበያ መሥራት ሲሆን፣ እዚያ ላይ ኢንቪስት ያደረጋል። ሁለተኛው አሁን እየሰራባቸው የሚገኙ ማሽኖች በጣም ጥሩ የሚባሉ ቢሆኑም፣ ዘመኑ ያፈራቸውን ማሽኖች ያስፈልጉታል። ገበያ ላይ አውቶሜሽን (ኮምፒዮተር መሠረት ያደረጉ ሲኤምሲ ማሽኖች›› በጣም እያደጉ ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ እነዚህ ማሽኖች እንዲኖሩት ይፈልጋል። ምክንያቱም አሁን አንድ ሺ400 ዓይነት የመኪና ካታሎግ ዓይነቶች ስላሉ ለእያንዳንዱ የሚሰራው ሥራ የተለያዩ ዓይነት ነው። ይህም ሆኖ ደግሞ ካታሎግ የሌላቸው መኪናዎች አሉ።
‹‹ለምሳሌ የቻይና መኪናዎች ካታሎግ የላቸውም። ስለዚህ እኛ የመኪኖችን ካታሎግ መሥራት ይጠበቅበናል፤ እንሰራለን፤ ሰርተን እንቆርጣለን። ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ማሽን ግን የለንም። ስለዚህ በቀጣይ ይህን ማሽን መግዛት፣ ወርክሾፕ እና የገበያ ተደራሽነት ማስፋት ላይ መሥራት ይጠበቅብናል›› ይላል።
‹‹ወደዚህ ሥራ ስገባ ብዙ ፈታኝ ነገሮች ገጥመውኝ ነበር፤ ነገር ግን በቤተሰቦቼ አጋዥነት ፈተናዎቹን በድል ተሻግሬ አሁን ላለሁበት ደረጃ ደርሻለሁ።›› የሚለው በኃይሉ፤ በመንግሥት በኩል የመሥሪያ ቦታ ድጋፍ ተደርጎለት እንደነበርም አስታውሰዋል። መሥሪያ ቦታ፣ መብራትና የመሳሰሉት እንዳልተሟሉለት አመልክቶ፣ በዚያ ቦታ ላይ ለመሥራት በመቸገሩ መልቀቁን ይገልጻል። ወደ ሥራ የሚገቡ ጀማሪዎችን ለማበረታት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል ሲል ጠይቋል።
ወደ ሥራ የሚገቡ ጀማሪ የፈጠራ ባለሙያዎች ከመሥራት ወደኋላ ማለት እንደሌለባቸውም ይመክራል። ብዙ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም፣ ችግሮቹን አልፈው ወደፊት ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ ይህን ማድረጋቸው ያለሙበት ለመድረስ ያስችላቸዋል ሲል ተናግሯል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም