ትከሻቸው ላይ ጣል ያደረጓትን ሻርፕ ወደፊት ሳብ አድርገው በአንድ እጃቸው ዓይናቸውን ይጠርጋሉ። በሌላ እጃቸው በርከት ያሉ ወረቀቶች እንዳሉት በመሙላቱ የሚያሳየውን ካኪ ፖስታ ይዘዋል። ሁኔታቸው ከላይ እስከታች እንድመለከታቸው አስገደደኝ። አንገታቸውን ወደ መሬት እንዳቀረቀሩ ዝግ ያለ ዕርምጃቸውን ቀጥለዋል። በመካከላችን የነበረው ርቀት እየቀነሰ መቀራረባችንም እየጨመረ መጣ።
ከአጠገቤ ሲደርሱ ሐዘን እንደጎዳው የሚያሳብቀውን አንገታቸውን ቀና አድርገው በማንባት ብዛት በቀሉት ዓይኖቻቸው በአርምሞ እየተመለከቱኝ ችግር አጋጥሟቸው አቤት የሚሉበት ሽተው መምጣታቸውን ነገሩኝ። አረፍ እንዲሉ ስጋብዛቸው ነበር የታመቀው ብሶታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ዓይኖቻቸው ድምፅ አልባ መንታ መንታ የእንባ ዘለላዎችን ያወርዱ የጀመሩት። እንዲረጋጉና ወደ ተቋማችን ምን እግር እንደጣላቸውም ጥያቄ አቀረብኩላቸው።
ከአንደበታቸው
ወደ ተቋሙ እንዲመጡ ያስገደዳቸው በፍርድ ቤት የተላለፈባቸው ልብ ሰባሪ ውሳኔ መሆኑን በመግለጽ፤ ከኦሮሚያ ክልል ከሰበታ እንደመጡ ነገሩን። የውሳኔው መነሻ ስለሆነው ጉዳይ ሲናገሩም በሚኖሩበት ከተማ በቀበሌ 01 የሚገኘው የቤት ቁጥሩ 1410 የሆነው መኖሪያ ቤታቸው እንደሆነ ገለጹልን። ይዞታውን በ1984 ዓ.ም በምሪት እንዳገኙት የሚናገሩት ወይዘሮ ታደለች ደምሴ፤ በአሁኑ ወቅት ቅሬታ ከሚያቀርቡባቸው የቀድሞ ባለቤታቸው ጋር በአንድ ጣሪያ ስር መኖር ሳይጀምሩ በፊት ሁለት ክፍል ቤት እንደነበራቸው ያስታውሳሉ። ሕይወትን በጋራ ለመግፋት ወስነው መኖር ከጀመሩ በኋላም በዚሁ ቤት አምስት ልጆችን አፍርተው አንዱን ቀብረዋል።
ምንም እንኳ ትዳራቸው ሕጋዊ ውል ያሰረው ባይሆንም ከውሃ አጣጫቸው ጋር የጀመሩት ሕይወት እንዳሰቡት ሳይሆን ይቀርና ባለቤታቸው ገባ ወጣ ሲሉ ይህን የተመለከቱ ሽማግሌዎችም አንድነታቸውን ሊመልሱ ሲያስታርቋቸው ይቆያሉ። ሆኖም ከስምንት ዓመታት በፊት ይኖሩበት ከነበረው ቤት ባለቤታቸው አቶ ቁምላቸው መሰሉ ጠቅልለው እንደወጡ ወይዘሮ ታደለች ይናገራሉ። ነገሩም እንዲህ በቀላሉ ሳይቋጭ ጉዳዩ የንብረት ክርክር አስነስቶ ወደ ፍርድ ቤት ያመራል። የወረዳ ፍርድ ቤት ባስቻለው ችሎት ላይ የሰነድ ማስረጃ ተመርምሮ የሰው ምስክሮችም ቀርበው ከተደመጡ በኋላ ንብረቱ ከጋብቻ በፊት የተፈራ በመሆኑ ለወይዘሮ ታደለች ይወሰንላቸዋል።
በወረዳው ፍርድ ያልረኩት አቶ ቁምላቸው፤ ወደ ክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያመራሉ። የራሳቸውና የቀድሞ ባለቤታቸው ጠበቆች ያስፈረሟቸው ሰነድ ፊደል አለመቁጠራቸው ምን ያክል እንደጎዳቸው ያወቁበት አጋጣሚም እንደሆነ በማንሳት ይረግሙታል። በወቅቱ በጋራ አራት ልጆችን ያፈሩ ወላጆችን የራሳቸው ጠበቃ ጨምሮ ተመሳጥረው እህትና ወንድም አድርገው ለክልሉ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዳቀረቧቸውም ያስታውሳሉ። ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ ዋናውን ቤት ለወይዘሮ ታደለች በመወሰን አምስት ክፍል ሰርቪስ ቤቱ ግን አቶ ቁምላቸው ወጣ ገባ እያሉ የተሠራ በመሆኑ የጣራና ግድግዳ ግምት ተገምቶ ግማሹ እንዲሰጣቸው ሲል የወረዳ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ያሻሽለዋል።
የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅሬታ የፈጠረባቸው አቶ ቁምላቸው፤ አቤቱታቸውን ይዘው ወደ ልዩ ዞን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቅናታቸውን ይናገራሉ። ፍርድ ቤቱም እኩል ይካፈሉ ሲል ይወስናል። ወይዘሮ ታደለችም ይግባኝ ወስደው ወደ ክልሉ ሰበር ማምራታቸውንና ጉዳዩን ገልጦ ሳይመለከት ከበር እንደመለሳቸው ነው የሚያስታውሱት።
ከፊደል ገበታ ቀርበው ከዓለማዊው ዕውቀት ባይቀስሙም በአንድ በኩል ሕይወት በልምዷ ከትልቅ ትምህርት ቤት አስገብታ ባሳየቻቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ያለ አባት ለብቻቸው በሚያስተምሯቸው ልጆቻቸው ውስጥ ትምህርትን በማግኘታቸው ጉዳዩ ከምን ፍጥነት ተጠንቶ ተወሰነ የሚል ጥያቄ በወይዘሮ ታደለች ውስጥ ይፈጠራል።
ከ15-20 በሚሆን ደቂቃ ውስጥ ተጠርተውም ጉዳዩ አልተጠናም ስላሉ ለእርሳቸው ደስታ እንጂ ጉዳዩ መመርመሩ እንደተገለጸላቸው ነው የሚናገሩት። በመሆኑም በጉዳዩ ላይ ያረፈው ውሳኔ የሚሻርበት አግባብ እንደሌለም ምላሽን ያገኛሉ።
ጉዳያቸውን ከኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይዘው ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማምራታቸቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ታደለች፤ ፍርድ ቤቱ በክልሉ ሰበር የተወሰነላቸውን ውሳኔ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ለእርሳቸው እንደተወሰነላቸው ይገልጻሉ። ከአራት ወራት ቆይታ በኋላም ደስታቸውን እንኳ በቅጡ ሳያጣጥሙ ያላቸው 320 ካሬ ሜትር ብቻ ቢሆንም የቀረ ንብረት እንዳለ በማድረግ የቀድሞ ባለቤታቸው አቶ ቁምላቸው ጠበቃ ጉዳዩን ዳግም በማንሳታቸው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ይመጣላቸዋል።
ወይዘሮ ታደለች፤ ለጉዳዩ አራት ጠበቃ መያዛቸውን ይገልፃሉ። በዚህም በርካታ ጥሪታቸውን እንደጨረሱም በጉንጫቸው የሚወርደውን እንባ አበስ እያደረጉ ያስረዳሉ። አረቄ አውጥተው እንጀራ ጋግረው አራት ልጆቻውን እንደሚያስተዳድሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ታደለች፤ ሥራቸውን ጥለው እንዳይሄዱና ጉዳዩን እንደሚጨርሱላቸው ከጠበቃቸው የተሰጣቸውን ተስፋ ሰንቀው እየተጠባቁ በአራት ወሩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔ የመሻሩን መርዶ ይሰማሉ።
ያሳደጓት የወንድማቸው ልጅ ሠርታ የመለወጥን ራዕይ ይዛ ከተሰደደችበት አረብ አገር በምትልከው ገንዘብና ክርክር የተነሳበት ቤት ዕድሳትም በእርሷ ድጎማ የተደረገ እንደሆነ ይናገራሉ። ‹‹ያዘመመችውን ጎጆዬን ልጆቼ እንዳያድጉባት ልነጠቅ ነው፤ የፍትህ ያለህ›› ሲሉም ጩኸታቸውን ያሰማሉ። አምስት ዓመታትን ፍርድ ቤት መጥናታቸውንም በምሬት ይናገራሉ።
ያሳደጓት ልጃቸው ደርሳላቸው ቤቱን መሥራታቸውን የሚያሳዩ የባንክ ቤት ደረተሠኞች መኖራቸውንና በአሁኑ ወቅት የሚሞግቷቸው የቀድሞ ባለቤታቸው እንኳን ቤት ለመሥራት የሚያስችል ለልጆች ቀለብ የሚሆን ተቆራጭ ማድረግ የሚችል የኢኮኖሚ አቅም እንደሌላቸው ነው የሚገልጹት። ለዚህም ደግሞ በ2006 ዓ.ም በሥር ፍርድ ቤት ላይ የልጆች ቀለብ አስመልክቶ ተከሰው የተወሰነው ውሳኔ ማሳያ ነው ይላሉ። ለዚህም ይረዳሉ ያሏቸውን ሰነዶች ከፖስታ ያወጡ ጀመር።
በቅድሚያም እ.አ.አ በ11/10/2017 ማለትም ከሁለት ዓመታት በፊት በዳሸን ባንክ ሰበታ ቅርንጫፍ በዌስተርን ዩኒየን በኩል ለወይዘሮ ታደለች 5 ሺህ 780 የአሜሪካ ዶላር በገንዘብ ዝውውር መቆጣጠሪያ ቁጥር 1750480188 በሆነ ላይ መላኩና በአገር ውስጥ ምንዛሬም 155 ሺህ 692 ብር ከ 97 ሣንቲም ተለውጦ እንደተሰጣቸው በደረሰኙ ይታያል። ቀጥለውም ይዞታው በስማቸው የሆነና ካርታ ቁጥሩ ሰ/454/84፣ ብድር እየወሰዱ ቤታቸውን መሥራታቸውን ለመግለጽ ከአፍሪካ መንደር የፋይናንስ አገልግሎት አቅራቢ አክስዮን ማህበር የደንበኛ መለያ ቁጥር 19000144 የሆነ ደብተር ብሎም ሌሎች ሰነዶችን ያሳዩን ጀመር።
የፍርድ ሂደት
የሰ/መ/ቁ.130007 መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመልካች ወይዘሮ ታደሉ ሆነው መዝገቡን መርምሮ የሰጠው የፍርድ ሂደትና ውሳኔ ከሰነዶቹ መካከል አንዱ ነው። የጉዳዩን አመጣጥም የባልና የሚስት የንብረት ክርክር መሆኑን በማተት፤ በወረዳ ፍርድ ቤት ላይ አቶ ቁምላቸው ከሳሽ ወይዘሮ ታደለች ደግሞ ተከሳሽ እንደነበሩ አስፍሯል። በዚህም አቶ ቁምላቸው ጋብቻ እንዲፈርስና የንብረት ክፍፍል እንዲደረግ ዳኝነት የጠየቁ ሲሆን፤ ወይዘሮ ታደለች ለሰበሩ ምክንያት የሆነውን ቤት የግል ንብረት ነው በማለት ተከራክረዋል።
ሰነዱ፤ ጉዳዩን የተመለከተው የሰበታ አዋስ ወረዳ ፍርድ ቤት ግራና ቀኙን ክርክርና የምስክሮችን ቃል ከሰማ በኋላ ለክርክሩ ምክንያት ከሆነው ቤት አምስት ክፍል ሰርቪስ ቤቶች ባልና ሚስት በትዳር ውስጥ እያሉ በጋራ የሠሩት መሆኑን በማስረጃ እንዳጋገጠ ያስቀምጣል።
ይህ ቤትም ከተገመተው ብር 65 ሺህ 668 ብር ከ75 ሣንቲም ለአቶ ቁምላቸው ድርሻቸው በመሆኑ ግማሹን የሰበሩ አመልካች የሆኑት ወይዘሮ ታደለች እንዲሰጡ ይወስናል። ትልቁን ቤት በተመለከተም ምንም እንኳ ጋብቻ ባይፈርስም ተጠሪ ከቤት ከወጡ በኋላ አመልካች ቤቱን የሠሩት መሆኑ ስለተመሰከረ ትልቁ ቤት አቶ ቁምላቸውን እንደማይመለከታቸው መወሰኑ የሰ/መ/ቁ.130007 መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም በወጣው የፍርድ ሂደቱን በሚያሳየው ሰነድ በዝርዝር ሰፍሮ ይገኛል።
የግራና ቀኙ በውሳኔው ላይ ቅር በመሰኘትም በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀርባሉ። አቶ ቁምላቸውም ትልቁ ቤት የወይዘሮ ታደለች ብቻ ተደርጎ መወሰኑ ያለአግባብ መሆኑን በመግለጽ፤ ቤቱ የጋራ ንብረት ነው ተብሎ መወሰን እንደሚገባቸው ቅሬታ ያነሳሉ።
በዚህም ሰርቪስ ቤቶችንም በተመለከተ ቤቱ ከተገመተው ግማሽ ድርሻ ብቻ እንዲወሰድ የተወሰነው ውሳኔ ታርሞ ከቤቱ ድርሻ በዓይነት እንዲያገኙ እንዲወሰን የሚል ሲሆን፤ ወይዘሮ ታደለች ደግሞ ሰርቪስ ቤቶቹም ቢሆኑ ለተጠሪ አይገባም በማለት ይግባኝ ያቀርባሉ።
የልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራና ቀኙን ይግባኝ ተቀብሎ ካከራከረ በኋላም ትልቁን ቤት በተመለከተ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ተቀብሎ ያፀናል። ነገር ግን አምስት ክፍል ሰርቪስ ቤቶቹ ግን የግራ ቀኙ ንብረቱን በዓይነት እኩል እንዲካፈሉ ወይም በይግባኝ ባይ /አቶ ቁምላቸው/ ፍላጎት የሰርቪስ ቤቶቹን ግምት ግማሽ መልስ ሰጪ /ወይዘሮ ታደለች/ ለይግባኝ ባይ በመክፈል እንዲያስቀሩት በማለት የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ያሻሽለዋል።
በውሳኔው ቅር የተሰኙት አቶ ቁምላቸውም ትልቁ ቤት የጋራ ሊሆን ይገባል ሲሉ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ያቀርባሉ። የይግባኝ ሰሚው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ይግባኙን ተቀብሎ የግራና ቀኙን ካከራከረ በኋላ በቁጥር 1410 የሆኑት ቤቶች ተመዝግበው የሚታወቁት በ320 ካሬ ሜትር ላይ የሚገኝ ለዚህ ክርክር ምክንያት የሆነው ሁሉ ለይግባኝ ባይ ወይንም ለአቶ ቁምላቸው እና መልስ ሰጪ/ ወይዘሮ ታደለች/ እኩል ይካፈሉ ሲል ውሳኔውን ያሳርፋል። ውሳኔውንም ወይዘሮ ታደለች ለማስቀየር ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታቸውን ማቅረባቸውንና በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 337 መሠረት ዝግ እንደተደረገባቸው በሰነዱ ሰፍሯል።
መጋቢት 29 ቀን 2009 የተደረገው የሰበር ችሎት ላይ የቀረበው አቤቱታም በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ንብረቱን ለጋራ እንዲካፈሉ የተወሰነውን ውሳኔ ለማስለወጥ ሲሆን፤ አቤቱታውም በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ያብራራል። የመጀመሪያው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ይግባኝ በመቀበል የሰጠው ውሳኔ ሥነ ሥርዓታዊ አይደለም የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የሚያከራክረውን ቤት የሚመለከት ሆኖ የአቶ ቁምላቸው አስተዋፅዖ በሌለበት በአመልካች ጥረት የተሠራውን ቤት የጋራ ንብረት ነው ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ እንዲታረም የሚል ነው።
የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በተጠሪ ይግባኝ ቅሬታ መነሻነት ለተጠሪ በሚጠቅም መልኩ የወረዳ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማሻሻል መወሰኑን ሰነዱ ዋቢ አድርጎ ያነሳል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ችሎትም በድጋሚ የተጠሪን ይግባኝ አቤቱታ ተቀብሎ በማየት የመወሰኑ አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ተደርጓል።
በዚህም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ችሎት በአቶ ቁምላቸው በድጋሚ ለሁለተኛ ጊዜ የቀረበውን ይግባኝ ተቀብሎ ማየቱ ሕጋዊ ነው ወይ? የሚል ጭብጥ ተይዞ ጉዳዩ መመርመሩ በሰነዱ በግልጽ ይታያል።
ለዚህ ሰበር ችሎት መከራከሪያ ምክንያት የሆነው ቤት የሰበታ አዋስ ወረዳ ፍርድ ቤትም ሆነ በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተመሳሳይ ውሳኔ መስጠታቸውን የሚያብራራው ሰነዱ፤ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩ በድጋሚ በይግባኝ ሲቀርብለት ይግባኙን ተቀብሎ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በማሻሻል መወሰኑንም ያስቀምጣል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 141/2000 አንቀጽ 29 በፍትሐ ብሔር ጉዳይ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የፀደቀ እንደሆነ ውሳኔው የመጨረሻ ይሆናል በማለት ይደነግጋል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በአቶ ቁምላቸው በድጋሚ ለሁለተኛ ጊዜ የቀረበውን ይግባኝ ተቀብሎ ማየቱ የተጠቀሰውን ድንጋጌ የጣሰ ነው ሲልም ይተቸዋል።
በተያዘው ጉዳይ በሰበታ አዋስ ወረዳ ፍርድ የተሰጠ ውሳኔ በዚህ ሰበር ተጠሪ ሆነው በቀረቡት አቶ ቁምላቸው አቅራቢነት በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታይቶ የፀደቀ በመሆኑ ሁለተኛ ይግባኝ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሊቀርብ የሚችልበት የሕግ አግባብ የለም ሲልም ትክክል እንዳልነበር ያስረዳል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም ይህንን ማረም ሲገባው የቀረበውን አቤቱታ መዝጋቱ ሲታይ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ እንደተገኘ መጋቢት 29 ቀን 2009 የዋለው የሰበር ሰሚ ችሎት ማስፈሩ ከሰነዱ ይታያል።
ሂደቱን መነሻ በማድረግም የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔውን ያሳርፋል። በዚህም የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 227899 በቀን 4/8/2008 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እንዲሁም የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 242816 በቀን 12/09/2008 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ፤ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 348/1/ መሠረት ይሽረዋል። በተጨማሪም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም በወጣ አዋጅ ቁጥር 141/2000 አንቀጽ 29 መሠረት ሁለተኛ ይግባኝ ማቅረብ አይቻልም ሲል ውሳኔውን ያሳርፋል።
በመዝገብ ቁጥር 268959 በቀን 13/10/2009 ለወይዘሮ ታደለች ባሉበት በሚል የተጻፈው ደብዳቤ ሌላኛው የተመለከትነው ሰነድ ነው። በተላከላቸው ደብዳቤ ላይ ሰፍሮ እንደሚገኘው፤ የሰበር ማመልከቻ ክርክር አመልካች አቶ ቁምላቸው መሰሉ እና መልስ ሰጪ መካከል ያለውን በተመለከተ በፍርድ ቤቱ ቀርቦ ከተመረመረ በኋላ መልስ ሰጪ ያስቀርባል ተብሏል ይላል። ስለሆነም ለ11/11/2009 ዓ.ም ከሰዓት በፊት ለሰበር ችሎት መልሳቸውን በጽሑፍ አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ ሲል ፍርድ ቤቱ ማዘዙን ያሳያል። በቀን 12/10/2009 ዓ.ም የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 325 ጊዜ ያለፈበት ይግባኝ ለማስፈቀድ የቀረበ ሲል ባሰፈረው ደብዳቤ ላይ አቶ ቁምላቸው መሰሉ በአመልካችነት የቀድሞ የትዳር አጋራቸው የነበሩትንና ወደ ተቋማችን መጥተው ቅሬታ ያቀረቡትን ወይዘሮ ታደለች ተጠሪ አድርጎ ያሰፍራል።
በሰበታ አዋስ ወረዳ ፍርድ ቤት የባልና ሚስት ፍቺ እና የንብረት ክፍፍል በመዝገብ ቁጥር 42455 ላይ ባቀረቡት ላይ ፍርድ ቤቱ ግራና ቀኝ ካከራከረ በኋላ በመካከላቸው ያለውን ጋብቻ ማፍረሱን ያስረዳሉ። ሆኖም አራት ክፍል ያለው ትልቅ ቤት በ1990 ዓ.ም በባልና ሚስት ቆይታ ውስጥ በጋራ የሠሩት የወይዘሮ ታደለች የግላቸው ነው መባሉን ማስፈራቸው በሰነዱ ይታያል።
የሠው ማስረጃ ሰርቪስ ቤት ስምንት ክፍል ነው ብለው ሲመሰክሩ ፍርድ ቤቱ በመቀነስ አምስት ክፍል ማለቱና ከአምስቱ ክፍል ውስጥ ደግሞ ድርሻቸው ሁለት ክፍል ከግማሽ እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ ቤትና ቤቱ ያረፈበትን መሬት በማካፈል ድርሻቸው የተሠራበት መሬት ለተጠሪ ወይንም ወይዘሮ ታደለች ከጋብቻ በፊት በግላቸው የተሰጣቸው ስለሆነ እርሳቸው የሁለት ክፍል ከግማሽ ክፍል ቤት ገንዘብ እንዲቀበሉ ውሳኔ ማሳረፉን የሰነድ ማስረጃዎቹ ያመላክታሉ።
አቶ ቁምላቸው፤ በውሳኔው ቅር በመሰኘት ለፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበው ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም በመዝገብ ቁጥር 23883 በሆነው ላይ ቅሬታቸውን ተቀብሎ ማየቱን ያትታል። በኋላም በቀን 23/2/2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ‹‹ትልቁ ቤት የአሁኗ ተጠሪ የግል ንብረት ነው!›› ብሎ የወረዳው ፍርድ ቤት የወሰነው እና ሰርቪስ ቤቶቹን አስመልክቶ ቤቱ የተሠራበት መሬት የተጠሪ ስለሆነ የግርግዳና ጣሪያ ግምት ብቻ እንዲቀበሉ ተደርጎ ውሳኔውን በማሻሻል ድርሻቸውን በዓይነት መቀበል እንዲችሉ መወሰኑን ያስታውሳሉ።
በየደረጃው የነበረውን ክርክር አቶ ቁምላቸው በማንሳት፤ በውሳኔው ቅር በመሰኘት ወይዘሮ ታደለች ወደ ኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም እንኳ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 242815 የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ማጽናቱን በአቤቱታው መግለጻቸውን በሰነዱ አስፍሯል።
ወይዘሮ ታደለች፤ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቅር በመሰኘት ቅሬታቸውን ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ማቅረባቸውም በሰነዱ ላይ ይነበባል። ሰበር ሰሚ ችሎትም ቅሬታቸውን ተመልክቶ ‹‹ያስቀርባል›› ካለ በኋላ ግራ እና ቀኝ ካከራከረ በኋላ በ29/7/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት የፋይል ቁጥር 130007 በሆነው ላይ በሰጠው ውሳኔ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ይግባኝ ተቀብሎ ለማየት ስልጣን ሳይኖረው ተቀብሎ ማየቱ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ነው በማለት መተቸቱን ያሳያል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጠው ውሳኔ መሠረት የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 23883 በሆነው ላይ የተሰጠው ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው ወደ ኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሲያቀርብ የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ በ23/2/2008 ዓ.ም ስለሆነ ጊዜው ያለፈበት እንደሆነ መግለጹን በሰነዱ ይታያል። በመሆኑም በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 325 መሠረት ማስፈቀጃ ካልቀረበ መዝገብ መከፈት የማይችል መሆኑ እንደተነገራቸው አቶ ቁምላቸው በአቤቱታቸው ማሰማታቸው ይነበባል።
አቶ ቁምላቸው፤ የይግባኝ ጊዜ ያለፈባቸው ቅሬታ ማቅረብ በነበረባቸው ቀን ሳያቀርቡ ቀርተው ሳይሆን የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወረዳውን ውሳኔ ማሻሻሉን በመግለጹ እንደሆነ አቅርበዋል። ውሳኔ ሲሻሻል ደግሞ ቅሬታ መቅረብ ያለበት ወደ ኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስለሆነ በዚህ ላይ በመሞርኮዝ ቅሬታዬን አቅርበው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ተቀብሎ ለማየት ሥልጣን ሳይኖረው ተቀብሎ አይቶ ውሳኔ ስለሰጠ፤ ተጠሪ ደግሞ ውሳኔውን በመቃወም ወደ ኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲሁም ፌዴራል በማቅረብ ደረጃ በደረጃ ሲታይ መቆየቱን በመግለጽ ሂደቱን ያብራራሉ።
ችሎቱም ጉዳዩን የሚያስረዱ ማስረጃዎች በመመልከት ጊዜ ያለፈበት በእርሳቸው ጉድለት ሳይሆን የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በከፍተኛ ፍርድ ቤት ላይ የቀረበውን ቅሬታ ተቀብሎ ለማየት ሥልጣን አለው? ወይም የለውም? ሳይል ተቀብሎ ውሳኔ ስለሰጠ ነው ይላል። ውሳኔውም በይግባኝ ታይቶ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ የቆየ በመሆኑ ችሎቱ ይህንን በመረዳት በከፍተኛ ፍርድ ቤት ያላቸውን ቅሬታ እንዲያይላቸው አቶ ቁምላቸው ይጠይቃሉ።
የሰበር መዝገብ ቁጥር 158502 የካቲት 25 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ ወይዘሮ ታደለች አመልካች በመሆን አቶ ቁምላቸው ተጠሪ ሆነው መቅረባቸው ሰፍሯል። በፍርድ ሂደቱም ሙሉ የጉዳዩን ዝርዝር ያትታል። በዚህም በዚህ ችሎት ላይ ተጠሪ የነበሩት አቶ ቁምላቸው በሰበታ አዋስ ወረዳ ፍርድ ቤት በቀን 10/03/2006 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ከአመልካች ወይዘሮ ታደለች ጋር የነበራቸው ጋብቻ ፈርሶ በጋብቻ ውስጥ ያፈሯቸውን የጋራ ንብረቶች አንድ ዋና መኖሪያ ቤት፣ ስምንት ሰርቪስ ቤቶችና የተለያዩ የቤት ዕቃዎችን አመልካች እንዲያካፍሉና ድርሻቸውን እንዲወሰንላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን ያሳያል።
በዚህ ችሎት ላይ አመልካች የነበሩት ወይዘሮ ታደለች ቀርበው በቀን 23/03/2006 ዓ.ም በሰጡት ምላሽ የአሁኑ ተጠሪ የስር ከሳሽ/ አብረው እንዳፈሩ የጠቀሱት ንብረት ከጋብቻ በፊት ያፈሩት ነው በማለት ያስተባብላሉ። ሁለት ክፍል ቤት ሊፈርስ ሲል ማደሳቸውንም እንደገለጹ በፍርዱ ላይ ይነበባል። ትዳራቸው ፈርሶ ከቤት ከወጡ በኋላም ቤቱ በላያቸው ላይ ሊፈርስባቸው ሲል ከሁለት ግለሰቦች ባገኙት ዕርዳታ የመጀመሪያው ቤት ፈርሶ 82 ቆርቆሮ ቤት መሥራታቸው ሰፍሯል።
ከከሳሹ በዚህኛው ችሎት ላይ ተጠሪ ሆነው ቀርበው ከነበሩት አቶ ቁምላቸው ጋር ከተገናኙ በኋላ በጋብቻ ውስጥ በሚገኘው ገቢ አንድም የሠሩት ቤት እንደሌለና የቤት ዕቃዎችን በተመለከተ ከሳሽ (ተጠሪ) ካቀረቡት ውስጥ የተወሰኑት እንዳሉና የጋራ መሆናቸውንም ያምናሉ ሲል ፍርድ ቤቱ በፍርዱ ላይ አስፍሮት ይታያል።
የሰበር መዝገብ ቁጥር 158502 የካቲት 25 ቀን 2011 ዓ.ም ላይ በዋለው የሰበር ችሎት ከሥር ፍርድ ቤት ጀምሮ የነበረውን ሂደት ደረጃ በደረጃ ያብራራል። በመጨረሻም የይግባኝ ሰሚ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኙን ተቀብሎ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ በቁጥር 1410 የሆኑት ቤቶች ተመዝግበው የሚታወቁት በ320 ካሬ ሜትር ላይ በመሆኑ ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ሁሉ አመልካችና ተጠሪ እኩል ይካፈሉ ሲል ይወስናል።
ይህን ተከትሎም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያሳረፈውን ውሳኔ ለማስቀየር ወይዘሮ ታደለች፤ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታቸውን ማቅረባቸውንና በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 337 መሠረት መዘጋቱን ሰፍሯል።
ቀጥለውም አቤቱታውን ይዘው ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀርባሉ። የሰበር አጣሪም አቤቱታቸውን ተቀብሎ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ ማድረጉን እያንዳንዱን ሂደት ያብራራል። በዚህም የቀረበውን አቤቱታ መዝጋቱ ሲታይ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ነው በማለት መወሰኑ በዚህ ሰነድ ላይ ይነበባል።
ውሳኔውን ተከትሎ አቶ ቁምላቸው ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር አቤቱታ ማቅረባቸው በባለ ስምንት ገጽ የፍርድና የውሳኔ ሰነድ ላይ ይነበባል። የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም አቤቱታውን ተቀብሎ የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ በኦሮሚያ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 79 መሠረት የባልና ሚስት ንብረት እንደ ጋራ ንብረት የሚገመት ስለሆነ ንብረቱ የግል ነው በሚል የሚከራከር ወገን ክርክሩን በማስረጃ አቅርቦ ይህንን የሕግ ግምት መስበር አለበት።
በጉዳዩ ላይ መልስ ሰጪዋ ወይዘሮ ታደለች ክርክር ያስነሳው መኖሪያ ቤት የግል ንብረታቸው ነው ለማለት መሠረት ያደረጉት ቀደም ሲል ከጋብቻ በፊት እንዳፈሩ ሳይሆን ከጋብቻ ኑሮ በኋላ አመልካች አቶ ቁምላቸው ከቤት ከወጡ በኋላ ‹‹ሠርቻለሁ›› የሚል ነው።
ግራ ቀኙ በጋብቻ እስካሉ ድረስ ወይንም ጋብቻቸው በሕግ ሳይፈርስ በጋራም ሆነ በግል ልፋት የሚገኝ ማንኛውም ንብረት የጋራ እንደሆነ በኦሮሚያ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 78 ሥር በመደንገጉ የግራ ቀኝ ጋብቻ ሳይፈርስ መልስ ሰጪዋ ወይዘሮ ታደለች ‹‹ቤቱን በግሌ ስለሠራሁ የግል ንብረቴ ነው›› በሚል የሚያቀርቡት ክርክር ከሕጉ አቋም ጋር የሚሄድ አለመሆኑንም የሰበር ችሎቱ ያስረዳል።
በግራ ቀኙ መካከል ክርክር ያስነሳው ቤት በሕግ መሠረት የጋራ ንብረት ስለሆነ የሥር ፍርድ ቤቶች ሕጋዊ መሠረት የሌለውን የመልስ ሰጪዋን ክርክር በመቀበል ዋናው መኖሪያ ቤት የመልስ ሰጪዋ የግሏ ንብረት ነው በማለት የሰጡት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለው ሆኖ ተገኝቷል ሲል ቀደም ብሎ በሰበር የተወሰነውን ውሳኔ ውድቅ የሚያደርግ ሌላ ፍርድ ይሰጣል።
በመቀጠልም በግራ ቀኝ መካከል ክርክር ያስነሳው ዋናው መኖሪያ ቤትም ሆነ ተያይዞ የሚገኝ ሰርቪስ ቤት ሁሉ የግራ ቀኝ የጋራ ንብረት ስለሆነ ግራ ቀኙ በስምምነት ተስማምተው ከተከፋፈሉ እንዲከፋፈሉ፣ ካልተስማሙ ደግሞ በዓይነት መከፋፈል የሚቻል ከሆነ ጉዳዩ በሚመለከተው አስተዳደር ላይ ተጣርቶ በዓይነት እንዲከፋፈል፣ ይህ የማይቻል ከሆነ በጨረታ ተሸጦ ለግራ ቀኙ እኩል እንዲከፋፈል ሲል ይወስናል።
የሰበር አቤቱታው የቀረበውም ውሳኔውን በመቃወም ሲሆን፤ ትልቁ መኖሪያ ቤት የጋራ ንብረት ነው ተብሎ መወሰኑ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ስለሆነ ሊታረም ይገባል የሚል መሆኑንም ይገልጻል። አቤቱታውን አጣሪው መርምሮ የጉዳዩ አከራካሪ የሆነው ዋናው ቤት አመልካች የሠሩት ከትዳር በፊት በተመሩት ይዞታ ላይ መሆኑን በሥር ፍርድ ቤት በማስረጃ ተረጋግጦ ሳለ የክልሉ ሰበር ወደ ማስረጃ ምዘና ገብቶ ቤቱ የጋራ ነው ያለበት አግባብነት መጣራት ያለበት መሆኑ ይታመንበታል። በመሆኑም ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ይቅረብ ሲል ትዕዛዝ ይሰጣል።
የነገሩ አመጣጥና የክርክሩ ሂደት ችሎቱ የተመለከተው ሲሆን፤ በውሳኔው ላይ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መፈፀም አለመፈፀሙም ተመርምሯል። ለዚህ የሰበር አቤቱታ ምክንያት የሆነው ቤት በተመለከተ የሥር ከሳሽ በዚህ ችሎት ደግሞ ተጠሪ አቶ ቁምላቸው እንዲሁም የአመልካች ወይዘሮ ታደለች ምስክሮች የመሠከሩትን ተያይዞ የቀረበው የውሳኔ ግልባጭ እንደሚያስረዳ በየካቲት 25 ቀን 2011 ዓ.ም ፍርድ ላይ ሰፍሮ ይገኛል። ከተረጋገጠው ፍሬ ነገር በመነሳት ለሰበር አቤቱታ ምክንያት የሆነውን ቤት ጉዳይ ሲመረመር ያረጋገጣቸውን ግኝቶችንም ያስቀምጣል።
አመልካች ተጠሪን ሳያገቡ በፊት ትንሽ ቤት የነበራቸው ሲሆን፤ ተጠሪን ካገቡ በኋላ ትልቁን ቤት መሥራታቸውንና ይህም ቤት ደግሞ በኋላ ፈርሶ የተሠራ መሆኑን በምርምሩ ካገኛቸው ግኝቶች መካከል እንደሆነ ያስቀምጣል። ቤቱ ፈርሶ ሲታደስም አቶ ቁምላቸው ከቤት ይውጡ እንጂ በግራ ቀኙ መካከል ያለው ጋብቻ የፈረሰ ያለመሆኑንም ጭምር ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፈርሶ የተሠራውን ቤት አመልካች በራሳቸው ገንዘብ የሠሩ ስለመሆኑ ያረጋገጡት ነገር የሌለ መሆኑን ነው። ይልቁንም የተጠሪ አንደኛ ምስክር ቤቱ የተሠራው ተጠሪ ማለትም አቶ ቁምላቸው ‹‹ከቤት ከመውጣታቸው በፊት በተዘጋጀ ፍልጥና ቆርቆሮ እንደሆነ መመስከራቸውን ተያይዞ የቀረበልን የውሳኔ ግልባጭ ያረጋግጣል›› በማለት ያስቀምጣል።
ማንኛውም በጋብቻ ውስጥ የተፈራ ንብረት የባልና ሚስት የጋራ ንብረት እንደሆነ ይገመታል የሚለው ሰነዱ፤ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 69/95 በአዋጅ ቁጥር83/96 እንደተሻሻለው አንቀጽ 78 እና 79 ድንጋዎችም ይህንን በግልጽ ያስረዳሉ ሲል ይተነትናል።
አመልካች በክርክራቸው ትልቁን ቤት አቶ ቁምላቸው ከቤት ከወጡ በኋላ እንደሠሩት ይግለጹ እንጂ ጋብቻቸው በሁኔታ የፈረሠ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ወይም አመልካች በግል ገቢያቸው ወይም ገንዘባቸው መሥራታቸውን እስካላረጋገጡ ድረስ የግራ ቀኙ ጋብቻ በሕግ ሳይፈርስ በጋራም ሆነ በግል ልፋት የሚገኝ ማንኛውም ንብረት የጋራ ንብረት እንደሆነ የተጠቀሰው ቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 78 በግልጽ ያስቀመጠ በመሆኑ ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ቤት የአመልካች የግል ንብረት እንደሆነ ተደርጎ የቀረበው ቅሬታ ሕጋዊ መሠረት ያለው ሆኖ አልተገኘም ሲል መዝገቡ ያሰፍራል።
አመልካች ከጋብቻ በፊት የነበራቸው ትንሽ ቤት ፈርሶ መሠራቱ በሥር ፍርድ ቤት የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ነው። የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 94652 ላይ ከጋብቻ በፊት በአንደኛው ተጋቢ ስም የነበረን የግል ንብረት በጋብቻ ወቅት በንብረቱ ላይ መሠረታዊ መሻሻል ቢደረግበትና ይሔው መሻሻል የተደረገው የባለንብረቱ የግል ገንዘብ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ ሕጉ ንብረቱ የጋራ ነው የሚል ግምት የሚወስድ ስለመሆኑ አስገዳጅ ትርጉም ሰጥቷል። በዚህም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ነገሩን በአግባቡ ተመልክቶ የሰጠው ውሳኔ የሚነቀፍ አይደለም ሲል ውሳኔውን ይደግፋል።
በመጨረሻም የሰበር አጣሪ የሰበር አቤቱታውን መርምሮ የጉዳዩ አከራካሪ የሆነው ዋናው ቤት ይዞታውን አመልካች ከጋብቻ በፊት የመመራታቸው ጉዳይ ሳይሆን በዚህ ይዞታ ላይ የተሠራው ቤት ግራ ቀኙ በጋብቻ ውስጥ እያሉ የተሠራ ነው? ወይስ አይደለም? በትዳር ውስጥ የተሠራ ከሆነ የጋራ ሊሆን ይገባል? ወይስ አይገባም? የሚለው መሠረታዊ ነገር ነው በሚል ያብራራል። በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 40/3/ እንዲሁም በተሻሻለው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ ሕገመንግሥት አንቀጽ 40(3) መሠረት የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው።
በተያዘው ጉዳይ አመልካች ይዞታውን ከጋብቻ በፊት ቢይዙም ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ቤት በጋብቻ ውስጥ መሠራቱ እስከተረጋገጠ ድረስ ይዞታው ለብቻው ተነጥሎ ሊታይ የሚችልበት ምክንያት አይኖርም። ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 29402 ላይ ቤት የጋራ ሀብት ነው ከተባለ ቤቱ የተሠራበት መሬት ላይ የጋራ ባለሀብቶቹን እኩል የመጠቀም መብት የሚኖራቸው ስለመሆኑ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የሰጠ ሲሆን፤ ትርጉሙም በየትኛውም ደረጃ በሚገኙት ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነት ያለው ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2/1/ ላይ በግልጽ መደንገጉን ይገልጻል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደ ማስረጃ ምዘና እንደገባ ተደርጎ በአጣሪ የተያዘው ጭብጥም ቢሆን በሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች ላይ የተመለከተውን የክርክሩን ይዘትና ውሳኔዎቹን በአግባቡ ያጤነ አይደለም ሲል ይተቸዋል። የቀረበውን ጉዳይ ተመልክቶ ማስረጃዎችን የሚመዝነው ፍርድ ቤት መሠረታዊ የማስረጃ ምዘና መርህን ከጣሰ እንደ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የሚቆጠር እንጂ ተራ የማስረጃ ምዘና ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል እንዳልሆነ ሊዘነጋ አይገባምም ይላል።
በማጠቃለያውም የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያልተፈፀመበት በመሆኑ በቀን 08/08/2010 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር 273508 የሰጠው ውሳኔ በፍትሐብሔር ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 348/1/ መሠረት የፀና ይሆናል ሲል ውሳኔውን ያሳርፋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጠው ውሳኔ ላይም የተፈፀመ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የለም ሲል ክርክር የተነሳበት ቤት በእኩል ይካፈሉ የሚለውን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የወሰነውን ውሳኔ ያፀናዋል። እኛም እነዚህን ሰነዶች ከተመለከትን በኋላ በጉዳዩ ላይ የሕግ ባለሙያና የሚመለከተው አካል ምን ይላል ስንል አነጋግረናል።
ባለሙያ ምን ይላል?
በፌዴራል በማንኛውም ፍርድ ቤቶች ጠበቃና የሕግ ባለሙያ አቶ ፍፁም አስራት በጉዳዩ ላይ ያረፉ ውሳኔዎችንና የፍርድ ሂደቶችን የሚያመላክቱ ሰነዶችን ተመልክተው በሰጡን አስተያየት፤ ሂደቱ ትክክለኛ ነው። ነገር ግን ውሳኔዎቹ በችሎቶቹ ላይ ተሰይመው የነበሩ ዳኞች የተለያዩ ማስረጃዎችን አገላብጠውና አድምጠው ትክክል ነው ብለው ያመኑበትን ነው የወሰኑት። ነገር ግን ሰበር ሰሚ ችሎት የማስረጃ ምዘና አያደርግም።
ማስረጃዎች የሚታዩት ታች በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ላይ ነው። ከዚያም ይግባኝ ሲቀርብና የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ተብሎ ሲታመን ሰበር ተመልክቶ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይናገራሉ። ታዲያ ይህ ከሆነ በክልሉ ሥር ፍርድ ቤትና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላይ የማስረጃ ምዘና ተደርጎ የተወሰኑ ውሳኔዎች ስለምን በክልሉ ሰበር ተሻሩ? የሚለው ጥያቄ ግን ሊመለስ አልቻለም።
ይህንን ይዘን አጠቃላይ በጉዳዩ ላይ የሚመለከተው አካል ምን ይላል? የሚለውን ለማድመጥ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በደብዳቤ ጠይቀናል። ሆኖም ጉዳዩን አስመልክቶ የሕግ ምሁር ሊተች እንደሚችል እንጂ የተወሰነው ውሳኔ ትክክል ነው ወይንም አይደለም በሚል መልኩ ማየት እንደማይቻልና መግለጽ የሚቻለውም የነበረውን ሂደት ከመዝገብ ላይ በመመልከት ብቻ እንደሆነ ተገልፆልናል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26 /2011
ፍዮሪ ተወልደ