የኢትዮጵያ የፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎ እና የኦሊምፒክ ኮሚቴው ተግባራት ተከትሎ የስፖርት ቤተሰቡ በብርቱ እየተቃወመው ይገኛል:: ይህንን እንዲሁም ተሳትፎውን በተመለከተም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፤ በብዛት ሲነሱ ለቆዩ ጉዳዮችም ምላሽ ሰጥቷል::
ከፓሪስ ኦሊምፒክ ጋር ተያይዞ ከተነሱ አወዛጋቢ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው በድብቅ የተከናወነው የኮሚቴው ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ምርጫ መሆኑ ይታወቃል:: ከዚህም ጋር ተያይዞ ኮሚቴው የሚመሠርቱት ብሄራዊ የስፖርት ማህበራት ባላወቅነውና ባልተሳተፍንበት ሁኔታ ምርጫው መደረጉ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሕግን እንዲሁም የዓለም አቀፉን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቻርተርን የሚጥስ በመሆኑ ሕገወጥ እንደሆነ ከሰሞኑ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ገልጸው ነበር:: ይህንን በሚመለከትም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ገብረጊዮርጊስ በሰጡት ምላሽ ‹‹ምርጫ የተካሄደው ሕግና ሥርዓትን ጠብቆ ነው ስለዚህም ትክክል ነው:: በቀረበው አቤቱታም አንረበሽም›› ብለዋል:: በተጨማሪም ክሱ ወደ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተላከ እንጂ ወደ ኮሚቴው የደረሰ ባለመሆኑ ተቋማዊ አሠራርን ያልተከተለ እንደሆነም አንስተዋል::
ኦሊምፒኩን ተከትሎ ሕዝቡን ካስከፉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ‹‹ኦሊምፒክ ተሳትፎ ነው›› የሚለው ሃሳብ ሲሆን፤ በአትሌቲክስ ስፖርት ሜዳሊያዎችን ስትሰበስብ ለቆየች ሀገር ተሳትፎ በሚል ቃል መወሰኑን በርካቶች ተችተው ነበር:: ለዚህም የኮሚቴው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ‹‹ሕዝባችን ያለመደው ቃል በመሆኑ ይቅርታ እንጠይቃለን›› ብለዋል:: ይሁን እንጂ ‹‹ተሳትፎ›› የሚለውን ቃል የተጠቀሙት ቻርተሩ (የኦሊምፒክ ፍልስፍና) ባስቀመጠው መሠረት እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሜዳሊያ አይገባውም ለማለት አይደለም:: በውድድሩ ወቅት በርካታ ሜዳሊያዎችን ማሳካት ባይቻልም ሲሠራ የቆየው ወርቅ፣ ብር ወይም ነሃስ ለማግኘት እንደሆነ መገንዘብ አስፈላጊ መሆኑንም አሳስበዋል::
ከሪዮ ኦሊምፒክ ጀምሮ ለጠፋው ውጤት ሁሉም እንደየድርሻው ተጠያቂ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ይጠቁማሉ:: ነገር ግን አትሌቶችን ማዘጋጀት፣ በፕሮጀክት መያዝ፣ ብሄራዊ አሠልጣኞችን መያዝና ማፍረስም የኮሚቴው ሥራ አይደለም:: የትኛውም ፌዴሬሽን እቅድ በማውጣት ለአሸናፊነት መሥራት ይኖርበታል፤ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ደግሞ በተቀመጠለትና በተሰጠው ኃላፊነት ልክ ድጋፍ ያደርጋል እንጂ ሥራቸው ውስጥ ጣልቃ አይገባም:: ስለዚህ ይህንን መሰል ጥያቄ ሊቀርብ የሚገባው ለብሄራዊ ፌዴሬሽኖች ነው፤ ባለፉት ወራት የፓሪስ ኦሊምፒክ የዝግጅት ወቅት ኮሚቴው ያጎደለው ነገር ካለ ግን ሊጠየቅ ይገባል:: ከዚያ ባለፈ ግን ‹‹የጅምላ ጭፍጨፋ ተገቢ አይደለም›› ሲሉ ጉዳዩን ወደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገፍተዋል::
ኢትዮጵያ በፓሪስ የኦሊምፒክ መድረክ ውጤት ያሳጣትና ተሳታፊ አትሌቶችም ከሚታወቁበት በተቃራኒ ተፎካካሪነታቸው አንሶ ለመታየቱ በርካታ ጉዳዮች በምክንያትነት ይነሳሉ:: ከእነዚህ መካከል አንዱ ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በምርጫው ሳይቀር ጣልቃ በመግባታቸው በመሆኑ ነው:: ለዚህም ኮሚቴው በመግለጫው ላይ ባቀረበው የፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ሪፖርት ላይ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው የማራቶን አትሌት ታምራት ቶላ ከተጠባባቂነት ተነስቶ ተሳታፊ እንዲሆን ኮሚቴው ሚና እንደነበረው በመግለጽ በራሱ ላይ መስክሯል:: ይሁንና ቅሬታ ሲያቀርቡ ለነበሩ ሌሎች አትሌቶች ምላሽ ያለመስጠታቸው በተለየ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል:: በተለይ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ጋር በተገናኘ ከአንድ በላይ ርቀት ተሳታፊ የነበረችውን አትሌት ጉዳፍ ጸጋይን ለማወያየት ቢሞከርም ካለችበት አቋምና ሀገሯን ለማስጠራት ከነበራት ጉጉት አንጻር አልተቻለም:: በውድድሩም ወቅት ባልተጠበቀ ሁኔታ ህመምም ስለነበረባት ውጤታማ ሳትሆን ቀርታለች::
የዮሚፍ ቀጄላ ቅሬታም በሁለት ርቀት የሚሮጠው በ10ሺ ሜትር ሜዳሊያ ካገኘ በሚል ቢሆንም የሆነ ነገር አልነበረም:: ሌላዋ መሰል ቅሬታዋን ያቀረበችው አትሌት ፍሬህይወት….. ከስፖርት አበረታቻ ቅመሞች ምርመራ አለማድረግ ጋር የተያያዘ መሆኑን በመግለጫው ተጠቁሟል:: ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን አትሌቷ በእጩ ዝርዝር ውስጥ ባለመኖሯ በምርመራው ያልተካተተች መሆኑን አንጸባርቋል:: ከዚህ ባለፈ አንድም አትሌት ምርጫ ላይ ፕሬዚዳንቱ እጃቸው እንደሌለ ነው ያረጋገጡት::
ከስፖርት ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ከብሄራዊ የስፖርት ማህበራት እንዲሁም ከስፖርት ሙያተኞች ሲነሱ የቆዩ ቅሬታዎችን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ እንዲሁም የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ ራሱን ከሥልጣን እንዲያነሳም በተደጋጋሚ ተጠይቆ ነበር:: ምላሻቸው ግን ‹‹ከዚህ ቀደም እግር ኳስን ጥዬ ወጥቻለሁ የመጣ ለውጥ ግን አልነበረም:: ጥሎ መውጣት መፍትሄ አይደለም፤ ስለዚህም ሥስልጣኑን አልለቅም›› ሲሉ ገልጸዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም