የቡና ቱሪዝም- ያልተገለጠው ዘርፍ ምን በረከት ይዞ ይሆን?

ኢትዮጵያ የምታመርተው ቡና በወጪ ንግድ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በተጨማሪ በቱሪዝም ዘርፍ ሀገሪቱን ለማስተዋወቅ ግዙፍ አቅም እንዳለው ይነገራል። በዘርፉ ዘለግ ያለ ልምድ ያላቸው ምሁራን ‹‹የቡና አመራረት ዘዴን ከውብ ባህላዊ የቡና አፈላል ጋር አዛምዶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ›› አዲስ የቱሪዝም መስህብ እንደሚፈጥር ይናገራሉ። የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመር ኢትዮጵያን በአዲስ መንገድ በማስተዋወቅ ረገድም የላቀ ድርሻ መያዝ እንደሚችል ይገልፃሉ።

የቡና መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ልዩ ጣዕም ያለውን ቡና እንደ አንድ የቱሪዝም መስህብ ለመጠቀም የተለያዩ ሙከራዎች መደረጋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ ዘላቂ በሆነና በተደራጀ መልኩ ተግባራዊ አለመደረጉ እንደ አንድ ክፍተት ይነሳል።

ከሰሞኑ ይህንን የኢትዮጵያን እምቅ አቅም ለመጠቀም እንዲሁም ሄድ መለስ እያለ የሚታየውን ሙከራ በዘላቂነት አስቀጥሎ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል እቅድ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በጋራ ይፋ አድርገዋል። እቅዱ የኢትዮጵያን ቡና ከግብይት ባሻገር በትብብርና በቅንጅት በቱሪዝም ዘርፍም ሀገሪቱን ለማስተዋወቅ እንዲችል ለማድረግ መሥራት ነው። ይህንን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ሁለቱ አካላት ከሰሞኑ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር ) ስምምነቱን አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ቡና ከምርት እስከ ግብይት ባለው ሂደት የሀገርን ገፅታ በመገንባት ለቱሪዝም ዘርፉ መጎልበት ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ከኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ቡናን ከቱሪዝሙ ዘርፍ ጋር በማስተሳሰር የቱሪስት መስህብ ማድረግን ያለመ ነው።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በዚህም በኢትዮጵያ የተለያዩ የቡና ዝርያዎችን በምርምር በማግኘት ምርቱን ለማሳደግ እና የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ቡናን ከማስተዋወቅም ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፉም ትልቅ ሚና እንዲኖረውና ትስስሩ እንዲጠናከር የማድረግ ሥራ ተገግባራዊ ይደረጋል። ቡና በጥራት ተመርቶና እሴት ተጨምሮበት ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ የማድረጉን ሥራ ከቱሪዝም ዘርፍ ጋር ለማስተሳሰር ይሠራል።

‹‹በቡና ተክል ልማት ውስጥ ሎጆችን እና መዝናኛ ሥፍራዎችን በመገንባት ቡና የቱሪስት መስህብ ይደረጋል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባለፈው በጀት ዓመት ከቡና ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ይናገራሉ። የቱሪዝም ዘርፉን ከቡና ምርትና ግብይት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ባህላዊ የአፈላል ሥርዓት ጋር ማስተሳሰር ከተቻለ ከሀገር ገፅታ ግንባታ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ አማራጭን ማስፋት እንደሚቻል አስረድተዋል።

‹‹የመግባቢያ ስምምነቱ ምን ማእቀፎች ይኖሩታል? የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽንስ በዚህ በኩል ምን ድርሻ አለው?›› የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ነጋ ወዳጆ በሰጡት ምላሽ ቡና ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱን ጠቅሰው፣ ከአራት ሺህ በላይ ጣዕምና ዝርያዎች እንዳሉትም ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ ጥቂቱ ብቻ እየተመረተ ወደ ገበያ እየቀረበ መሆኑን አመልክተው፣ ምርቱም በዓለም ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆን መሪና ተመራጭ እንደሆነም ተናግረዋል።

‹‹ትልቅ ተቀባይነት ያለውና ባለ ልዩ ጣዕም የሆነውን የኢትዮጵያን ቡና የቱሪዝም አካል ለማድረግ አልተሠራም›› የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ቡናን ከኢትዮጵያ ወስደው በማብቀል ተወዳዳሪ የሆኑ ሀገራት ግን በቡና ቱሪዝም ላይ በስፋት በመሥራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ይገልፃሉ። ይህንን እውነታ መቀየር እንደሚያስፈልግና ኢትዮጵያም የዚህ ድርሻ ተጋሪ መሆን እንደሚገባት አመልክተዋል።

አቶ ነጋ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ቱሪዝምን ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ አንዱ በማድረግ የፖሊሲ ማሻሻያ አድርጓል፡፡ በዚህም ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት ተሠጥቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተገነቡ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎች እና የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችም ይህንን ልዩ ትኩረት የሚያጎሉ ለዘርፉ መነቃቃት የሚፈጥሩ ናቸው ይህም በዓለም ላይ ካሉ የመስህብ ቦታዎች ኢትዮጵያ ቀዳሚ ተመራጭ እንድትሆን እድል ይፈጥራል። ይህን ታላቅ ተግባር በቡና ቱሪዝም ለመድገምና ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ለማስከፈት መሞከር ይኖርባታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም በዓመት በርካታ ሚሊዮን ተጓዦችን የሚያስተናግድ የአፍሪካ ኩራት ሆኖ እያለ ኢትዮጵያ ግን በሚፈለገው ልክ ከቱሪስቶች ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም ያሉት አቶ ነጋ፤ አየር መንገዱን ተጠቅመው እንደ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ታንዛኒያ፣ ዛንዚባር፣ ዚምቧቤ፣ ዛምቢያና ደቡብ አፍሪካ ያሉት ሀገሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህ ሀገራት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያመላልሳቸውን ቱሪስቶች ተጠቅመው የቱሪዝም ዘርፋቸውን ማላቃቸውን ጠቅሰው፣ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ዝቅተኛ መጠን ያለው ቁጥር ማስመዝገቧ እንደሚያስቆጭም ይናገራሉ። ይህ የሚሆንበት ምክንያትም ኢትዮጵያ ያላትን መስህብና የተፈጥሮ ሀብት (በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች እና እንደ ቡና ያሉትን ሀብቶችን) በበቂ ሁኔታ ማስተዋወቅ ባለመቻሏ እንደሆነም ያመለክታሉ።

ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳሉት፤ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሰፋፊ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም የኢትዮጵያን በተለይ የክልሉን የመስህብ ሀብቶች የማስተዋወቅና የማልማት ሥራ እያከናወነ ነው።

ከዚህ ባሻገር በቅርቡ ቡናን በልዩ ትኩረት በማስተዋወቅ፣ መዳረሻዎችን በማልማት እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያት ኢትዮጵያውያንን እንዲወክል በማድረግ መሥራት ቢቻል ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም ማስፋት እንደሚቻል ታምኖበታል። ይህንን እቅድ መሬት ለማውረድ እየተሰራ ይገኛል፡፡

‹‹የኦሮሚያ ክልል አብዛኛዎቹ ዞኖች ቡና አብቃይ ናቸው›› የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ እስከ 70 በመቶው የሚሆነው የኢትዮጵያ የቡና ምርት የሚገኘው ከዚሁ ክልል መሆኑን ይገልፃሉ። ከዚህ ባሻገር ቡና አብቃይ የሆኑት አካባቢዎች ያላቸው ተፈጥሮና መልከዓምድራዊ አቀማመጥ ውበት ልዩ መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም እነዚህን ሀብቶች ከቡና ጋር አስተሳስሮ በቱሪዝም ዘርፉ ቢሠራ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣትና ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ማሳደግ እንደሚቻል ያስረዳሉ። ኮሚሽኑም ይህንን ታሳቢ ያደረገ እቅድ በማውጣት ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ይገልፃሉ።

የቡና አምራቹ አርሶ አደር አዲስ የኑሮ ዘይቤ እንዲጀምር መሥራት ያስፈልጋል የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ቡና ከማምረት ባሻገር በማሳ ውስጥ የሚተገበረውን ሙሉ ሂደት ለቱሪስቱ ማስጎብኘት እንዲችል፤ ከቡና እርሻ ጀምሮ፣ ለቀማውን፣ መፈልፈሉንና ማድረቁን ጨምሮ ተፈልቶ ለመጠጥ እስኪውል ድረስ ያለው ሂደት ለጉብኝት በመክፈት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ እንደሚያስፈልግም ይገልፃሉ።

ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን ጋር የተፈራረመው ስምምነትም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ያነሳሉ። ከቡና ምርት ባሻገርም የሻይ ቅጠል አብቃይ አካባቢዎች ታሳቢ ያደረገ እቅድ መኖሩን ጠቁመዋል። በክልሉም ወደ 30 ሺህ ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ ሻይ እየለማ መሆኑን ማሳ እየለማ መሆኑን አንስተው ቱሪዝሙ ይህንን ያካተተ እንደሚሆንም ገልፀዋል።

እንደ አቶ ነጋ ገለፃ፤ የቡናና ሻይ ግብይት በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በኩል የሚያልፍ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ቡና እና ሻይ በሚገበያዩበት ጊዜ ምርቱን ለሽያጭ ከማቅረብ ባሻገር ኢትዮጵያን በቱሪዝም በማስተዋወቅ በኩል ያለውን አቅም እንዲጠቀሙ የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል። ባለሥልጣኑ ከግብይቱ ባሻገር በቡናና ሻይ ልማት ላይ ትልቅ ደርሻ ያለው በመሆኑ ከመሠረተ ልማት፣ ከሎጅ፣ በቡና ማሳ ውስጥ ለጎብኚዎች ምቹ የአገልግሎት መስጫ መዳረሻዎችን ከማልማት አኳያ በጋራ ድጋፍ አድርጎ በመሥራት የበኩሉን መወጣት ይችላል። የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽንም የክልሉን የቡና ቱሪዝም ከማስተዋወቅ አንፃር በቅንጅት አብሮ ለመሥራት ተዘጋጅቷል።

የቡና ቱሪዝም ዋናው ባለቤት ከትንሽ አስከ ትልቅ የእርሻ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ናቸው የሚሉት አቶ ነጋ፤ ዋናው ተግባር የሚሠራውም በባለቤቶቹ መሆኑን ይገልፃሉ። ህብረተሰቡን የማንቃት፣ አዳዲስ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ ይህን መሰል ሃሳብ መኖሩን የማሳየት ሃላፊነቱን ኮሚሽኑና የባለሥልጣን መሥሪያቤቱ ሃላፊነት ወስደው እንደሚሠሩም ያስረዳሉ።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የቡና ቱሪዝም ተግባራዊ የሚደረግባቸው የክልሉ አካባቢዎችን መለየቱን ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ነጋ ይገልፃሉ። 70 በመቶ የሚሆነው ቡና ከዚሁ ክልል የሚገኝ እንደመሆኑም በርካታ ለቱሪዝም መስመር የሚሆኑ አካባቢዎች መኖራቸውን ይገልፃሉ። በተጨማሪ የቡና አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች በሙሉ የቡና ቱሪዝም ማካሄድ እንደሚቻልም ያስረዳሉ።

መነሻቸውን ከአዲስ አበባ የሚያደርጉ ጎብኚዎች በደቡብ ምእራብ በኩል በወሊሶ አድርገው፣ በጅማ፣ ቡኖ በደሌ፣ ወደ ሊሙ አሊያም ወደ ኢሉ ባቡር መሄድ እንደሚችሉ እና የቡና ማሳዎችን፣ የአፈላል ሥርዓቱን እንዲሁም የተፈጥሮ ውበትና መልከዓ ምድሩን መመልከትና የማይረሱ ትዝታዎችን ገብይተው መመለስ እንደሚችሉ አቶ ነጋ ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የቡና ቱሪዝም መስመሮች መኖራቸውን ገልፀው፣ ጉጂንና ሲዳማን ማስተሳሰር እንደሚቻል ያስረዳሉ። የሀገር ወስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በእነዚህ አካባቢዎች የቡና ቱሪዝም በስፋት ማግኘት እንደሚችሉም ይገልፃሉ።

አቶ ነጋ ሌላው ቡና አብቃይ የሆነው የክልሉ አካባቢ ‹‹ነን ሰቡ›› የሚባለው ቦታ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጎብኚዎች በዚያ አድርገው ወደ ባሌ በመሻገር ትልቅ የቡና ጫካ ወዳለበት አረና፣ ደሎ መና አካባቢ ማራኪ ጉብኝት ማድረግ እንደሚችሉ ይገልፃሉ።

ሀረር የቡና ሀገር መሆኑን ጠቅሰው፣ ከኢሉ አባቦር፣ ከጋምቤላ ጀምሮ ወደ ሀረር ሲኬድ ኢትዮጵያን በሁለት አቋርጦ መሄድ የሚችል የቡና ቱሪዝም መስመር መዘርጋት እንደሚቻል ያነሳሉ። በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጪ በርካታ የቡና አብቃይ አካባቢዎች እንዳሉ አመልክተው፣ እነርሱን በማስተሳሰር ግዙፍ አዲስ የቱሪዝም የጉብኝት መዳረሻ መፍጠር እንደሚቻልም ይገልፃሉ። ጎብኚውም ልዩ ልዩ ባህል፣ የኑሮ ዘይቤን እንዲሁም መልከዓ ምድርን እየተመለከተ ከተፈጥሮ ጋር ራሱን በማስተሳሰር የማይዘነጋ ትዝታን ቋጥሮ መመለስ እንደሚችል ነው የገለፁት።

ምክትል ኮሚሽነሩ ፤ የመገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን፣ ማህበረሰቡም ቡናን ከማምረት ባሻገር ያልተገለጠ የቱሪዝም እድል መኖሩን እንዲያውቅ ግንዛቤ የመፍጠር፣ የማስተዋወቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ይህን በትብብር ማድረግ ሲቻል የሚፈለገውን ውጤት በአጭር ጊዜ ማሳካት ቀላል እንደሚሆን ገልፀዋል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን እሁድ ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You