የረጅም ርቀት ወርቆች ለምን ከኢትዮጵያ ራቁ?

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ቻምፒዮናዎችና ኦሊምፒክን በመሳሰሉ ታላላቅ የውድድር መድረኮች በረጅም ርቀት ሩጫ በርካታ ድሎችን በማስመዝገብ ከዓለም ሀገራት ቀዳሚውን ሥፍራ ትይዛለች። በየውድድሩ ከሰበሰበቻቸው ሜዳሊያዎች የሚልቁትም በ10 እና 5ሺህ ሜትር ርቀቶች የተገኙ ናቸው። ይህ የኢትዮጵያ የባህል ስፖርት ተደርጎ የሚቆጠርና በርካታ ታሪክ ሰሪ አትሌቶችን ያፈራው ርቀት፤ ባለፉት ሶስት ኦሊምፒኮች ዝቅተኛ ውጤት እየተመዘገበበት ይገኛል፡፡

በፓሪስ ኦሊምፒክ በእነዚህ ርቀቶች የተመዘገበው የሜዳሊያ ቁጥር ደግሞ በታሪክ ዝቅተኛው ሲሆን፤ ይህም ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው። በወንዶች 10 ሺ ሜትር ብቸኛው የብር ሜዳሊያ ቢመዘገብም በሴቶች ግን ከ32 ዓመታት በኋላ ሜዳሊያ ማግኘት አልተቻለም። በ5ሺህ ሜትርም በተመሳሳይ በሁለቱም ጾታዎች ውጤት ማስመዝገብ ሳይቻል ቀርቷል። በዓለም ቻምፒናም ቢሆን በርቀቱ እንደተለመደው ጠንካራ አትሌቶችን ማፍራት አልተቻለም። ለውጤት መጥፋትና እንደቀደመው ድልን ማስቀጠል ያልተቻለበት ምክንያትም አሳሳቢ ነው።

በርቀቶቹ ትልቅ ስም ካላቸው ሰዎች መካከል የቀድሞ አትሌትና በብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ከ 25 ዓመት በላይ ያገለገሉት ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ፣ በረጅም ርቀት የውጤት መቀነስ አሁን የመጣ ችግር ሳይሆን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ መሆኑን ይገልጻሉ። በፓሪስ ኦሊምፒክ በተለይ በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር በሁለቱም ፆታ ይመዘገባል ተብሎ የተጠበቀው የወርቅ ሜዳሊያ አልተመዘገበም። በቶኪዮ ኦሊምፒክም በ10 ሺህ ሜትር በአትሌት ሰለሞን ባረጋ የወርቅ ሜዳሊያ ብቻ ሲመዘገብ ለምን የሚል ጥያቄ ማንሳት ይገባ ነበር ይላሉ አንጋፋው አትሌትና አሠልጣኝ። ሲንከባለል የቆየው የረጅም ርቀት የውጤት ማጣት ድንገት በሚመዘገብ ውጤት ተሸፍኖ በመምጣቱ ፓሪስ ላይ አንድም የወርቅ ሜዳሊያ ሳይመዘገብ ሊቀር እንደቻለም ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሠልጣኞች ማህበር ሊቀመንበርና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ኮሚቴ አባል የሆኑት አሠልጣኝ ቶሎሳ፤ አስቀድሞ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውጤት መገምገም እንደነበረበት ይናገራሉ። ሻምበል ቶሎሳ በረጅም ዓመት የአሠልጣኝነት ዘመናቸው አብረዋቸው ከሚሠሩት አሠልጣኞች ጋር በመሆን አትሌቶችን በሥልጠና ገምግሞና ብቃታቸውን አይተው እንደሚመርጡ ያስታውሳሉ። አሁን ግን ኦሊምፒክን የሚያክል ትልቅ የውድድር መድረክ ተካሂዶ በኦሊምፒክ ኮሚቴው እና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለመገምገሙ ውጤቱ እየወረደ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ውድድሮቹ ሲገመገሙ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍም ክትትል መደረግ ነበረበት ባይ ናቸው። ይህ ባለመሆኑም የወርቅ ሜዳሊያ ሳይመዘገብና ቀርቷል። በሴቶች እንደነረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ ጥሩነሽ ዲባባና መሠረት ደፋር ጥምር ድሎችን ያስመዘገበቡት ርቀት ቢሆንም ከሜዳሊያ ውጪ መሆን ካለፈው ስህተት ትምህርት አለመውሰድ ነውም ይላሉ።

 

እንደ ሻምበል ቶሎሳ ማብራሪያ፣ ፓሪስ ላይ በወንዶች 10ሺህ ሜትር የነበረው የአትሌቶች አሯሯጥና የታክቲክ ስህተት እንደሆነና ከአሠልጣኞች የተሰጠ ምክር ሊሆን እንደማይችልም ያክላሉ። በሥልጠና ዘመናቸው የተቃራኒ ጉልበትን ለመፈተሽ አትሌቶች ፍጥነት እንዲጨምሩ ምክር በመስጠት የማይቆረጡ ከሆነ ተመልሶ ቦታ በመያዝ ፍጥነት ላለው ሰው ቦታ እንዲሰጡ ይደረጋል። አሁን ግን ያ ሳይሆን ከመጀመርያው ፍጥነትን ጨምረው በመዳከም ከሜዳሊያ ውጪ መሆን ችለዋል። ከመጀመርያው ፍጥነታቸውን ባይጨምሩና መጨረሻ ቦታ በመያዝ ቀድመው ቢወጡ ከዩጋንዳዊው አትሌት እኩል መፎካከር ይችሉ ነበር። በሴቶቹ ከአትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ውጪ ያሉት የልምድ ማነስ ያለባቸው ሲሆኑ፣ ጉዳፍም በውድድር መደራረብ ብቃቷ ወርዷል። በሶስት ርቀቶች ለመሮጥ ወስና ከምትገባ በአንዱ ጠንክራ ብትቀርብ፣ በ10 ሺህ ሜትር ውጤታማ መሆን ትችል ነበር።

የቡድን ሥራን ለመተግበርም የአትሌቶች አቅም የማይመጣጠን በመሆኑና ተነጣጥሎ በመሥራታቸው ውጤቱ ማሽቆልቆል ችሏል። ይህ ነገር ለወደ ፊቱ ታይቶ አሠራር የማይቀየር ከሆነ ችግሩ እንደማይቀረፍም ይናገራሉ። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ውጤቶች የመጣበት ብሔራዊ ቡድን ሳይጠና ማፍረሱ በውጤታማነት እንዳይቀጥል በማድረጉ ብሔራዊ ቡድኑ ተመልሶ መቋቋም ይኖርበታል ይላሉ። አትሌቲክስ የኢትዮጵያ አንድነት መገለጫ በመሆኑ አሠራሩ መፈተሽ እንደሚኖርበትም ይጠቁማሉ፡፡

የሁለት ኦሊምፒኮች የ10 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ጀግናው አትሌት ስለሺ ስህን በበኩሉ፣ በርቀቱ የውጤት መጥፋት ምክንያት የአትሌቶች በጋራ ዝግጅት አለማድረግ፣ የአንድነት፣ የመተዋወቅና የመተጋገዝ መንፈስ እንዳይፈጠር ማድረጉን ይናገራል። በተጨማሪም የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ተግባብተው የምርጫ መስፈርትና የሥልጠና ሥርዓትን ያለመዘርጋታቸው ምክንያት ነው ይላል። በመሆኑም ተግባብተውና ቅሬታን በማያስነሳ መልኩ ለሁሉም ግልጽ መስፈርትን አስቀምጦ አትሌቶችን ባላቸው ውጤት መርጦ በግልና በጋራ ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ባይ ነው፡፡

በፓሪስ ኦሊምፒክ አትሌቶቹ የሚችሉትን እንዳደረጉ ያስታወሰው ስለሺ፣ የሥልጠና መንገዱ በደንብ መፈተሽ እንደሚኖርበትና አትሌቶች ላይ ጫና በማያሳድር ሁኔታ ውጤታማ በሚሆኑበት ርቀት ብቻ ሊወዳደሩ ይገባል ይላል። በርካታ መስመር የሳቱ አሠራሮች መስተዋላቸውን የሚገልጸው አንጋፋው አትሌት፣ በሥራ አስፈጻሚ ሳይሆን በአሠልጣኞች የሚመራ ፌዴሬሽን እንደሚመስልም ይናገራል። ውድድሩ የተሳትፎ ነው የሚባለው ትክክል እንዳልሆነ እና በእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ከሚመራ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውጤት መጠበቅ ፈታኝ እንደሆነ ያስረዳል። መድረኩ ለአትሌቶችና ለሀገር ያለው ክብር ትልቅና ብዙ ሜዳሊያዎች የተመዘገበበት በመሆኑ መቀለድ አስፈላጊ አይደለም ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።

‹‹በቶኪዮ ኦሊምፒክ ተፈጥረው የነበሩ ችግሮች እየተንከባለሉ በመምጣታቸው ኦሊምፒክ ኮሚቴው መፈተሽ ይኖርበታል›› ያለው ስለሺ፣ ከሶሰት ዓመት በፊት የተፈጠረው ችግር ወደ ፓሪስ እንዳይሄድ ኮሚቴው ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ምን መደረግ አለበት በሚለው ጉዳይ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውንም ያስታውሳል። ኮሚቴው ከፌዴሬሽኖች ጋር ተግባብቶ ስለማይሠራ አሠራሩ ተፈትሾና ተገምግሞ በመንግሥት አቅጣጫ መቀመጥ እንደሚኖርበት አክሏል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You