መቼም የክረምት መልኮች ብዙ ናቸው። ቆም ብለን ሁኔታዎችን እንታዘብ ካልን ደግሞ አጋጣሚዎች በየአቅጣጫው ያሣዩናል። ክረምቱ ሲቃረብ፣ ዝናቡ ‹‹መጣሁ›› ሲል ዓእምሯችን አስቀድሞ የሚያስበው አይጠፋም። ክረምት በባህርይው እንደበጋው ደረቅ አይደለምና ቀድመው ቢፈሩት፣ ቢጠነቀቁት አይገርምም።
ክረምት በመጣ ጊዜ የወንዝ ዳር ቤቶች ዕንቅልፍ ይሉት ብርቃቸው ነው። ደሳሳ ጎጆዎች ፣ የሚያፈሱ ጣራዎች፣ ጎድጓዳ መንደሮች ሁሉ ምቾት አልባ ይሆናሉ። የክረምት ዝናብ ቆላ ደጋ ጥሎ ምድርን አረስርሶ ብቻ አይበቃውም። ደርቆ ከከረመው መሬት ያለ አቧራ ጭቃ ሆኖ እስኪላቆጥ የየዕለት ግብሩ ከበረከት ይሻገራል፡፡
ዝናቡ ጠንከር ብሎ በመጣ ጊዜ እንደዋዘ ደርሶ፣ ያሻውን አርጥቦ ብቻ አይመለስም። ከመሬት ያገኘውን እየጠረገ፣ ስር ይዞ የኖረውን እየገነደሰ መሬትን አጥቧት፣ ሞልጯት ያልፋል። ገና የረጠበው ጠፈፍ ሳይል፣ ‹‹እግዚኦ! ማረን! አውጣን ›› ተብሎ ሳያበቃ ደግሞ አጋጣሚው መልሶ ራሱን ሊደግም ይችላል። ይህ እንግዲህ ክረምትን ከፍስሐው አሻግረን ‹‹ቁጣውን ጣለብን፣ መአቱን አመጣብን ›› በምንል ጊዜ የሚጋጥም ሀቅ ነው፡፡
ተፈጥሮ ምንጊዜም ውሉን አይስትም። ፀሀይ ብርዱን፣ ዶፍ በረዶውን ሲያዘንብ በምክንያት ነው። ለእንዲህ አይነቱ እውነት ደግሞ በይሁንታ የሚለወጥ፣ በማስጠንቀቂያ የሚቀየር ምርጫ የለም። ተፈጥሮ ፣ ተፈጥሮ ነውና አምነን እንቀበለዋን፣ ፈቅደን እንኖረዋለን።
አንዳንዴ ተፈጥሮ ፊቱን ሲያዞርብን ጥፋቱ ይከፋል። በጋው ላይ ያልነበረ አንዳች ምልክት በክረምቱ ደርሶ ባህርይው ይለወጣል። ጥቂት ያልነው ሁሉ ገዝፎ.፣ ሁኔታው ተቀይሮ ለሰው ልጆች መኖር ጠንቅ ይሆናል። ይህን ጉዳይ ስናነሳ በርካታ ሀቆች ወደ ራሳችን መምጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡
ዛሬ ዓለማችን በተፈጥሮ አደጋዎች ስትናጥ ፣ ስትፈተን ፣ ውላ ታድራች። በግግር በረዶ መቅለጥ፣ በመሬት መራድና መንሸራተት፣ በአውሎንፋስና ውሃ መጥለቅለቅ በሰደድ እሳትና በሌሎችም። ለዚህ ሁሉ ጥፋት ግን በአንድም ይሁን በሌላ የሰው ልጅ እጆች አስተዋጽኦው የላቀ ነው። ሰው ተፈጥሮን አክብሮ ከመያዝ ይልቅ ለተቸረው ድንቅ ስጦታ ግዴለሽ መሆኑ ዛሬም ድረስ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል።
ወደእኛ ሀገር እንመለስ። አሁን የምንገኝበት ጊዜ የክረምት ወቅት ነው። ክረምታችን ምንጊዜም ቀኑን ቆጥሮ፣ ወራትን አስልቶ የሚደርስ ነውና ገብቶ እስከሚወጣ በራሱ ባህርይ ይገዛል። ወራቱ ላይ የጎበዙ ብርቱዎች ጊዜውን በወጉ ተጠቅመው አዝምረውና አርሰው የሚጎርሱበት ነው፡፡
በክረምት የሚታሰበው ዝናብና ጭቃ ብቻ አይደለም። በጊዜው በረከቶች ልሥራ ፣ልጠቀም የሚል ከተገኘ ወቅቱ ለእርሱ ከወርቅ በላይ ይመዝናል። ከዚህ እውነታ ወጣ ብለን ስናየው ደግሞ ክረምት በተለይ ለከተማ ነዋሪዎች ከችግሮች ጋር የሚታሰብ ከባድ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል።
ዛሬ ላይ በመኖሪያ አካባቢዎቻችን ጥቂት በማይባሉ ሥፍራዎች ቆሻሻ አብሮን ውሎ ያድራል። ለዓይን የሚከብድ ለአፍንጫ፣ የሚሰነፍጥ፣ ለእይታ በእጅጉ የሚያስጠላ ቆሻሻ ለእኛ ብርቃችን አይደለም። ከተማችን ሁሌም ከቆሻሻነት መልኳ ተላቀቀች፣ ጸዳች ሲባል አይሰማም። ቀኑን ሙሉ ሲጠርጉ ቆሻሻን ሲያስወግዱ የሚውሉ ሠራተኞች ማግስቱንም መኪና ሞልተው ሲሄዱ ይታያል። ይህ ደግሞ ክረምቱ ላይ ሲሆን ጉዳቱ የከፋ ነው። ቱቦ ውስጥ የከረመ ቆሻሻ፣ በዝናብ የራሰ ቆሻሻ፣ ሆን ብሎ የሚጣል ቆሻሻ በአንድ ያብሩና ሽታቸውን ሊናገሩት ይከብዳል፡፡
በጋ በሆነ ጊዜ ደረቅ ቆሻሻው ራሱን ችሎ የሚወገድ ነው። ክረምት ላይ ግን ለሚጣለው ቆሻሻ ሌላ ሃይል ይጨመርለታል። በተለይ እንደነገሩ ዝናብ አግኝቶት የከረመ ካለ ችግሩ ከህመም በላይ ነው። ማንም ይህን እንደ ግድ ሊቀበለው የኑሮ ሁኔታዎች ያለምዱታል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች ቆሻሻን በቀን ከቤት አውጥቶ መጣል በሕግ ተከልክሏል። እንደቀድሞው በቀንና ባሻው ሰአት ቆሻሻ የሚጥል ሰው ከተገኘ ቅጣቱ ከፍ ያለ ይሆናል። አስገራሚው ጉዳይ ግን ቀን የተከለከው ሕግ ተገልብጦ ምሽት ላይ መተግበሩ ነው። ደንቡ ሲወጣ ግን ለተጠቃሚዎች ቀንና ሰአት ተለይቶ ነበር፡፡
ለአንዳንድ ሰዎች ይህ አይነቱ መመሪያ ያመቻቸው ይመስላል። የቤት፣ የግቢያቸውን ያለ የሌለ ቆሻሻ አውጥተው የሚጥሉት ሁሌም ምሽት ላይ ሆኗል። አብዛኞቹ ‹‹አዩኝ አላዩኝ›› በሚል ጨለማን ይተገናሉ። የእነሱን በምሽት መድረሰ የሚናፍቁ ቋጠሮ በርባሪዎች ደግሞ ከስፍራው እስኪርቁላቸው አይጠብቁም። በየላስቲኩ ያለውን ምናምን ለመበርበር ይፈጥናሉ። የሚፈልጉት ነገር ፣ ከማይፈልጉት ቆሻሻ እስኪለይ አካባቢው ለመዝረክረክ አፍታ አይቆይም፡፡
የተጣለው ውዳቂ በየቦታው ሲበተን ደግሞ ሊያነሳው ዞር የሚል አይገኝም። መዝረክረኩ ለውሻና ድመት ሲሳይ ሆኖ ስፍራው በሚያስነውር እይታ ይሞላል። እንደተለመደው ቆሻሻን የሚያስወግዱ ሠራተኞች ያለሰአታቸው ብቅ አይሉም።
ቀኑ በክፉ ሽታና ለዓይን በሚያስቀይም እይታ ታጅቦ ይውላል። ምሽት ደግሞ ሁሉም እንደልምዱ ሆኖ ይቀጥላል። ቆሻሻውን የሚያነሱት ስራቸውን ጨርሰው ሲሄዱ የሚጥሉት ደግሞ በእግራቸው ይተካሉ። ‹‹ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ›› ሂደቱ አይቋረጥም፡፡
በአብዛኞቹ የከተማችን አካባቢዎች ያሉ የውሃ መውረጃ ቱቦዎች ክረምት ላይ በቆሻሻ ይደፈናሉ። ዝናብ ጠብ ካለ አልያም ከባድ ሆኖ ከጣለ ዓይናችን ተአምር ያያል። ጎርፉ መሄጃ መስመር የለውም። ወደ አስፓልት ገንፍሎ ይወጣል። በአፍታ ቆይታ መውጫ መግቢያ መንገዶች ይዘጋሉ። ይህኔ መኪኖች እግረኞች፣ ከአንድ ቦታ ለሰአታት ሊታገቱ ግድ ነው። እንዲህ በሆነ ጊዜ ቀድሞ ባልተለመደ ሁኔታ አስፓልቱ በጎርፍ ተሞልቶ ይዘጋል። የውሃ ሙላቱ ሄዶ እስኪያበቃም ተጎልቶ መቆየት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡
የዝናቡ አጋጣሚ በተለይ ምሽት ላይ ችግሩን ያብሰዋል። በመዘጋጋቱ ምክንያት በሚኖር የረዘመ ቆይታ ብዙዎች በሰአቱ ለቤታቸው እንዳይገቡ ምክንያት ነው። ከጨለማው መግፋት ጋርም በርካቶቹ ለዝርፊያና እንግልት ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡
ብዙ ጊዜ የመንገድ ላይ ጎርፍ ጥፋቱ ከፍ ያለ ነው። በሱቆች ዳርቻ ያሉ የሽያጭ ዕቃዎችን አግበስብሶ ይወስዳል። እግረኞችን አብዝቶ ይፈትናል። የመንገድ ላይ አካፋዮችን፣ ጠቃሚ የሀገር ሀብቶችን ያወድማል። ይህን የዚህን ሁሉ ችግር የመነሻ ምንጭ እንመርምር ከተባለ መልሱ አንድና ግልጽ ነው። ከየቤታችን ፣ ከየመንደራችን እያወጣን እንደዋዛ የምንጥለው ቆሻሻ፡፡
በያዝነው ክረምት በዚሁ የመነሻ ችግር ሳቢያ ብዙዎቻችን ከመንገድ ላይ እናመሻለን። ለመራመድ፤ ለመሻገር ተቸግረንም ድንገቴውን የጎርፍ ሙላት ስንለምን እንቆያለን። ጥቂት የማይባሉ ወገኖች ደግሞ ሥራ ውለው ሲገቡ ቤታቸው እንዳይሆን ሆኖ ያገኙታል፡፡
የቆሻሻ አጠቃቀማችን ችግር ከራሳችን አልፎ በዓለም ጭምር ስማችን በክፉ እንዲነሳ አድርጓል። ዛሬም ግን ለዚህ እንከናችን ዘላቂ መፍትሄ እየፈለግን አይደለም። አሁንም ከእኛ የምናስወግደውን ቆሻሻ በየመንገዱ እንጥላለን። ዛሬም ከበሽታና ፣ ከከፋ ጉንፋን አልወጣንም። ዝናብ በጎበኘን ቁጥር አስፓልቶቻችን ጀልባ የሚሹ ይመስላል። አሁንም ከችግርና ከጎዳና ላይ ጎርፍ አልተላቀቅንም፡፡
አንዳንዴ የከተማዋ የጽዳት ሠራተኞች ድካም በእጅጉ ያሳዝናል። በ‹‹ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ሂደት ሲመላለሱ መኖራቸው እንዳለ ሆኖ ሥራቸው ያለመፍትሄ መቀጠሉ አስገራሚ ያስብላል። ሁሌም በጋሪ ሞልተው የሚወስዱት የቆሻሻ ክምር በአብዛኛው የሚዛቀው ከየቱቦዎቹ ነው፡፡
ለከተማችን መንገድ ማሳለጫ ተብለው በሚሠሩ መንገዶች ላይ የሚዘጋጁ ቱቦዎች ከፍተኛ ወጪ የተከፈለባቸው ነው። እነዚህ የሀገር ሀብቶች ግን በወጉ ተሰርተው እንኳን ሳይጠናቀቁ ሆዳቸው በቆሻሻ ይታጨቃል። ልማደኛው ጎርፍ ደርሶ ዳርቻውን ሲያጥለቀልቅ ችግሩን የመታደግ አቅም የላቸውም። ማዳን ሲገባቸው እነሱም ሰለባዎች ይሆናሉ፡፡
ከዚህ አጋጣሚ በኋላም ሆነ በፊት በየዕለቱ የጎረሷቸውን ውዳቂዎች ጠርጎ የማውጣት ግዴታ የተጣለው በእነዚሁ መከረኛ የጽዳት ሠራተኞች ትከሻ ነው። በየቀኑ ቆሻሻው ይታጨቃል። በየቀኑ ጠርገው ያወጣሉ። እንደ እኔ ግን ንብረትን ለጉዳት ዳርጎ ከማበላሸትና ጉልበት በከንቱ ከማባከን መፍትሄው ቢበጅ ይሻላል ባይ ነኝ፡፡
አሁን ላይ በየአካባቢው ተሠርተው የተጠናቀቁ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገዶች ጥቂቶች አይደሉም። ከግንባታው ጋር የተቀበሩና ክፍት የተተው ትላልቅ ቱቦዎች ደግሞ ያለአንዳች አገልግሎት ይታያሉ። እነዚህ ቱቦዎች የቆሻሻ ምሽግ ናቸው። አሳቢ ቢገኝ ኖሮ በወቅቱ ሽራ ማስጀመር ፣ አልያም በጠንካራ ሽፋን መጋረድ ያስፈልግ ነበር።
እንዲህ ከተሞከረ አገልግሎት የሚሰጡት ቱቦዎች ጠቀሜታ ለተሠሩለት ዓላማ ብቻ ይሆናል። ቆሻሻ ማጨቃቸው ይቀርና ለውሃ መውረጃ ብቻ ይሆናሉ። ይህ የኔ አስተያየት፣ የቢሆን ምክርና ግሳፄ ነው። ያው የሚሰማ ከተገኘ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም