ኢትዮጵያ ለሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታና ስነምህዳር ካላቸው እና ተመራጭ ከሆኑ የዓለም ሀገራት አንዷ ነች። በተለይም የአየር ንብረቷ፣ ስነምህዳሯና ሰፊ የሰው ሀብቷ በዘርፉ መዋእለ ንዋያቸውን ስራ ላይ ለማዋል ለሚሹ ባለሀብቶች ሳቢ እንደሚያደርጋት ይገለጻል።
ይህንን እምቅ አቅም በመጠቀም ረገድ ያላት ተሞክሮ ከሁለት አስርት ዓመታት የማይዘልና ለምጣኔ ሀብት እድገትም የሚገባውን ያህል አስተዋፅኦ አበርክቷል የሚባል አለመሆኑም እየተጠቆመ ነው። በሀገሪቱ የግብርና ኢንቨስትመንት የሚገባው ያህል ማደግ ላለመቻሉና ካለው እምቅ አቅም አኳያ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳያበረክት አድርገዋል በሚል ከሚጠቀሱ ተግዳሮቶች መካከል የመሬትና የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ዋነኛዎቹ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይጠቀሳል።
የዘርፉን ችግሮች ከመፍታት አኳያ መንግሥት የተለያዩ ተግባሮችን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል። ከእነዚህም መካከል ከሰሞኑ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ስርነቀል በሚባል ደረጃ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዋነኛው ነው። ይህ ማሻሻያ በተለይ በኢንቨስትመንትና ንግድ ላይ ለተሰማሩ ተዋናዮች አዲስ ተስፋ የፈነጠቀ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተናገሩ ናቸው። ማሻሻያው በኢኮኖሚው ላይ ለረጅም ጊዜ የቆዩ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት እና ዘላቂ እድገት ለማስፈን እንደሚያስችልም ታምኖበታል።
ማሻሻያው በተለይ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩና ምርቶቻቸውን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚልኩ ባለሀብቶች የዘመናት ጥያቄና የሥራ ማነቆ የሆነባቸውን የውጭ ምንዛሬ ጥያቄ የሚመልስ እንደሆነም ይጠቀሳል። ለመሆኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለአምራች ኃይሉ ምን ይዞ መጣ? ማሻሻያውን ተከትሎ የሚመጡ ለውጦችን መቋቋም የሚያስችል ነበራዊ ሁኔታስ ምንድን ነው? የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው በሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ለዚህ ምላሽ አላቸው።
አቶ ካሳሁን ስንታየሁ በኦሮሚያ ክልል ሆለታ የሚገኘውና በደቡብ አሜሪካውያን ባለሀብቶች የተመሰረተው አፍሪ ፍላወር ኩባንያ ሲስተም አድሚኒስተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅታቸው ላለፉት አስርት ዓመታት ከ40 አይነት በላይ አበቦችን በማምረት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገባል። በ74 ሄክታር ላይ ያረፈው ይኸው የአበባ ልማት፣ ከ650 ለሚልቁ ዜጎችም የሥራ እድል የፈጠረ ነው። በቀጣዮቹ ዓመታት ኢንቨስትመንቱን የማስፋፋትና የሠራተኞቹንም ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ አቅዶ እየሰራ ነው። መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያደርገው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን አቶ ካሳሁን ጠቅሰው፤ በተለይ ለአበባ ኢንቨስትመንት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች አቅርቦት፣ ጊዜውን የሚዋጁ ቴክኖሎጂዎችንና የአሰራር ሥርዓቶችን መዘርጋት ላይ በርካታ ችግሮች እንደሚስተዋሉ አመልክተዋል።
ድርጅቱ በኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ልማት ላይ በቆየባቸው ዓመታት እነዚህን ችግሮች ተቋቁሞ ኢንቨስትመንቱን ለማስቀጠል ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፣ በተለይ የድርጅታቸው ዋነኛ ምርት የሆነው ‘ሶፊሊያ’ የሚባለው አበባ ለመፍካት የሚያስፈልገውን ስኳር ለማግኘት ለረጅም ጊዜ መቸገሩ ለሥራው ማነቆ ሆኖበት መቆየቱን ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል ድርጅታቸው የአበባ ማሸጊያና ኬሚካሎችን ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስመጣ ተናግረው፣ ለዚህም የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ፈታኝ ሁኔታ እንደሚያጋጥመው ያነሳሉ። ‹‹ማሸጊያ ካርቶንም ሆነ ኬሚካል ለማምጣት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ከፍተኛ ችግር ነው የሚያጋጥመን፤ በዚህ ምክንያት እንደምንፈልገው መንቀሳቀስም ሆነ ምርቶቻችን ለመላክ ተግዳሮት ሆኖብን ቆይቷል›› ሲሉ ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት ድርጅታቸው ከመንግሥት አካላት ጋር ባደረገው የረጅም ጊዜ ውይይት የስኳር ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ይገልጻሉ። በቅርቡ ሀገሪቱ ወደ ሙሉ ትግበራ ያስገባችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተለይ በሆርቲካልቸር ልማት ላይ ለተሰማሩ አካላት ተስፋ የፈነጠቀ መሆኑን አቶ ካሳሁን አስታውቀዋል።
‹‹ መንግሥት ኢኮኖሚውን ለመታደግ እየወሰዳቸው የሚገኙት ቁርጠኛ ውሳኔዎች በተለይ ለኢንቨስትመንት ማበብ በር የሚከፍቱ ናቸው። በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በርካታ ባለሀብቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ያደርጋል፤ የገቡትም ልማታቸውን እንዲያስፋፉ ያነሳሳል›› በማለት ያስረዳሉ።
‹‹ከዚህ ቀደም የውጭ ምንዛሬ በብሔራዊ ባንክ ይያዝብን ነበር፤ በዚህ ምክንያት ግብዓቶችን እንደፈለግን ማስመጣት፤ ማምረትም ሆነ መላክ ፈተና ይሆንብን ነበር፤ አሁን መንግሥት ባለሀብቱ ዶላር በቀላሉ ከባንክ ሄዶ የሚያገኝበትን ሁኔታ በመፍጠሩ ኢንቨስትመንቱ የበለጠ እንዲያድግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል›› በማለትም ያብራራሉ። ይህ ሲሆንም ደግሞ ምርት ልኮ የሚያገኘውን የውጭ ምንዛሬ ውጭ ሳያስቀር ወደ ሀገር እንዲገባ ማድረግ እንደሚያስችል አቶ ካሳሁን ይገልፃሉ። ኢንቨስትመንቱ ባደገ ቁጥር ደግሞ ሰፊ የሥራ እድል ይፈጥራል፤ በስሩ የሚሰሩትንም ዜጎች የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል እምነት አላቸው።
የሉሲ እርሻ ልማት የኮሜርሻል ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ መኮንን ዛጋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በሀገር ውስጥ ባለሀብት የተመሰረተው ድርጅታቸው ላለፉት 25 ዓመታት በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ሰፊ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይም አርባ ምንጭ፣ ኦሞ እና ገዋኔ አካባቢዎች ላይ ባሉት እርሻዎቹ የተቀናጁ የግብርና ስራዎችን ይሰራል፤ በዋናነት የተመሰከረለትንና ተፈጥሯዊ (ኦርጋኒክ) የፍራፍሬና አትክልት ምርቶችን እንዲሁም ጥጥ፣ ጥራጥሬና የቅባት እህሎችንም በስፋት በማምረት ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመላክም ይታወቃል። ‹‹ድርጅታችን በዋናነት ሙዝ፣ የቅባትና ጥራጥሬ እህሎችን ለመካከለኛው ምሥራቅ፣ ለምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት እንዲሁም ታይዋን፣ ሞሪሽየስና ታንዛኒያ ደግሞ የጥጥ ምርት በመላክ ለሀገራችን በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ያስገባል›› ያሉት አቶ መኮንን ፤ በአሁኑ ወቅት ለአንድ ሺ 200 ዜጎች ቋሚ እንዲሁም ከስምንት ሺ ለሚልቁ የአካባቢው ነዋሪዎች ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ያስረዳሉ።
ድርጅቱ ጥሬ የግብርና ምርቶችን ከመላክ በዘለለ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ለመላክና የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን በእጥፍ ለማሳደግ እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ያመለክታሉ። ከእርሻው ጎን ለጎን አግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪውን በመቀላቀል ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል የመፍጠር ራዕይም አለው ይላሉ።
ድርጅቱ ይህንን ሰፊ የልማት ስራውን ለማሳካት ግን የመንገድና የኃይል መሰረተ ልማት፣ የመሬትና የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እንደስጋት የሚያየው መሆኑን አቶ መኮንን አመልክተዋል። ‹‹ በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ለተሰማሩ አካላት የመንገድና የኃይል መሰረተ ልማት እንደልብ አለመኖር ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል›› የሚሉት አቶ መኮንን፤ የፋይናንስ አቅርቦቱም ውስንነት ያለበት መሆኑ ኢንቨስትመንቱ እንዳይስፋፋ አድርጎታል የሚል እምነት አላቸው። በዚህ ረገድ መንግሥት በቅርቡ የወሰደው እርምጃ በብዙዎቹ የዘርፉ ተዋናዮች ዘንድ ተስፋ ያጫረ ስለመሆኑም ይናገራሉ።
‹‹የፋይናንስ እጥረት አምራቹን አንቆ በአንድ ቦታ የሚያስቀር አንገብጋቢ ችግር ነው፤ አሁን ላይ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ይህንን ችግር ይፈታልናል ብለን እንጠብቃለን፤ በተለይ እንደእኛ ላሉ የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለሚያቀርቡ ባለሀብቶች በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪና የተሻለ ዋጋ እንድናገኝ ያደርጋል›› ይላሉ።
ድርጅቱ በማሻሻያው የፋይናንስ እጥረቱ ይፈታል የሚል እምነት እንዳለው ጠቅሰው፤ የተሻሉ የገበያ አማራጮችን ለማስፋት እንደሚረዳውም ነው ያስታወቁት። በዚህ ረገድ ድርጅታቸው ማሻሻያው የሚያመጣውን ምቹ እድል በምን መልኩ ሊጠቀም እንደሚገባው አስቀድሞ ለማየት ጥረት ማድረጉን ይናገራሉ። ማሻሻያው ዘርፉን መቀላቀል ለሚሹ ትልልቅ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በር እንደሚከፍት ተናግረው፣ ድርጅታቸው በምን መልኩ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚገባው የራሱን ጥናት ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ያብራራሉ። ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮችም ማሻሻያው ለትልልቅ ኩባንያዎች በር እንደሚከፍት እየጠቆሙ መሆናቸውን ተናግረው፤ ከዚህ አንፃር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅባቸው አቶ መኮንን አስታውቀዋል። በተለይ ምርታማነትንም ሆነ ጥራትን ማሻሻል ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ ይገባል የሚል እምነት አላቸው። ለዚህ ደግሞ አምራች ኃይሉ ድርጅታዊ አቋሙን ማጠናከርና ከዓለም ገበያ ጋር ተወዳዳሪ መሆን የሚችል ድርጅት መፍጠር እንደሚጠበቅበት ያመለክታሉ።
‹‹ሁላችንም የዘርፉ አንቀሳቃሾች መጀመሪያ ውስጣዊ አቅማችንን ማጠናከር ላይ ትኩረት ልናደርግ ይገባል፤ የምርት ጥራትን ማሻሻልና አማራጭ ገበያዎችን መፈለግ ስንችል ነው ተወዳዳሪ ሆነን የምንዘልቀው›› ሲሉም መክረዋል።
የሆርቲካልቸር አምራቾች ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴድሮስ ዘውዴ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ለሆርቲካልቸር ምቹ ከሆኑ ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል የምትመደብ ብትሆንም፣ ከዚህ አንፃር ባለፉት ዓመታት ዘርፉ መጠነኛ የሚባል እድገት ከማስመዝገብ ባለፈ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በሥራ ፈጠራ በሌሎችም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች አነስተኛ አስተዋፅኦ ነው እያደረገ የቆየው። ይህ የሆነውም በዋናነት በመሬት፣ በፋይናንስና የሎጅስቲክስ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ባሉ ችግሮች ምክንያት ነው። በተለይም ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ማቅረብ የሚያስችል አቅም ቢኖራትም ይህንን አቅም መጠቀም ላይ ውስንነት ይስተዋላል።
በኢትዮጵያ ካለው እምቅ አቅም አኳያ፤ በተለይም ሰፊና የሚለማ መሬት፣ ጥራት ያለው የገፀ ምድርም ሆነ የከርሰ ምድር ውሃ አላት። ለመካከለኛውና ለአውሮፓ ገበያም ቅርብ ናት፤ ይሁንና ያለውን ምቹ ሁኔታ መጠቀም ላይ ክፍተት ይስተዋላል ሲሉ ያብራራሉ። በዘርፉ የሚታየውን ችግር በመፍታት ረገድ መንግሥትም ሆነ ማህበራቸው ቅንጅት ፈጥረው ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አቶ ቴድሮስ ጠቅሰዋል።
በዚህም መጠነ ሰፊ የሚባል እድገት ማስመዝገቡን ይናገራሉ። ‹‹ባለፉት ዓመታት መንግሥት ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ ወሳኝ የሚባሉ እርምጃዎችን ወስዷል፤ ከእነዚህም መካከል እንደቴሌኮም ያሉና በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበሩ ተቋማትን ነጻ /ሊብራላይዝድ/ በማድረጉ በርካታ የውጭ ኢንቨስትመንቶች እንዲመጡ ምክንያት ሆኗል›› ይላሉ። የሆርቲካልቸር ኢንዱስትሪ በተለይ በወጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ተናግረው፣ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ለመገናኘት የቴሌ ኮም መሰረተ ልማት መስፋፋት ወሳኝ በመሆኑ ውሳኔው ጠቃሚ መሆኑን ያስረዳሉ። በሌላ በኩል የነፃ ገበያ ቀጣና መፈቀዱ ሌላው ዘርፉ ዳግም እንዲያንሰራራ እንደሚያደርገው አቶ ቴድሮስ ያመለክታሉ።
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የግብዓትና የፋይናንስ አቅርቦቱ ሙሉ ለሙሉ መፈታት ከቻለ ደግሞ የዘርፉ ተወናዮች በዓለም ገበያ ላይ የበለጠ ተፎካካሪ መሆን እንደሚችሉ ያስገነዝባሉ። ‹‹ ማሻሻያው መደረጉ በራሱ ኢንቨስተሩ እንደልብ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርገው በመሆኑ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እንዲያመጣ ያደርገዋል፤ ኢትዮጵያ ያላትን የሆርቲካልቸር አቅምም በአግባቡ ተጠቅማ ልማቷን እንድታፋጥን ያግዛታል የሚል እምነት አለኝ›› ሲሉም ነው ያስታወቁት።
እንደ አቶ ቴዎድሮስ ማብራሪያ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ካፒታል ይዘው የሚመጡ በመሆኑ ሁኔታ የሀገር ውስጡንም የግል ዘርፍ ያነቃቃል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም በሆርቲካልቸርም ሆነ በሌላ ኢንቨስትመንት ላይ ለተሰማሩ አካላት ተጨማሪ እድል ይዞ ይመጣል።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን በማሻሻል ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ አቅም ይፈጥርላቸዋል። ገበያም ይዘው የሚመጡ በመሆኑ የሀገር ውስጥ አምራቾች እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በአግባቡ መጠቀም የሚያስችላቸውን አቅም ሊያጎለብቱ ይገባል። ዝግጁነታቸውን አሁን የዓለም ኢንቨስትመንት በሚመጥን መልኩ ማዳበር ይጠበቅባቸዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9 /2016 ዓ.ም