“የኢትዮጵያ ታሪክ ከአትሌቲክስና ኦሊምፒክ ውጤት ጋር የተቆራኘ ነው” – የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ

በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ትናንት ማለዳ ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ምሽቱንም ፕሬዚዳንት ሳሕለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ለቡድኑ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የክብር ሽልማት፣ የማበረታቻ እና የእራት ግብዣ መርሐ-ግብር ተካሂዷል። በመርሐ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ፣ በፓሪስ ኦሊምፒክ የመክፈቻ ሥነሥርዓት ላይ በተገኙበት ወቅት ብዙዎች ኢትዮጵያ በርካታ ሜዳሊያ እንደምታገኝ ሲገልፁላቸው እንደነበረ አስታውሰዋል። ይህም ኢትዮጵያና የኦሊምፒክ አትሌቲክስ ከውጤት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ማሳያ አድርገው ጠቅሰዋል። ፓሪስ ላይ በከፍተኛ ተጋድሎ ሜዳሊያ ያስመዘገቡና ውጤት ለማምጣት ለጣሩት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

ፕሬዘዳንቷ ባለፈው ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ወቅት ቡድኑን ሲቀበሉ ከሦስት ዓመት በፊት ያደረጉትን ንግግር በመድገም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የአትሌቶቻችንን ድል አድራጊነትና የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊነት የመጠበቅ ባሕል ቢኖረውም ቶኪዮ ላይ ይህንን ማሳካት እንዳልተቻለ አስታውሰው ያለፈው ንግግራቸው ለአሁኑ የፓሪስ ውጤትም እንደሚሠራ ለማስረዳት ሞክረዋል። ችግሮች ሲፈጠሩ መመርመርና ማወቅ ብሎም ለቀጣይ ማስተካከል እንደሚገባ የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ ፓሪስ ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን በዝምታ ማለፍ እንደማይገባ ገልፀዋል። በዚህም ለቀጣይ ኦሊምፒክ ችግሮችን ቀርፎ መዘጋጀት የሚገባው ካሁኑ መሆኑን ጠቁመዋል። “የአትሌቲክስና ኦሊምፒክ ተቋማዊ ብቃታቸው ሊፈተሽና ሊታይ ሊመረመር ይገባል፣ የዓለምን ሁኔታ በሚመጥን መልኩ ዳግም ሊዋቀሩ ይገባል” በማለትም በቶኪዮ ኦሊምፒክ መልስ ያደረጉትን ንግግር ደግመው አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰና ሌሎች ሀገሮች እየበለጡን በመሆኑ ይህን የውጤት ቀውስ መቀረፍ ይኖርበታልም ብለዋል። የሀገር ኩራት የሆኑ አትሌቶቻችን በዓለም አደባባይ ማምጣት የሚችሉትን ውጤት እንዲያመጡ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ መሥራት ያለባቸው የቤት ሥራ እንዳለም ፕሬዚዳንቷ አሳስበዋል።

በሽልማት መርሐግብሩ ውጤት ባይቀናቸውም ለተሳተፉ አትሌቶች ከ75 ሺ ብር እስከ 300 ሺ ብር የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል። ከፍተኛ ተጋድሎን በማድረግ የብር ሜዳሊያን ያስመዘገቡ አትሌቶች አራት ሚሊዮን ብር ሲሸለሙ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበው አትሌት ታምራት ቶላ የ7 ሚሊዮን ብርና የወርቅ ኒሻን ተሸላሚ መሆን ችሏል። ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለም ላደረገው ጥሩ ተሳትፎ ከፍተኛ የወርቅ ኒሻን ተሸላሚ ሆኗል። ለአሠልጣኞች ከ50 ሺ ብር ጀምሮ አትሌቶቻቸው እንዳስመዘገቡት ውጤት የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል። የወርቅ ላመጣ አሠልጣኝ የ 2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል። አትሌት ለሜቻ ግርማ በልዩ ተሸላሚነት 2 ሚሊዮን ብር ተሸልሟል።

የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ፣ የኦሊምፒክ ስፖርት ሀገራት በአንድ መንደር ተሰባስበው የሀገራቸውን ገጽታ የሚገነቡበትና ሰንደቅ ዓላማቸውን ከፍ የሚያደርጉበት ሠላማዊ መድረክ እንደሆነ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን በታሪካዊ ድሎችም ጭምር በዓለም ዘንድ ትጠበቃለች። ይህም የሆነው በትብብር የማይቻለውን ሁሉ ችለን ሰለምናሳይ ነውም ብለዋል። የተመዘገበው ውጤት አበረታች ቢሆንም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ውጤታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ብርቱ ፈተና እንደገጠመው ያለፉት ሁለት ኦሊምፒኮች ማሳያ እንደሆኑም ገልጸዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ለሚታዩ ችግሮች ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በጥናትና ውይይት ከአሠራር፣ አደረጃጀትና አመራር አንጻር የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት በልዩ ትኩረት ይሠራል ብለዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You