የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ኢራን በእስራኤል ላይ ለመፈጸም ያሰበችውን የአጸፋ ምላሽ እንድታቆም ጠየቁ::
የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ እስማኤል ሀኒየህ በቴህራን መገደሉን ተከትሎ በቴልአቪቭ ላይ ከኢራን ይፈጸማል ተብሎ የሚጠበቀው የአጸፋ ምላሽ እየተጠበቀ ነው::
ይህን ተከትሎም ቀጣናው ወደለየለት ጦርነት ሊመራ እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት አንዣቧል::
ኪር ስታርመር ከኢራኑ ፕሬዚዳንት ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት የአጸፋ ጥቃቱ ከፍተኛ አደጋን የሚያስከትል የጋዛውን ጦርነት ማብቂያም ሊያራዝም የሚችል ሁነት በመሆኑ በጉዳዩ ላይ እንዲያጤኑበት ጠይቀዋል::
የቀድሞው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከቀድሞው የኢራን ፕሬዚዳንት ሀሰን ሩሀኒ ጋር በ2021 ካደረጉት የስልክ ንግግር ቀጥሎ ከሦስት ዓመታት ወዲህ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በቀጥታ ሲነጋገሩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው::
ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና አሜሪካ ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመሰነዝር እንድትታቀብ የጋራ መግለጫ ካወጡ በኋላ ሁለቱ መሪዎች ለ30 ደቂቃ የስልክ ውይይት አድርገዋል::
ምዕራባውያኑ በጋራ ካወጡት መግለጫ ባለፈ እሥራኤል ከኢራን እና በሽብርተኛነት ከተፈረጁ ታጣቂ ቡድኖች የሚሰነዘርባትን ጥቃት መመከት ትችል ዘንድ እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል::
የኢራን እና የብሪታንያ መሪዎች በነበራቸው የስልክ ቆይታ ከጋዛው ጦርነት ባለፈ በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ዙሪያም መክረዋል::
ለዘብተኛ የሚባሉት አዲሱ የኢራን ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዚሽኪያን ሀገራቸው ከምዕራቡ ዓለም ጋር የገባችበትን ውጥረት ለማርገብ እና ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ቃል ገብተዋል::
ቢቢሲ እንደዘገበው ፕሬዚዳንቱ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ሁኔታዎችን ለማሻሻል ከሚወስዷቸው ርምጃዎች መካከል እሥራኤል ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት ማስቀረት አንዱ ሊሆን ይችላል::
ሆኖም ውሳኔው ከፕሬዚዳንቱ ባለፈ የሃይማኖታዊ መሪውን አያቶላ አሊ ሀሚኒን ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል::
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በእሥራኤል ላይ ጥቃት የመሰነዘር እቅድ እንዳልተቀየረ እና በትክክለኛው ሰዓት እና ቦታ ተመጣጣኝ እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጧል፡
አሜሪካ በበኩሏ በቀጣናው ከፍተኛ የጦር መሣሪያዎችን እና የውጊያ መርከቦችን ያስጠጋች ሲሆን በትላንትናው እለት 154 የቶምሃውክ ክሩስ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፍ የሚችለውን ሰርጓጅ መርከብ ወደ ቀጣናው ልካለች::
ቴህራን በእሥራኤል ላይ ምን አይነት ጥቃት ልትሰነዝር እንደምችል ቦታው እና ጊዜው እስካሁን ባይታወቀም እሥራኤል እና አጋሮቿ ሊሰነዘር የሚችለውን ጥቃት ለመከላከል ከፍተኛ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ::
በመጪው ሐሙስ የእሥራኤል እና የሀማስ መሪዎች በተኩስ አቁም እና ታጋቾችን በማስለቀቅ ዙሪያ በአፋጣኝ እንዲደራደሩ በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት በድርድሩ በጎ ውጤት የሚገኝ ከሆነ የቀጣናውን ውጥረት በመጠኑም ቢሆን ሊያረግበው እንደሚችል ይጠበቃል::
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም