የትርክት ዕዳ እና ድህነት

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የጻፈው ‹‹የትርክት ዕዳና በረከት›› መጽሐፍ ባለፉት ሳምንታት አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል:: በፋና እና በዋልታ ቴሌቪዥን ቀርቦ ለጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ ሰጥቷል:: ከመጽሐፉም ሆነ ከጸሐፊው ተጨማሪ ማብራሪያዎች (በቃለ መጠይቆች) የምንረዳው ነገር የትርክት ዕዳ ምን ያህል ወደ ድህነት እንደሚወስደን ነው:: የመጽሐፉን ይዘት በተመለከተ በሌላ ዓምድ የሚታይ ስለሚሆን ለዛሬው ግን ትርክት ላይ ያለኝን ትዝብት ላጋራ::

እስኪ ፖለቲከኞቻችንን ልብ በሉ! መድረክ ባገኙ ቁጥር፣ በመገናኛ ብዙኃን ለቃለ መጠይቅ በተጋበዙ ቁጥር፣ በብዛት የሚያወሩት ስለምንድነው? በሀገሪቱ ውስጥ ስለሚባክነው ሀብት ያወራሉ? ይህን እምቅ ሀብት ይዘን ለምን ድሃ ሆንን ብለው ይቆጫሉ? ስለጤና እና የኢኮኖሚ ዘርፎች ያወራሉ?

ሁሉም ለማለት በሚያስችል ሁኔታ የሚያወሩት ‹‹እገሌ እገሌን በድሏል›› የሚል ነው:: አሁን ላለ ችግር ያለፈውን መርገም ነው:: 100 እና 200 ዓመት ወደኋላ እየተመለሱ እገሌ የእገሌን ዝርያ ጨፍጭፏል የሚል ነው:: እገሌ የሚባል ዓፄ እዚህ ቦታ እንደዚህ አድርጓል የሚል ነው:: ይህን አጀንዳ በጣም ከመደጋገማቸው የተነሳ ወጣቱ ትውልድም በዚሁ ትርክት ተቀረጸ:: ስለዚህ የጋራ ማንነት እንዳይኖር አደረጉ ማለት ነው:: ወደ ግጭት ሄድን ማለት ነው:: ግጭቶች ደግሞ ለድህነት ዳረጉን ማለት ነው::

ዓለም እያወራና እየሠራ ያለው ስለወደፊቱ ነው:: 22ኛው ክፍለ ዘመን ምን ሊሆን ይችላል? እየተባለ ነው:: ያለፈውን ዘመን የሚጠቀመው ከዚህ ነው የተነሳን ለማለት ብቻ ነው:: የሠለጠነው ዓለም ከ100 እና 200 ዓመት በፊት በነበረ ድርጊት አይጨቃጨቅም:: በ22ኛው ክፍለ ዘመን ምን አይነት የሰው ልጅ አኗኗር እንደሚኖር እያሰበ ነው::

እኛስ? እኛ ደግሞ የምናስበው ስለ 22ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ ሳይሆን ስለ 19ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ ነው:: ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ ማለት ነው:: ሁልጊዜ ወደኋላ ብቻ የምናስብ ከሆነ ትውልዱ ዘመናዊ አይሆንም:: በትርክትና ጥላቻ የተበረዘ ይሆናል:: በጥላቻ ትርክት ከተበረዘ ደግሞ ወደ ግጭት ያመራል ማለት ነው:: ግጭት ደግሞ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ ድህነት ላይ ይጥለናል::

ግጭት ድህነት ላይ ይጥለናል ሲባል በጦርነቱ የሚወድመው ንብረት ብቻ አይደለም:: እንዲያውም በጦርነቱ በቀጥታ ከሚወድመው በላይ አደገኛ የሚሆነው ሥነ ልቦናዊና አካባቢያዊ ጫናው ነው:: በግጭቶች ምክንያት ሰዎች ሥራ ለመሥራት አያስቡም:: የረጅም ጊዜ ዕቅድ አይኖራቸውም:: እስኪ ወደዚህ አካባቢ ሄጄ እንዲህ አይነት ሥራ ልሥራ፣ ይህን ከዚህ አካባቢ ገዝቼ እዚህኛው አካባቢ ልሽጥ…. የሚሉ የሥራ ሀሳቦች አይኖሩም:: ይህ የሚሆነው ግጭቶች ባሉበት አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ምንም ግጭት በሌለባቸው አካባቢዎችም ጭምር ነው:: ምክንያቱም ሀገራዊ አጀንዳው እገታና ጦርነት ከሆነ የሥራ ወኔዎች ይቀዛቀዛሉ:: ለምሳሌ፤ በመዝናኛው ዘርፍ በኩል ያሉ የሥራ ዘርፎች ይቀዘቅዛሉ:: ስለዚህ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየተፈጠረ ነው ማለት ነው::

ይህ ሁሉ የሆነው እንግዲህ በፖለቲከኞች የትርክት ዕዳ ነው:: የማያውቀውን የ10ኛ ትውልድ ዝርያውን እየጠሩ እገሌ እንዲህ አድርጎብሃል እያሉ አዕምሮው ላይ በሠሩት ሥራ ነው:: በሠላም ይኖር የነበረውን ኅብረተሰብ በጥርጣሬ እንዲተያይ በማድረጋቸው ነው:: ገዥ መንግሥታትን ከአንድ አካባቢ ሕዝብ ጋር በማያያዝ ‹‹እነርሱ ናቸው›› የሚል የተሳሳተ ትርክት በመዘርጋቱ ነው::

እኔ ስለ ዛሬው እና ስለ ነገው ነው ማሰብ ያለብኝ:: ከ200 ዓመት በፊት ከነበረ አንድ የእኛ ሰፈር ሰው፤ ዛሬ ላይ በሕይወት ያለ የሞያሌ ሰው ይቀርበኛል:: ምክንያቱም የዚህ ትውልድ ሰዎች ነን:: እኔ የመሐል ሀገሩ ሰውና አንድ የሞያሌ ወይም የዓዲግራት ወይም የመተማ ሰው ብዙ የሚያገናኘን ነገር አለ:: ብዙ የጋራ ነገር አለን:: እኔና ከ200 ዓመት በፊት የነበረው ሰውየ ግን ምንም የሚያገናኘን ነገር የለም:: ያ ዘመን እና አሁን እኔ ያለሁበት ዘመን ሌላ ዓለም እና ሌላ ዓለም ማለት ነው:: ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ከ800 ሺህ ዓመት በፊት ገና በሁለት እግር ቆሞ መሄድ የጀመርንበት ነበር:: ከዚያ በፊት ዝንጀሮ መሳይ ነበርን:: ስለዚህ ጊዜው እየራቀ በሄደ ቁጥር ጭራሽ ሌላ ዝርያ እና ሌላ ዝርያ ሁሉ ልንሆን እንችላለን ማለት ነው:: ታዲያ በምን ዕዳዬ ነው ከመቶ ምናምን ዘመናት በፊት በነበሩ ሰዎች ጣጣ እኔ የምጨቃጨቀው? ምን አይነት ኋላቀርነት ነው?

ያለፈ ዘመን ለጥናትና ምርምር፣ ከዚህ ተነስተን እዚህ ደረስን… ለማለት ነው እንጂ መዋል ያለበት፤ በዚያኛው መነጽር የዛሬውን ለማየት አይደለም:: ያ ዘመን እና ይህ ዘመን አይነፃፀርም:: ደርሶ የእገሌ ዘር ነኝ ማለት ልክ አይሆንም::

በጥንት ዘመን የሰው ልጅ በለቀማ እና በአደን ይኖር ነበር:: አደን ማለት ልክ እንደ ዛሬው ሕክምና፣ ምሕንድስና፣ ፓይለት… አንድ የሥራ ዘርፍ ነበር:: የሚኖረው በማደን ነበር:: ዛሬስ? ዛሬ ነውር ነው፤ የእንስሳት መብት ጠባቂ ተቋማት ተፈጥረዋል:: ብዙ እንስሳት የቤት ሆነው ተላምደዋል:: የዱር የሆኑትም ጥብቅ እና ብርቅዬ ተብለው ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው:: ይህ በሥልጣኔ የመጣ ነው::

ልክ በዚህ የዘመን ቅደም ተከተል መሠረት ከመቶ ምናምን ዘመናት በፊት ጨካኝ ድርጊቶች ቢኖሩ ይገርማል ወይ? ሰብዓዊ ሥነ ልቦናዊ ከዛሬው ጋር ይነፃፀራል ወይ? በዛሬ መነጽር ለምን እናየዋለን? ሲቀጥል ደግሞ እኛ ከሺህ ዘመናት በፊት ከነበረው እየባስን አይለም ወይ? ሰው ከነነፍሱ ሲቃጠል እያየን አይደለም ወይ? ከዚያኛው ይልቅ ለምን ይህኛው አልቆጨንም፣ አላስገረመንም?

የድሮ ነገር ትርክት ላይ መሟጨጭ የሰነፎች ነው:: ስለዛሬው ማሰብ የማይችሉ ሰዎች የሚያደርጉት ነው:: ዘመኑ የደረሰበት ልዕልና ላይ ያልደረሱ ሰዎች የሚያደርጉት ነው:: ‹‹ያኔ እንዲህ ተደርጎ ነበርና…›› ማለት የዛሬውን መረዳት አለመቻል ነው::

ወዲህ ደግሞ በድሮ ነገር መፎከርም እልም ያለ ስንፍና ነው:: ለምንድነው ከ100 ዓመት በፊት በነበረ ሰው የሚፎክር? ፉከራው ብቻ እኮ አይደለም ችግሩ! ጭራሽ የሚፎክርባቸው ሰዎች ካደረጉት በተቃራኒው ሆኖ መፎከሩ ነው እንጂ:: የእነርሱን ሰብዓዊነትም ሆነ አስተዋይነት የሌለው መሆኑ ነው:: ከ100 እና ከ200 ዓመት በፊት በነበሩ ሰዎች ስም እየፎከረ እሱ ግን ከእነርሱ ያነሰ ሰብዓዊነትና አስተዋይነት ያለው ነው::

የሰው ልጅ በየዘመኑ የራሱን መልክና ቅርጽ ይይዛል:: ከዛሬ 100 ዓመት በኋላ ምናልባትም ሁላችንም አንኖርም፤ ይህንንም እያሰብን::

ስንፍናችን ከብዙ ዘመናት በፊት የነበረው ላይ ብቻ አይደለም:: ትናንት ያየነውን፣ በሕይወት ኖረን ያሳለፍነውን ሁሉ እንክዳለን:: ይህም በትርክት ጫና የሚመጣ ነው:: የኖርኩበትን ዘመን ማንም ሊያጭበረብረኝ አይችልም:: ብዙ ፖለቲከኞች ግን ራሳቸውን የጥፋቱ አካል ከማድረቅ ይልቅ እገሌ እንዲህ ስላደረገብኝ ነው የሚል ሰበብ ይፈልጋሉ:: ገዥ መንግሥትን ከሕዝብ ጋር በማገናኘት ‹‹ተረኝነት፣ ወገንተኝነት፣ የእነ እገሌ የበላይነት…›› በማለት ሕዝብ ጭምር በጥርጣሬ እንዲተያይ ያደርጋሉ:: አንድ መንግሥት መወቀስ ካለበት አመራርነት ላይ ያሉትን እንጂ ተራው ሕዝብም ምን አድርጓል?

ለሚመጣው ትውልድ የሚሆን ነገር ነው ማስቀመጥ ያለብን:: ለትልውድ ነው የምንሠራው ካልን የምናደርገው ነገር ለትውልድ ይሆናል ወይ? የሚለውን ልብ ማለት አለብን:: ስለዚህ የትርክት ዕዳ ከድህነት ወደ ድህነት እየወሰደን ነውና ለትውልድ እናስብ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You