ዜና ትንታኔ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በተደረገ ክትትል እና ቁጥጥር በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሠማርተው በተገኙ ሰባት ሺህ 676 ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
ማሻሻያው ተግባራዊ ከተደረገበት ጀምሮ በተካሄደ የገበያ ክትትል እና ማረጋጋት ሥራ እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ አለአግባብ ዋጋ በጨመሩ ሰባት ሺህ 312 ተቋማት ላይ የማሸግ እንዲሁም በ42 ተቋማት ላይ ፈቃድ የማገድ ርምጃ መወሰዱንም ይፋ ተደርጓል፡፡
በተመሳሳይ የ36 የንግድ ተቋማት ፈቃድ ሲሰረዝ፣ በ286 ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ደግሞ የእስራት ቅጣት ተጥሏል፡፡ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ መመሪያ ትግበራ እና በንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚደረገው ክትትል እና ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለመሆኑ መንግሥት በነጋዴዎች ላይ እየወሰደ ያለው ርምጃ ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል ወይ? ስንል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን ጠይቀናል። የፐብሊክ ፖሊሲና ምጣኔ ሀብት ምሑሩ ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ በአዲስ አበባ አብዛኛዎቹ ምርቶች የሚሸጡት ከጥቁር ገበያ በተገኘ ምንዛሪ ዋጋ ነው።
ይህም ማለት አንድን ዶላር በመቶ ሃያ ብር ገዝተው ከውጭ ሀገር ባመጡት ምርት ላይ ትርፋቸውን ጨምረው ምርቱን ለኅብረተሰቡ ያቀርባሉ ማለት ነው። ከዚህ በመነሳት አሁን ላይ ነጋዴዎች የዋጋ ጭማሪ ማድረግ የለባቸውም ማለት ነው። የነጋዴዎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሕዝቡን ሠላም ይፈታተናል። በዚህም የመጀመሪያዎቹ ተጎጂዎች እነሱ ናቸው። መንግሥት ነጋዴዎች ላይ ከሚወስደው ርምጃ ባሻገር ሰፊ የማስተማር ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ ያብራራሉ።
ሌላው መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ከማሳወቁ በፊት መሠረታዊ ምርቶችን በብዛት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱን መግለጽ ነበረበት ያሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ ይህም ነጋዴዎች በመጋዘን ያስቀመጡትን ምርት አውጥተው እንዲሸጡ ያደርጋል ነው ያሉት።
አሁን ላይ መንግሥት ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባቸውን ምርቶች ለሕዝብና ለነጋዴው እያሳወቀ መሆኑን የገለጹት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ ይህ ተግባር ቀድሞ የተደረገ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ መልካም እንደሚሆን ተናግረዋል። በዚህም ነጋዴው ከርምጃ ኅብረተሰቡ ደግሞ ከዋጋ ጭማሪ ይድን እንደነበር ይገልጻሉ።
ሕዝብን እየበዘበዙ እንዲሁም ራስን እያበለፀጉ የትም መኖር እንደማይቻል ለነጋዴዎች ማስተማር ይገባል። ሕዝብን የሚጎዳ ተግባር ማኅበራዊ ቀውስ የሚፈጥር እና እራሱን ነጋዴውን ፈተና የሚጥል መሆኑን ማሳወቅ ይገባል ብለዋል። ለዚህም የሚዲያ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የሰጡት የብድርና የድጋፍ ገንዘብ የኢኮኖሚ መሸጋገሪያ መሆኑን ገልጸው፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው ሲሠሩ እና የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ኢኮኖሚው ጠንካራ ይሆናል ባይ ናቸው።
ይህም የሥራ አጥ ቁጥርን ይቀንሳል። በዚህም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያድጋል። ይችን አጭር የውዥንብር ጊዜ መንግሥት ሊያደርግ የሚገባው ከሕዝብ ጥቆማ እየተቀበለ ቁጥጥሩን ማጠናከር አለበት። ለዚህም ከወረዳዎች፣ ከሲቪል ማኅበራትና ከሚዲያ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት አለበት ነው ያሉት።
ምክንያቱም አንዳንዴ ነጋዴዎች ሳያውቁ ሀገሪቱን ቀውስ ውስጥ ሊከቱ ይችላሉ። በዚህም ነጋዴው ተጎጂ መሆኑን ማሳየት ይገባል ያሉት ቆስጠንጢኖስ፤ ብዙ ሀገሮች የዋጋ ወሰን ያደርጋሉ። ለአብነት ሜክሲኮ ወደ 170 እቃዎች ላይ የዋጋ ወሰን አድርጋለች። ግብፅንም ብንመለከት ለሃምሳ ዓመት የዳቦ ዋጋ አልቀየረችም።
እነዚህንና መሰል ውሳኔዎችን መከተል የዋጋ ንረት ለመከላከል ይረዳል። ይህም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳይጎዱ ያደርጋል ያሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ በሀገራችን አሳታፊ እድገት እንዲመጣ ያደርጋል ብለዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ክቡር ገና፤ አለአግባብ ዋጋ በጨመሩ ነጋዴዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም ባይ ናቸው። ነጋዴው የዋጋ ጭማሪ እያደረገ ያለው የውጭ ምንዛሪ የመግዣ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት ነው ይላሉ። ይህንን ሁኔታ ለመከላከል በነጋዴዎች ላይ ርምጃ ሲወሰድ ይታያል ነው ያሉት።
ነጋዴው ካፒታሉን ካጣ ወደ ንግዱ በቀላሉ መመለስ ስለማይችል የሚወሰደው ርምጃ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ሊሆን ይገባል ያሉት አቶ ክቡር ገና፤ ዘላቂ መፍትሔው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለውጭ ገበያ ምርቶችን በስፋት ማቅረብ መሆኑን ያብራራሉ።
የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ወደ ውጭ መላክ፣ በቂ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት የውጭ ኢንቨስተሮችን መሳብ፣ የሀገሪቱን ሠላም መጠበቅ እና የሀገር ውስጥ አምራቾችን ማበረታታት ከርምጃው በሻገር ዘላቂ መፍትሔ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 /2016 ዓ.ም