የኦሊምፒክ ቡድኑ ዛሬ እውቅናና ሽልማት ተዘጋጅቶለታል

በ33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማለዳ ወደ ሃገሩ ተመልሷል። ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ባሉት የአትሌቲክስ ውድድሮች የተካፈለው ልዑካን ቡድን 1 የወርቅ እና 3 የብር በጥቅሉ 4 ሜዳሊያዎችን ማስመዝገቡ ይታወቃል። ከዓለም 47ኛ ከአፍሪካ ደግሞ 4ኛ ደረጃን የያዘው ቡድኑ ጠዋት 12 ሰዓት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ሲደርስም በከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች አቀባበል ተደርጎለታል።

ኢትዮጵያ ከሜልቦርን እስከ ፓሪስ በተካሄዱ 15 የኦሊምፒክ መድረኮች ላይ ተወካዮቿን ያሳተፈች ሲሆን፤ በዚህም 24 የወርቅ፣ 13 የብር እና 23 የነሐስ በጥቅሉ 62 ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ ችላለች። ከትናንት በስቲያ በተጠናቀቀው የፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎዋ እንደተጠበቀው ባይሆንም በተለያዩ ርቀቶች ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል። የወርቅ ሜዳሊያው በጀግናው አትሌት ታምራት ቶላ የማራቶን ውድድር ሲመዘገብ የኦሊምፒክ ክብረወሰንን በመስበርም አትሌቱ የድርብ ድል ባለቤት ሊሆን ችሏል። በሴቶች ማራቶንም እጅግ ጠንካራ በነበረው ፉክክር የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ ትዕግስት አሰፋ የብር ሜዳሊያ አጥልቃለች። በ10ሺ ሜትርም አትሌት በሪሁ አረጋዊ እና ወጣቷ የ800 ሜትር አትሌት ፅጌ ድጉማ የተቀሩትን የብር ሜዳሊያዎች አስገኝተዋል።

በወንዶች 3ሺ ሜትር መሰናክል የዓለም ክብረወሰን ባለቤቱ አትሌት ለሜቻ ግርማ ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያ የሚያገኝበት ሰፊ ዕድል ቢኖረውም ውድድሩን ሊያጠናቅቅ ሲቃረብ በመውደቁ በአሳዛኝ ሁኔታ ፉክክሩን ማጠናቀቅ አልቻለም። በሌላ በኩል በአጨራረስ እንዲሁም ውድድርን ከማንበብና ተወዳዳሪን የተለየ ስልት ከመከተል ጋር የተገናኘ ስህተት በተለያዩ ርቀቶች ሜዳሊያዎች እንዳይመዘገቡ ምክንያት ሆኗል። ኢትዮጵያ ቀድሞም የታወቀችበትና ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› የሚል ቅጽል ያገኘችበት እንዲሁም ለውጤታማነቷ ከፍተኛ ሚና ሲጫወት የቆየው የቡድን ሥራ በዚህ ኦሊምፒክ ጎልቶ አልታየም። በአትሌቶች ሊተገበሩ የተሞከሩ የቡድን ሥራዎችም በአግባቡ ተግባራዊ አለመሆናቸውም ታይቷል።

ወደ ፓሪስ ከነበረው ጉዞ አስቀድሞ ሲከሰቱ የነበሩ አነጋጋሪ ጉዳዮችና አወዛጋቢ አካሄዶች ውድድሩ በሚካሄድበት ስፍራም ተጠናክሮ የቀጠለበት ነበር። የስፖርት ቤተሰቡን አንገት ካስደፉ ድርጊቶች ባለፈ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሜዳሊያዎች ይመዘገቡባቸው በነበሩ ርቀቶች ተፎካካሪ ሆኖ አለመገኘትም ኢትዮጵያ በዝቅተኛ የሜዳሊያ ቁጥር ተሳትፎዋ እንዲደመደም አድርጓል። ከሲድኒ እስከ ሪዮ ባሉት 5 ኦሊምፒኮች ኢትዮጵያ ያስቆጠረቻቸው ሜዳሊያዎች በእያንዳንዳቸው 7 እና 8 ሲሆን፤ በቶኪዮ እና በፓሪስ ኦሊምፒኮች የተመዘገበው የሜዳሊያ ቁጥር ግን በእኩል 4 ብቻ ነው። የወርቅ ሜዳሊያ ቁጥሩም ወደ አንድ ከወረደ ከ2016ቱ ሪዮ አንስቶ ይህ ሦስተኛው ኦሊምፒክ ነው።

ኢትዮጵያ እአአ በ1980 የሞስኮ ኦሊምፒክ በሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ‹‹ማርሽ ቀያሪው›› 5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ከተመዘገበበት ጊዜ አንስቶ በተካሄዱት ኦሊምፒኮች በርቀቶቹ ስኬታማ ሃገር ልትሆን ችላለች። በዓለም አቀፍ ደረጃም የኢትዮጵያ መታወቂያ በሆኑት በእነዚህ ርቀቶች የቤጂንግ ኦሊምፒክ (እአአ 2008) በአትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ በሁለቱም ርቀት አሸናፊነት 4 የወርቅ ሜዳሊያዎች የተገኙበት በታሪክ ስኬታማው ውድድር ነው። በተቀሩት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ተሳትፎዎችም ከእነዚህ ርቀቶች ቢያንስ በአንዱ አንድ የወርቅ ሜዳሊያ ይገኝ ነበር። በአንጻሩ ፓሪስ ላይ በወንዶች ምድብ አንድ የብር ሜዳሊያ ብቻ ከማስመዝገብ ባለፈ ኢትዮጵያ የቀደመ የርቀቱ የበላይነቷና ተፈሪነቷ አለመኖሩ የታየበት ሆኗል።

ማለዳ ላይ ወደሃገሩ የገባው የኦሊምፒክ ቡድን ዛሬ ከሰዓት በኋላ በብሔራዊ ቤተመንግስት የአቀባበል መርሐ ግብር ተዘጋጅቶለታል። በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ አማካኝነትም ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች የክብር ሽልማት፣ የማበረታቻ እና የእራት ግብዣ መርሐ ግብር እንደሚኖር የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር አስታውቋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You