አሜሪካ ውጥረት ወደተባባሰበት መካከለኛው ምሥራቅ ባሕር ሰርጓጅ ሚሳኤል ላከች። ከባሕር ሰርጓጅ ሚሳኤሉ ቀድሞ የሚደርስ የአየር መሣሪያ እንደተላከም የአሜሪካ መከላከያ ፀሐፊ ሎይድ ኦስተን ገልጸዋል።
ከፍተኛው የሐማስ መሪና ከፍተኛ የሄዝቦላህ አመራሮች መገደላቸውን ተከትሎ ቀጣናዊ ግጭት እንደሚፈጠር ተሰግቷል። አሜሪካም ስጋቱን ተከትላ መሣሪያዎቿን ልካለች። አሜሪካ መሣሪያዎቹን መላኳ እሥራኤልን ከኢራን ለመከላከል ቁርጠኛ መሆኗን ያሳያል ሲሉ ሎይድ ኦስተን ተናግረዋል። “አጋራችንን ለመከላከል ማንኛውንም አማራጭ እንከተላለን” ብለዋል።
ኢራን ለሐማስ ከፍተኛ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሐኒያ ግድያ መቼ እና እንዴት አፀፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ እየተጠበቀ ይገኛል። በሐኒያ ግድያ ኢራን እሥራኤልን ተጠያቂ አድርጋለች። እሥራኤል ከግድያው ጀርባ እንዳለች በስፋት ቢታመንም ስለ ጉዳዩ ምንም አላለችም።
ዩኤስኤስ ጆርጅያ የተባለውን ባሕር ሰርጓጅ ሚሳኤል አሜሪካ መላኳን ፔንታጐን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል። ኤፍ-32 ሲ ተዋጊ ጀት የያዘው ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲበርም ትዕዛዝ ተሰጥቷል። ኢራን ምን እያቀደች እንዳለ ግልጽ አይደለም።
እሥራኤል ላይ ጥቃት ሊሰነዝር የሚችለው ሄዝቦላህም ጭምር ነው። የሄዝቦላህ ከፍተኛ ኮማንደር ፉዓድ ሹክር መገደሉን ተከትሎ ሄዝቦላህ አፀፋዊ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
በካታር፣ ጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር መርሀን ካማራቫ እንዳሉት፣ አሜሪካ በይፋ ባሕር ሰርጓጅ መላኳ “ኢራን እና ሄዝቦላህን ለማስፈራራት” ያለመ ነው። “ኢራን አንዳች ነገር እያቀደች ነው። ጥቃት መሰንዘሯ አይቀርም” ብለዋል።
ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በርካታ በረራዎች ተሰርዘዋል። ሉፍታንዛ ወደ ቴል አቪቭ፣ ቤሩት፣ ኤርቢል፣ ቴህራን እና ኦማን እስከ አውሮፓውያኑ ነሐሴ 21 ድረስ በረራ መሰረዙን አስታውቋል። ኤር ፍራንስም ወደ ቤሩት በረራ የሰረዘ ሲሆን፣ ስዊዝ ኤር ወደ ቴል አቪቭ እና ቤሩት በረራ አቋርጧል። ኤርባልቲክ እና ኢዚጀት አየር መንገዶችም በረራ እንደሚሰርዙ ገልጸዋል።
ከወራት በፊት ሶርያ ውስጥ ያለው የኢራን ቆንስላ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ኢራን እሥራኤል ላይ ጥቃት መሰንዘሯ ይታወሳል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች ወደ እሥራኤል ተተኩሰዋል።
የጆ ባይደን አስተዳደር በጋዛ የተኩስ አቁም ተደርጎ እስራኤላውያን ታጋቾች እንዲለቀቁ ለማድረግ ንግግሩን እንደሚቀጥል አስታውቋል። ሐማስ በበኩሉ እስራኤል ለድርድር የቀረቡትን ነጥቦች መቀበል እንዳለባት ለአሜሪካ ገልጿል። ሆኖም በንግግር ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆኑን ቡድኑ አክሏል።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ንግግሮች ያልተሳኩት በሐማስ ምክንያት ነው ብትልም፣ የእሥራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት አሜሪካ ቀኝ ዘመም ጥምር ፓርቲ ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ስምምነት ባለማድረግ ተጠያቂ ታደርጋለች።
ዋይት ሃውስ ባለፈው ሳምንት በይፋ እሥራኤላዊውን የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሊል ስሚትሮች ወቅሷል። ሚኒስትሩ እሥራኤል አሜሪካ ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳትቀበል ይገፋፋሉ። የዋይት ሃውስ ብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ሚኒስትሩ “ስህተት ሠርተዋል” ብለዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ይሻሉ። “ከዚህ በኋላ መዘግየት እንደሌለበት እንስማማለን። መረጋጋት እንዲሰፍን እና ነገሮች እንዳይባባሱ ጥረት እንቀጥላለን” ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም