ተማሪዎች በዕረፍት ጊዜያቸው

ዜና ሐተታ

የክረምት ወቅት ለተማሪዎች ረጅሙ የእረፍት ጊዜ ነው። ይህን የእረፍት ጊዜ ተማሪዎች በምን መልኩ ያሳልፉታል የሚለው የአብዛኛው ወላጅ ጥያቄ ነው። በተለይም ከአኗኗራችን መቀያየርና ከቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ልጆች ከእኩዮቻቸው ጋር ይልቅ ስክሪን በመመልከት የሚያሳልፉት ጊዜ እየሰፋ መጥቷል።

የሥነልቦና ባለሙያ አቶ አቤል እስጢፋኖስ እንደሚሉት አሁን አሁን ልጆች ላይ ለሚታዩ የተግባቦት እድገት ውስንነቶች ስክሪን ላይ ረጅም ሰዓት ማሳለፍ አንዱ ምክንያት ነው። እንደእርሳቸው ገለፃ በእኛ ሀገር ደረጃ ልጆች ትምህርት የሚጀምሩበት ወይንም ወደ ቅድመ መደበኛ ትምህርት የሚገቡበት ዕድሜ አራት ዓመት ነው።

በዚህ ዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ልጆች የጀመሩበትን ዓመት ትምህርት አጠናቀው ክረምትን ቤት ውስጥ በምን ያሳልፉ በምንልበት ጊዜ በተለይም ኮንዶሚኒየም ወይንም አፓርታማ ላይ የሚኖሩ ወላጆች እንደድሮ ልጆቹ ራሳቸው ወጥተው እንዲጫወቱ ላይፈቅዱ ይችላሉ ልጆች ቴሌቪዥን እያዩና ጌሞችን እየተጫወቱ ረጅም ሰዓት ያሳልፋሉ።

ይህ ደግሞ ተግባቦታቸውና ማኅበራዊ ግንኙነታቸው ሊያድግ የሚችልበት ዕድሜ ላይ ከመሆናቸው አንፃር አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ባይ ናቸው። በዚህ የዕድሜ ክልል ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ዕድሜ ላይ ላሉ ልጆች ስክሪን ላይ ረጅም ሰዓት ማሳለፍ አሉታዊ ተፅዕኖው የጎላ ከመሆኑ አኳያ ወላጆች የልጆቻቸው ስክሪን አጠቃቀም ላይ ገደብ ማበጀት እንደሚገባቸው ይገልፃሉ።

ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባይችሉ እንኳ ከአንድ ሰዓት የበለጠ ጊዜ ስክሪን ላይ እንዳያሳልፉ የሚመከር መሆኑን ጠቅሰው፤ ለምሳሌ አንድ ልጅ በተፈቀደለት አንድ ሰዓት የሆነ አጭር ፊልም ቢያይ እዛ ፊልም ላይ ምን እንዳየ መጠየቅና ታሪኩን ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው እንዲናገር ማድረግ ይገባል።

አልያም ልጁ ስክሪኑን ብቻ እንዲያይ ከማድረግ ይልቅ ሙዚቃዎችን ከፍተን ከሙዚቃው ጋር እየተንቀሳቀሰ ሌሎች ችሎታዎችን እንዲያዳብር በማድረግ ወደ ጠቀሜታ የምናመጣበት መንገድ ቢኖር የተሻለ እንደሚሆንም ባለሙያው ይመክራሉ።

ይህ እንዳለ ሆኖ የተማሪዎች የክረምት ውሎ በምን መልኩ ማለፍ አለበት ለሚለው ጥያቄ ወላጆች ልጆቻቸው የሚወዷቸውን ነገሮች እያዩ ለምሳሌ የእግር ኳስ፣ የሙዚቃ፣ የስዕል እና ሌሎችም ፍላጎቶች ካላቸው የክረምት ጊዜያቸው እነዚህን ፍላጎቶቻቸውን የሚያዳብሩበትን መንገድ ታሳቢ ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የተለያዩ የክረምት ፕሮግራም ሥልጠናዎች እንዲወስዱ ማመቻቸትም ራሳቸውን በተሻለ እንዲገልፁ፣ አዳዲስ ነገሮችን እንዲቀስሙና ፍላጎታቸውን እንዲያዳብሩ ማድረግ ተመራጭ መሆኑንም ይናገራሉ፡

ክፍያ አንፃር ሁሉም ወላጅ ይህን ማድረግ ላይችል ስለሚችል መናፈሻዎችና የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች ሄደው እንዲያሳልፉ ማድረግም የተሻለ ነው ይላሉ። ይህም ከሌሎች ጋር በመግባባት የቋንቋ፣ የተግባቦት እና የማኅበራዊ ግንኙነታቸውን እንዲያጎለበቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ወላጆች የልጆቻቸውን የትምህርት ውጤት በማየት ደከም ያሉባቸውን ትምህርቶች እንዲያጠኑ ማድረግ እንደ አንድ የክረምት ጊዜ ማሳለፊያ ከመሆኑ ባሻገር ለቀጣይ ዓመት ትምህርትም ከእኩዮቻቸው ጋር ባልተናነሰ ዝግጁ እንደሚያደርጋቸው ገልፀው፤ ሙሉ የክረምት ጊዜያቸውን ግን ከትምህርት ጋር የተያያዙ ነገሮች ላይ ብቻ እንዲያሳልፉ ማድረግ ብቻውን ጠቀሜታ ስለማይኖረው ከዛ ጎን ለጎን በተቻለ አቅም አዳዲስ ነገሮችን የሚሞክሩበትን ጊዜ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ያብራራሉ።

በአጠቃላይ የክረምት ወይንም የእረፍት ጊዜያቸው ተማሪዎች ያላቸውን የቋንቋ እድገት፣ የጨዋታ ክህሎት እና የማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ቢያዳብሩበት ይመረጣል። ምክንያቱም ውጤቱ የአዕምሮ ብቃታቸው የተሻለ እንዲሆንና ነገሮችን ከብዙ አቅጣጫዎች ማየት እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑን ያስረዳሉ።

ከዚህ አኳያ ወላጆች ልጆቻቸው አዳዲስ ክህሎቶችን እንዲለምዱ የሚያደርጉበት ጊዜ ቢሆን የተሻለ ነው ሲሉ የሥነልቦና ባለሙያው አቶ አቤል እስጢፋኖስ አብራርተዋል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ወይዘሮ ዮርዳኖስ ተክሌ ተማሪዎች በእረፍት ጊዜያቸው ለተሻለ የትምህርት ውጤት ብቻ ሳይሆን ለተሻለ ሁለንተናዊ ዕድገታቸውም ማንበባቸው ወሳኝ ሚና አለው ።

ተማሪዎች የክረምት ወይም የእረፍት ጊዜያቸውን ትምህርት ነክ የሆኑ መጽሐፍቶችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አይነት መጽሐፍት ከመዝናናቱና እረፍት ከማድረጉ ጎን ለጎን ቢያነቡ ለቀጣይ ዓመት ትምህርት በአዲስ መንፈስ ከመዘጋጀት አንፃር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል በማለት ሀሳባቸውን ሰጥተውናል።

ነፃነት ዓለሙ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም

Recommended For You