ኢንስቲትዩቱ ባሕላዊ መድኃኒቶች በዘመናዊ መንገድ ተመርተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሠራ ነው

አዲስ አበባ፦ በባሕላዊ መንገድ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ሃገር በቀል ዕፅዋት ላይ ምርምር በማድረግ በዘመናዊ መንገድ ተመርተው ወደ ገበያ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሡ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ በባሕላዊ መንገድ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ሃገር በቀል ዕፅዋት ላይ ምርምር በማድረግ በዘመናዊ መንገድ ተመርተው ወደ ገበያ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እየሠራ ነው። እነዚህ መድኃኒትነት ያላቸው ዕፅዋት በተቋሙ ግቢ ውስጥ በተዘጋጀላቸው መካነ-ዕፅዋት እየተተከሉ ይገኛሉ።

ይህም ዕፅዋቱ እንዳይጠፉ ጥበቃ ለማድረግ እና ተመራማሪዎችም በቀላሉ እንዲያገኟቸው እንደሚያስችል ያስረዱት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ ኢንስቲትዩቱ በ2017 በጀት ዓመት የባሕል ሕክምና ምርምር ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል። ለዚህም ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከጤና ቢሮዎች ጋር በጥምረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዚህም የክልልና የከተማ ጤና ቢሮዎች በየአካባቢያቸው ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በትብብር መሥራት እንዲችሉ ክላስተር መደራጀቱን የገለጹት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ ለአብነት የምሥራቅ ኢትዮጵያ የጤና ክላስተር በሚል የሰመራ ዩኒቨርሲቲን እና ከአፋር ጤና ቢሮ ጋር በክላስተር የማደራጀት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።

ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ፣ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ ከቀብሪ ደሐር ዩኒቨርሲቲ፣ ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከኦሮሚያ፣ ከድሬዳዋ፣ ከሐረር፣ ከሶማሌ ጤና ቢሮዎች ጋር በመሆን በየአካባቢው ያሉ የባሕል ሕክምና እውቀቶችን ከዘመናዊ ሕክምና ጋር ለማዋሓድ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሚከናወን ተግባር ነው። ሀገራዊ የሕክምና መድኃኒቶችን የማምረት አቅም ለማሳደግ ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ያሉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፤ የባሕል ሕክምና ምርምር የሁሉም ዩኒቨርሲቲዎችና ጤና ቢሮዎች አጀንዳ መሆኑ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ብለዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ኢንስቲትዩቱ ከባሕል ሕክምና አዋቂዎች ማኅበር ጋር በጥምረት ይሠራል። ። በ2017 በጀት ዓመት ሳምንታት የሚቆይ መድረክ እንደሚኖር ጠቁመዋል። ይህም የእርስ በእርስ እውቀቶች እና የልምድ ልውውጥ መድረክ ይሆናል ነው ያሉት።

በዚህም በጋራ መሥራት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ከመለየት ባለፈ ተግባራዊ የሚደረጉበት ሁኔታዎች ላይ ውይይት ይደረጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ኢንስቲትዩቱ የባሕል ሕክምና ምርምርና ልማት የሚመለከት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ይሠራል። ይህም ለቀጣይ ሥራዎች በር እንደሚከፍት ተናግረዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You