-ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ ሙሉ ቃል
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከሰሞኑ በተሻሻለው የምርጫ አዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀጽ 2 (1) መሠረት ለሕወሓት የምዝገባ ምስክር ወረቀት መስጠቱን ገልጧል። መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት በሕግና በተቋማዊ ነፃነት የሚወስኑትን ውሳኔ ይቀበላል። ያደንቃል። የለውጡ አንዱ ፍሬ ነውና።
ሕወሓት ሕጋዊ ሰውነቱን ያጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ እና የሥነ ምግባር አዋጅ መሠረት ባስተላለፈው ውሳኔ መሆኑ ይታወሳል። ቦርዱ ፖርቲው በኃይል እና በአመፅ እንቅስቃሴ በመሳተፉ የፓርቲውን ምዝገባ እንዲሠረዝ በመወሰኑ፣ ሕወሓት ሕጋዊ ሰውነቱን ማጣቱ ይታወቃል። ይህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሓትን ሽብርተኛ ብሎ ከመፈረጁ በፊት የተላለፈ እና ራሱን ችሎ የሚቆም፣ የራሱ የሕግ መሠረት ያለው ውሳኔ ነው።
የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈጸም የፌዴራል መንግሥት በስምምነቱ የገባው ግዴታ የሕወሓት የሽብርተኝነት ፍረጃ እንዲነሣ ሂደቱን የማሣለጥ ኃላፊነት ነው (የስምምነቱ አንቀጽ 7 (2) (C)):: የፌዴራል መንግሥት የሕወሓትን የሕግ ሰውነት እና የምዝገባ ጉዳይ በተመለከተ በፕሪቶሪያ ስምምነት ውስጥ የወሰደው የተለየ ኃላፊነት ወይም ግዴታ አልነበረም። እንዲሁም ሕወሓት በፕሪቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 7 (1) (A) መሠረት የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት፣ ሕጎች፣ የፌዴራል ተቋማትን እና ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ሥልጣን የማክበር ግዴታ ገብቷል። ስለዚህ ሕወሓት የሀገሪቱን የፖለቲካ ፖርቲዎች የምዝገባ ሕግ እና የምርጫ ቦርድን ሥልጣን በማክበር የመሥራት ግዴታ እንዳለበት ግልጽ ነው።
ስለሆነም፣ ከፕሪቶሪያ ስምምነት አኳያም ሲታይ የሕወሓት የሕግ ሰውነት ጉዳይ አግባብነት ባለው ሕግ እና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሠራር መሠረት ብቻ እልባት ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ ነው። የፌዴራል መንግሥት በዚህ ረገድ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ከሕወሐት አመራሮች ጋር ተደጋጋሚ ምክክሮችን በማድረግ፣ ሕወሓት እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሕጋዊ ዕውቅና እንዲኖረው ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
በዚህ ረገድ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቋም፣ ሕወሓት ማንኛውም አዲስ የፖለቲካ ፖርቲ በሚመሠረትበት ሥርዓት እና አግባብ መሠረት እንደ አዲስ ፖርቲ በመደራጀት ሊመዘገብ እና ዕውቅና ሊያገኝ ይችላል፣ ከዚህ ውጪ ግን ሕጋዊ ሰውነት ሊያገኝ የሚችልበት ሕጋዊ አሠራር የለም የሚል ነበር። በሕወሓት በኩል የነበረው አቋም ነባር እና እድሜ ጠገብ የፖለቲካ ድርጅት ስለሆንኩኝ እንደ አዲስ ፓርቲ ልመዘገብ አይገባም፣ ጉዳዩ የሕግ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ስለሆነ የተለየ የፖለቲካ ውሳኔ ይፈልጋል የሚል ነው።
እነዚህን የተለያዩ አቋሞች እና ፍላጎቶችን ከግምት በማስገባት፣ ሠላምን የማጽናት አስፈላጊነትን፣ እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማትን ነፃነት እና ገለልተኝነት ባገናዘበ መልኩ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት የተሻለው መንገድ፣ ሕውሓትም ሆነ ሌሎች የትጥቅ እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ቡድኖች ወደ ሕጋዊ መሥመር ሊመጡ የሚችሉበትን መንገድ የሚያመቻች የሕግ ማሻሻያ ማድረግ እንደሆነ በፌዴራል መንግሥት በኩል ታምኖበት አስፈላጊው የሕግ ማሻሻያ ለሕዝብ ተወካዮች ቀርቦ ፀድቋል።
በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ፣ በተሻሻለው የአዋጁ ድንጋጌ መሠረት ሕወሓት የሕግ ሰውነት እንዲያገኝ ለማድረግ አስፈላጊ ወይም ቅድመ ሁኔታ የሆነው የሠላም ስምምነት መፈጸምን አስመልክቶ የፍትሕ ሚኒስቴር ለምርጫ ቦርድ ድብዳቤ ጽፏል።
በዚህም የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነት ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ከመንግሥት በኩል ሊደረግ የሚችለው ሁሉ ተደርጓል። የፌዴራል መንግሥት ከግማሽ ርቀት በላይ ሄዶ፣ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ከሚጠበቅበት እና ካለበት ግዴታ አልፎ ከምርጫ ቦርድ እና ከሕወሓት ጋር በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ውይይቶች አድርጓል።
በተደረገው የሕግ ማሻሻያ መሠረት ምርጫ ቦርድ ሕወሓትን በመመዝገብ ድርጅቱ ሕጋዊ ሰውነት እና ዕውቅና እንዲኖረው ለቦርዱ የትብብር ጥያቄ አቅርቧል። ይህንንም ተከትሎ ሕወሓት ሕጋዊ ሰውነት እና ዕውቅና ለማግኘት የሚጠበቅበት የፓርቲ ሰነዶቹን ማለትም የፓርቲውን ፕሮግራም እና ሕገ ደንብ፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ሰነዶችን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማቅረብ በተሻሻለው አዋጅ መሠረት ተመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቷል።
ስለሆነም የምዝገባ እና የሕግ ሰውነትን ጉዳይ በዚህ በመቋጨት፤ የሁሉም ባለድርሻ አካል ርብርብ፣ ሠላምን በማጽናት፣ በመልሶ ግንባታ እና በልማት አጀንዳ ላይ ሊሆን ይገባል። አላስፈላጊ እና ሕዝብን የማይጠቅም፣ ትርጉም አልባ ንትርክን አስወግደን ለሕዝብ ረብ ያላቸው ጉልህ የሠላም እና የልማት አጀንዳዎች ላይ ልናተኩር ይገባል።
ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም