በቀጣይ ቀናት በሚኖረው ዝናብ የመሬት መንሸራተትና የወንዞች ሙላት ሊያጋጥም ይችላል

አዲስ አበባ፡- በሚቀጥሉት 20 ቀናት በሚኖረው ዝናብ የመሬት መንሸራተትና የወንዞች ሙላት እንዲሁም ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያጋጥም እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ማኅበረሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲሁም ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢፕድ በላከው መግለጫ፤ በቀጣይ ቀናት በሚጥለው ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና የወንዞች ሙላት ሊያጋጥም ስለሚችል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት በዓባይ ተከዜ፣ ባሮአኮቦ፣ ኦሞ፣ ጊቤ፣ አዋሽ፣ አፋር ደናክል፣ የላይኛው እና የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛው የገናሌ ዳዋ እና ዋቤ ሸበሌ ተፋሰሶች መካከለኛና በጣም ከፍተኛ እርጥበት እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል።

ተዳፋታማ በሆኑ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተትና መሰንጠቅ፣ እንዲሁም የሰብል በጎርፍ የመጠረግ ሁኔታዎች እንዳይኖር መጠንቀቅ ያስፈልጋል ያለው ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው፤ በተጨማሪም እርጥበት በሚበዛባቸው አካባቢዎች የሰብል በሽታ እንዳይከሰት ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁሟል።

እንደ ኢንስቲትዩቱ ገለጻ፤ በሁሉም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ። አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናት በፀሐይ ኃይል ታግዞ ከሚፈጠረው ጠንካራ የሆነ የደመና ክምችት ምክንያት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በረዶና ነጎድጓድ የቀላቀለ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይከሰታል።

በሌላ በኩል ወደ ግድቦች የሚገባው ውሃ ከፍተኛ በመሆኑ አሁናዊ የውሃ ከፍታቸው አስጊ በሆነባቸው እንደ ፊንጫ፣ ጣና በለስ፣ ከሰምና ርብ የመሳሰሉት የኃይል ማመንጫ እና የመስኖ ግድቦች ላይ የቅርብ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመግለጫው ተገልጿል።

በተመሳሳይ በሚቀጥሉት ስምንት ቀናት በምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በሰሜን ምስራቅ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች አልፎ አልፎ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚያስከትል ከባድ ዝናብ እንደሚኖር አስታውቋል።

በመደበኛ ሁኔታ በነሐሴ ሁለተኛው አስር ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይበልጥ የሚጠናከሩበት መሆኑን የጠቀሰው ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው፤ አልፎ አልፎ የሚኖረው ፀሐይ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ጠንካራ፣ ቁልል ደመና፣ በረዶ፣ ነጐድጓድ፣ መብረቅና ከባድ ዝናብ እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ አመላክቷል።

በሁሉም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ የወቅቱ ዝናብ እንደሚቀጥል እና በአንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖርም ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው ጠቁሟል።

የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚጠበቀው እርጥበት ለመኸር ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎች፣ ለጓሮ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች የውሃ ፍላጎት መሟላት እንዲሁም በምስራቅ እና ሰሜን ምስራቅ ለሚገኙት አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የግጦሽ ሣርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You