በ33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ተሳትፎ በሴቶች የማራቶን ብር ሜዳሊያ ተደምድሟል፡፡ የዓለም የማራቶን ክብረወሰን ባለቤቷ ጀግና አትሌት ትዕግስት አሰፋ እጅግ ፈታኝ በነበረው ፉክክር፤ በመጨረሻዎቹ ሜትሮች ተቀድማ የብር ሜዳሊያ አጥልቃለች፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በመድረኩ 1 የወርቅ እና 3 የብር በጥቅሉ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ተሳትፎዋን አጠናቃለች፡፡
በዳገታማነቱ እጅግ ከባድ በተባለው የፓሪስ ኦሊምፒክ ማራቶን፤ በተለይ በሴቶች ምድብ ፍጹም ጠንካራና እስከመጨረሻው አሸናፊ አትሌቶችን መለየት አዳጋች የሆነ ውድድር ተደርጓል፡፡ ምርጥ የዓለም ማራቶን አትሌቶች በተካፈሉበት በዚህ ውድድር በተለይ የኢትዮጵያ፣ የኬንያ እና የኔዘርላንድስ አትሌቶች ትከሻ ለትከሻ ተያይዘው በመሮጥ እስከመጨረሻው ተጉዘዋል፡፡ ርቀቱ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሜትሮች ሲቀሩት ተስፈንጥራ የወጣችው ትዕግስት በተፎካካሪዋ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰን ብትገፈተርም ሚዛኗን ጠብቃ በመሮጥ የወርቅ ሜዳሊያው ለማጥለቅ አድናቆት የተቸረው ትግል አድርጋለች፡፡ በመጨረሻም በኢትዮጵያዊቷ ቲኪ ገላና 2012 ላይ የተመዘገበው የኦሊምፒክ ክብረወሰን በአንድ ደቂቃ ተሻሽሎ በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድ አትሌት ሲፈን ሃሰን የበላይነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡
በዚህ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉት አትሌት ትዕግስት አሰፋ፣ አማኔ በሪሶ እና መገርቱ ዓለሙ ሲሆኑ፤ ከውድድሩ አስቀድሞ ከፍተኛ አሸናፊነት ግምት አግኝተው ነበር፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌት የሆነችው ትዕግስት ባለፈው ዓመት የበርሊን ማራቶንን 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ በመሮጥ የዓለም ክብረወሰኑን የሰበረችው እንዲሁም በቡዳፔስቱ የዓለም ቻምፒዮን መሆን የቻለችው ጠንካራዋ አትሌት አማኔ በሪሶ ፓሪስ ላይ ያሳዩት የቡድን ሥራ አስደናቂ ነበር፡፡
ከ40ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ለአሸናፊነት ተፎካካሪ ከነበረው ቡድን አማኔ ተቆርጣ ብትቀርም በጽናቷ ለአትሌቶች ሁሉ ተምሳሌት የሆነችው ትዕግስት ግን ለሀገሯ ሜዳሊያውን ለማስመዝገብ እስከመጨረሻው ታግላለች፡፡ በዚህም 2:22:58 በሆነ ሰዓት በሦስት ሰከንድ ተቀድማ የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች፡፡ ይህም በኦሊምፒክ የሴቶች ማራቶን የብር ሜዳሊያ ያጠለቀች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አድርጓታል፡፡
በኦሊምፒክ የሴቶች ማራቶን በአትሌት ፋጡማ ሮባ የ1996 የአትላንታ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊትና ፈርቀዳጅ ስትሆን ቲኪ ገላና በ2012 የለንደን ኦሊምፒክ በርቀቱ ሁለተኛውን ክብር አስመዝግባለች፡፡ በቀጣዩ የሪዮ ኦሊምፒክ ማሬ ዲባባ የነሃስ ሜዳሊያ ስታገኝ፤ ትዕግስትን ትናንት የብር ጨምሮ አክላበታለች፡፡
ለረጅም ጊዜ በጉዳት ምክንያት ከአትሌቲክሱ ርቃ የቆየችው ትዕግስት በህክምና ባለሙያዎች ዳግም ወደ ሩጫ እንዳትመለስ ቢነገራትም እጅ ሳትሰጥ ጠንክራ በመሥራት የማራቶን የዓለም ክብረወሰን ባለቤትና የኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ለመሆን በቅታለች፡፡ በ2022 እና 2023 የበርሊን ማራቶንን በማሸነፍ ለዚህ ኦሊምፒክ ስትታጭ በዝግጅት ወቅት ውድድሩ ወደ ሚካሄድበት ስፍራ በራሷ ወጪ ተጉዛ ጥናት በማድረግ ጭምር ነው ለዚህ ክብር የበቃችው፡፡ አምና የቦስተን ማራቶን አሸናፊ የነበረችው የዓለም ቻምፒዮና አማኔ አብዛኛውን የውድድር ርቀት በተፎካካሪነት በመሮጥ 5ኛ ደረጃን ስትይዝ የገባችበት ሰዓትም 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ57 ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቦላታል፡፡ ሌላኛዋ አትሌት መገርቱ ዓለሙ ደግሞ ውድድሩን አቋርጣለች፡፡
በ10ሺህ እና 5ሺ ሜትር ርቀቶች የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አትሌት ሲፋን ሃሰን በማራቶንም አስደናቂ ብቃት በማሳየት አሸናፊ ሆናለች፡፡ አትሌቷ 2 ሰዓት ከ22 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ በሆነ ሰዓት የኦሊምፒክ ክብረወሰንን ከእጇ በማስገባት ጭምር ፓሪስ ላይ 3 ሜዳሊያዎችን አጥልቃለች፡፡ ኬንያዊቷ አትሌት ሄለን ኦቤሪ ደግሞ በ2 ሰዓት ከ23 ሰከንድ ከ10 ሰከንድ በመግባት ለሀገሯ የነሃስ ሜዳሊያውን አስገኝታለች፡፡
በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ በመካከለኛ እና ረጅም ርቀት 33 አትሌቶችን በፓሪስ ኦሊምፒክ ያሳተፈችው ኢትዮጵያ በመድረኩ 1 የወርቅ እና 3 የብር በጥቅሉ 4 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ፉክክሯን ቋጭታለች፡፡ በዚህም በዓለም የደረጃ ሰንጠረዡ 46ኛ ላይ ስትቀመጥ በአፍሪካ ደግሞ ኬንያ፣ አልጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካን በመከተል 4ኛዋ ሀገር ሆናለች፡፡ ትናንት በተጠናቀቀው በዚህ ኦሊምፒክ ላይም ቻይና፣ አሜሪካ እና ጃፓን በርካታ ሜዳሊያዎችን በማስቆጠር ቀዳሚዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም