የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው መነሻና መድረሻ

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ተግባራዊ ከሆነ ውሎ አድሯል። በነዚህ ቀናቶች ውስጥ የተለያዩ ሃሳቦች መነሳታቸው አልቀረም። የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሀገሪቱን የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ በማድረግ ሂደቱ በመቀላጠፍ ላይ ይገኛል።

በሥራ ላይ የዋለው ይህ ማሻሻያ ፕሮግራም ሀገራችን ኢትዮጵያን በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪ ወደሆነና በገበያ ላይ በተመሰረተ የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት እንደሚያሸጋግራት እና በኢኮኖሚው ውስጥ ለረጅም ጊዜ ገዝፎ የሰነበተውን የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት መዛባት እንደሚያስተካክል እምነት ተጥሎበታል።

የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው በአዲሱ የውጪ ምንዛሪ መምሪያ መሠረት ተግባራዊነቱ የሚቀጥል ሲሆን ይህ የምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ ግብር ላይ የተመሰረተ በቀጣይም በሥራ ላይ ከሚውሉ ሰፊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መሀል አንዱ ነው። ዋና አላማውም ቀጣይነት ባለው፣ ሰፊና ተደራሽነቱ የገዘፈ፣ ሁሉን አሳታፊ የኢኮኖሚ እድገትን ማረጋገጥ ነው።

የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር ውጤት ተኮር በሆነ አላማ የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን አድርጓል። የፖሊሲ ማሻሻያው በጥናትና ምርምር የተደገፈ ያረጀውን የሚቀይር፣ ለሀገር የተሻለ የለውጥ አቅጣጫን የሚቀይስ፣ በውስጥና በውጪ የምንዛሪ አስተዳደር ላይ አዲስና አዋጪ ሕግጋትን የደነገገ ነው። ከማሻሻያዎቹ መሀል.. የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጪ ምንዛሪ ተመን በባንኮችና በደንበኞች መፈቃቀድ ወደሚወሰንበት የገበያ ሥርዓት ተሸጋግሯል።

በአዲሱ የማሻሻያ ፖሊሲ የውጪ ምንዛሪን ለብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታ ቀርቷል። ላኪዎችና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጪ ምንዛሪ ለራሳቸው ማስቀረት ሲችሉ ይህም ለግሉ ሴክተር የሚሰጠውን የውጪ ምንዛሪ በበለጠ ያሻሽለዋል። ቀደም ሲል በ38 የገቢ ንግድ ሸቀጦች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ ተነስቶ ምርቶቹ ወደሀገር የሚገቡበት አቅጣጫ ተቀምጧል። ወደ ውጪ የሚደረግ የካፒታል ሂሳብ ፍሰት እንደ በፊቱ የተገደበ ሲሆን የውጪ ምንዛሪ ገበያው ለገቢ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ግን ነፃ ሆኗል።

ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች ካፈሩት የውጪ ምንዛሪ ገቢ ለራሳቸው ያስቀሩት የነበረውን 40 ፐርሰንት ወደ 50 እድገት አሳይቷል። ከማሻሻያው በፊት ባንኮች ለተለያዩ የገቢ ሸቀጦች የሚጠቀሙበት የውጪ ምንዛሪ አሰራርና አደላደል ደንቦች ቀሪ ሆነዋል። በሥራ ላይ ካሉና በባንኮች ከተቋቋሙ የውጪ ምንዛሪ ቢሮዎች በተጨማሪ ባንክ ያልሆኑ የግል የውጪ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዲቋቋሙ አቅጣጫ ተቀምጧል። በገበያ ዋጋ የውጪ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ እንዲገዙና እንዲለውጡ የሥራ ፈቃድ ተችሯቸዋል።

ሌላው የማሻሻያው አካል የሆነው ሸቀጦችን በፍራንኮ ቫሉታ ወደ ሀገር ውስጥ ያለማስገባት የተጣሉ ክልከላዎች በአዲስ ሥርዓት በቅርቡ መታየታቸው ነው። የውጭ ተቋማት፣ በውጭ ኢንቨስተሮች እና በትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዲያስፖራ) የተከፈቱ የውጪ ምንዛሪ ሂሳቦችን አስተዳደር የሚመለከቱ በርካታ ሕጎች ላልተዋል። እንዲሁም በሀገር ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ከውጭ የሚላክላቸውን ሀዋላ፣ በውጪ ምንዛሪ የሚከፈል ደሞዝን፣ የኪራይ ገቢን እና ሌሎች ገቢዎችን የሚያስቀምጡባቸውን የውጭ አገልግሎት ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ ተፈቅዷል።

የግል ኩባንያዎች ወይም ባንኮች በሚወስዷቸው የውጪ ብድሮች ላይ ይከፍሉት የነበረው የወለድ ተመን ጣሪያ ተነስቷል። መመዘኛውን የሚያሟሉ የውጭ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ሰነድ ሙዓለ ንዋይ ገበያ (Ethiopian Securities Exchange) እንዲሳተፉ ተደርጓል። በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚሰሩ ኩባንያዎች የውጪ ምንዛሪ ገቢያቸውን ሙሉ በሙሉ ለራሳቸው መያዝን ጨምሮ ልዩ የውጪ ምንዛሪ አጠቃቀም መብት ተሰቷቸዋል።

ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት የሚጓዙ ወይም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ሊይዙ በሚገባ የውጪ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ተጥለው የነበሩ የተለያዩ ደንቦች ላልተዋል። ከላይ የተዘረዘሩት ከአስር በላይ የሆኑ የማሻሻያ ፖሊሲዎች ቀጣዩንና በተስፋ የሚጠበቀውን የሀገራችንን እድገት የሚወስኑ እንዲሁም ከቀረው ዓለም ጋር ያለንን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠነክሩ እንደሚሆኑ ይታመናል።

እኚህ የማሻሻያ ፖሊሲዎች የአስር ዓመቱን የመንግሥት የልማት መሪ እቅድና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራምን በመሳሰሉ ወሳኝ ሰነዶች ውስጥ ከሰፈሩት የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫዎች ጋር የተቀናጁ እንዲሁም ከሌሎች የእቅድ ዘርፎች ጋር መሳ ለመሳ የቆሙ ናቸው። የሪፎርም ሰነዶቹ ኢኮኖሚው እየተወሳሰበና እያደገ ሲሄድ ሀገሪቱ በሂደት በገበያ ላይ ወደተመሰረተ የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት እንደምትሸጋገር የሚመሰክሩ ናቸው።

የውጪ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ ያስፈለገበት ዋነኛ አላማ በበፊቱ ነባር ሥርዓት የነበረውን ተግዳሮት ለመቅረፍ እንዲሁም በጥቂት ተግዳሮት የተሻለ ሀገራዊ ተስፋን ለማምጣት ከመሻት እንደሆነ እሙን ነው። ቀደም ባለው ጊዜ ከአምራቹ ዘርፍ ይልቅ ጥቂት ሕገ ወጦችና ደላሎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት፣ ስር የሰደደ የውጪ ምንዛሪ እጥረት እንዲከሰት መንገድ የቀደደ ነበር። በዚህም ሳቢያ በርካታ የንግድ ድርጅቶችና ባለሀብቶች ተጎጂ ሆነዋል። የውጪ ንግድና የፋብሪካ ምርቶችን ለማስፋፋት፣ የውጪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የሀገሪቱን የውጪ ምንዛሪ አሃዝ ለማሳደግ የተቀመጡ ፖሊሲዎችንና ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል።

ከዚህ አኳያ በአዲሱ የፖሊሲ ማሻሻያ መሠረት በገበያ የሚወሰን የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት በርካታ ኢኮኖሚያዊ በረከቶች አሉት። ለአብነት ብንመለከት የውጪ ምንዛሪ ገቢ በሚያስገኙ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ይጠቅማል። ወደውጭ የሚላኩ እንደቡና፣ ሰሊጥ፣ የቅባት እህሎች፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጫት የመሳሰሉ ምርቶችን የሚያመርቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

የቁም እንስሳትንና የሥጋ ተዋጽኦችን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አርብቶ አደሮችና ነጋዴዎች፣ በወጪ ንግድ ዘርፍ የተሰማሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የፋብሪካ ሠራተኞች፣ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ አያሌ ዜጎችና አምራቾች፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ላይ የሚሰሩ በሺህ የሚቆጠሩ ነጋዴዎች፣ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ዘመድ፣ ጓደኛ የውጪ ምንዛሪ የሚላክላቸው በሚሊዮን የሚሰሉ የሀዋላ ተጠቃሚዎች በተጨማሪም ከውጭ ሀገር ገንዘብ ፈሰስ የሚደረግላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የግል ተቋማት እንዲሁም ሌሎች አካላት የዚህ ማሻሻያ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ።

ሌላው የውጪ ምንዛሪ ማሻሻያው ሊያስገኝ የሚችለው ጥቅም የሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ገቢ በተገቢው ሁኔታ ወደሀገር ውስጥ መግባቱንና ለዜጎችና ለአምራች ዘርፎች ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ ያግዛል። ቀደም ሲል የነበረው የውጪ ምንዛሪ ፖሊሲ የኮንትሮባንድ ንግድን የሚያበረታታ፣ ላኪዎችና አስመጪዎች የሸቀጦችን ዋጋ ከሕግ አግባብ ውጭ ከፍ ወይም ዝቅ እንዲያደርጉ እድል የሚሰጥ፣ የካፒታል ሽሽትን የሚያበረታቱ፣ ሀገር ማግኘት የሚገባትን ጥቅምና የውጪ ምንዛሪ ገቢ እንዳታገኝ እክል የሚፈጥሩ ነበሩ። በተሻሻለው አዲሱ የፖሊሲ ሥርዓት እነዚህ ሁሉ የሚስተካከሉበት ከሕግ አግባብ ውጭ ያሉ አካሄዶች የሚተረቁበት ነው።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታት የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉና እንዲያስፋፉ የሚያበረታታ መሆኑ ነው። እንዲሁም ኢትዮጵያ ታምርት በተሰኘው የሀገር በቀል እሳቤ እቅድ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች የዚህ እድል ተጠቃሚ ይሆናሉ። ከቅርብ አመታት ወዲህ የግሉን ዘርፍ ለማሳደግና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እንዲሁም ኢኮኖሚውን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት እና ምቹ ለማድረግ እየተሄደበት ያለውን እንቅስቃሴ የሚደግፍና የሚያበረታታ መሆኑ ሌላው የማሻሻያ ፖሊሲ በረከት ነው። ቀደም ሲል ለግል ዘርፉ ዝግ የነበሩ እንደ ቴሌኮም፣ ሎጀስቲክስ፣ ባንክ፣ ካፒታል ገበያ፣ ጅምላና ችርቻሮ ንግድ የመሳሰሉ ዘርፎችን ክፍት ማድረግ አብሮ የሚነሳ ጉዳይ ነው።

የውጪ ምንዛሪ ማሻሻያው የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ የውጭ የቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ፣ የንግድ ሥርዓታችንንም ከአጎራባችና ከአቻ ሀገራት ጋር የተስማማ እንዲሆን በማሳለጥ በኩል ሚናው የጎላ ነው። ሀገራችን የውጪ ምንዛሪ እጥረት ሰለባ ናት። ከሕዝብ ብዛት፣ ከሰው ኃይል፣ ከግብዓት፣ ከተሻሻለ ሎጀስቲክ፣ ከኃይል አቅርቦት፣ ከአየር ሁኔታና ከማዕድን አኳያ በብዙ መልኩ ለኢንቨስትመንት ምቹና ሳቢ ሀገር ብትሆንም በአስቸጋሪ የውጪ ምንዛሬ ፖሊሲ ሳቢያ ግን በሚፈለገው መልኩ ተጠቃሚ ስትሆን አይታይም። የውጪ ምንዛሪ የፖሊሲ ማሻሻያ ደግሞ ይሄን ተግዳሮት በመቅረፍ ረገድ አዋጪ ነው።

በኢኮኖሚው ውስጥ ተሰግስገው ያሉ ኢመደበኛነትንና ሕገ ወጥነትን ሲያበረታቱ የቆዩ የንግድ አሰራሮችን ያስተካክለው። በግርድፉ ስናየው የምንዛሪ ማሻሻያው የውጪ ምንዛሪ እጥረትን የሚቀርፍ፣ የንግድ ተወዳዳሪነትን የሚያበረታ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ ያለውን ተነሳሽነት በማጠንከር የላቀ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

የፖሊሲ ማሻሻያው ዝም ብሎ አሊያም በችኮላ ወደትግበራ የገባ ሳይሆን በሰፊ ቅድመ ዝግጅት ራሱን አዘጋጅቶ ወደሥራ የገባ ነው። እንደ መጀመሪያ አንዳንድ ተግዳሮቶች የሚኖሩ ቢሆንም ለነዚህ ምላሽ የሚሆኑ የመፍትሔ አማራጮችንም ይዟል። በተለይም አነስተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን የኑሮ ጫና ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከደሞዝ ጭማሪ ባለፈ እንደ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ መድኃኒትና የምግብ ዘይትን በመሳሰሉ ከውጭ በሚገቡ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ድጎማ በማድረግ እጁን አገብቷል።

ሌላው በከፍተኛ የዋጋ ንረት ሕይወትን ማሸነፍ ላቃታቸው የመንግሥትን የበጀት ጉድለት በማይጎዳ መልኩ የደሞዝ ጭማሪ መደረጉ ነው። በተጨማሪም በከተማና በገጠር ለሚገኙ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች በሴፍቲኔት በኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ ተመቻችቷል። ከዚህ ጋር አብሮ የሚነሳው ለማህበራዊ ወጪ እና ለእዳ ክፍያ የሚሆን ገንዘብ በርዳታ መልክ መገኘቱ ነው። ከነዚህ የመፍትሔ አማራጮች ጎን ለጎን በገንዘብና በፊስካል ፖሊሲዎች መካከል ውህደትን ለመፍጠር ብሔራዊ ባንክና የገንዘብ ሚኒስቴር ትብብር ፈጥረዋል።

በውጪ ምንዛሪ ማሻሻያ ፖሊሲ ዙሪያ እንደማጠቃለያ ሊነሳ የሚችለው ከአተገባበሩ ጋር አብሮ የሚነሳው ተጠባቂው የኢኮኖሚ እድገታችን ነው። ከሌሎች አጋዥ የማክሮ ኢኮኖሚ እሳቤዎች ጋር ተሰልፎ በቀጣይ የተሻለችን ኢትዮጵያ እንድናይ እድል ይፈጥራል። በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የማክሮ ኢኮኖሚ ትንታኔ መሠረት በሀገራችን በመተግበር ላይ ያሉ የማሻሻያ ፖሊሲዎች እድገትን የሚያፋጥኑ፣ የዋጋ ንረትን የሚያላሉ፣ የፊስካል አቅምን የሚያሳድጉ፣ የወጪ ንግድና የውጭ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋትና የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ የውጪ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ተብሏል።

በዚህ ትንታኔ መሰረት በማሻሻያ ፖሊሲዎቹ በኩል በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሀገራችን ኢኮኖሚ በአማካይ 8 በመቶ ያክል እንደሚያድግ፣ የዋጋ ንረቱ ወደአስር በመቶ ዝቅ እንደሚል፣ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አኳያ ያለው ድርሻ 11 በመቶ እንደሚሆን፣ የመንግሥት እዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 35 በመቶ ዝቅ ያለ ድርሻ እንደሚኖረው፣ የወጪና ገቢ ንግድ ዋጋ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ፣ ቀጥታ የውጪ ኢንቨስትመንት ወደ 8 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያሻቅብ፣ ዓለም አቀፍ የመጠባበቂያ ክምችት ደግሞ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ እድገት እንደሚያመጣ ትንበያው ገልጿል። የዚህ ትንበያ መነሻ ሃሳብ በመሆን ያገለገለው ሰሞነኛው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ መሆኑ ደግሞ ነገን ተስፋ እንድናደርግ እድል የሚሰጠን ነው።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You