አሜሪካ ለሳኡዲ አረቢያ በሚደረግ የመሣሪያ ሽያጭ ላይ ጥላው የነበረውን እግድ ለማንሳት ወሰነች።
የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር አሜሪካ ለሳኡዲ አረቢያ የጦር መሣሪያ እንዳትሸጥ ጥሎት የነበረው ማዕቀብ ለማንሳት መወሰኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚስቴር አስታውቋል።
አሜሪካ ማዕቀቡን የጣለችው ሳኡዲ አረቢያ በየመን ጦርነት የነበራት ሚና እንዲቀንስ ጫና ለማድረግ ነበር። አንድ ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን እንደተናገሩት ከመሬት ወደ አየር የሚተኮሱ ሚሳይሎችን ለሳኡዲ የመሸጥ እግድ መነሳቱን ማረጋገጣቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ባለስልጣኑ እንደገለጹት አሜሪካ ሁኔታዎችን እየገመገመች እና ከኮንቬንሽናል አርምስ ትራስፈር ፖሊሲ ጋር የማይቃረን መሆኑን እያረጋገጠች ለሳኡዲ የጦር መሣሪያ ታስተላልፋለች።
አስተዳደሩ እግዱን ለማንሳት መወሰኑን ለኮንግረሱ ማስረዳቱን የኮኔግሬሽናል ረዳት ተናግረዋል።
“ሳኡዲዎች የሚመለከታቸውን አድርገዋል፤ ስለዚህ በእኛ በኩል የሚጠበቅብንን ለማድረግ ተዘጋጅተናል” ሱሉ አንድ ከፍተኛ የባይደን አስተዳደር ባለሥልጣን ገልጸዋል።
በአሜሪካ ሕግ መሠረት ዋና ዋና ዓለምአቀፍ የመሣሪያ ሽያጭ ስምምነቶች ከመጽደቃቸው በፊት በኮንግረስ ወይም በተወካዮች ምክርቤት ቀርበው መጽደቅ ይኖርባቸዋል።
የዲሞክራት እና የሪፐብሊካን ተወካዮች ሳኡዲ አረቢያ በየመን እያደረገች ባለው ዘመቻ ንጹሃን መገደላቸውን እና የሠብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን በመጥቀስ ባለፉት ዓመታት ለሳኡዲ በሚደረገው የጦር መሣሪያ ሽያጭ ላይ ስጋታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
ነገርግን ይህ ተቃውሞ ሀማስ በእስራኤል ላይ ከባድ የተባለውን ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ብጥብጥ ከተነሳ በኋላ ቀዝቀዝ ሊል ችሏል።
የአስተዳደሩ ባለሥልጣን እንደናገሩት ሳኡዲ እና የየመኖቹ ሀውቲዎች በተመድ አማካኝነት በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2022 የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ሳኡዲ አረቢያ በየመን ላይ ስትፈጽም የነበረውን የአየር ጥቃት ያቆመች ሲሆን ሀውቲዎችም ወደ ሳኡዲ ግዛት መተኮሳቸውን አቁመዋል።
የየመን ጦርነት ኢራን እና ሳኡዲ አረቢያ ከሚያደርጓቸው በርካታ የእጅ አዙር ጦርነቶች አንዱ እንደሆነ ይጠቀሳል።
በሳኡዲ አረቢያ የሚደገፈውን የየመን መንግሥት በፈረንጆቹ 2014 መጨረሻ ከሰንዓ ያነሱት ሀውቲዎች ከ2015 ጀምሮ በሳኡዲ አረቢያ የሚመራውን ጥምር ኃይል ሲዋጉ ቆይተዋል። ጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመናውያን እንዲገደሉ እና 80 በመቶ የሚሆነው የየመን ሕዝብ በርዳታ ላይ ጥገኛ እንዲሆን አድርጎታል።
ባይደን በፈረንጆቹ 2021 ለሳኡዲ በሚደረግ የጦር መሣሪያ ሽያጭ ላይ እግድ የጣሉት፣ ሳኡዲ በየመን በምታደርገው ዘመቻ በንጹሃን ላይ ከፍተኛ ግድያ አድርሳለች በሚል ምክንያት ነበር።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም