ከፀሐይ እና ከጨረቃ እምነትንና እውነትን ፍለጋውድ

የሰው ልጅ በእምነትና በእውነት ላይ በመንገሥ (በመቆም) ህልውናውን የሚገነባ እና የሚተክል የማንነቱ ባለዳ ነው። አንድም ሰሪ፣ አንድም ተሰሪ ነው። የእምነቱም ፤ የእውነቱም ማረጋገጫ ወይም መግለጫ ሀሰሳው ሩቅና ጠናና ነው። ከሙከራዎቹ መካከል ጨረቃንና ፀሐይን አንድም ከሚሰጡት ጥቅም ፣ አንድም ከውበትና ሃይል (ብርሃን) ፣ በርሱ (በሰው) ሕይወት ላይ ያላቸው ከፍተኛ ተፅዕኖ ከልዕለ ሃይል አንፃር (ይተረጉማል) ተተርጉሟል።

በእኔ እምነት በቀደመው ዘመን ሚት ብቸኛው የእምነትና የእውነት ገላጭ የነበረ ይመስለኛል። በያዝነው የሠለጠነ ዘመን ደግሞ ሳይንስ የተጋድሎ ሜዳ በመሆን እውነትንም፤ እምነትንም ማስተንተኛው(መቅረጫ) ነው፤ ለሰው። ስለሆነም ሰው ሙዳይ፣ ሚትና ሳይንስ ደግሞ አለላ ናቸው። ታዲያ በቀላሉ የማይዘለቅበትን እልፍኝ በወፍ በረር ( ከዚህም፤ ከዛም) ሰበዞቹን ለመቃኘት እሞክራለሁ። ከጨለማ ገፋፊዋ፣ የተመስጦና የውበት ተምሳሌት ጨረቃ እንጀምር።

ሉናር ቴዮሪ {Lunar Theory} የጨረቃን እንቅስቃሴ ከክዋክብት አንፃር በሂሳባዊ ስሌት የመግለፅ (የማስቀመጥ) እሳቤ ነው። ይህ ቴዮሪ የሚመሰረተው አንድም በቀደመ የእውቀቱ ግስጋሴ (ማለትም ሂሳባዊ ስሌቶች፣ መሠረታዊ እሳቤዎች) እና መጠናዊ (quantitative)ስሌት፣ አሊጎሪዝም እና የጅኦሜትሪ ስዕላዊ መግለጫ (የጨረቃን አቀማመጥ ከጊዜ ስሌት ጋር የሚያሳይ) ናቸው።

ሉናር ቴዮሪ ከ2000 ዓመታት በላይ የዳበረ ታሪክ ያለው የምርምር ዘርፍ ነው። በመሆኑም ዘመናዊ ቅርፅ የያዘው ካለፉት ሶስት ክፍለ ዘመናት ወዲህ ነው። በአሁኑ ወቅት ለመሠረታዊ ምርምር እና ለቴክኖሎጂ ግብዓት (ዓላማ) አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ሉናር ቴዮሪ ከጥንት እስካለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ባደረገው የእድገት ግስጋሴ ውስጥ የማይተካ ሙያዊ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ምሁራን ከነሥልጣኔ ዘመናቸው ሰፍረው ይገኛሉ።

የተፈጥሮን ጉልበትም ሆነ ውበት በቋንቋና በስሌት ለመተርጎም የሚሄድበትን ርቀት ትዕምርታዊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። እውነቱንና እምነቱን ፈለገ ወይም አሰሰ የምለው ለዚህ ነው። ሰው የእውነቱ ባሪያ ነውና፤ ይፈልጋል። ይጨብጣል። ያፀናል። አንድም በልማድ ሰነድነት ፤ አንድም በንድፈሃሳብ ደረጃ ያሰርጻል። ይተክላል። ታዲያ የሚተክለው የራሱን እውነት ነው፤ የሚተረጎም እስከሆነ ድረስ።

ሉናር ሚት(Lunar Myth) የጨረቃ አምልኮት ወይም አምላክን የሚገልፁ ተረኮች ስያሜ ነው። በጥንታዊ ተረኮች አማካኝነት የጨረቃን እንቅስቃሴ፣ መጠን (ምዕራፎች)እና አቅጣጫ ሂደቶች የሚያስቃኝ አምልኮታዊ ሥርዓትም ነው።

የጨረቃ አምላክ(Lunar Deity) የጨረቃ አምላክ ወይም አማልክት የሚገለፅበት አምልኮ ሲሆን አንዳንዴ ደግሞ ልክ ሕይወት እንዳለው ሰው ሊቆጠር ይችላል። ይህ አምልኮ እንደየባህሉ ልዩነቶች የተለያዩ አገልግሎቶች እና ልማዶች(ሥርዓቶች) አሉት። ነገር ግን በአመዛኙ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ናቸው። በጥንታዊ እምነቶች ውስጥ በርካታ የጨረቃ አማልክቶች የመገኘታቸው ምስጢርም ይኸው ልዩነት ነው።

አማልክቶቹ በተለያዩ ዓለማት በአይነትም ሆነ በፆታ የተለያዩ ናቸው። ለአብነትም የግሪኳ ሴት አማልክት ‹‹ሰሊን››(selene) እና የሮማዋ አማልክት ‹‹ሉና›› (luna) እንዲሁም የቻይናዋ ‹‹ቻንጊ››(chang’e) ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም አፍሪካዊ ከሆኑ የጨረቃ አማልክት መካከል አቡክ ‹‹Abuk›› ተጠቃሽ ሲሆን የእምነት (የሚት) ስሙ ደግሞ ‹‹ዲንካ›› (Dink) ይባላል። የአማልክቱ ‹‹መለኮታዊ›› ተግባርም ውልደት(fertility)፣ምግባር (morality) ፣ ፈጠራ(creativity) እና ፍቅር (love) ናቸው። የእምነቱ በረከቶች በመሆናቸው ለመመለኩ ምክንያቶች ናቸው።

የጨረቃ ምዕራፎች እና ግርዶሽ መሬት ላይ ሆነን ጨረቃን ካየናት በአንፀባራቂ ‹‹ግራጫ›› ገፅታዋ ላይ የፀሐይ ብርሃን ተንፀባርቋል ማለት ነው። ይህ ማለት ጨረቃ ብርሃን አታመነጭም፤ ከፀሐይ ያረፈባትን ታንፀባርቃለች እንጂ ፤ ልክ መሬት ላይ በቀን እንደሚሆነው።

በወር ውስጥ የምንመለከተው የተለያዩ የጨረቃ ገፅታዎች ‹‹የጨረቃ ምዕራፎች›› (lunar phases) ይባላል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የጨረቃ ምህዋር (orbits) በመሬት ዙሪያ እና የመሬት ምህዋር (ንፍቀ ክበብ) ተፅዕኖ በፀሐይ ዙሪያ ስለሆነ ነው። ይህ ሁሉ የእንቅስቃሴ ውጤት ነው።

በጨረቃ ግርዶሽ ወቅት መሬት በፀሐይና በጨረቃ መካከል ትሆናለች። ይህም የፀሐይን ብርሃን በመገደብ (በማስቀረት) ጨረቃ በጥቅጥቅ ጨለማ እንድትዋጥ ያደርጋታል። አንዳንዴ ደግሞ የመሬት ጥላ ጨረቃን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሊጋርዳት ይችላል። ይህም ሂደት በሁለት ይከፈላል። እነሱም፡- ሙሉ ግርዶሽ እና ከፊል ግርዶሽ ናቸው። እያንዳንዳቸውን እንደሚከተለው እንመልከት።

ሀ.ሙሉ ግርዶሽ (Total lunar eclipse)፡-ጨረቃ እና ፀሐይ ከመሬት በተቃራኒ አቅጣጫ ሲሆኑ የሚፈጠር የግርዶሽ አይነት ነው። ማለትም መሬት የፀሐይን ብርሃን ሙሉ በሙሉ በመጋረድ ጨረቃ ላይ ጥላዋን ታጠላለች።

ለ.ከፊል ግርዶሽ (partial lunar eclipse)፡-የመሬት ከፊል ገፅታ ብቻ ጥላውን በጨረቃ ላይ ሲያሳርፍ የሚፈጠር የግርዶሽ አይነት ነው።

ሉናር የጊዜ አቆጣጠር ተምሳሌት ከሆኑት መካከል የቻይና ሉናር የዘመን አቆጣጠር (Chinese Lunar Calen­dar) አንዱ ነው። ከሌሎች የሚለየው የፀሐይን ሥርዓት ደርቦ መጠቀሙ ነው። የወር ለውጡ የሚመሠረተው አንዴ በፀሐይ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጨረቃ ሥርዓቶች ላይ ነው። የወሩ ርዝማኔ የሚመሠረተው በሁለቱ አዲስ ጨረቃዎች መካከል ባለው የጊዜ ርቀት አማካኝነት ነው። ይህ የጨረቃ ወር ስያሜ የተወሰደው ከፀሐይ ሥርዓት(solar system) ነው።

የፀሐይ ሚት (Solar Myth) የፀሐይ እምነት ወይም አምላክ ተረክ (ሚት) ነው። ይህም በባህላዊ ተረኮች መነሻነት የፀሐይን እንቅስቃሴ (motion)፣ተፅዕኖ እና አቅጣጫ መግለጫ ሙያም ነው። ይህን እሳቤ የሚያጠና የሳይንስ ዘርፍ ሶላሪዝም(solarism) ይባላል። ሶላሪዝም የጥንት ፎክሎራዊ ተረኮችን እና ሌጀንዶችን መነሻ በማድረግ የተፈጥሮንና በዋናነት የፀሐይን እንቅስቃሴ፣ መጠን የሚመረምር፣ የሚፈክርና የሚተነትን የጥናት መስክ ነው።

እንደ ‹‹ሙለር››(Müller’s) ገለፃ ከሆነ ሶላር ሚት የተገኘው ወይም የተወለደው ከኢንዶ-ኤሮፓ የቋንቋ ጥናት ነው። በሙለር እምነት ‹‹ሳንስክሪት›› ቋንቋ በርካታ የፀሐይ አማላክትን ስሞች ወይም ስያሜዎች የሚጠቀም ሲሆን ይህም ሁኔታ በሌሎች ቋንቋዎች በተመሳሳይ መልኩ አገልግሎት ላይ መዋሉን ታዝቧል። ይህም የሚትን ድንበር ዘለል (ተሻጋሪነት) ባህሪ ጠቋሚ መሆኑን ታዝቧል።

የፀሐይ አምላክ(Solar Deities) በፀሐይ የተወከለ አምላክ ወይም አማልክት ሲሆን የሃይል እና የጥንካሬ ተምሳሌት ነው። የፀሐይ እምነት ወይም አምልኮ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በተለያየ መንገድ ወይም ስልት የተገለጠ እውነታ ነው። ለአብነትም በአፍሪካ እንደ ‹‹ማጀክ››(magec) (Tenerife god­dess of the sun and Light) እና ‹‹ኢንያንጋ›› ደግሞ በበርካታ ሕዝብ ዘንድ የጨረቃ አምላክ ተደርገው ይመለካሉ። እንዲሁም በግብፅ ሚቶሎጂ ውስጥ ‹‹ኼፕሪ››(kheori) ደግሞ የፀሐይ መውጫ ፣ የፈጠራ እና የአዲስ ሕይወት ተምሳሌት(አምላክ) ሆኖ ይመለካል። እንዲሁም ‹‹ራ››(Ra) የፀሐይ አምላክ ነው። ከፀሐይ አማልክቶች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው።

አፍሪካዊ የሆኑት፡- አንያንው (Anyanwu)፣ ማጀክ ( Magec)፣ አንነጋ (iNyanga) እና የዙሉ ሕዝቦች ናቸው። እንዲሁም ራ (Ra) በግብፆች ዘንድ የፀሐይ አምላክ በመባል ይመለካል። ሰክመት (Sekhmet) ደግሞ የጦር እና የፀሐይ አምላክ ተደርጎ የሚታመንበት ነው።

በአጠቃላይ ሉናር እና ሶላር ሚት ቴዮሪ ለበርካታ የሙያ ዘርፎች ግብዓት የሚሆኑ እሳቤዎች፣ ምልከታዎች ያቀፈ ነው። በድህረ ዘመናዊነት የሳይንስ ምርምር አማካኝነት የሙያዎችን ድንበር የጣሰ እና በከፍተኛ ደረጃ ያስተሳሰረ እሳቤ ነው፤ ሚት። የተለያዩ ተረኮች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ግለሰባዊ ፋይዳ እንደ ሳይኮሎጂ፣ አንትሮፖሎጂ፣ ሶሾሎጂ እና ፍልስፍና እንዲሁም ነገረመለኮት ወዘተ…ያሉ ሙያዎች ጉዳይ (ተጠኝ) የሆነ ሙያ ነው።

ሚት በባህሪው ምናባዊ ተረክ በመሆኑ ኩሸት ነው። ይህ ደግሞ ተምሳሌታዊ በመሆኑ ከዘወትራዊ ኑሮ የራቀ እና የጠነነ ነው። በመሆኑም ተረኮቹ እውነት ሆነው መተረካቸው የእምነት መጣረስ ያስከትላሉ የሚል እይታ አለኝ። የሃይማኖቶቹ አጀማመርም ሆነ ቀኖና መሠረት ማጠየቂያም ጭምር ነው። ማለትም ከሚትነት ወደ ዶግማና ቀኖና የተለወጡ የአምልኮ ተቋምነት የተቀየሩት በሂደት ነው። ያም ሆኖ ሚታዊ ተረክ የታጨቀባቸው የአምልኮ ሰነዶች አሏቸው።

ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You