
ዜና ትንታኔ
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ከሚመረተው የቡና ምርት አፍሪካ የምትሸፍነው 12 በመቶውን ብቻ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2023 በዓለም አቀፍ ደረጃ 495 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከቡና ምርት የተገኘ ሲሆን አፍሪካ ከዚህ ውስጥ ያገኘችው ከአንድ በመቶ በታች መሆኑን በማሳያነት ማንሳት ይቻላል፡፡
በካምፓላ በተካሄደው የቡድን 25 የአፍሪካ ቡና አብቃይ ሀገራት ጉባዔ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና ንግዱን ለማስፋፋት ቡናን ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ የማጣጣምና የህብረቱ ስትራቴጂክ ሸቀጥ ሆኖ እንዲሰየም ውሳኔ ተላልፏል፡፡
በመቀጠልም ባለፈው የካቲት ወር 2016 ዓ.ም በተካሄደው 37ኛው የአፍሪካ የመሪዎች መደበኛ ጉባዔ ላይ ቡና የአፍሪካ ህብረት 2063 አጀንዳ እንደ አንድ ስትራቴጂካዊ ምርት ያጸደቀ ሲሆን የአፍሪካ ቡና አብቃይ ሀገራት ድርጅትንም የአፍሪካ ህብረት ልዩ ኤጀንሲ አድርጎ ሾሟል፡፡
ለመሆኑ የአፍሪካ ቡና አብቃይ ሀገራት ድርጅት ህብረቱ ያስተላለፈው ውሳኔ የሚያስገኘው ፋይዳ ምንድነው?
የአፍሪካ ቡና አብቃይ ሀገራት ድርጅት ሊቀ መንበር እና የኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ፣ ቡና የህብረቱ ስትራቴጂካዊ ሸቀጥ ተድርጎ መሰየሙ ከኢኮኖሚ አንጻር ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ ውሳኔው ለአፍሪካ ቡና አምራች ገበሬዎች መልካም ዜና ነው ይላሉ።
ቡና የአፍሪካ ዋነኛ ምርት እንዲሆን የተወሰነው ውሳኔ ዋና ጠቀሜታው በተለይም የአፍሪካ መሪዎች በቅርቡ ተግባራዊ ያደረጉት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ላይ በመመሥረት ከአንዱ የአፍሪካ ጫፍ ወደ ሌላኛው የአህጉሪቱ ጫፍ ቡናን በተመሳሳይ ታሪፍ፣ ጥራት፣ ሕግና መመዘኛ መገበያየት እንዲያስችል ማድረጉ የሚያስችል መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም በአህጉሪቱ ውስጥ ላሉና ቡና አምራች ላልሆኑ ሀገራት የቡና ምርት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡
በሌላ በኩል ውሳኔው የቡና ምርት፣ ጥራትና ንግዱን ለመደገፍ የአፍሪካ ልማት ባንክን ጨምሮ የአፍሪካ የፋይናንስ ተቋማት በቡና ምርት ላይ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ልዩ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነውም ይላሉ፡፡
ቡና በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 መካተቱ አፍሪካ ከዚህ በኋላ በቡና ምርት ዙሪያ የተባበረ ድምጽ እንዲኖራት የሚያደርግ ከመሆኑ ባሻገር ዓለም ላይ ቡናን በተመለከተ የትኛውም ውሳኔ ላይ እንደ አንድ የምትወስን ይሆናል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
የአፍሪካ ቡና በአሁኑ ጊዜ ወደ ገበያ እየቀረበ ካለው 99 በመቶው በጥሬው ነው የሚሉት ሊቀመንበሩ፤ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ተብሎ የተያዘው አፍሪካ የቡና ምርቷ ላይ እሴትን ጨምራ ወደ ገበያ በማቅረብ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ይገባል የሚል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና የወጪ ንግድ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን ያነሱት ሊቀመንበሩ፤ ይህም እስካሁን ካሉት ዓመታት ከፍተኛው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
አሁን ላይ የቡና የወጪ ንግድ በኢትዮጵያ ካለው አጠቃላይ የወጪ ንግድ 36 በመቶውን መያዙን በመጠቆም፤ ይህም ለሀገሪቱ ቡና ወሳኝ ምርት መሆኑን ማሳያ እንደማሳያ የሚጠቀስ ያስረዳሉ፡፡
ሊቀመንበሩ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በቡና ምርት ላይ ኑሯቸውን መሠረት ያደረጉ አምስት ሚሊዮን አባወራ ያሉባት ሀገር መሆኗ እና በቡና ምርት ከአፍሪካ ኡጋንዳን በማስከተል የምትመራ መሆኗ ውሳኔው ከየትኛውም የአፍሪካ ሀገራት የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋታል ይላሉ፡፡
ባለፉት ዓመታት በተደረጉ ጥረቶች ውሳኔው እንዲተላለፍ በመደረጉና ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቡና አብቃይ ድርጅትን በሊቀመንበርነት እንድትመራ መደረጉ የኢትዮጵያን ቡና ለሌሎች ሀገራት ለማቅረብ፤ ለመገበያየት እና የንግድ መዳረሻዎችን ለማስፋት ትልቅ እድል ይዞ የመጣ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
እድሉን በመጠቀምም በቡና ምርት፣ ጥራት እንዲሁም ንግድ ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሊዮን እንደሚሉት ፤ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአፍሪካ ዜጎች ኑሯቸው በቡና ምርት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ከዘርፉ የሚገኘውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡
ቀጣናዊ ትብብርን ማስፋት ፣ የሥራ እድሎች መፍጠር ፣ ከአፍሪካ ህብረት ዋና ተግባራት መካከል ናቸው ያሉት አምባሳደር ጆሴፍ በመሆኑም ውሳኔው የአፍሪካ ቡና አብቃይ ሀገራት ቡናን በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ሥርዓት እንዲገበያዩ የሚያደርግ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
አምባሳደሯ ፤ ግብዓቶችን ማሰባሰብ፣ በኢንዱስትሪዎች ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ እሴት የተጨመረበት ቡና ለገበያ ማቅረብና ከዚህ ቀደም ያሉ አሠራሮችን መቀየር ይኖርብናል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
የአፍሪካ ቡና አብቃይ ሀገራት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አምባሳደር ሰለሞን ሩተጋ እንደሚሉት ፤ የውሳኔው ዋና ራዕይ የአፍሪካን የቡና ዘርፍ እሴት በመጨመር ወደ ላቀ ስኬት ማሸጋገር ነው። በዓለም ዙሪያ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግም የዲፕሎማሲ ሥራው ወሳኝ በመሆኑ እሱ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ይላሉ፡፡
በዓለም ላይ በትልቅነቱ ሁለተኛ ደረጃ የያዘው የቡና ምርት የሚገባውን ያህል ትኩረት እንዳላገኘ የሚናገሩት ዋና ጸሃፊው በአሁኑ ጊዜም እንደ ሞሮኮ እና አልጄሪያ ያሉ ሀገራት ወደ ድርጅቱ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ቡና በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና በኩል እንዲገበያዩ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የአፍሪካ ህብረት ቡናን እንደ ስትራቴጂካዊ ምርት መውሰዱ የአፍሪካ ሀገራት በቡና ላይ እንዲሁም በገበያው ላይ አንድ አቋም እንዲይዙ ያስችላል።
ከ13 በመቶ በላይ የአፍሪካ ሀገራት ቡናን ሲያስገቡ አህጉሪቱ ደግሞ 12 በመቶ ምርቱን ለዓለም ገበያ እያበረከተች ነው የሚሉት ዶ/ር አዱኛ ቡናን ወደ አፍሪካ ገበያ መላክ አምራቾችን ብቻ ሳይሆን ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም