ዩክሬን ወደ ደቡባዊ ምዕራብ ሩሲያ የኩርስክ ግዛት ዘልቃ በመግባት የፈጸመችውን ድንገተኛ ወረራ ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት የገቡበት ከባድ ውጊያ ስድስተኛውን ቀን ይዟል።
በዓለማችን ትልቁ የሚባለው የኒውክሌር ጣቢያ በሚገኝበት በኩርስክ ግዛቷ ያልተጠበቀ ጥቃት የገጠማት ሩሲያ የአስቸኳይ ጊዜ ከማወጅ በተጨማሪ ተጠባባቂ ጦሯንም ጠርታለች።
ሁለቱ ሀገራት በድንበራቸው ላይ እያደረጉት ያለው ውጊያ የተፋፋመ ሲሆን፣ ሩሲያ ይህንን ለመመከት ተጨማሪ የጦር መሣሪያዎችን ወደ ሥፍራው እየላከች ትገኛለች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር “የሩሲያን ግዛት ለመውረር የሞከሩ የዩክሬን ታጣቂ ኃይሎችን” እየተፋለመ መሆኑን አስታውቋል።
ሩሲያ ጠላት ባለችው ኃይል የተፈጸመባትን የወረራ ሙከራ ለማክሸፍም የአየር እና የመሬት ኃይሏን አቀናጅታ እየተጠቀመች መሆኑንም ገልጻለች።
የሁለቱ ሀገራት ጦርነት ከተጀመረበት ወቅት በተለየ ከፍተኛ እና ያልተጠበቀ ነው የተባለው የማክሰኞ፣ ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም. የዩክሬን ጥቃት ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ የዩክሬን ወታደሮች የተሳተፉበት ነው።
የዩክሬን ምንጮች ጥቃቱ ከኩርስክ ጋር በሚዋሰነው ሰሜናዊ የዩክሬኗ ግዛት ሰሚ ላይ ሩሲያ ካቀደችው የወረራ ጥቃት በፊት የተፈጸመ “ቀዳሚ መብረቃዊ ጥቃት” ነው ማለታቸው ተዘግቧል።
የዩክሬን ወታደሮች ወደ ምዕራብ ሩሲያ ዘልቀው መግባታቸው ሞስኮን ከማስደንገጥ በተጨማሪ፣ የድንበር መከላከያዋ ደካማ መሆኑን ያሳየ እንዲሁም ወደ አውሮፓ በሚቀርበው የተፈጥሮ ጋዝ መስመር ላይ አደጋ የደቀነ ተብሏል።
ኪዬቭ ማክሰኞ ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም. በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን በማሰማራት፣ በታጠቁ ተሽከርካሪዎች፣ በከባድ መሣሪያዎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በመታገዝ ነበር ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ዘልቃ የገባችው።
ባለፈው ዓመት እንዲሁ የኩርስክን ግዛት እና አጎራባችዋን ቤልጎሮድን ለዩክሬን ወግነው እየተዋጉ ያሉ ሩሲያውያን አጠር ላለ ጊዜ ወረራ ፈጽመውባት ነበር።
ማክሰኞ ማለዳ የዩክሬን ኃይሎች የሩሲያን ድንበር አቋርጠው 5 ሺህ ነዋሪዎች ወዳሉባት ሱድዛ ከተማ ገቡ። ሱድዛ የሩሲያ የተፈጥሮ ጋዝ በዩክሬን በኩል ወደ አውሮፓ የሚደርስባት ብቸኛዋ የመተላለፊያ ጣቢያ እና ቁልፍ የምትባል ስፍራ ናት።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2016 ዓ.ም