መልካቁንጡሬ- በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ 12ኛው የኢትዮጵያ ቅርስ

ኢትዮጵያ በዓለም በቱሪስት መስህብ ሀብት ከሚታወቁ ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች። ቀደምት የሰው ልጅ ስልጣኔ ደረጃን የሚያመለክቱ ቅርሶች፣ የምድራችንን የተፈጥሮ ስብጥርና ውበት የሚያሳዩ ሀብቶች፣ ማህበራዊ መስተጋብርንና የኑሮ ዘይቤን የሚያመለክቱ ባህላዊ እሴቶችን የያዘች ስለመሆኗ የሚያሳዩ አያሌ ብዝሃ ቅርሶች ባለቤት ነች።

ከእነዚህ ሀብቶች ውስጥ ደግሞ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡ ይገኛሉ። በሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት ብዛት ያላቸው መስህቦችን በማስመዝገብ ረገድም ከዓለማችን ጥቂት ሀገሮች ውስጥ ተርታ ትመደባለች።

ኢትዮጵያ በያዝነው ዓመት ብቻ አራት የሚደርሱ ቅርሶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን አስመዝግባለች። ከእነዚህ ውስጥ የጌዲዮ ማህበረሰብን ባህል፣ የኑሮ ዘይቤ፣ ጥበብ እና ከተፈጥሮ ጋር የመኖር ብልሃት የሚያሳየው ‹‹የጌዲዮ ባህላዊ መልከዓ ምድርና ደን አጠበቀበቅ ስርዓት›› ተጠቃሽ ነው። የብዝሀ ተፈጥሮ ስብጥር የያዘው የቀይ ቀበሮ መገኛው፣ የአየር ንብረት ስርዓት የሚያስጠብቁ ደኖች ያሉበት የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክም ሌላኛው በዩኔስኮ የተመዘገበ የተፈጥሮ ሀብት ነው።

ይህ ዓመት ከእነዚህ ሀብቶች በተጨማሪም ኢትዮጵያ በባህልና በአርኮዮሎጂ ዘርፍ ሁለት ተጨማሪ ቅርሶችን ያስመዘገበችበት ነው። አንዱ የዓለም ቅርስ የሀረሪ ማህበረሰብን ባህላዊ እሴት የሚያሳየው ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ ደማቅ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ትእይንት የሚካሄድበት የሸዋል ኢድ ክብረ በዓል ነው። እነዚህ ቅርሶች ኢትዮጵያ ገና በጥልቅ ያልተዳሰሱ፣ በመስህብነታቸው ወደር የማይገኝላቸው አያሌ ቅርሶች መገኛ መሆኗን ያመለከቱ ናቸው። ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችም ትኩረታቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያደርጉና የጉዞ እቅድ እንዲያወጡ ገፊ ምክንያት የሚሆኑ ሀብቶችም ናቸው።

የ2016 ዓም ሳይጠናቀቅ ዩኔስኮ ለኢትዮጵያውያን ያሰማው ሌላኛው ብስራት ደግሞ በአርኪዮሎጂ ዘርፍ የተመዘገበው የመልካቁንጡሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንትሮፖሎጂ መካነ-ቅርስ ስፍራ ነው። ይህ ቅርስ ኢትዮጵያ በዓመቱ ካስመዘገበቻቸው አራት ቅርሶች ውስጥ አንደኛውና የመጨረሻው ሲሆን፣ ከሰሞኑም በልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙሃን ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት ተመልክተናል። የዝግጅት ክፍላችንም ከሳምንት በፊት በዩኔስኮ እውቅና ያገኘውን ይህ ቅርስ የተመዘገበባቸውን መስፈርቶችና በውስጡ የያዛቸውን እውነታዎች ይመለከታል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ባሳለፍነው የሐምሌ ወር ሰፊ መሰናዶ በማዘጋጀት ሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዓመት እድሜ ያላትን እና ከዛሬ 50 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ አፋር ክልል በአርኪዮሎጂና ፓሊዮንትሮፖሎጂ ተመራማሪዎች የተገኘችውን የድንቅነሽ ሉሲ እዮቤልዩ በዓል ማክበሩ ይታወሳል። ይህ በዓል ከመጠናቀቁ በፊት ነበር የመልካቁንጡሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንትሮፖሊጂ መካነ ስፍራ በዩኒስኮ መመዝገቡ ይፋ የተደረገው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የመልካቁንጡሬ የዩኒስኮ ይፋዊ ምዝገባ ከመካሄዱ አስቀድሞ ‹‹ቀደምት የሰው ልጆች መገኛ የሆነችውን ድንቅ ሀገር ጎብኙ›› በማለት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንቅ ሀገር በሆነችው ኢትዮጵያ በርካታ የዓለም ቅርሶች መኖራቸውን ተናግረው፤ ይህን መጥቶ መጎብኘት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ይህንን ይፋዊ ምዝገባና እውቅና አስመልክቶም የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በቅርቡ በህንድ ኒውዴሊህ በተካሄደውና ቅርሱ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ላደረገው ጉባኤ በላኩት መልእክት ይህ ቅርስ የተመዘገበው ሉሲ የተገኘችበት 50ኛ ዓመት በሚከበርበት ወቅት መሆኑ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትርጉም ያለው እንደሆነ ተናግረዋል። በእርግጥም ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት መሆኗን ለዓለም ተጨማሪ ማረጋገጫ የሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል። ቅርሱ ተጠብቆ እንዲቆይም የኢትዮጵያ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ በመልእክታቸው ላይ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

የዝግጅት ክፍላችን የመካነ-ቅርስ ስፍራ መመዝገብን አስመልክቶ ዩኔስኮ ሀብቱን በየትኛው ዘርፍ እንደመዘገበው፣ ምን አይነት መስፈርቶችን እንዳሟላና ስፍራው ምን ምን ሀብቶችን እና ግኝቶችን እንዳካተተ የቅርስ ባለስልጣን ጠይቆ ነበር። በዚህም የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ እና የሥራ አስፈፃሚው ተወካይ ወይዘሮ አዳነች አሻግሬ የሚከተለውን መረጃ አድርሰውናል።

እንደ ሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪዋ ገለፃ፤ የመልካ ቁንጡሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንትሮፖሎጂ መካነ-ቅርስ ስፍራ በህንድ ኒው ደልሂ ከሐምሌ 21 ቀን እስከ ሐምሌ 31 ቀን 2024 በተካሄደው የዩኔስኮ የዓለም-ቅርስ ኮሚቴ 46ኛ ዓመታዊ መደበኛ ጉባዔ በዓለም-አቀፍ ቅርስነት ተመዝግቧል:: የመልካ ቁንጡሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንትሮፖሎጂ መካነ-ቅርስ ስፍራ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በቀርሳ ማሊማ እና በሰዋታ አዋሽ ወረዳዎች የሚገኝ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአዋሽ መልካ ከተማ ከአዋሽ ወንዝ ድልድይ አለፍ ብሎ ፣ 2 ኪሎ ሜትር ወደ ቀኝ ገባ ብሎ የላይኛው አዋሽ ተፋሰስ ዳርቻ ላይ ይገኛል:: መልካ ቆንጡሬ የስምጥ ሸለቆ ዋና አካል ሲሆን ከባህር ጠለል በላይ በ2000 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል::

ወይዘሮ አዳነች የተቋማቸውን ምርምር እና ጥናት ውጤትን ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት፤ መካነ-ቅርሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው እ.ኤ.አ በ1963 ጀራርድ ዴከር በሚባል በሆላንድ የስነ-ውሃ ጥናት (Hydrologist) ባለሙያ ነው። በ1964 ለመጀመሪያ ጊዜ በሳይንሳዊ ዘዴ በፈረንሳዊ የአርኪዮሎጂ ባለሙያ ጄራርድ ፓሉድ በተመራ የጥናት ቡድን ጥናትና ምርምር ተካሂዷል:: ከዚህ ወቅት ጀምሮ በዓለም ላይ በሚገኙ ተመራማሪዎች ጥናት የተደረገበት ሲሆን፤ መካነ-ቅርሱ ካለው እምቅ የጥናትና ምርምር አቅም አንጻር በዓለም-ቅርስነት በዩኔስኮ ጊዜያዊ (tentative list) ዝርዝር ውስጥ እ.ኤ.አ 2012 ጀምሮ እንዲመዘገብ መደረጉን ያስረዳሉ::

‹‹የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ቅርሱን በዓለም-ቅርስነት ሊያስመዘግበው የሚያስችሉትን ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል›› ያሉት የሕዝብ ግንኙነት የቡድን መሪዋ፤ ከእነዚህም መካከል የቅርስ መምረጫ ሰነድ (Nomination Dossier)፣ የቅርስ አስተዳደር ሰነድ (Site Management Plan) እና የወሰን ክለላ በማዘጋጀት ለዩኔስኮ 2011 ዓ.ም መላኩን ይገልጻሉ:: በተቋሙ በተላከው ዶሴ ላይ ከዩኔስኮ አስተያየት እና የማስተካከያ ግብዓቶች ከተገኙ በኋላ ከአይኮሞስ እና አይዩሲን /International Council of Monuments and Sites እና The International Union for Conservation of Nature/ የተውጣጣ አንድ የገምጋሚ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የመስክ ግምገማ እንዲያካሂድ ተደርጓል፤ ከዚያም የመልካ ቁንጡሬ ባልጬት መካነ-ቅርስ እ.ኤ.አ ከሐምሌ 21 ቀን እስከ ሐምሌ 31 ቀን 2024 ዓ.ም በህንድ ኒው ደልሂ በተካሄደ የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ-ቅርስ ኮሚቴ 46ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ በዓለም-አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ተደርጓል::

እንደ ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዋ ገለፃ፤ የመልካ ቁንጡሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንትሮፖሎጂ መካነ-ቅርስ ዩኔስኮ ካስቀመጣቸው አስር የቅርስ መምረጫ መስፈርቶች መካከል ሦስቱን መስፈርቶች ማለትም መስፈርት 3 ፣ መስፈርት 4፣ እና መስፈርት 5 በማሟላት በዓለም-አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ተደርጓል::

የእነዚህ መስፈርቶች አንድምታም የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ አንድ ቅርስ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ሲመዘግብ ከመስፈርቱ ባሻገር የቅርሱ የላቀ ሁለንተናዊ እሴት (Outstanding Universal Value)፣ የቅርሱ እውነተኛ ፋይዳ (Authenticity) እንዲሁም ሙሉእነት (integrity) ታሳቢ ይደረጋል::

የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪዋ ወይዘሮ አዳነች ይህ መካነ-ቅርስ ከዚህ እንደሚከተለው በቀረበው የላቀ ሁለንተናዊ እሴት መመረጡን አስረድተው፤ መስፈርቶች በቀጣይ በዝርዝር የምንመለከታቸውን ፋይዳዎች መያዙንም ነግረውናል። እነዚህ ዝርዝሮች የዩኔስኮን አስር የቅርስ መምረጫ መስፈርቶች መካከል እንደሆኑም አስረድተውናል።

መስፈርት ሦስት (Criteria III)

ለሰው ልጅ ህያው ወይም የጠፋ ባህል ወይም የስልጣኔ ደረጃን ለመዘከር የሚያስችል ፋይዳ ያለው መሆኑ፣ ከዚህ መስፈርት አንጻር የመልካ ቁንጡሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንትሮፖሎጂ መካነ-ቅርስ በሰው ዘር አመጣጥ ጥናት የሚታወቁ ህያው እና የጠፉ ባህሎችን የሚዘክሩ ቅሬተ አካላትን የያዘ ከመሆኑም በላይ ጥንታዊው ሰው ይጠቀምባቸው የነበሩ የድንጋይ ዘመን ቴክኖሎጂ በማበል የሚታወቁትን አራቱን የድንጋይ ዘመን ቴክኖሎጂዎች አንድ ላይ አጣምሮ ይዞ የሚገኝ ብቸኛ መካነ-ቅርስ በመሆኑ ነው::

መስፈርት አራት (Criteria IV)

ይህ መስፈረት በሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ ጉልህ ደረጃዎችን ለሚያሳይ የቴክኖሎጂ ወይም የመልክዓ-ምድር አቀማመጥ ጥናት የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑ፣ ከዚህ መስፈርት አንጻር የመልካ ቁንጡሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንትሮፖሎጂ መካነ-ቅርስ ስፍራ በሰው ዘሮች ጥናት የሚታወቁ ቅሪተ አካላትን፣ ቅሬቶችን የያዘ ሲሆን ከሁለት ሚሊዮን ዓመት ጀምሮ የነበረውን ያልተቆራረጠ ዝግመተ-ለውጥ የሚያሳዩ የሳይንስ ግኝቶችን የያዘ ስፍራ ነው:: በአካባቢው በጥንት ዘመን የነበረውን አየር ንብረት (Paleo-enviorment and climate) ለማጥናት የሚረዳ ልዩ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ነው::

መስፈርት አምስት (Criteria V)

ይህ መስፈርት የሰውን ልጅ ባህል ወይም የሰውና የተፈጥሮ መስተጋብር፣ የሰዎችን ሠፈር የሚዘክር ፋይዳ ያለው ሲሆን በተለይም ይህ ባህላዊ ፋይዳ በማይቀለበስ ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭ በመሆኑ የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑ፣

የመልካ ቁንጡሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንትሮፖሎጂ መካነ-ቅርስ የጥንታዊ ሰዎች ለድንጋይ መሳሪያነት የተጠቀሙበት ቴክኖሎጂን የሚወክሉ ቅሬቶች እና የጥንት ሰዎችን አሰፋፈር የሚያሳየው ጥንታዊ አሠፋፈር በማይቀለበስ ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭነት የሚያሳይ መካነ-ቅርስ ስፍራ በመሆኑ ነው::

በአጠቃላይ የመልካ ቁንጡሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንትሮፖሎጂ መካነ-ቅርስ ከአዲስ አበባ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝና የተለያዩ ቅሬተ አካላትን የያዘ ሙዚየም ያለው ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ይበልጥ የሚያጠናክር እና እምቅ አቅም ያለው የጥናትና ምርምር ስፍራ ሲሆን፤ ለአዲስ አበባ ባለው ቅርበት እና ቅርሱ ከያዘው የላቀ ሁለንተናዊ እሴት አንጻር ተመራጭ የቱሪስት መስህብ እና ድንቅ የቅርስ ሀብት ነው::

እንደ መውጫ

ኢትዮጵያን ምድረ ቀደምት ካሰኛት ምክንያቶች አንደኛው የሰው ዘር መገኛ መሆኗ ነው። በሀገሪቱ ከሰባት ሚሊዮን ዓመት ጀምሮ እስከ 200 ሺህ ዓመታት የተለያዩ የሰው ልጅ ዝርያዎች ሳይቆራረጡ የተገኙባት ብቸኛ ሀገር ነች።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከዛሬ 50 ዓመት በፊትን ከተገኘችው ድንቅነሽ (ሉሲ) ባሻገር ኢትዮጵያ እውነተኛዋ የሰው ዘር መገኛ ምድረ ቀደምት መሆኗን የሚያስረዱ በፓሊዮአንትሮፖሎጂ ምርምር የተገኙ ቅሪተ አካሎች በሀገሪቱ ይገኛሉ። ከዚህ ውስጥ ዛሬ በስፋት የዳሰስነው የመልካ ቁንጡሬ ባልጩት አርኪዮሎጂና ፓሊዮንትሮፖሎጂ መካነ-ቅርስ አንዱ ነው። ይህ ሀብት የጥንታዊ ሰዎች ለድንጋይ መሳሪያነት የተጠቀሙበት ቴክኖሎጂን የሚወክሉ ቅሬቶች እና የጥንት ሰዎችን አሰፋፈር ያሳያል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2016 ዓ.ም

Recommended For You