መሰረት…
የገጠር ልጅ ነች እንደእኩዮቿ ከብቶች ስታግድ ስትዘል፣ስትቦርቅ አድጋለች። ገበሬዎቹ እናት አባቷ፣ በሷ ደስታ ሰላም አላቸው። ልጃቸው ፈገግ ስትል ውስጣቸው ሰላም ያገኛል። ሁሌም ዓለሟን አይተው የልባቸውን መሙላት ይሻሉ።
ትንሽዋ መሰረት ከወላጆቿ ፈቃድ አትወጣም። እነሱ ያሏትን ትሰማለች፤ በትዕዛዛቸው ታድራለች። እሷ እንደ ባልንጀሮቿ ትምህርትቤት ልትሄድ ዕድል የላትም። ከቤት ውላ እንደአቅሟ የተሰጣትን ልትሰራ ግድ ሆኗል።
ዋል አደር ሲል ልጅነቷን፣ ቀንበጥነቷን ያዩ ዓይኖች በትኩረት ይከተሏት ያዙ ። ስትወጣ ስትገባ እየቃኙ ለብዙ የሚያስቧት በረከቱ። ይህ አጋጣሚ ከአንድ እውነት ሊያደርሳት ግድ ሆነ። ከእሷ ዝምድናን ከሚሹት መሀል አንድ ሰው ወላጇን ለጋብቻ ጠየቀ። መሰረት ለታ ገና ቀንበጥ ልጅ ናት። እናት አባት ግን ‹‹አይሆንም፣እምቢኝ››አላሉም። ጋብቻውን በይሁንታ ተቀበሉ ።
ሙሽሪት ልመጂ…
ከወላጆቿ ቤት በወግ ማዕረግ ተድራ የወጣችው ጉብል የትዳርን ሀሁ ጀመረች። ልጅ ብትሆንም የኑሮ ወጉ አልጠፋትም። ጎጇዋን ልታቀና፤ ህይወቷን ልትመራ ደፋ ቀና ማለት ያዘች። ባልና ሚስት በመጀመሪያዎቹ ወራት መልካም የሚባል ጊዜ አሳለፉ።
መሰረት በወላጆቿ እንጂ በእሷ ፍላጎት አልተዳረችም። የገባችበትን ሕይወት ግን ባትወደውም እየኖረችው ነው። ባለቤቷ በመልካም ገበሬነቱ ይታወቃል። ይህ ማንነቱ ግን ለእሷ ክብር አልሆነም። ውሎ አድሮ ፀባዩ ከበዳት። ወጥቶ በተመለሰ ቁጥር ሞቅ ብሎት ይገባል። ይህ ባህርይው ከእሷ አላስማማውም። በቤቱ ጭቅጭቅና ንትርክ ሰፈነ ።
ሰላም ያጣው ጎጆ መፍትሄ አላገኘም። አባወራው ከሞቅታ አልፎ ሰክሮ መንገዳገድ ጀመረ። እንዲህ በሆነ ቁጥር ከሚስቱ መጋጨት ፣ መጣላቱ ቀጠለ። የምትለውን መስማት መቀበል አይፈልግምና ጭቅጭቁ ቅያሜ ፈጠረ ቂም በቀል ቋጠረ።
መሰረት ትዳሩ አልተመቻትም። ባለቤቷ እየሰከረ እያሰቃያት ነው። የእሷ ብቻ ‹‹ለቤት ለትዳሬ›› ማለት መፍትሄ አላመጣም። ባሏ በሰከረ ጊዜ በክፉ ንግግሩ ያስቀይማታል። ታዝናለች፣ ታለቅሳለች። ስለእሷ ሆኖ መላ የሚላት፣ የሚረዳት፣ ወዳጅ ዘመድ ጎኗ የለም።
አንድ ቀን መሰረት እጅግ ያዘነችበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ባለቤቷ ከብቶቹን በሙሉ ሸጦ ብር መቀበሉን አወቀች። ውስጧ ደነዘዘ፣ አንገቷን ደፍታ አዘነች፤ የአሁኑ ለቅሶዋ ግን የቀድሞው አይነት አልነበረም። ሀዘኗ ከፋ፣ ዕንባዋ መሪር ሆነ።
የባልና ሚስቱ ከብቶች የጋራ ሀብት ናቸው። ጥማድ በሬዎቹ ያርሳሉ። ጥገት ላሞቹ ይታለባሉ። አሁን ግን በቤቱ ይህ አይነት ታሪክ አይቀጥልም፤ የጎጇቸውን ህልውና የጎደለ፣ የጨለመ ይመስላል። መሰረት ከዚህ በኋላ ‹‹ኑሮዬ ፣ቤቴ የምትለው ታሪክ የለም።
አሁን የባልና ሚስቱ ትዳር ንፋስ ገብቶታል። ወይዘሮዋ አብራው ላለመሆን ቆርጣለች። ‹‹ባሏን ፈታ ትዳሯን አፍርሳ ወላጆቿ ቤት ገባች›› መባልን ደግሞ አትሻም። እንዲያም ሆኖ ልቧ አርቆ እየተጓዘ፤ ውስጧ ብዙ እያሰበ ነው።
መሰረት ተወልዳ ያደገችበትን የጅዳ ቀበሌና ቀዬ ለቃ ልትወጣ ቆረጠች። ሀሳቧ እንዲሳካ ማንም ሳያያት ጠፍታ፣ ተደብቃ መሆን አለበት። ያሳበችው አልቀረም። አንድ ማለዳ አካባቢውን ትታ ርቃ ተጓዘች። ያያት የተከተላት የለም። ‹‹እፎይ›› አለች ።
አዲስ አበባ…
አሁን ሳታስበው ልትኖረው የተገደደችበትን ህይወት ልትጀምር ነው። እግሮቿ መሀል አዲስ አበባ አድርሰዋታል። መሰረት ለአገሩ ባዳ ፣ ለሰው እንግዳ ነች። ዘመድ ወዳጅ ትለው የቅርብ ሰው አታውቅም። ለመኖር፣ ህይወትን ለመቀጠል ጉልበቷን፣ ላቧን ልትከፍል ግድ ነው።
መሰረትን የቀረቧት የባዳ ዘመዶች ለእሷ የሚሆን ስራ ፈለጉላት። ቤት ኪራይ ሳትል ውላ የምታድርበት ስራ ተገኘ። ከሰው ቤት መቀጠር ምርጫዋ የሆነው ወይዘሮ በሆነው ሁሉ አልከፋትም። ትናንት ቤት፣ ንብረት፣ ትዳርና ወግ ነበራት። ዛሬ ደግሞ ዝቅ ብላ ፣ ልታድር ፣ በላብ በወዟ ልትኖር ግድ ብሏል። የአዲስ አበባን ህይወት በሰው ቤት ስራ የጀመረችው ወይዘሮ ስለ ትናንት መርሳት ጀመረች። ዛሬን እየኖረች፣ ነገዋን ማሰብ፣ ማቀድ ስትይዝ አዲስ ህይወትን ተላመደች።
ዓመታትን በሰው ቤት ሥራ …
የአዲስ አበባ ህይወት ለመሰረት እምብዛም አልከበደም። ባህርይዋ መልካም ነውና ከብዙዎች ተግባብታለች። ተቀጥራ በምትሰራበት ቤት የወር ደመወዝ አላት። የሚከፈላትን ቆጥባ ያሻትን ታደርጋለች። መሰረት እንደዋዛ ጊዜያቶችን ቆጠረች፣ ስምንት ዓመታትን በሰው ቤት ተቀጥራ አሳለፈች።
የሰው ቤት ስራ መልከ ብዙ ነው። አንዱ ጥሩ ሲሆን ሌላው ይከፋል። ደመወዝ በአግባቡ የሚከፍል እንዳለ፣ ጉልበት የሚበዘብዝ በነጻ የሚያሰራ አይጠፋም። አሁን መሰረት ዓመታትን በሰው ቤት ስራ ከፍላለች። ውስጧ ‹‹በሰው ቤት ስራ፣ በብቸኝነት›› እስከ መቼ እያለ ያስጨንቃታል።
የእህል ውሃ ነገር…
አሁን መሰረት ከአንድ ሰው ጋር ደጋግማ እየታየች ነው። ዓመታትን በብቸኝነት መኖሯ አጋር እንድትሻ አድርጓታል። ከሰው ቤት ስራ ወጥታ ትዳር ብትይዝ ጎጆ ብትቀልስ ፈቃዷ ነው። ይህ እንዲሆን ውስጧ ከተመኘ ቆይቷል።
መሰረት የተዋወቀችው ሰው መልካምነቱን ታውቃለች። ሁሌም ስለእሷ ያስባል። ስለነገ ህይወታቸው ያቅዳል። ሃሳቧን አክባሪ ነውና ተጋብተው እንዲኖሩ ይሁንታውን ሰጥቷል። መሰረት አሁን ደስተኛ ነች። የፈረሰው ጎጆዋ የተበተነው ትዳሯ መልካም ሆኖ ሊታደስ ነው። ከልቧ ፈጣሪዋን አመሰገነች።
ሦስት ጉልቻ…
መሰረት ለትዳር ከመረጠችው አጋሯ ጋር ኑሮን ጀመረች። ባለቤቷ ባህርይው አልተለወጠም። ትናንት እንደምታውቀው በመልካምነቱ ቀጠለ። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ጎጇቸው በልጅ ስጦታ ተባረከ። የጥንዶቹ ህይወት፣ መከባበር፣ መተሳሰብ የሞላበት ነው። ‹‹አንቺ ትብሽ፣ አንተ›› ይሉት እውነት በእነሱ ቤት ጎልቶ ይታያል። መሰረት የትናንት ሕይወቷን ረሳች። ስለዛሬው ደግሞ ፈጣሪዋን አመሰገነች።
የመጀመሪያ ልጃቸው ለቤቱ የፍቅር ብርሀን ሆናለች። እናት አባት ሁሌም ስለእሷ ህይወት ያስባሉ። ነገ ተምራ፣ቁምነገር ደርሳ የሚያዩበት ግዜ ይናፍቃቸዋል። አባወራው ጠንካራ ጎልማሳ ነው። ግንበኝነቱን ጥበቃውን አፈራርቆ ይሰራል። ብርቱዋ ወይዘሮም ስለቤቷ አታርፍም። የባሏ ክንድ ሆና ትዳሯን ትመራለች።
የመጀመሪያዋ ልጅ ጥቂት ማደግ ስትጀምር መሰረት ነፍሰጡር መሆኗን አወቀች። አባወራው ተደሰተ ። ሁለቱም ልጃቸው እህት አልያም ወንድም ብታገኝ አይጠሉም። ቤተሰባቸው ቢበራከት፣ቤታቸው በልጅ በረከት ቢሞላ ደስ ይላቸዋል።
መሰረት የባሏን ሰላም ውሎ መግባት ትናፍቃለች፡ስራ ሲበዛበት እንዳይደክመው፣እንዳይበሳጭ ማድረግ የእሷ ግዴታ ነው። አባወራው ቤቱ ሲደርስ በልጁ ሳቅ ሩጫ ፣በሚስቱ ደስታ ፈገግታ ይረካል። የጥንዶቹ የትዳር ህይወት መልካም እንደሆነ ቀጥሏል።
ከቀናት በአንዱ
አንድ ቀን የመሰረት ባለቤት ከስራው አቋርጦ ቤቱ ደረሰ። ወይዘሮዋ የባለቤቷን ገጽታ አስተዋለች። ፍጹም ጤነኛ አይመስልም። እንደደነገጠች ምክንያቱን ጠየቀች ‹አሞኛል››ከማለት የዘለለ አላስረዳትም። ለሊቱ በህመም፣ በጭንቀት አለፈ። ማግስቱን አባወራው ተነስቶ ለመቆም ለመሄድ ሞከረ። አልቻለም።
የአባወራው ቀናት ያስቆጠረ ሕመም ያለአንዳች ለውጥ አብሮት ከረመ። ሁኔታውን ያዩ አንዳንዶች ድንገቴ ሽውታ ምች ሆኖበት እንደጎዳው ተናገሩ ። ሌሎች ደግሞ ከባድ ብርድ መሆኑን ገመቱ። እንዲያም ሆኖ መፍትሄ ሳይገኝ ከአልጋው መዋሉ ቀጠለ። ይህን ያስተዋሉ የቅርብ ዘመዶች ወዳጅ ጓደኛ መድኃኒት አቅምሶታል ብለው ደመደሙ።
ይህን ሁሉ የምትሰማው ነፍሰጡሯ ወይዘሮ ስለመፍትሄው ጨነቃት። ባለቤቷ ስለሕመሙ ብዙ ቢገመትም መድኃኒቱን አላገኘም። ችግሩ እየባሰ፣እየጨመረ ነው። አሁን ወደ ህክምና ሊሄድ ግድ ሆናል። ከሆስፒታል ሲወስዱት አልጋ ይዞ መታከም እንዳለበት ተነገረው።
በድንገት አልጋ የያዘው አባወራ ለአስራ አምስት ቀናት በጽኑ ሕመም ቆየ ። አንድ ቀን ግን ለመኖር ሲታገልበት ከከረመው ችግር ማለፍ ተሳነው። ዓይኖቹ ላይ ከፈቱ ተከደኑ ። ዳግም ካሸለበበት አልነቃም። ይህ ክፉ እውነት ከእሱ ጋር ብዙ ላሰበችው ወይዘሮ ድንገቴ ስብራት ሆነ።
መሰረት ሁለተኛ ልጇን የስድስት ወር ነፍሰጡር ናት። የመጀመሪያ ልጃቸውም ነፍስ ያላወቀች ጨቅላ ነች። ባሏን ቀብራ ሀዘን ስትቀመጥ ወደፊት ወደኋላ በጭንቀት እየናወዘች ብዙ አሰበች። አሁን ከልብ የምትወደውን፣የሚጨነቅ፣ የሚያስብላትን ሰው ሞት ነጥቋታል።
ምን ይዛ ምን እንደምትጨብጥ ግራ ገባት ። ከመቼውም በላይ ብቸኝነት፣ ባይተዋርነት ዘልቆ ተሰማት። በሆዷ ያለው አዲስ እንግዳ ‹‹መጣሁ›› እያለ ያስጨንቃት ይዟል።
አዲስ ሕይወት…
አሁን ሀዘንተኛዋ መሰረት ሦስት ራሷን ከችግር ወድቃለች። የምትከፍለው የቤት ኪራይ፣የምትበላው በቂ ምግብ ከእጇ የለም። ችግሯን የተረዱ አንዳንዶች ቀረብ ብለው ያይዋታል። ከእነሱ መሀል ያላቸውን የሚያካፍሏት ብዙ ናቸው። ሳሙና፣ዘይት የሚገዙላት፣ ስኳር ዱቄት የሚቋጥሩላት አልጠፉም።
ዋል አደር ሲል መሰረት ስለቤት ኪራይ ማሰብ መጨነቅ ሕመሟ ሆነ። ያላትን ከፍላ ወር እስኪሞላ ያለው ጊዜ ፈተናዋን ያስቆጥራታል። ከምትኖርበት ካራ አካባቢ የምትከፍለው የቤት ኪራይ አቅሟን የሚመጥን አይደለም። ወጣ ማለቱ እንደሚበጅ አስባ ከሌሎች ጋር መከረች።
ችግር ደጋግሞ የጎበኛት ወይዘሮ ሁለት ልጆቿን ይዛ ‹‹ጣፎ›› ወደሚባል አካባቢ አቀናች። በዚህ ስፍራ ያገኘችው መኖሪያ በክፍያው እስካሁን ከቆየችበት የተሻለ ነው። ልጆቿን አቅምሳ የተረፋትን ለመክፈል ጥቂት ዕድል ይሰጣታል። ደግነቱ በዚህ ሁኔታ ብዙ አልቆየችም። ንብረት ጠባቂ ሆና በቤቱ እንድትኖር ተመቻቸላት።
ዛሬ ላይ መሰረት በየቤቱ እየዞረች በጉልበት ስራ ታድራለች፤በመንደሩ የሚጋገር እንጀራ፣የሚታጠብ ልብስ የሚቆላ አሻሮና እንኩሮ ከእሷ አያልፍም። የራሷም ሆኑ የባለቤቷ ዘመዶች እንዴት ነሽ ብለዋት አያውቁም። ችግሯን የሚረዱ ልበ መልካሞች ግን ሁሌም ከጎኗ ናቸው። ከባሏ ሞት በኋላ ያገኘቻትኝ ልጇን ‹‹ህይወት››ስትል ሰይማታለች።
ህይወት ለእሷ ብዙ ነገሯ ነች። የትዳር አጋሯ የመጨረሻ ስጦታ፣ የበርካታ ችግሮቿ ማስታወሻ ። የእሷ ማንነት ያለፈችውን፣ ያለችበትንና የወደፊቱን ጭምር ቁልጭ አድርጎ ያሳያታል።
መሰረት ሁለቱም ልጆቿ ተምረው ቁምነገር እንዲደርሱ ትሻለች። እሷ በልጅነቷ የተነጠቀችውን መልካም ዕድሎች በእነሱ ህይወት እንዲደገም አትፈልግም፡፤ ባለችበት አካባቢ የልጆቿ እኩዮች ደብተር ይዘው ተምረው ሲመለሱ ማየቷ አልቀረም። የእሷን ልጆች እንደእነሱ አድርጎ ለማስተማር እጅ ያጥራታል።
በየጊዜው ሲያልፉ ፣ ሲያገድሙ የምታያቸው ልጆች በአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች ተከፍሎላቸው የሚማሩ ናቸው ። ስለተማሪዎቹ ሁሌም ደስ ይላታል። ልጆቿን ግን እንደእነሱ አድርጋ ማስተማር፣የትምህርት ቁሳቁስን ማሟላት አይቻላትም። በየቀኑ በዓይኖቿ እየሸኘች ከመቀበል ውጪምርጫ ካጣች ቆይታለች።
መሰረት አንዳንዴ ሆድ ብሷት ታለቅሳለች። የባሏ ሞት፣የእሷ ድካምና የልጆቿ እንግልት ሁሌም እንዳሳሰባት ነው። አንዳንዴ ደግሞ ዕንባዋን የሚያብሱ ፣ቁስሏን የሚያክሙ ልበ ቀናዎች ከጎኗ አይጠፉም።
ህይወትና ትምህርት…
ዛሬ የህይወት የትምህርት ጉዳይ መፍትሄ አግኝቷል። በአካባቢው የሚገኝ ‹ኦርቶተ›› የተባለ አካዳሚ ልጇን እንደራሱ ልጆች ተቀብሎ በነጻ እያስተማራላት ነው። ዛሬ ህይወት ከባልንጀሮቿ እኩል በትምህርት ገበታ ተቀምጣለች። የአፀደ ህጻናት ቆይታዋን አጠናቃም ወደ አንደኛ ክፍል ለመሻገር እየተዘጋጀች ነው።
የኦርቶተ አካዳሚ እንደእሷ ችግር ለጎበኛቸው እናቶች ዕንባን የሚያብስ አጋር ነው። ልጆች ተምረው ነገ ሀገር እንደሚገነቡ፣ወገኖቻቸውን እንደሚያግዙ ያውቃል። በተለያዩ ችግሮች ይህን ዕድል ለተነፈጉ ተማሪዎች በሩ ክፍት ነው። መሰረት ዛሬ በልጇ መልካም ዕድል ዕንባዋ ታብሷል። ፈገግታዋ ተመልሷል።
መሰረት አሁን ላይ የረባ ስራ የላትም። ለልጆቿ መኖር ግን የማትሆነው፣የማትከፍለው ዋጋው የለም። በየቤቱ አዛባ መዛቅ ፣የጉልበት ስራን መፈለግ ግዴታዋ ነው። ህይወት እንደእኩዮቿ ተምራ ካሰበችው ብትደርስ ደስ ይላታል። አንዳንዴ ስራ ባለበት ቦታ ይዛት ትሄዳለች። ልጇ የዕለት ድካሟን ባየች ጊዜ ሸክሟን ለማቅለል፣ክንዷ ለመሆን ብዙ ትመኛለች። ስታድግ፣ስትማር ፣በዚህ ስራ እንደማጥቀጥል ደጋግማ ስትነግራት በተለየ መተማመን ነው።
መሰረት ጠንካራና ብርቱ እናት ነች። ልጆቿን ለማሳደግ ያልሆነችው የለም። ብዙ ዋጋ የከፈለችባት ህይወት አድጋ ተምራ ቁምነገር እንድትደርስ ትመኛለች። ዛሬ እናት መሰረት ስለህይወት ማንነት ዙሪያዋን ዘብ ቆማለች።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም