አንዳንዴ የት ይደርሳል ያላችሁት የፍቅር ግንኙነት፣ ጓደኝነት፣ ትዳር ወይም ቢዝነስ ባለመግባባት ምክንያት በአጭር ሲቀጭ ታያላችሁ። ታዲያ እንዴት ነው ራሳችንን ተግባቢ የምናደርገው? ከሰዎች ጋር ነው የምንኖረው። እኛ ሰዎች ደግሞ እንደ ዓይን ቀለማችን ፀባያችንም ይለያያል። አንዳንድ ሰው ዝምተኛ ነው። አንዳንድ ሰው ነገረኛ ነው። አንዳንድ ሰው ሰላማዊ ነው። አንዳንድ ሰው ስሜታዊ ነው። አንዳንድ ሰው ቁጡ ነው። እንዳንድ ሰው ረጋ ያለና ታጋሽ ነው። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች በዙሪያችን አሉ። ታዲያ እንዴት ነው የምንግባባው? ሥራው በደምብ እንዲሰራ፣ የፍቅር ግንኙነቱ፣ ትዳሩ፣ ጓደኝነቱ ጥሩ እንዲሆን ተግባቢ መሆን አለብን። እንዴት ነው በአጭር ጊዜ ሰዎችን ተግባብተንና ተረድተን የልባችንን እውነት የምናሳያቸው? የምንነግራቸው ? የምናሳምናቸው እንዴት ነው?
የመጀመሪያው ሰዎችን ጠንቅቆ ማወቅ ነው። ትዳሮች የሚፈርሱት፣ የፍቅር ግንኙነቶች የሚበላሹት፣ ሰዎች እየተዋደዱ የሚለያዩት አንድ መሠረታዊ ነገር ስለማያውቁ ነው። የሰው ልጅ ሰውን የሚያምነው ወይም የሚግባባው በሶስት መንገድ ነው። አንደኛ በመስማት ነው። ሁለተኛ በሚያየው ነገር ነው። ሶስተኛ በስሜት ንክኪ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ከአንድ ሰው ጋር ስትግባባ እሱ የሚያምንህ በምትነግረው ነገር ሊሆን ይችላል። አንተ እያሳየኸው እርሱ ስትነግረው ሊሆን ይችላል የሚሰማህ። ወይ ደግሞ አንተ እያስረዳኸውና እየነገርከው ነው ግን እሱ አይቶ ይሆናል ማመን የሚፈልገው።
ለምሳሌ ሴቶች በመስማት ነው ፍቅር የሚይዛቸው ይባላል። በቃ በጆሯቸው በሚገባው ነገር። ስለዛ ሰው በሚሰሙትና በሚነግሯቸው ነገር በፍቅር ይወድቃሉ። ወንዶች ደግሞ በሚያዩት ነገር በፍቅር ይወድቃሉ ይባላል። ሁኔታዋንና መልኳን አይተዋት ሊማረኩ ይችላሉ። ስለዚህ ወንዶች በሚያዩት፤ ሴቶች በሚሰሙት ነገር በፍቅር ይወድቃሉ ይባላል። አሁን አንተ የምትግባባው ሰው የሚያመዝነው በየትኛው መልኩ ነው? የሚያምንህ ሲያይ ነው፣ በምትነግረው ነው ወይስ በስሜት ነው?
ለምሳሌ አንዳንድ አለቆች አርፍዳችሁ ስትመጡ ምክንያቱን ስትነግሯቸው አያምኗችሁም። መንገዱ ተዘጋግቶ ነው ያረፍደኩት ስትሏቸው አይሰሟችሁም። ‹‹አንተን አላምንህም›› ይሏችኋል። ግን ደግሞ እንዳጋጣሚ ስታረፍዱ ስልካችሁን አውጥታችሁ ፎቶ ብታነሱና ለአለቃችሁ ‹‹አየኸው መንገዱ እንዴት እንደተዘጋጋ›› ብትሉት ከምትነግሩት ይልቅ ፎቶውን አይቶ ‹‹አንተ እውነትህን ነው ተዘጋግቶ ነበር። አይ እንደውም ጥሩ ሰዓት ደርሰሃል›› ብሎ ሊረዳህ ይችላል። አያችሁ አንዳንድ ሰው ስትነግሩት አይሰማም። ስታሳዩት ነው የሚሰማው። ስለዚህ አንተ ከዛ ሰው ጋር መግባባት ከፈለክ በምን መልኩ ነው ቶሎ የሚረዳህ?፣ ስሜቱን ፍንቅል የሚያደርገው?፣ ስትነግረው ነው? ወይስ ሲያይ ነው? ወይስ በስሜት ስትግባባው ነው?
ለምሳሌ አንዳንድ አስቂኝ የፍቅር ግንኙነቶች አሉ። በጣም ይዋደዳሉ እኮ! ግን እንዲለያዩ ብዙ ምክንያት አላቸው። ለምሳሌ እሷ ፍቅሩን እንዲገልፅላት የምትፈልገው እንዲነግራት ነው። በምትሰማው ነው ፍቅር ላይ የምትወድቀው። እርሱ ግን ሰርፕራይዝ ያደርጋታል። እራት ይጋብዛታል። የሆነ ነገር ገዝቶ ይመጣል። ፍቅሩን በተግባር ያሳያታል። ግን አይነግራትም። እወድሻለሁ፤ አፈቅርሻለሁ አይላትም። ላንቺ ያለኝ ስሜት እኮ አልገባሽም እያለ በአፉ አይነግራትም። እሷ ደግሞ እንዲነግራት ትፈልጋለች። ስለዚህ የሚወዳት አይመስላትም። ‹‹ውይ አንተ እቃ ነው የምትገዛው፤ ምን እንዲህ ነው የምታርገው፣ እንደምትወደኝ እኔ አላውቅም›› ትለዋለች። በዚህ ምክንያት ይጣላሉ። አይስማሙም። አያችሁ እሷ መስማት ነዋ የምትፈልገው።
አንዳንድ ትዳር ደግሞ አለ እሷ የምትፈልገው በተግባር እንዲያሳያት ነው። እሱ ደግሞ ይነግራታል። ‹‹እኔ እኮ በጣም ነው የምወድሽ›› ይላታል። በአጭሩ ጅንጀና ላይ ጎበዝ ነው። በስልክ አጭር መልዕክት ይልክላታል። ይደውልላታል። ፍቅሩን ይነግራታል። እሷ ግን ከእርሱ የምትፈልገው ፍቅሩን በተግባር እንዲያሳያት ነው። ወይ ወስዶ እንዲጋብዛት፤ ወይ ደግሞ ፊልም እንዲያዩ አልያም ሰርፕራይዝ እንዲያደርጋት ሊሆን ይችላል የምትፈልገው። እርሱ ደግሞ በንግግር ነው ተግባሩ። ችግሩ እእህ ጋር ነው። አያችሁ አልተግባቡም ማለት ነው። ግን እኮ ሊዋደዱ ይችላሉ። እሷ ‹‹አይ እርሱ አይረዳኝም›› ትላለች። ለምን? እርሷ የምትፈልገው ተግባሩን ነበር።
አንዳንዶች ደግሞ ስሜት የሚወዱ ናቸው። መተህ እቅፍ እንድታደርጋቸው፣ እንድትግባባቸው፣ በስሜት እንድትረዳቸው ይፈልጋሉ። አንዳንድ ሰው ደግሞ የሆነ ነገር ማድረግና መንገር እንድትወደው የሚያደርገው ይመስለዋል። አለመግባባት ነው። ስለዚህ ሰዎች በምን ዓይነት መንገድ ነው የሚረዱን የሚለውን ማወቅ በጣም ወሳኝ ነው። አንተ ስትሰማው ነው ደስ የሚለው፣ ስትነግረው ነው፣ ስታሳየው ነው፣ በስሜት ነው በቃ! ይህን መረዳት በጣም ወሳኝ ነው።
ሁለተኛው ሰዎችን እንድናሳምንና ከሰዎች ጋር እንድንግባባ የሚያደርገን የራስን ጥቅም አለማስቀደም ነው። ለምሳሌ አንድ ነጋዴ መንገድ ላይ ቆሞ እስኪ ይችን እቃ ግዙኝ፤ እንደው ምሳ መብያዬ ናት ቢል ማንም ዞር ብሎ አያየውም። ዘመናዊ ልመና ብለን ነው ጥለነው የምንሄደው። ምክንያቱም ምሳ መብያዬ ስላለ ‹‹እኔ እቃ የምገዛው እሱን ምሳ ላጋብዝ ነው›› ብለን ነው የምንሄደው። እቃው ቢያስፈልገን ራሱ ከዛ ሰው አንገዛውም። ምንም ነገር የምናደርገው ለሰው ብለን አይደለም። ለራሳችን ነው። እቃ ስንገዛ ለነጋዴው አስበን አይደለም።
እቃ ብቻ አይደለም ሃሳቦች ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ለእኛ ከጠቀመን ነው የምናደርገው። ለዛ ሰው ብለን የምናደርገው ነገር የለም። ወዳጄ! ሃሳብህን የሚቀበሉህ ለአንተ ብለው አይደለም። እነርሱ ካመኑበት ነው። ስለዚህ አንተ የእነሱን ስሜት፣ ሃሳብ፣ ጥቅም ወይም ፍላጎት ቅድሚያ ሰጥተህ ካስተናገድካቸው ምንም ነገር ብትጠይቃቸው፣ ምንም ነገር ብታስቸግራቸው ይስማማሉ። ይህ ነው ሰዎችን የማሳመን ጥበብ ማለት። የሚፈልጉትን ቀድመህ ትሰጣቸዋለህ። በመጨረሻ አንተ የምትፈልገውን ትወስዳለህ። ስለዚህ ለራስህ ቅድሚያ አትስጥ ለእነርሱ ፍላጎት ቅድሚያ ስጥ።
ሶስተኛው ተግባቢና አሳማኝ የሚያደርገን መንገድ ጊዜና ሁኔታ ላይ ብልህ መሆን ነው። ለምሳሌ ክረምት ላይ ቲ ሸርት አትሸጡም። ወይም የቲሸርት ገበያ ይቀዘቅዛል። ምክንያቱም ብርድ ነው፤ ማነው ቲ ሸርት የሚያደርገው? አያችሁ! ሰዎች ፊታቸው ክረምት ሆኖ ድብርት ላይ ሆነው መጥፎ ስሜት ላይ ሆነው አንተ የፈለከውን ነገር ብትነግራቸው አይቀበሉህም። አየህ አንድ ነገር ለማድረግ፤ ሰዎች እንዲሰሙህ ጊዜና ሁኔታዎችን መረዳት አለብህ። በትክክለኛው ቦታ፣ ሁኔታና ጊዜ ላይ መገኘት አለብህ። አንድ ነገር ስትናገር ያ ሰው ያለበት የስሜት ደረጃ ወይም ሁኔታ በጣም ወሳኝ ነው። በተለይ ደስ ብሎት ተረጋግቶ ከሆነ ምንም ብትነግረው ሊቀበልህ፣ ሊሰማህና ሊያምንህ ይችላል።
ግን ስሜቱን አይተህ ያለበት ሁኔታ ጥሩ ካልሆነ ከቻልክ ከድብርቱ አውጥተህ፣ አረጋግተኸው፣ ጭንቀቱን አራግፈህለት የፈለከውን ነገር ብትነግረው ሊያምንህ ይችላል። ነገር ግን በዛ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አንድ ነገር ብታደርግ አይቀበልህም። ስለዚህ ብልጥ ከሆንክ ጊዜና ሁኔታ ላይ ብልህ ወይም ጥሩ መሆን አለብህ። ያኔ ተግባቢ ያደርግሃል። ያኔ ሰዎችን ማሳመን ላንተ ቀላል ይሆናል። ጊዜና ሁኔታን በደንብ መጠበቅ አለብህ።
አራተኛው ደግሞ ሁሌም ቢሆን ስሜትን መቆጣጠር መቻል ነው። አንድ ሰው በጣም ተግባቢና ሰዎችን ማሳመን የሚፈልግ ከሆነ የራሱን ስሜት መቆጣጠር አለበት። አብረሃቸው የምትኖራቸው ሰዎች ፍቅረኛህ፣ ጓደኛህ ወይ የትዳር አጋርህ ወይ አብሮህ የሚሰራህ ሰው በጣም ስሜታዊና ቁጡ ሊሆን ይችላል። ያንን ሰው የምታሳምነው፣ የምትግባባው ግን እንደሱ ቁጡ ሆነህ አይደለም። ስሜትህን ተቆጣጥረህ ነው።
ለምሳሌ ሴቶች በጣም ሲናደዱ ስለችግሩ ማውራት ይፈልጋሉ። ወንዶች ደግሞ ሲበሳጩ ልጉም ነው የሚሉት። ፀጥ ነው የሚሉት። አይምሯቸው ውስጥ ነው የሚያሰላስሉት። ሴቶች ግን ያወራሉ። ለምሳሌ አጠገብህ ያለችው ሴት ስትናደድ ዝም ብለህ ስማት። ያናደዳትን ያበሳጫትን ስታብራራ ‹‹እንዲህ ሆነ እንዴ አሃ!›› እያልክ ዝም ብለህ ስማት። መፍትሔ አትንገራት። እሷ ስታወራ እኩል አታውራ። ዝም ብለህ አድምጣት። ጆሮህን ነው የምትፈልገው። ምን መሰለህ መፍትሔውን መጨረሻ ላይ ልትነግራት ትችላለህ። አድምጠሃት ስትጨርስ ልክ እሷ ስትረጋጋ መፍትሔውን ብትነግራት በደንብ ታደምጥሃለች። ሴት ልጅ ምክር ትሰማለች። ግን የምትሰማህ እሷ ያወራችውን ከጨረሰች በኋላ ነው።
ወንድ ልጅ ደግሞ ሲበሳጭ ፀጥ ይላል። ‹‹ምን ሆነህ ነው? ምን ተፈጠረ?›› ማለት የለብሽም። ዝም ብለሽ ዝምታውን አስጨርሺው። በቃ ዝም ብለሽ እይው። ንዴቱን ውጦ አስልቶ ሲጨርስ ራሱ ያወራሻል። ‹‹ዛሬ እንዲህ ተፈጥሮ እኮ ነው የተበሳጨሁት›› ይልሻል። አንቺ ሳትጠይቂው፡ ያለበለዚያ ምን ሆነህ ብለሽ የምትጨቀጭቂው ከሆነ ይባስ ይናደድና ሌላ ነገር መዞ ልትጣሉ ትችላላችሁ። እስከ መጨረሻው ልትለያዩም ትችላላችሁ። ስለዚህ ከተናደደ ዝም ብለሽ አድምጪው። ወይ ዝም በይው። ማውራት ሲጀምር አድምጪው። ከዛ ሰምተሸ ስትጨርሺ አድንቂው። ‹‹አንተ እኮ ይሄን መፍታት አቅቶህ አይደለም ዝም ብለህ ነው የተናደድከው›› ብለሽ አበረታቺው። እንዳትመክሪው! ወንድ ልጅ ምክር አይወድም። አድናቆት ነው የሚፈልገው።
አምስተኛው መፍትሔ የሚያወሩትን መድገም ነው። ከሰዎች ጋር መግባባትና ልታሳምናቸው ከፈለክ የሚያወሩትን ስማቸውና መሃል ላይ አስቁመህ ‹‹ግን ገብቶኛል እንዲዚህ ነው ያልከው መሰለኝ አይደል›› ብለህ ቃል በቃል ያ ሰው የነገረህን ነገር ድገምለት። ደስ ይለዋል። እየተከታተልከው እንደሆነ ይገባዋል። ‹‹አዎ! እኮ ባይገርምህ›› እያለ የልቡን ሁሉ ይነግርሃል። ለምን? እያደመጥከው ነዋ! የልቡን እውነት እየተረዳህለት ነው።
እዚህ ጋር ሁለት ጥቅም ታገኛለህ። አንደኛ ከዛ ሰው ጋር እስከ ጥግ ድረስ ትግባባለህ። ለምን እያደመጥከው ነው። በዛ ላይ ደግሞ የነገረህን እየከለስክለት ነው። ሁለተኛ ያ ሰው አውርቶ ሲጨርስ የፈለከውን ነገር ብጠይቀው እሺ ይልሃል። ለምን? አድምጠኸዋላ! ባለውለታው ነህ። ሰዎች እንደ መደመጥ የሚያስደስታቸው ነገር የለም። ስለዚህ አድምጠኸው ስትጨርስ የፈለከውን ብታዘው የፈለከውን ሁሉ ያደርግልሃል።
ስድስተኛውና የመጨረሻው መፍትሔ ለቃል መታመን ነው። አንዳንዴ ሰዎች ንግግርህ ብቻ ላያሳምናቸው ይችላል። በተግባር ማየት ይፈልጋሉ። ዓለም ላይ በጣም የምናደንቃቸው መሪዎች ለተግባራቸው የታመኑ ናቸው። ለዛ ነው በጣም የምናከብራቸው፤ የምናደንቃቸው። አንተም አንዳንዴ በዙሪያህ ያሉ ሰዎች ንግግርህን ሰምተው ላይቀበሉህ፣ ላይረዱህ፣ ላይሙህ ይችላሉ። በቃ! ‹‹እኔ ሰዎችን አላሳምንም ማለት ነው›› አትበል። አንተ እነሱን የምታሰምነው በንግግርህ አይደለም። በተግባርህ ነው።
አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሊንቁህ ይችላሉ። አንተን መቀበል ላይፈልጉ ይችላሉ። ቦታ ላይሰጡህ፤ ያንተ ነገር ላይዋጥላቸው ይችላል። እየነገርካቸው ላይሰሙህ ይችላሉ። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች የሚሰሙህ በድርጊትህ ነው። ለእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ራስህን ቀይረህ በተግባር አሳያቸው። ለአንዳንድ ሰዎች ጣፋጩ በቀል በእነርሱ ፊት የሚያስደነግጥ ስኬትን መጎናፀፍ ነው። ራስህን ለውጠህ ሲያዩ ያኔ ከንግግርህ በላይ ተግባርህ ያስተምራቸዋል። ስለዚህ ለቃልህ ታመን። ያልከውን ነገር በሕይወትህ ግለጥ። አየህ አንዳንዴ ንግግርህ ብቻ አያሳምንም። ተግባርህ ማሳመን አለበት።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም