‹‹አትቀጡብኝ›› ልመና!

ባለፈው እሮብ ነው። አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ኮንዶሚኒያም አካባቢ ከአንድ ምግብ ቤት ምሳ ልበላ ተቀምጫለሁ። የአዲስ አበባ ፖሊስ መለያ ያለው አንድ ተሽከርካሪ የድምፅ ማጉያ (ማይክራፎን) ተገጥሞለት ልመና መሰል ማስጠንቀቂያ እየሰጠ ወዳለሁበት ቦታ ተቃረበ። የዚህ አይነት ድምፅ በተደጋጋሚ የምሰማው ስለሆነ ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር።

በድንገት ግን ካለሁበት ምግብ ቤት ውስጥ ያሉት ሰዎች መተረማመስ ጀመሩ። የምግብ ቤቱ ባለቤት ትመስለኛለች ‹‹ኧረ ቶሎ በሉ ሳይፈቱባችሁ!›› ትላለች። አንዳንድ ደንበኞችም ‹‹ሊፈቱባችሁ ነው ተነሱ!›› ይላሉ። ይህኔ የተሽከርካሪዎች ባለቤቶች (አሽከርካሪዎች) የጀመሩትን የቢራ ብርጭቆ እየጨለጡ፣ ሻይ የያዙት ሻዩን፣ ቡና የያዙትም ቡናውን… አንዳንዶቹ እየጨረሱ፣ አንዳንዶቹ እየተውት መሯሯጥ ጀመሩ። ምግብ ያዘዙትም ‹‹ቴክ አዌይ (የሚወሰድ) አድርጊልኝ›› እያሉ መሮጥ ጀመሩ። ጉዳዩ የትራፊክ ፖሊሶች መንገድ ላይ ተሽከርካሪ ያቆሙ ሰዎችን እያስነሱ ነበር።

ቦታው የኮሪደር ልማቱ አካል ስለሆነ አዲስ መንገድ እየተሠራበት ነው። በዚህ ቦታ ላይ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ከተከለከለ ቆይቷል። በተለይ እየተሠራ ያለው እንኳን አቁሞ መሄድ ለማለፍ እንኳን በምልክቶች ሲዘጋ የቆየ መንገድ ነው። እንኳን አቁሞ ምግብ ቤት ወይም መጠጥ ቤት ለመቀመጥ በቅጽበት ለማለፍ እንኳን የደኅንነት ስጋት ያለበት ነው፤ ምክንያቱም ግንባታ እየተካሄደበት ያለበት ቦታ ነው።

በሌላ በኩል የኮሪደር ልማቱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ሁሉ (በተጠናቀቁትም ሆነ ገና እየተሠሩ ባሉት) አስፋልት ላይ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ከተከለከለ ቆይቷል። በዚህ የዲጂታል ዘመን ይህን መረጃ ያልሰማ አሽከርካሪ ይኖራል ብሎ ማሰብ አይቻልም። በቀልድም ሆነ በቁም ነገር የማኅበራዊ ሚዲያዎች አጀንዳ ከሆነ ቆይቷል። ዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃንም ጠዋት ማታ የሚናገሩት ነው። እንኳን መንገድ ላይ ተሽከርካሪ አቁሞ የጠፋ አሽከርካሪ፣ ያለአግባብ በእግረኛ መንገድ ላይ የሄደ እግረኛ ሳይቀር እየተቀጣ ነው። በአሽከርካሪነት ሥራ ላይ ያለ ሰው እንዴት ይህ መረጃ ይጠፋዋል? ስለዚህ በቸልተኝነት ነው ማለት ነው።

ብዙ ማኅበራዊ ጉዳዮች እንደሚኖሩባቸው አውቃለሁ። ተሽከርካሪ አቁሞ የሚጠፋው ሁሉ ጃምቦ ቤት ገብቶ ነው ማለት አይደለም። ሁሉም ሊዝናና ነው ማለት አይደለም። ብዙ አስገዳጅ የሚሆኑ ማኅበራዊ ጉዳዮች አሉ። ዳሩ ግን ማኅበራዊ ጉዳይን መከወን የሚቻለው ሕግ እየጣሱ አይደለም። አንድ አሠራር ሕግ ነው ተብሎ ከተከለከለ በቃ ሕግ ነው! አስፋልት ላይ ዳር አስይዞ መቆም የተከለከለው ያለምክንያት አይደለም። ለአደጋ አጋላጭ ስለሆነ፣ መንገድ እያጠበበ ስለሆነ… በአጠቃላይ አለማቆሙ የተሻለ ሆኖ ስለተገኘ ነው። ለዚህ ደግሞ ሕግ ወጥቶለት ተከልክሏል። ስለዚህ በምንም አግባብ ሕግ መጣስ ትክክል ሊሆን አይችልም ማለት ነው።

በዚህ በተከለከለ ቦታ ላይ ተሽከርካሪ አቁመው የሄዱ ሰዎች ቢቀጡ ጥፋቱ የማን ነው? ታርጋ ቢፈታባቸው የፈታውን ሕጋዊ አካል በክፋት ቢኮንኑ ያምርባቸዋል ወይ? ሕግ ሲከበርም፣ ሕግ አላስከብር ሲሉም ወቅሰን ይዘለቃል ወይ?

በድምፅ ማጉያ (ማይክራፎን) ልመና መሰል ማስጠንቀቂያ እየተናገረ ሲመጣ የሆነ በክፋት የተሞላ ሰውየ ሆን ብሎ ሰውን ለመጉዳት እንደሚመጣ አድርገው ነው የሚያዩት። ‹‹መጡ ደግሞ!›› አይነት የመሰላቸት ስሜት ነው ያላቸው። የሚገርመው ግን የትራፊክ ፖሊሶቹ ምንም ማስጠንቀቂያ ሳይናገሩ እየፈቱ መሄድ ይችሉ ነበር። ምክንያቱም ተሽከርካሪው የቆመበት ቦታ የተከለከለ ቦታ ነው። ደንብ ተላልፏል። የተሽከርካሪውን ታርጋ ቁጥር እየጠራ ‹‹….. ቶሎ አንሳ!›› ሲል ነበር። ይህ በበጎ ነው መታየት ያለበት። ምክንያቱም አትቀጣብኝ እያለ እየለመነ ነው። ከመቀጣትህ በፊት አንሳው እያለ ዕድል እየሰጠ ነው። ከየጃምቦ ቤቱ እየጠራ እየለመናቸው ነው። መውቀስ ያለብን ሕግ ሲጣስ እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉ ሕግና ደንብ አስከባሪዎችን እንጂ ሕግና ደንብ የሚያስከብሩትን አይደለም።

ይህ ልማዳችን አደገኛ የሆነ ኋላቀር ልማድ ነው። ለምሳሌ፤ ፖሊስን መውቀስና መጥላት ያለብን ሌባን ሲተባበር መሆን ሲገባው፤ ሌባን ሊይዝ የሚመጣን ፖሊስ ‹‹መጡ ደግሞ!›› የሚሉ አሉ። ‹‹መጡብህ!›› የሚሉ አሉ። ልንወቅሰው የሚገባ ሕግና ደንብ ከተላለፈ አሽከርካሪ ላይ ጉቦ የሚቀበል የትራፊክ ፖሊስን እንጂ ሕግ የተላለፈውን አሽከርካሪ የሚቀጣውን አይደለም። አንዳንድ ሰዎች እነርሱ እየሄዱበት ያለው ታክሲ ሕግ ተላልፎ ሲቀጣ ራሱ ትራፊኩን ይራገማሉ፤ ይሳደባሉ። በዚያች ቅጽበት ለሄዱበት ታክሲ መወገናቸው ነው። መወገንና መተባበር እኮ ለበጎ ነገር እንጂ ለጥፋት አይደለም!

በነገራችን ላይ በድፍረት መናገርና መወያየት ያለብን ነገር ሕግና ደንብ ላይ ያለን አመለካከት በጣም ኋላቀር ነው። ነገሮችን የምናየው ከሕግና ከመርሕ አንፃር ሳይሆን ከግለሰብ ማንነት ጋር ነው። ለምሳሌ፤ ሕግና ደንብ የተላለፈ አንድን አሽከርካሪ የሆነ የትራፊክ ፖሊስ ሲቀጣው ‹‹አቤት ክፋት›› ይባላል። ‹‹ክፋቱ ነው እንጂ ምናለ ቢያልፈው›› ይባላል። ሕጉ እኮ ይከለክላል፤ ለምን ከትራፊክ ፖሊሱ ግለሰባዊ ክፋትና ደግነት ጋር ይያያዛል። ትራፊኩ ለምን የገዳም መነኩሴ አይሆንም! ሕግ ከሆነ ሕግ ነው። ሲጀመር ደግነት ማለት ሕግ መጣስ ሳይሆን ሕግና ደንብን ማክበር ነው። ደግነት ማለት ማጭበርበርና ማታለልን ማበረታታት እና ማለፍ ሳይሆን በሐቅ መሥራት ነው። በልማዳችን ግን እንደ የዋህና መልካም ሰው የምናየው ሕግና ደንብን እየጣሰ አጭበርባሪን የሚተባበር ሰው ነው።

በትምህርት ቤት እንኳን የሚወደድ አስተማሪ ተማሪ የማይቆጣጠር፣ ፈተና የማያከብድ፣ ክፍለ ጊዜ የሚቀጣ ነው። በተቃራኒው ሕግና ደንብ የሚያከብር፣ ተማሪ ሲዝረከረክ የሚቀጣ አይወደድም። ይሄ ልማዳችን ነው ያደገው። በዚህ ምክንያት ነው ለአንድ ተቋም ወይም ዘርፍ ኃላፊ ሲሾም ከሕግና ደንቡ ይልቅ የሰውየው ባሕሪ ላይ ትኩረት የሚደረገው። ተቋሙ ምን መተዳደሪያ ሕግና ደንብ አለው ከማለት ይልቅ ሰውየው (ኃላፊው) ምን አይነት ባሕሪ አለው የሚለው ላይ ትኩረት ይደረጋል። ይሄ ማለት የተቋሙ ሠራተኛ የሚተዳደረው በሕግና ደንቡ ሳይሆን በኃላፊው ግላዊ ባሕሪ ነው ማለት ነው።

በነገራችን ላይ አንዳንድ ኃላፊዎችም ባሕሪያቸው በዚሁ ልማድ የተቃኘ ነው። ቀልባቸው ያልወደደውን ሠራተኛ ‹‹ቆይ ሳልሠራልህ! ቆይ ዋጋህን ሳልሰጥህ! እንዲህ ባላደርገው እኔ አይደለሁም!….›› አይነት ፉከራ ይፎክራሉ። ሠራተኛው የሚቀጣው ከመርሕ አንፃር ሳይሆን በአለቃው ግለሰባዊ አተያይ ይሆናል ማለት ነው።

በእነዚህ አጓጉል ልማዶች ስለለመድን ነው ሕግና ደንብ ከማክበር ይልቅ ነገሩን በክፋትና ደግነት የምናየው። ሕግ ከተባለ ሕግ ነው። ሕግን ማስከበር ኃላፊነት የተሰጠው ሰውየ ግዴታ ነው። ሕግ ማክበርም የተገልጋዩና የዜጋው ግዴታ ነው። ስለዚህ የተከለከለ ነገር አናድርግ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You