ዛሬ የዘመን እንግዳ ያደረግናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሀገር ልማትና ጥናት ኮሌጅ የአካባቢና ልማት ማዕከል (Center for Environment and Development) መምህሩን ፕሮፌሰር በላይ ስማኔ (ዶ/ር)ን ነው፡፡ ፕሮፌሰር በላይ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሩሲያ ከሚገኘው ቲሚርያዝቭ የግብርና አካዳሚ (Timiriazev Agricultural Academy) እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ኔዘርላንድስ ከሚገኘው የዋግንገን የግብርና ዩኒቨርሲቲ (Wageningen Agricultural University) በግብርና እና የአካባቢ ሳይንስ አግኝተዋል፡፡
እንግዳችን፣ በግላቸውና ከሙያ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በጥናትና ምርምር የተሰሩ ጥናታዊ ፅሁፎችን በታወቁ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ መጽሔቶች ላይ ለህትመት አብቅተዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አገልግሎት የሰጡ ሲሆን፤ ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎቶችና የሙያ ነክ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ፕሮፌሰር በላይ፣ በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ በአማራ ክልል ደግሞ የስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ሲዳ) ዳይሬክተርም ሆነው ሰርተዋል፡፡ የዛሬው የዘመን እንግዳችን መጽሐፍ ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል፡፡
ከሰሞኑን በተለያዩ ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የየዘርፉን ባለሙያ እና የመንግሥት ባለስልጣናትን በመጋበዝ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የውይይት መድረኮችን የሚያዘጋጀው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፤ እንደተለመደው አንድ መድረክ አዘጋጅቶ የዘርፉ ምሁራን ሃሳባቸውን እንዲያጋሩ አድርጓል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ያለመረጋገጡ መንስኤው ላይ ያጠነጠነ ሲሆን፤ ከዘርፉ የተጋበዙ ምሁራን ምላሽ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ ሰጥተውባቸዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም የዘመን እንግዳ ያደረጋቸው ፕሮፌሰር በላይን በመሆኑ በእንግዳ ገጹ በዕለቱ የነበረውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ዓመታት እና የአሁኑ የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ሁኔታ እንዴት ይዳስሱታል?
ፕሮፌሰር በላይ፡– ግብርናን በሚገባ አውቀዋለሁ ብዬ እገምታለሁ። ምክንያቱም በዘርፉ ረዘም ላሉ ዓመታት ሰርቻለሁ። በምግብ ዋስትና ላይም ብዙ ነገሩ ላይ ግንዛቤው አለኝ ብዬ አምናለሁ። ባለፉት ዓመታት ግብርና እና የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ሀገር አቀፍም፤ ዓለም አቀፍም ድርጅቶች በሰፊው ሲሳተፉ ቆይተዋል። በዘርፉ በርካታ ሙከራዎችም ተደርገዋል።
ወደዋናው ጥያቄ ከመግባቴ በፊት ምርት እና ምርታማነት በተወሰነ ደረጃ አለ፤ ለምሳሌ እኤአ በ1990 ወደ አስር ኩንታል የነበረው አማካይ ምርት እኤአ በ2011 ላይ ወደ 20 ኩንታል መድረስ ችሏል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በ2022 እስከ 23 ኩንታል ደርሷል። ስለዚህ ሙከራዎች አሉ ማለት ይቻላል።
ከሁሉም ወገን የምግብ ዋስትናንም ሆነ ግብርናን ለማሻሻል ጥረት ተደርጓል። ይሁን እንጂ የምግብ ዋስትና የሚረጋገጠው አንድ ማኅበረሰብ ወይም አንድ ዜጋ ሁልጊዜ በቂ፣ አስተማማኝ እና ገንቢ የሆነ ምግብ ሲያገኝ ነው የሚለውን አባባል/ጥናት ከወሰድን የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ገና በሰፊው አልተረጋገጠም ማለት ይቻላል።
እስከ 2019 እኤአ ድረስ መረጃዎች የሚያሳዩት እንዲሁም እስከ 2020 ድረስ በምግብ ዋስትና የተረጋገጠላቸው ሰዎች ቁጥራቸው በመቶኛ ሲሰላ የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም ከዚያ ወዲህ ደግሞ የመጨመር አዝማሚያ ታይቷል። የምግብ ዋስትና ማጣትም በመስፋፋት ደረጃ እንዲዚሁ ወደ 58 ነጥብ አንድ በመቶ የደረሰ ነው። ይህ በቁጥር ሲታይ ከሰሃራ በታች አፍሪካ እጅግ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ነው።
ሌላው የምግብ ዋስትና ማሳያችን የመቀንጨር መስፋፋት ሲሆን፣ ይህም አሁን በሚታየው እስከ 34 ነጥብ አራት በመቶ ውስጥ ይገኛል። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ የምግብ ዋስትና ሁኔታ በተለይ ደግሞ ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች ከፍተኛ እና ውስብስብ የሆነ ችግር ስላለበት በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ዋስትና አልተረጋገጠም። ስለሆነም ለማረጋገጥ በጣም ብዙ ስራዎች መስራት ይጠበቅብናል እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጡ መንስዔው ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር በላይ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። ነገር ግን የተለያዩ ውስብስብ የሆኑና እርስ በእርሳቸው እንኳን ለማስታረቅ የማይመቹ ፈተናዎች ኢትዮጵያንም አፍሪካንም እየተፈራረቁ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያ የአየር ንብረት ለውጥ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ እኤአ ከ1960 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ወደ አንድ ነጥብ አንድ ዲግሪ ሴልሼየስ ሙቀት ጨምሯል። የዝናቡም ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም።
እስከ 2050 ድረስ እስከ ሶስት ዲግሪ ሴልሼየስ በኢትዮጵያ ውስጥ ሙቀት ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። በዚያው ልክ የዝናቡ ስርጭትም ሆነ የጎርፉ እና የድርቁ ሁኔታ በጣም ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ሁኔታ በእያንዳንዱ ዲግሪ ሴልሼየስ ጭማሪ እስከ አስር በመቶ የሚሆነም ምርታማነት ይቀንሳል የሚል ጥናት አለ። ስለዚህ አንዱ ችግር ይህ ነው ማለት ነው፡።
ሁለተኛው ትልቁ ችግር የሕዝብ ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ነው። የሕዝብ መጨመር ደግሞ የፈተፈጥሮ ሀብት ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍ ያለ ነው ማለት ይቻላል። ለዚህ አንድ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። እኤአ በ2020 ላይ 117 ሚሊዮን ሕዝብ ነበር፣ መሃል ላይ ያሉትን ዓመታት ትተን በ2050 ደግሞ ወደ 215 ሚሊዮን ሕዝብ አሁን ባለው የሕዝብ መጨመር ስሌት ሲሰላ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ በግብርና እይታ የራሱ የሆኑ ትርጉም አለው። ይህ ሕዝብ መብላት ይፈልጋል፤ ምግቡን ሊያበስልበት የሚያስችል ማገዶ ይፈልጋል፤ መኖሪያ የሚሆነውን ቤት መስራትም እንዲሁ ይፈልጋል።
ስለዚህ የሕዝብ መጠጋጋትን ብንወስድ አሁን የሕዝብ ጥግግት በስኩዌር ኪሎ ሜትር 105 ሰው ነው። የዛሬ 20 እና 30 ዓመት ማለትም በ2050 የሕዝብ ጥግት በስኩዌር ኪሎ ሜትር ወደ 193 ሰው ይደርሳል። ይህንን ኢኮሎጂውን በምናይበት ጊዜ የኢትዮጵያ መሬት ልትሸከም ትችላለች ወይ? የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳና እንድናስብ የሚያደርግ ነው። እሱ ብቻ ሳይሆን በምግብ ፍላጎት በኩልም በ2030 እኤአ ወደ 12 ሚሊዮን ቶን ዛሬ ከምናመርተው ጭማሪ ማግኘት አለብን ተብሎ የሚጠበቅ ነው። በ2050 ደግሞ ይህ ቁጥር የት ሊደርስ እንደሚችል ማስላቱ አይከብድም። ነገር ግን ዋናው ነገር እንችላለን ወይ? የሚለው ነው።
ሶስተኛው ምክንያት የማኅበራዊ አለመረጋጋት ነው። ይህን የማኅበራዊ አለመረጋጋት (ሶሻል ዲስራፕሽን) እንለዋለን። ማኅበራዊ አለመረጋጋት ውስጣዊ ወይም ውጪዊ ሊሆን ይችላል። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ግብርናን በአግባቡ ለመስራት እና የተመረተውንም ምርት ከቦታ ቦታ ለመውሰድ የማኅበራዊ አለመረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ይህ ማኅበራዊ አለመረጋጋት ግጭትም ሌላም ልንለው እንችላለን። ይህ የማኅበራዊ አለመረጋጋት በኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ዋስትና ላለመረጋገጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
በሚያስገርም ሁኔታ እኔ በተመረቅሁበት ወቅት የወር ደመወዜ ስምንት ኩንታል ጤፍ ይገዛ ነበር። አሁን ከ33 ዓመት በኋላ ሙሉ ፕሮፌሰር ሆኜ የወር ደመወዜ አንድ ኩንታል ጤፍ መግዛት ተስኖታል። እናም አንዱ በአብዛኛው የአዲስ አበባ የገበያው ሁኔታ እንዲቀዛቀዝ ያደረገው በሌሎች አካባቢ ያለው የማኅበራዊ አለመረጋጋት ያመጣው ፈተና ነው።
ሰላም እና ደህንነት ከሌለ እጅግ በጣም በከፍተኛ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ችግር ውስጥ የሚገባ ይሆናል። ይህ ብቻ ሳይሆን ውጪያዊ በሆነ ምክንያትም የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ እንፈተናለን። ለምሳሌ የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት አንዱ ነው፤ አሁን ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመካከለኛው ሀገር ጦርነት አለ፤ እነዚህ ጦርነቶች እና የሰላም መታጣቶች በአብዛኛው የግብርና ግብዓትን የምንጠቀም ስለሆነ በከፍተኛ ደረጃ የምግብ ዋስትናችንን ጎድቶብናል።
አራተኛው የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓት በጊዜውም በአግባቡም በበቂ ሁኔታ መቅረብ አለመቻሉ ለምግብ ዋስትናችን አለመረጋገጥ ሌላው ምክንያት ነው። ለምሳሌ ምርጥ ዘርን መውሰድ እንችላለን። አሁን የሚመረተው ይመስለኛል ከ15 ወይም ከ16 በመቶ በላይ አይሸፍንም። የምግብ ሥርዓቱን በተመለከተ በተለይ የመሰረተ ልማት አብዛኛው የምናመርተው ምርት በጊዜው ፕሮሰስ ካልተረገ እና በጊዜው የገበያው ሁኔታ ካልተመቻቸና ተጠቃሚው ዘንድ መድረስ ካልቻለ ሊበላሽ የሚችል ነው። ይህ የምግብ ሥርዓቱ አለመጎልበት እና ኢንዱስትሪዎች ምግብ ነክ የሆኑ ፕሮሰሶችን አለመጀመራቸው ከፍተኛ ችግር ያለበት ይመስለኛል።
ሌላው በሕዝብ ቁጥር ብዛት የተነሳ እና ከአስተራረስ ዘይቤያችን ኋላቀርነት የተነሳ የመሬታችን መጎሳቆል እጅግ በጣም በከፍተኛ ደረጃ የምግብ ማምረትን ቀንሶብናል። ለምሳሌ ስለማውቀው አካባቢ መናገር እፈልጋለሁ። ጎጃም ውስጥ አብዛኛው አርሶ አደር ከጤፍ፣ ከስንዴ እና ከገብስ ምርት እየወጣ ወደ ባህር ዛፍ ምርት እየገባ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? በሚል ስናጠና አብዛኛው የዚያ አካባቢ አፈር አሲዳማ በመሆኑ የተነሳ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢ መሬት መጎሳቆል ብዙ የመስኖ ቦታዎች ጨዋማ በመሆናቸው ነው። አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩ እና የግሉ ሴክተር የኢኮኖሚ አቅም አለመመጣጠን ነው። በእኔ እምነት እነዚህ ምክንያቶች ናቸው በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ላለመረጋገጡ መንስዔ የሆኑት ባይ ነኝ፤ እነዚህ ደግሞ አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር የተወሳሰቡ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል ምን መደረግ አለበት?
ፕሮፌሰር በላይ፡– የምግብ ዋስትናውን ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ስመለከት የኢትዮጵያ ግብርና፣ የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና በጣም የተቆላለፉ ችግሮች ያሉባቸው ናቸው። በተለይም ቁልፍልፍ ያደረጓቸው ችግሮች ከሴክተሩ ውጭ ያሉ ችግሮች ናቸው። የተለያዩ ባለድርሻዎች የሚጫወቱበትና እጅግ ውስብስብ ችግር ያለበት ነው የሚመስለኝ። ስለዚህ ለማሻሻል መደረግ ያለበት አንዱ በጥናት በተደገፈ ፖሊሲ እና ተቋማዊ አደረጃጀት ላይ ማበረታቻ ማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- መደረግ ያለበት ምን አይነት ማበረታቻ ነው?
ፕሮፌሰር በላይ፡- አንደኛ የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና ለማሻሻል ከሚያስችሉት ውስጥ አንዱ የግብዓት ድጎማ ማድረግ ነው። ለምሳሌ ይህ ግብዓት ድጎማ ድሮ የነበረ ነው። አሁን ግን የዚህ አይነት የግብዓት ድጎማ ቆሟል። ነገር ግን ወሳኝ ነው። ይህ አይነቱ የድጎማ አሰራር በብዙ የአውሮፓ እና የኢስያ ሀገራት የሚተገበር ነው። እኛ ግን ይህን የድጎማ አሰራር አቋርጠናል፤ ይሁን እንጂ በጉዳዩ ሊታሰብበት የሚገባ ነው።
ሁለተኛው የምግብ ዋስትናን ለማሻሻል የግብርና መሰረተ ልማትን ማሳደግ ወሳኝ ነው። መሰረተ ልማትንም ማሻሻል፤ ከግብርና ጋር የተያያዙ አግሮ ኢንዱስትሪዎችንም ማስፋፋት መልካም ነው። መንገዶችንም የተሻለ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ሶስተኛው ደግሞ ምርምር እና ልማትን በእውቀት እና በክህሎት እንዲመራ ማድረግ መልካም ነው። በተለይ ኤክስቴንሽኑን ከፖለቲካው መነጠል ያስፈልጋል። የፖለቲካ ሥርዓቱን የሚያከናውነው አካል የልማቱን ስራ ለመስራት እጅግ ፈተና ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል። ሌላው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትን በእውቀት፣ በልምድ፣ በሳይንስ የሚመሩ ተቋማት ማድረግ አስፈላጊ ነው።
ሌላው ሁሉም ነገር ከገበያ እና ከመሰረተ ልማት ቀጥሎ ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ ችግር ውስጥ ያለችው በተፈጥሮ ሀብት መጎሳቆል ነው። የተፈጥሮ ሀብት መጎሳቆልን ለማስቀረት በእያንዳንዱ አግሮ ኢኮሎጂ እና ሥርዓተ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ላይ በአግባቡ በተጠና መልክ ቢሰራ መልካም ነው። የተፈጥሮ ሀብት ሲሰራ መደረግ ያለበት በግብርና ባለሙያው እና በአርሶ አደሩ መካከል ስምምነት ነው። ካለው የመሬት ጥበት የተነሳ አርሶ አደሩ እርከኑ ሰፋ ሰፋ እንዲል ሲፈልግ የግብርና ባለሙያው ደግሞ በተባለው መሰረት ነው መስራት የሚፈልገው። ስለዚህ የሚደረገው በስምምነት ነው። ያ በስምምነት ላይ ተመስርቶ የተሰራው የእርከን አሰራር ጥሩ መሆኑ ቀርቶ መጥፎ የሚሆንበት ሁኔታ አለ።
ሌላው የምርምር እና የኤክስቴንሽን ስራዎችን በእውቀት፣ በስነ ምህዳር እና የግብርና ስርዓትን ያማከሉ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይ ኢትዮጵያ በጣም የተለያየ ስብጥር ያላት ሀገር ነች። በብዙ መንገድ ከባህል ጀምሮ፣ ከአፈሩ እና ከአየሩም ጭምር የተለያየ ስለሆነ የኤክስቴንሽን ሥርዓቱን እና ምርምሮችን ማጠናከር ተገቢ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ አሁንም አጥብቄ የምገልጸው በግብርና ግብዓት በአብዛኛው ማዳበሪያ እና ጸረ ተባይ መከላከያ ሀገር ውስጥ የሚመረትበት ሁኔታ መፈጠር አለበት የሚለውን ነው።
ለምሳሌ ማዳበሪያን በተመለከተ በሙሉ ልብ የምናገረው ለማዳበሪያ ግብዓትነት የሚያገለግል ብዙ ጥሬ እቃ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ነው። ከጋዙ ጀምሮ ከሰልን፣ ፖታሽየምን የመሰለ ጥሬ እቃ አለ። ስለዚህ ቅድሚያ ሰጥቶ ልክ እንደ ሀገራዊ ስሜት ሀገር አደጋ ውስጥ በምትገባበት ሰዓት እንደሚሰማን አይነት ስሜት ወስዶ ኢትዮጵያ ማዳበሪያን እና ምርጥ ዘርን በተመለከተ ራሷን እንድትችል የሚደረግ መንገድ ቢፈልግ የተሻለ ነው። በተቋም ደረጃ ደግሞ ብዙዎቹ በተለይ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የነበሩ ተቋማት አንዳንዶቹ የሉም፤ ፈርሰዋል፡። አንዳንዶቹም የሚቀያየሩት ቶሎ ቶሎ ነው። ስለዚህ ይህንን የቁጥጥር አገልግሎትን ማዘመን እና በእውቀት እንዲመራ ማድረግ ተመራጭ ነው። አሁን ካለን የምግብ ዋስትና እና ካለን የተፈጥሮ ሀብት፣ በተለይ እግዚአብሔር ከቸረን ጸጋ የተነሳ በብዙ መንገድ የምግብ ዋስትናችንን ማሻሻል የምንችል ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ እና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የማን ኃላፊነት ነው? ከማንስ ምን ይጠበቃል? በእርስዎ እይታ የምግብ ዋስትና በኢትዮጵያ ባለቤት አለው ወይ?
ፕሮፌሰር በላይ፡– የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብዙ ተዋናዮች አሉ። የምግብ ዋስትናን በማረጋገጡ ረገድ አንድ ተቋም ብቻ የሚሰራው ጉዳይ አይደለም። በሀገር አቀፍ ደረጃና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ኃላፊነቱ የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን የበርካቶች ነው። ለምሳሌ በዝርዝር እንያቸው ከተባለ የመጀመሪያው እና ትልቁ ተዋናይ መንግሥት ነው። መንግሥት አግባብነት ያለው ማኅብረሰቡን ያማከለ ፖሊሲ ማውጣት እና እንዲሁም ሊተገበር በሚችል መልኩ የመንግሥቱን ኃላፊነት መወጣት አለበት። ይህ ጉዳይ ከመንግሥት የሚጠበቅ ነው። ፖሊሲዎች በብዛት አሉ፤ ነገር ግን ወደ ተግባራዊነታቸው ሲመጣ ምንም ነገር የለም። ስለሆነም ለዚህ መፍትሔ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ትልቁ ተዋናይ መንግሥት ነው ባይ ነኝ። አስቀድሜ የጠቀስኳቸውን የድጎማን፣ የመሬት አጠቃቀምን እንዲሁም የቁጥጥር ሥርዓቱን ጨምሮ ብዙዎቹን ይመለከታል።
ሁለተኛው የምርምር ተቋማት አሁን ባለው አሰራር ሳይሆን በተለይ ስነ ምህዳሩን እና የግብርና ሥርዓቱን በአማከለ መልኩ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ ማውጣት እና ማፍለቅ፤ መሞከር እና ማሰራጨት ላይ በሰፊው መሳተፍ የሚገባቸው ይመስለኛል። ሶስተኛው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየሰራን ያለነው ምንድን ነው? ብለን መጠየቅ መቻል አለብን። የምናስተምረው ትምህርትስ ተግባራዊ እየሆነ ነው ወይ? ልንልም ይገባል።
እኔ በተግባር ያጋጠመኝን ነገር መጥቀስ እወዳለሁ። በአንድ ወቅት በዓለማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና የኤክስቴንሽን ኃላፊ ነበርኩ። በወቅቱም አዋቂ ነኝ ባይ ነበርኩ። በስውዲሽ (ሲዳ) የልማት ተራድኦ ለተወሰነ ጊዜ የአማራ ክልል አስተባባሪ አድርጎ በምርምር ዘርፉ ላከኝ። ወደስፍራው ሳቀና የመጀመሪያ መዳረሻ ያደረኩት ወሎ አማራ ሳይንት ወደሚባለው ነው። በስፍራው ስደርስ ወደ አምስት ሰዓት አካባቢ ነበር። የግብርና ቢሮው ሁሉ ዝግ ነው። በወቅቱ ያሰብኩትና የገረመኝ ነገር ቢኖር ‘እንዴት ከዓለማያ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ የዘርፉ ባለሙያዎች ቢሮውን ዘግተው ይሄዳሉ? እንዴት ሥራ አይሰሩም?’ የሚል ነበር። በዚህ ብቻ አላበቃሁም፤ በሆነው ነገር ትንሽ ቁጭት ብጤ ሸንቆጥ አደረገኝ እና በስፍራው ያገኘሁትን የጥበቃ ሰራተኛ ስለሁኔታው ይገልጽልኝ ዘንድ ጠየቅኩት። አክዬም ‘በላይ ስማኔ የተባለ ሰው ይፈልጋችኋል’ በልልኝ ብዬ በድፍረት ላኩት። ከዚያ በፊት ግን የጥበቃ ሰራተኛው አንድ ነገር ጠቆም አድርጎኝ ነበር። እሱም “ለእኛም ቀን አወጡልን፤ ለእነርሱም ጥሩ ሆነላቸው” የሚል ነበር። እንዲያ ማለታቸው ትርጉሙ ድሮ ድንች እና ቲማቲም እንተክልበት የነበረ ማሳ ላይ በአሁኑ ወቅት ጫት እያመረትን ለእነርሱ መሸጥ ጀምረናል፤ እነርሱ ደግሞ ቤታቸው እየተዝናኑ ይኖራሉ የሚልም ሃሳብ ሰማሁ።
ይህንን ሃሳብ እያሰላሰልኩ ቆየሁና የእኔን መምጣት የሰሙ የአለማያ ዩኒቨርሲቲ ምሩቆቹም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሩቆቹም ተሰባሰቡ። ብዙዎቹ የሚያውቁኝ በስም ነበርና ፊት ለፊት ተገናኘን። ከዚያ ውስጥ አንድ የእኔ ተማሪ የሆነ፤ የፕላንት ሳይንስ በደንብ ያስተማርኩት የግብርና ሰራተኛ የሆነው ተነስቶ “ዶክተር በላይ አሁን አለማያ ባገኝህ ዜሮ ነበር ለአንተ የምስጥህ” አለኝ። በጣም ደነገጥኩ። ምክንያቱም እኔ የማስተምረው ሳይንሱን ነው። “አንተ ስለጂን ስለኤሌክትሮን እያልክ ስታወራ ጂን ያልካትን አይተሃታል? ያላየኸውን ነገር ስትነግረን እኛም አፋችንን ከፍተን ስናዳምጥህ ቆየን። ” አለኝ።
ከዚያም በአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ማዕከል ያሉ አርሶ አደሮችን ሰብስቦ “እንግዲህ ሰዎች! አሁን ኤክስፐርት መጥቷልና እዚህ ስለሁኔታው ያስረዳናል። አትክልት እንዴት መሆን እንዳለበት ያስረዳናል” ብሎ ሁለት ማሳዎችን አሳየኝ። ማሳዎቹ ላይ ያለው ስንዴ እና ገብስ ነበር። ይህን ያለው የፕላንት ሳይንስ ምሩቅ ነው። ነገር ግን እንዴት አድርጎ ይለየው? የሆነው ሌላ ነው። ሌላኛውም ተነስቶ እንዲሁ ዩኒቨርሲቲ በነበረበት ወቅት ብዙ ጊዜ ክፍል የማይገኝ የግብርና ቢሮው ሰራተኛ፤ ሌላ ሌላ ነገር ተናገረና ‘ጫት ብንቅም ወንጀለኞች እናንተ ናችሁ’ ወደሚለው ድምዳሜ መጣ። ከዚህ ነገር በወቅቱ ብዙ ትምህርት መውሰድ ችያለሁ።
ስለዚህ ከፍተኛ ትምህርት የምንሰጠው ትምህርት በውጭ ሀገር ትምህርት ላይ የተመሰረተ ነው። የእኛ የትምህርት ሁኔታ ተግባር ተኮር ሳይሆን ከፈረንጆች የለቀምነውን የምናስተምር ሲሆን፤ የእኛን ኋላቀር ነው ብለን ወደኋላ መጣላችን ላይ ተሳስተናል። ስለሆነም የግብርና ትምህርት አሰጣጣችን በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል ያለበት ይመስለኛል።
ሌላው የኤክስቴንሽን አገልግሎቱን ስናይ እውነት ለመናገር ኢትዮጵያውያን በጣም ጠንካሮች ናቸው። ለግብርና ባለሙያዎች ትልቅ ከበሬታ አለኝ። ከግብርና ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል አጋጣሚዎችን አግኝቼ መሃላቸው ሆኜ ሰርቻለሁ። የእውቀት ሽግግር አለ። ነገር ግን በተለያየ ጫና ተወጥረው ተይዘዋል። ስለዚህ እነርሱን ማላቀቅ እና ወደትክክለኛ ስራቸው ወይም ዘርፋቸው እንዲመጡ ማድረግ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ።
ሌላው አርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ በተለያየ መንገድ ግንዛቤው እንዲኖራቸው ማስተማርና ማሳየት ያስፈልጋል። በተለይም ደግሞ ዝናብ አጠር በሆኑ ቦታዎች እጅግ በከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠበቅ፣ ያሉትን ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ በመጠቀም፣ ምርታማነትን ማሳደግ ያሻል።
በሌላ በኩል ደግሞ የግል ባለሀብቱን ማንቀሳቀስ ተገቢ ነው። በተለይ በግብርና ምርት ላይ የተሰማሩ ሆነ በአግሮፕሮሰሲንግ ላይ የተሰማሩ በአብዛኛው በትርፍ ከፍታ ላይ የተንጠላጠሉ ናቸው እንጂ ቀጣይነት ባለው መልኩ እነርሱም እየሰሩ ያሉት አርሶ አደሩም በሚጠቀምበት መንገድ እየሄዱ አይደለም ማለት ይቻላል።
አንዳንዴም ምርጥ ዘር ላይ ከገበያ እስከመግዛት የሚታይ የአሰራር ክፍተት አለ፤ ይህን ሁኔታ ለግል ባለሀብቱ ግንዛቤ ማስጨበጥ እና ማሳወቅ ትክክል ይመስለኛል። ምክንያቱም የግል ባለሀብቶች ሀገር በቀል እውቀትንም ከግምት ማስገባት ይጠበቅባቸዋል። በግብርናው ላይ የተሰማሩ የግል ባለሀብቶች ትርፍን ለማሳደግ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ባለው ልማት ላይ በማተኮር ሀገር ተጠቃሚ እንድትሆንም ሊሰሩ ይገባል።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በተመለከተ ደግሞ ስለእነርሱ ባሰብኩ ጊዜ እድሜዬ በጨመረ ቁጥር ተስፋ አስቆራጭ እየሆኑብኝ መጥዋል ማለት እችላለሁ። ምክንያቱም የሚመጡት ፕሮጀክቶች እና የሚመጣው ገንዘብ ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ ስለሚመጣ ነው። የኢትዮጵያን የግብርና ችግር በአግባቡ ለመፍታት ያቃታት ሀገር በቀል የሆነ ቴክኖሎጂ እና በሀገር በቀል ሳይንቲስቶች የሚመራ ባለመሆኑ ነው። ከዚህ የተነሳ ብዙ የተመሰቃቀለ ይመስለኛል። እነዚህን ሀገር በቀል የሆኑ እውቀቶችን መመለስ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ ጠንካራ ተቋም እና መልካም አስተዳደር ያስፈልገናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።
ፕሮፌሰር በላይ፡- አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም