የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በከፍተኛ የማዕድን ሀብት ክምችቱ ይታወቃል። በክልሉ ለኢንዱስትሪ እና ለኮንስትራክሽን ግብዓት ሊውሉ የሚችሉ ማዕድናት በብዛት ይገኛሉ፤ ለጌጣጌጥና ለመሳሰሉት ሊውሉ የሚችሉ ልዩ ልዩ የከበሩ ማዕድናት እና ሌሎች በርካታ ማዕድናትም ይገኙበታል። ከእነዚህ ማዕድናት መካከል የድንጋይ ከሰልና የከበሩ ማዕድናትን በብዛት ወደ ማምረት ተገብቷል።
የክልሉ የማዕድን ሀብት በጥናት እየተለየ ልማት ላይ እንዲውል እየተደረገ እንዳለ ሁሉ ጥናት ያልተደረገባቸውንም በጥናት እንዲለዩ እየተደረገ ነው። እነዚህን ማዕድናት በማልማት ረገድም በርካታ አምራቾች ፍቃድ የወሰዱበት ሁኔታ እንዳለም ከክልሉ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኦላዶ ኦሎ ክልሉ እንደ አዲስ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በማዕድን ዘርፍ በርካታ ሥራዎች ለመሥራት አቅዶ መንቀሳቀሱን ይገልጻሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ክልሉ ለኮንስትራክሽን እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት እንደ ድንጋይ ከሰል፣ ቪንቶናይት፣ ዶሎማይት፣ ካኦሊን የመሳሰሉ እንዲሁም የከበሩ ማዕድናት በብዛት ይገኙበታል። የብረትና ብረት ነክ ማዕድናት ክምችት መኖሩም በጥናት ተለይቷል። ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተደረገው ጥናት በክልሉ በጎፋ፣ በደቡብ ኦሞ እና በባስኬቶ ዞኖች የብረት ማዕድናት ክምችት መኖሩን ማረጋገጥ ተችሏል። የከበሩ ማዕድናትም እንዲሁ በጋሞ፣ በኮንሶ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በአማሮ እና በቡርጂ ዞኖች በስፋት እንደሚገኙ ተረጋግጧል።
በክልሉ ሊትየም የተሰኘው ማዕድን መኖሩን የሚጠቁሙ የድንጋይ ዓይነቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ በጋሞ፣ በኮንሶ እና በአሌ ዞኖች የሊትየም ማዕድናት አመላካቾች መታየታቸውን ተናግረዋል። ማዕድናቱን ለማምረት የሚፈልጉ ባለሀብቶች የምርምራ ፍቃድ ወሰደው በፍለጋ ላይ መሰማራታቸውንም ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ክልሉ በማዕድን ሀብቶች ላይ ጠቋሚ ጥናት ያደርጋል። ባለሀብቱ ደግሞ በዚህ መነሻነት ዝርዝር ጥናት አድርጎ ፍቃድ ወስዶ ወደ ማምረት ሥራ የሚገባበት አሠራርም ተዘርግቷል።
ክልሉ በቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በ2015 በጀት ዓመት የታቀደውን መነሻ ያደረገና የዚህ ክልል ድርሻ ምን ያህል ሊሆን ይችላል ተብሎ የተዘጋጀ እቅድን ሲተገብር መቆየቱን ምክትል ቢሮ ኃላፊ አስታውቀዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ለማከናወን ከታቀዱት ተግባራት መካከል ዋናዎቹ የማዕድን አለኝታ(ሀብት) ጥናት ማካሄድ፣ የአነስተኛና ባሕላዊ የኮንስትራሽን ማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ መስጠት፣ ከሮያሊቲ እና ከሌሎች ክፍያዎች ገቢ ማግኘት፣ በዘርፉ ሥራ አጥ ወጣቶች እንዲደራጁ በማድረግ የሥራ እድል መፍጠር እና የማዕድን ዘርፍ ምርት አቅርቦትን ማሳደግ በሚሉት ላይ ትኩረት በማድረግ ብዙ ተሰርቷል።
በተያዘው በጀት ዓመት የማዕድን አለኝታ ጥናትን በ150 ኪሎ ሜትር ካሬ መሬት ላይ ለማካሄድ ታቅዶ፤ 105 ኪሎ ሜትር ካሬ መሬት የሚሸፈን ጥናት ተካሄዷል። ማዕድን ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ፈቃድ ከመስጠት አኳያም ለአንድ ሺ102 የአነስተኛና ባሕላዊ የኮንስትራሽን ማዕድን አምራቾች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ፣ ለ983 አምራቾች ፈቃድ ተሰጥቷል።
በዚህም መሠረት በተያዘው በጀት ዓመት ከሮያሊቲ እና ከሌሎች ክፍያዎች 160 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ፣ ከ206 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ሲሉም አመልከተዋል። እቅዱ በሁለተኛው ሩብ ዓመት የተከለሰበት ሁኔታ እንደነበረም አስታውሰው፣ እቅዱና የተገኘው ገቢ ግን ሊመጣጠን አልቻለም ብለዋል። ይህ የሆነበት ዋንኛ ምክንያት መነሻው በትክክል የክልሉን የማዕድን ገቢ ማሳየት ስላልቻለ መሆኑን ይገልጻሉ።
የክልሉ 80 በመቶ ያህል ገቢ የተገኘው በተፈጥሮ የማዕድን አለኝታ ካላቸው አምስቱ (ከጋሞ፣ ከወላይታ፣ ከኮንሶ፣ ከአሪ እና ከደቡብ ኦሞ) ዞኖች መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀሪው ገቢ የተገኘው ከሌሎች ዞኖች፣ ከማዕድን ፈቃድ እና ከሌሎች ክፍያዎች መሆኑን ገልጸዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊ እንደሚሉት፤ የሮያሊቲ ክፍያ ማለት ማንኛውም ማዕድን አምራች ማዕድኑን እንዳወጣ ከሚያደርገው ሽያጭ ለመንግሥት የሚፈጽመው ክፍያ ነው። ክፍያው እንደ የክልሉ ሁኔታ የተለያየ ቢሆንም፣ እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግን አምራቹ ከሽያጩ አምስት በመቶ ያህሉን ለክልሉ ገቢ ማስገባት ይጠበቅበታል። ከቅጣት፣ ከፈቃድ እድሳት፣ ከማህበረሰብ ልማት ክፍያዎች፣ ከአካባቢ ጥበቃ ማቋቋሚያ ፈንድ እና የመሳሰሉት የተገኙትን ገቢዎችንም ያጠቃልላል።
የማዕድን ዘርፍ ምርት አቅርቦትን ለማሳደግ ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናት (አሸዋ፣ ድንጋይ እና የመሳሳሉትን) አራት ሚሊዮን ሜትር ኪዮብ ለማምረት ታቅዶ፤ ከሦስት ሚሊዮን ሜትር ኪዮብ በላይ ማምረት ተችሏል። በበጀት ዓመቱ በጌጣጌጥ ማዕድን ምርት 39 ቶን የጌጣጌጥ ማዕድናት ለማምረት ታቅዶ፤ 28 ቶን በማምረት ለገበያ ማቅረብ ተችሏል።
ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ እንደ ድንጋይ ከሰልና ዶሎማይት የመሳሳሉትን 50ሺ ቶን ለማምረት ታቅዶ፤ 569ሺ ቶን ተመርቷል። እነዚህ ምርቶች በአብዛኛው ከሁለት ዞኖች የተገኙ ሲሆን ፤ የጋሞ ዞን ቦረዳ ወረዳ የድንጋይ ከሰል እንዲሁም የደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ የዶሎማይት ማዕድናትን በማምረት ይታወቃሉ። ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት አፈጻጸሙ ከእቅድ በላይ የሆነበት ምክንያት የተያዘው መነሻ እቅድ ትክክለኛውን መረጃ የሚያሳይ ባለመሆኑ ነው ሲሉ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ይናገራሉ።
የማዕድን ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የሚችል እንደመሆኑ በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ለ16ሺ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ነበር ያሉት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፣ በበጀት ዓመቱ ለ15ሺ 455 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል። ይህም አፈጻጸም 96 ነጥብ 5 በመቶ ነው ብለዋል።
የክልሉ የማዕድን ሀብቶች የሚገኙባቸውን አካባቢዎች ለማወቅ የሚያስችሉ ተጨማሪ ጥናቶች መካሄዳቸውን የጠቀሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ የማዕድን አለኝታ (ሀብት) በተፈጥሮ በብዛት የሚገኝባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ሁሉ በተወሰነ መልኩ ማዕድን ያላቸው ዞኖች እንዳሉም ይገልጻሉ። ይብዛም ይነስም መጠኑ ይለያይ እንጂ በክልሉ ሁሉም ዞኖች ላይ የማዕድን ሀብት ክምችት እንዳለ መረጋገጡን ጠቅሰው፣ በጥናት ላይ ተመስርቶ ለማልማት የባለሀብቶችን የዘርፉ የነቃ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
ምክትል የቢሮ ኃላፊው በክልሉ በማዕድን ልማት ላይ ብዙ ባለሀብቶች ተሰማርተው የሚገኙ ቢሆንም እንደብዛታቸው እየሰሩ አይደሉም ሲሉም ይገልጻሉ። ለእዚህም የቦረዳ የድንጋይ ከሰል ማምረት ሥራን በማሳያነት ያነሳሉ።
እሳቸው እንዳመለከቱት፤ በዚህ ቦታ 47 የሚሆኑ ባለሀብቶች የማምረት ፈቃድ ወሰደዋል። ይሁን እንጂ እስካሁን ባለው ሂደት ሥራውን የጀመሩት 17 ያህሉ ብቻ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥም አምስቱ ሥራውን ጀመረው ግብዓት በማጣት ወይም በገጠማቸው ፋይናንስ ችግር ምክንያት ሥራውን ያቆሙ ሲሆን፤ 12ቱ ግን በማምረት ሥራ ላይ ይገኛሉ።
በተመሳሳይ በደቡብ ኦሞ ዞን ዶሎማይት በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩት 17 ያህል አምራቾች ቢሆኑም፣ ከእነዚህ መካከል አሁን ላይ በሥራ ላይ የሚገኘው አንድ አምራች ብቻ ነው። ቀሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሥራው አልገቡም።
የማዕድን ሥራ ትልቅ ካፒታል ስለሚፈልግ አብዛኞቹ አምራቾች ፈቃድ ወስደው ጥናቱን ሲያሳኩና ወደ ምርት ሲገቡ አቅማቸው ይፈተናል። በተፈጥሮ የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች እንዳሉም አቶ አላዶ ጠቅሰው፣ ወደ ምርት ሲገቡ የጥራትና የግብዓት ብዛት መቀነስ ሲገጥማቸው ወደኋላ የሚመለሱበትና ሥራውን እስከ ማቆም የሚደርሱበት ሁኔታ እንዳለም አመልክተዋል።
‹‹የማዕድን ዘርፍ የካበተ ልምድ ያላቸው የተማሩ ባለሙያዎች /ጂኦሎጂስቶችን የማዕድን ኢንጂነሮችን/ ይፈልጋል፤ በጥናት የተደገፈ ሥራ መሥራትንም ይጠይቃል›› ሲሉም ተናግረው፣ ክልሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባለሙያ እጥረት ዋንኛ ተግዳሮት እንደሆነበትም ይናገራሉ። የበጀት እጥረት፣ የመሠረተ ልማት አለመኖር፣ ሕገ ወጥነት መስፋፋት እና የገበያ ትስስር ከሚያገጥሙ ተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
አቶ አላዶ እንዳብራሩት፤ ማዕድን በጣም ሩቅና ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት ባልተሟላባቸው አካባቢዎች ላይ ሊገኝ ስለሚችል የመሠረተ ልማት አለመኖር ከፍተኛ ተግዳሮት ሊሆን ይችላል። ሌላኛው የማዕድን ዘርፉ ትልቅ ተግዳሮት የሕገ ወጥነት (ሕገ ወጥ የማዕድን ማምረትና ማዘዋወር) መስፋፋት ነው። አንዳንዱ ማዕድን በቀላሉ ሊያዝ የሚችልና ለማዘዋወር ስለሚያመች ዘርፉ ለሕገ ወጥነት የሚጋለጥበት እድል ሰፊ ነው። በተለይ የከበሩ ማዕድናትን ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ ለማዘዋወር በእጅጉ ያመቻል፤ ይህም ሁኔታ በእነሱ ላይ የሚፈጸም ዝውውርን የመቆጣጠሩን ሥራ አስቸጋሪ እንዲሆን ካደረጉት መካከል ይጠቀሳል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የገበያ ትስስር አለመኖሩም በማዕድን ዘርፉ የሚነሳ ሌላኛው ተግዳሮት ነው። በክልሉ በሚመረቱ ማዕድናት የገበያ ትስስር ላይ ትልቅ ተግዳሮት ይታያል። ተግዳሮቶቹን ለመፍታት እስከታች ያለው መዋቅር ድረስ ግንዛቤን የማስፋት ሥራ ከመሥራት ባሻገር ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ለማምጣት እየተሰራ ይገኛል።
በገበያ ትስስር ረገድም ግልጸኝነት የጎደላቸው አሰራሮች ስላሉ ይህን ችግር ለመቅረፍ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። ‹‹በቅርቡ እንደ ክልል ማዕድኑ ከሚመረትበት ቦታ አንስቶ እስከ ፋብሪካ ድረስ ያለውን የገበያ ትስስር የሚያሳዩ ጥናቶች ለማየት ሞክረናል። ከሌሎች ክልሎች ተሞክሮ ለመወሰድ በደቡብ ምዕራብ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለውን የገበያ ስንሰለቱ ለመመልከት ተሞክሯል። በርግጥ ሁለቱም ክልሎች ተመሳሳይ ችግሮች ያለባቸው ቢሆንም፣ እንደ ሀገርም ተነጋግሮ መፍትሔ ለማስቀመጥ ይረዳ ዘንድ ያሉትን ችግሮች ለመለየት ሞክረናል። በመሆኑም የገበያ ትስስር በሲስተም እየተመራ እንዳልሆነ ለመገንዘብ ችለናል›› ይላሉ።
በቀጣይ በገበያ ትስስር ረገድ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን በመለየት ለመፍታትና ባለሀብቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ትክክለኛ ጥቅም እንዲያገኝ ለማድረግ እንዲሁም መንግሥትም የሚያገኘውን ገቢ እንዲያሳደግ ለማስቻል ከሌሎች ክልሎች ጋር በመሆን በጋራ እንደሚሰራ አመላክተዋል።
አሁን ላይ በክልሉ ያለው ማዕድን በተበታተነ መልኩ ነው እየለማ ያለው የሚሉት ምክትል ኃላፊው፤ በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች ማዕድኑን በተበታተነ መልኩ የሚያለሙበት ሁኔታ መኖሩ ሥራውን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጓታል። በክልሉ በማዕድን ዘርፉ ተሰማርተው ለማምረት ፍቃድ የወሰዱትንም ሆነ በምርመራ ሂደት ላይ ያሉት በርካታ አምራቾች ወደ አንድ በማምጣት ማሰባሰብ ያስፈልጋል ይላሉ።
በቀጣይ አቅሙ ያላቸውን አልሚዎች በመለየት በዘርፉ ለማሰማራት እንዲሁም የማዕድን አቅምን በጥናት በመለየት እንደሚሰራም ገልጸዋል፤ የማልማቱን ሥራ ጀምረው የማይተውትን፣ አምርተው ራሳቸውንም ሆነ ሀገርን እንዲጠቅሙ ማበረታታት ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል።
አቅም ያላቸው በከፍተኛ አቅምና ቴክኖሎጂ ማምረት የሚችሉ ትላልቅ ኩባንያዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማደረግ በትኩረት መሥራት ይጠይቃል ሲሉም አስታውቀው፣ በክልሉ የማዕድን ዘርፍ ላይ ለመስማራት የሚፈልጉ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች በክልሉ ያለውን እምቅ የማዕድን ሀብት በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም