አዳዲስ የኢንቨስትመንት አሠራር ሥርዓቶችና የሚጠበቁ ውጤቶች

ባለፈው 2016 በጀት ዓመት በብዙ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተስፋ ሰጭ ውጤት እንደተመዘገበ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገልጿል። ኮሚሽኑ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን በማሻሻል፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስተዋወቅና ኢንቨስትመንትን በማሳለጥ፣ የድኅረ ኢንቨስትመንት ድጋፍ በመስጠት፣ የኢንቨስትመንት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አመራርና አስተዳደር ተግባራትን በማከናወን የወጪ ንግድንና ተኪ ምርትን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ የዘርፎችንና የባለሃብቶችን ትስስር እና የክህሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳደግ ያስቻሉ ተግባሮችን አከናውኗል።

በዚህም ባለፈው የበጀት ዓመት ሦስት ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል። 329 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶች ተሰጥተዋል። ፈቃድ ከወሰዱ ባለሃብቶች መካከል ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት በማምረቻ ዘርፍ የሚሰማሩ ናቸው። ከሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች 115 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል። ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመግባት ፍላጎት ካሳዩ 70 ድርጅቶች ጋር የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈርመዋል። በዘጠኝ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በሚገኙ 205 ፕሮጀክቶች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ተከናውነዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ወቅታዊ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ውስጥ ባስገባና የሀገርን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት ክለሳዎች ተጠናቀው አዳዲስ ድርድሮች ተደርገዋል። ከአዳዲስ ቀጣናዊና ክልላዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም ተከናውነዋል። የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አቅሞችና መልካም ዕድሎች በበርካታ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረሞችና ኤግዚቢሽኖች ላይ እንዲተዋወቁም ተደርጓል።

ኮሚሽኑ በ2017 የበጀት ዓመት አዳዲስ የኢንቨስትመንት አሠራር ሥርዓቶችን በመተግበር የተሻለ ሀገራዊ የኢንቨስትመንት አቅም ለመፍጠር እንደታቀደም ገልጿል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ወይዘሮ ሐና አርዓያሥላሴ በበጀት ዓመቱ በዘርፉ እስካሁን ከተገኘው ውጤት የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ መታቀዱን አመልክተዋል። እሳቸው እንደሚሉት፣ ኮሚሽኑ የሀገሪቱን እምቅ ሀብት በመጠቀም ጥራት ያለው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በመጨመር፣ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ያለውን ድርሻ የማሳደግ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለወቅቱ የሚመጥኑ አዳዲስ አሠራሮችን ይተገብራል።

‹‹በበጀት ዓመቱ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት አዲስ መሠረት ለመጣል የሚያስችል እቅድ ተዘጋጅቷል። አዳዲስ የኢንቨስትመንት ሕግጋት ወደ ሥራ መግባታቸውን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ይዞታ/አሠራር እየተቀየረ መምጣቱን፣ ተለዋዋጭ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች መታየታቸውን.ወዘተ ተከትሎ ኮሚሽኑ እስካሁን ከነበሩት አሠራሮች የተለዩ ሥርዓቶችን በመቅረፅ ወደ ተግባር ገብቷል›› በማለት ያስረዳሉ።

የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን በማሻሻል፣ የኢንቨስትመንት አቅምና ዕድሎችን በማስተዋወቅ፣ ኢንቨስትመንትን በማሳለጥ፣ የድኅረ ኢንቨስትመንት ድጋፍ በማድረግ፣ የኢንቨስትመንት ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አመራርና አስተዳደር ተግባራትን በማከናወን ረገድ የሚተገበሩት አሠራሮች፤ የወጪ ንግድንና ተኪ ምርትን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ የዘርፎችንና የባለሃብቶችን ትስስር እና የክህሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግርን የማሳደግ ግቦችን ትርጉም ባለው መልኩ ያሻሽላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን በማሻሻል ረገድ በበጀት ዓመቱ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ሕጎችን ወደ ሥራ የማስገባት ተግባር ነው፤ የሎጂስቲክስ ቅልጥፍናን ለማሻሻል የሚያስችሉ አሠራሮችም ወደ ሥራ ይገባሉ።

‹‹ከኢንቨስተሮች ጋር በምናደርጋቸው ውይይቶች እንደተረዳነው ኢንቨስተሮቹን ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል ዋናዎቹ የውጭ ምንዛሪና ተያያዥ ችግሮች እንዲሁም የሎጂስቲክስ ሥርዓቱ ናቸው›› ያሉት ከሚሽነሯ፣ የውጭ ምንዛሪ ችግሩ በብሔራዊ ባንክ እየተሠሩ ባሉ ሪፎርሞች መፍትሔ ያገኛል የሚል እምነት አለን ሲሉም ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የሎጂስቲክስ ሥርዓቱ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማከናወን ማነቆ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ነው፤ በቅልጥፍናም ሆነ በዋጋ ረገድ ብዙ ችግሮች አሉበት። ስለሆነም ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆኑ አሠራሮች ወደ ሥራ ይገባሉ። መንግሥት ኢንቨስተሮች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚሰጣቸው ገንዘብ ነክና ገንዘብ ነክ ያልሆኑ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች አሉ። ተወዳዳሪነትን መገምገምና ከዚህ የተሻለ ተወዳዳሪ ለመሆን ምን ማድረግ እንደሚገባ ጥናት ሠርቶ ምክረ ሃሳብ የማቅረብ እቅድ ተይዟል። እነዚህ ተግባራት ለኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታውን የማሻሻል እቅድ አካል ናቸው።

ወይዘሮ ሐና ባለፈው የበጀት ዓመት የጅምላና ችርቻሮን ጨምሮ ለብዙ ዓመታት ዝግ የነበሩ የንግድ ዘርፎች ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት እንዲሆኑ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ መፈቀዱን አስታውሰው፣ መመሪያው ከወጣ በኋላ ኮሚሽኑ ቅድመ ዝግጅቶችን (መመሪያው ወደ ሥራ የሚገባበትን ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፣ ለሠራተኞች ሥልጠና መስጠት…) ሲያደርግ እንደቆየም ገልጸዋል። ባለሃብቶች ፍላጎቶችን በማሳየታቸው መስፈርቶቹን ማሟላታቸውን በማረጋገጥ ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግ ይገልፃሉ። ስለሆነም ከንግድ ዘርፎች መከፈት ጋር ተያይዞ በ2017 በጀት ዓመት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንደሚጠበቁ ጠቁመዋል።

ባለፈው የበጀት ዓመት የተከናወኑ የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት ክለሳዎችን፣ አዳዲስ ድርድሮችን እና ቀጣናዊና ክልላዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን ወደ ተግባር በመለወጥ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለማግኘትም ታቅዷል። ‹‹ኢትዮጵያ ‹ብሪክስ›ን (BRICS) መቀላቀሏን ተከትሎ ከ‹ብሪክስ› አባል ሀገራት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ የተጀመሩ እንዲሁም ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ተጠቃሚ ለመሆን የሚያግዙ ሥራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

አብዛኞቹ ኢንቨስትመንቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ የጠቆሙት ወይዘሮ ሐና፣ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ስልቶች ከአምራች ዘርፍ ውጭ ያሉትን የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ማበረታታትና ማስፋፋት በሚያስችል መልኩ እንደተቀረፁ ይናገራሉ። ‹‹ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በቀጣናው ብዙ ጂኦፖለቲካል ለውጦችን አስተናግደናል። ስለሆነም አዳዲስ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ዕድሎችን መሠረት ያደረገ የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ያስፈልገናል። የዓለም አቀፍ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ሂደት እየተለወጠ መጥቷል። በተለይም የኮቪድ ወረርሽኝን (COVID-19) ተከትሎ የዓለም አቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት የእሴት ሰንሰለት (Global Value Chain) አሠራር እየተለወጠ ነው። ›› ሲሉም አስገንዝበዋል።

ብዙ አምራቾች የምርት ስፍራዎቻቸውን ወደየሀገሮቻቸው የመመለስ አዝማሚያ ውስጥ ናቸው ያሉት ኮሚሽነሯ፣ ይህን ተከትሎም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየቀነሰ ይገኛል ይላሉ። ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማቆየትና ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተሻለ አገልግሎት መስጠትና የሀገራችንን ሀብቶች ማስተዋወቅ አለብን ብለዋል።

‹‹አሁን ሀገሪቱን የምናስተዋውቅበት መንገድ ከ10 ዓመታት በፊት ያስተዋወቅንበት ከሆነ ውጤታማ መሆን አንችልም። ስለዚህ ይህን ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ለውጥን ታሳቢ ያደረገ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን እቅድ ያስፈልገናል›› በማለት አዳዲስ የኢንቨስትመንት አቅምና ዕድል ማስተዋወቂያ መንገዶች መዘጋጀታቸውን ያስረዳሉ።

እንደወይዘሮ ሐና ገለፃ፣ በበጀት ዓመቱ አዳዲስ ሕግጋትን በመተግበር፣ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ምንጮችን በመጠቀም እና የተሻሻሉ የፕሮሞሽን አሠራሮችን ሥራ ላይ በማዋል አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እንዲሁም ለ341 ፕሮጀክቶች (ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጭ) አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶችን ለመስጠት ታቅዷል። አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያስችሉ የፈቃድ አሰጣጥ፣ የማበረታቻና የክትትል ሥርዓቶች ይተገበራሉ። ባለሃብቶች አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን እንዲያገኙ በመርዳት እና አዳዲስ ዘርፎችን በማልማት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግም ታቅዷል።

ባለፈው የበጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ከባቢን በማሻሻል ረገድ ከተከናወኑ ዐበይት ተግባራት መካከል አንዱ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁና ወደ ሥራ መግባቱ ነው። አዋጁ አዳዲስ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን ይፈጥራል። ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ላይ ተሠማርታ ቆይታለች። በፓርኮቹ ልማት ላይ በተገኙት ውጤቶችና ባጋጠሙት ተግዳሮቶች ላይ ዝርዝር ጥናት ተደርጎ ከፓርኮቹ የተሻለ ውጤት ለማግኘት የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ፀድቋል።

አዋጁ ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን፣ የሎጂስቲክስ እና ከማምረት ውጭ ያሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ለማሳለጥ የሚያስችል ማዕቀፍ ነው። ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላል። የ2017 በጀት ዓመት እቅድም ይህን ተግባር ታሳቢ ያደረገ ነው።

በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ 45 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶችን ለመስጠት ታቅዷል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተመርተው ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች መካከል ትልቁን ድርሻ ከያዘው ከአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ምርት ዘርፍ ባሻገር በሌሎች ዘርፎች የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከር ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት እቅድ ተይዟል።

ከሥራ ፈጠራና ኤክስፖርት በተጨማሪ የትስስር እና የእውቀት ሽግግር ግቦች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅና ለማጠናከር የሚያስችል የመረጃ አሰባሰብና ትንተና ሥርዓት ይተገበራል። በ2017 በጀት ዓመት በትኩረት ከሚከናወኑ ተግባራት መካል አንዱ የመረጃ አሰባሰብና ትንተና ሥርዓትን የማጠናከር ሥራ እንደሆነ ወይዘሮ ሐና ያስረዳሉ።

‹‹እንደሀገር ከኢንቨስትመንት የምንፈልጋቸው ግቦች ኤክስፖርት፣ ሥራ ፈጠራ፣ ትስስር እና የእውቀትና የክህሎት ሽግግር ናቸው። ከእነዚህ መካከል እስካሁን ድረስ የተሻለ መረጃ ያለን በኤክስፖርትና በሥራ ፈጠራ መስኮች ነው። በትስስርና ሽግግር ረገድ ያለን እውቀትና መረጃ በቂ አይደለም›› ያሉት ኮሚሽነሯ፣ ስለዚህ በቀጣይ ዓመታት ለዚህ መሠረት የሚሆን የመረጃ አሰባሰብ ሥርዓት ሊኖረን ይገባል ብለዋል። ‹‹ለሀገራችን ዘላቂ እድገት በሚሆን መልኩ ትክክለኛ እውቀትና ክህሎት እየተላለፈ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለዚህም የመረጃ አሰባሰብና ትንተና ሥርዓትን የማጠናከር ሥራ ትኩረት ያገኛል›› በማለት ያብራራሉ።

በክትትልና ቁጥጥር ረገድ ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ባሉ ፕሮጀክቶች ላይ ይበልጥ ከማተኮር በመሻገር በበጀት ዓመቱ ከፓርክ ውጭ ያሉትን ጨምሮ በ142 ፕሮጀክቶች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ አስፈላጊ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ታቅዷል። ተኪ ምርቶችን የማምረት አቅምን ማሳደግ፣ ከክልሎች ጋር ያለውን ቅንጅት ማጠናከር እና ፕሮጀክቶችን ወደ ምርት ማሸጋገርም በበጀት ዓመቱ ትኩረት የሚቸራቸው ሌሎች ተግባራት ናቸው።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 2 / 2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You