ሲቢኢ ብር ፕላስ- ለቀልጣፋና ምቹ የክፍያ አገልግሎት

ዲጂታል ክፍያ ከጥሬ ገንዘብ ልውውጥ በመውጣት በክፍያ ካርድ፤ ኤሌክትሮኒክ ገንዘብ፤ ገንዘብ በራሳቸው በሚከፍሉ ማሽኖች (ኤ ቲ ኤም)፣ ገንዘብ በሚያስተላልፉ ማሽኖች፣ በሞባይል ስልክ እና በመሳሰሉት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ገንዘብን ማስተላለፍ እና ክፍያ መፈፀም ማለት ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ያብራራሉ።

በዚህ የክፍያ ሥርዓት የሚዘዋወረው ገንዘብ መጠንም በኢትዮጵያ በሁለትና ሶስት እጥፍ እያደገ መምጣቱንም መረጃዎች ይጠቁማሉ። በተለይም በአሁኑ ወቅት የሞባይል ግብይት ከፍተኛ እድገት ማስመዝገብ እንደቻለ ያመለክታሉ። ይህንን ተከትሎ መንግሥት የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት አካታችና በኃላፊነት ስሜት የሚመራ ሥነ ምህዳር እንዲኖረው የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱ ይታወቃል። ስትራቴጂው የተዘጋጀው አካታችና በኃላፊነት ስሜት የሚተገበር የዲጂታል ክፍያ ሥነ ምህዳር መገንባት ለኢትዮጵያ ሕዝብና ኢኮኖሚ እጅግ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ሲሆን፣ በተጨማሪም አስቻይ ሁኔታን በመፍጠር በኩል እምነት በመታመኑ ነው።

የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን መተግበር ግልጽነትና ውጤታማነትን ከማስፈን፣ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ፣ የፋይናንስ አካታችነትና ሁሉን አቀፍ እድገት ከማምጣት አኳያ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል ተብሎ ይታመናል።

በጥሬ ገንዘብ መጠቀምን በመተው ወደ ዲጂታል አማራጭ መሄድ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ያግዛል፣ የሕዝቦችን የኑሮ ሁኔታ የማሻሻል አጋጣሚዎችንም ይፈጥራል። የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ሰነዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የክፍያ ሥነ-ምህዳሩን በማዘመን ውስን የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ ያለውና የፋይናንስ አካታችነቱ የጎለበተ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ፍኖተ ካርታ በመሆን ያገለግላል።

በኢትዮጵያ የዲጂታል ዘዴዎችን ተጠቅሞ የክፍያ ሂደትን ለማቀላጠፍ በሚደረጉ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል። ለዚህም መንግሥት የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባትና ቁልፍ የሆነውን የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት በማዘመን መመሪያና ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ አስቻይ ሁኔታዎች መፍጠሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

አሁን እየተሰራበት ያለው የወረቀት ገንዘብ ልውውጥ ባለበት መቀጠል እንደማይቻል ይታመናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአጠቃቀም ምቹ ቀላል፣ ቀልጣፋና ፈጣን የሆነውን የኦንላይን ክፍያ ድርጅቶች ተግባራዊ እያደረጉ መምጣታቸውም በዚሁ ምክንያት ነው።

ከአካውንት ወደ አካውንት፣ ወደ ዋሌት እና ወደ ሌሎች ባንኮች ገንዘብ ማስተላለፍና በጥቅሉ የኦንላይን ባንኪንግ ሥርዓትን በመዘርጋት በኩል ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከልም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይጠቀሳል። በሲቢኢ ብር አገልግሎቱ በስፋት የሚታወቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎቱን በማስፋት ቀልጣፋ እና ለአገልግሎት ምቹ የሆነውን ሲቢኢ ብር ፕላስን ደግሞ ይዞ መጥቷል።

ባንኩ ሲቢኢ ብር ፕላስ (CBEBirr Plus) በሚል በአዲስ መልክ አሻሽሎ ያቀረበውን የሲቢኢ አገልግሎት ደንበኞች መተግበሪያውን በማውረድ በቀላሉ መጠቀም እንደሚችሉም ባንኩ አስታውቋል። ባንኩ ሲቢኢ ብር ፕላስን በቅርቡ በይፋ ሥራ ባስጀመረበት ወቅት እንዳስታወቀው፤ የሲቢኢ ብር ተጠቃሚዎች ቁጥር ከአስራ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

ባንኩ እንዳስታወቀው፤ የሲቢኢ ብር አገልግሎትን በሰኔ 2009 ዓ.ም እንደ አንድ ዲጂታል የባንክ አገልግሎት አማራጭ አድርጎ የጀመረ ሲሆን፤ አገልግሎቱን በየጊዜው በማሻሻል የተጠቃሚዎችን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ ችሏል።

ባንኩ በይፋ ሥራ ያስጀመረው ‘የሲቢኢ ብር ፕላስ’ መተግበሪያ በርካታ አገልግሎቶችን በማካተት ለአጠቃቀም ቀላል እና ምቹ እንዲሁም ቀልጣፋ ተደርጎ ተሻሽሎ የቀረበ ነው።

ሲቢኢ ብር ፕላስ መደበኛ አካውንትን ከሲቢኢ ብር ጋር ማስተሳሰር የሚያስችል በመሆኑ በቀላሉ ገንዘብ ወደ ሲቢኢ ብር መሳብ፣ የነዳጅ ክፍያን መፈጸም፣ ገንዘብ ለመላክ፣ ማንኛውንም የግዢ ክፍያ ለመፈጸም፣ የተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎችን መፈጸም፣ የኮንዶሚኒየም ብድር ክፍያ መፈጸም፣ የአየር ሰዓት ጥቅል አገልግሎት መግዛት ያስችላል።

ሲቢኢ ብር በሞባይል ገንዘብ ንግድ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የተሰለፈና በዋሌት ቢዝነስ ወደ ገበያ የመጣ ሲቢኢ ብር የዲጂታል ሶሉሽን ምርት ሲሆን፣ ሲቢኢ ብር የተለያዩ የዕድገት ደረጃዎችን እያለፈ የመጣ ሲሆን፤ የገበያ ድርሻውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ፕላት ፎርም ወይም መተግበሪያ ነው። በተለይም በአንዳንድ መስኮች የገበያ ድርሻው በሀገሪቱ የዘርፉ ገበያ እስከ 90 በመቶ የደረሰ ግዙፍ የቴክኖሎጂ አማራጭ ነው። ይህ ተሻሽሎ የቀረበው ሲቢኢ ብር አሁን ላይ ከመደበኛ አካውንት ጋር በመተሳሰር በርካታ አገልግሎቶችን ይሰጣል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰው ኃይል ምክትል ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ እንዳሉት፤ ተሻሽሎ የቀረበው ሲቢኢ ብር በርካታ አዳዲስ አገልግሎቶችን የሚሰጥ፣ የደንበኞችን ጊዜ የሚቆጥብና ምቾታቸውን የሚጠብቁ አማራጮችን ይዞ የቀረበ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀዳሚ ከሆነባቸው አገልግሎቶች መካከል የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ይጠቀሳል። በዚህ አገልግሎትም የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት ያደረጉና በየዘመኑ ሥራ ላይ የዋሉ የባንክ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ያዋሉ የባንክ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል።

ባንኩ በኢንተርኔት፣ በሞባይል፣ ካርድ ባንኪንግ፣ በሞባይል መኒና የዲጂታል ባንኪንግ ክፍያዎችን ተደራሽ በማድረግ በየጊዜው የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች እያሳደገ መጥቷል። አሁን እየቀረበ ባለው የአገልግሎት ምቹነትና አስተማማኝነት የተነሳ የደንበኞችን ቁጥር እያሳደገ መምጣት ችሏል።

የደንበኞች ቁጥር መጨመር ብቻም ሳይሆን፤ በዲጂታል አማራጮች አማካኝነት የሚፈጸመው የገንዘብ ዝውውርና የክፍያ መጠን በእጅጉ እያደገ መጥቷል። በመሆኑም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በባንኩ ከተፈጸመው ከአንድ ነጥብ አምስት ስድስት ቢሊዮን የሚበልጥ የገንዘብ ዝውውር ወይም 31 ትሪሊዮን የሚጠጋ ብር ውስጥ በዲጅታል ባንኪንግ አማራጮች አማካኝነት የተፈጸመው 72 በመቶ ድርሻ ይዟል።

ከዲጂታል ባንኪንግ አማራጮች መካከል የአብዛኛውን ማህበረሰብ አቅምና ፍላጎት ያማከለውና በርካታ አገልግሎቶች የቀረቡበት የሲቢኢ ብር የተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም ሞባይል መኒ አገልግሎት አንዱ መሆኑን አቶ ኤፍሬም ጠቅሰው፣ ከዛሬ ሰባት ዓመት አስቀድሞ የቀረበው ይህ አገልግሎት በተለይም እንደ ውሃ፣ የኤሌክትሪክና ሌሎች መሰል የክፍያ አገልግሎቶችን ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው መክፈል እንዲችሉ በማድረግ ተመራጭ መሆን ችሏል ብለዋል።

ይህም የበርካታ ደንበኞችን ወጪ፣ ጊዜና ድካም በማስቀረት አስተማማኝ አገልግሎት ማቅረብ አስችሏል ሲሉም ተናግረው፣ በዚሁ ቀልጣፋና ለአጠቃቀም ምቹ በሆነው አገልግሎት ከባንኩ ጋር አብረው የሰሩ ተቋማት የአገልግሎት ገቢያቸውን በአግባቡ መሰብሰብ እንዲችሉ በማድረግ ትልቅ አቅም እንደፈጠረላቸውም አስታውቀዋል።

የሲቢኢ ብር አገልግሎት ከተጀመረ ከሁለት ዓመት በኋላ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንደነበሩት ያስታወሱት አቶ ኤፍሬም፤ በቀጣይ ዓመት 189 ከመቶ የሚደርስ አፈጻጸም በማስመዝገብ የተጠቃሚዎቹን ቁጥር ከስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ማድረስ እንደቻለ ተናግረዋል። በዚህ ጊዜ ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችና በሲቢኢ ብር አማካኝነት ይፈጸሙ የነበሩ ግይብቶችና የገንዘብ ዝውውሮች በዓይነትና በመጠን ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸውንም አስታውቀዋል። በመሆኑም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ማጠቃለያ የሲቢኢ ብር ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት ማለትም አገልግሎቱን በተከታታይ የተጠቀሙ ደንበኞችን ቁጥር በእጥፍ በማሳደግ 12 ሚሊዮን ማድረስ እንደተቻለም ተመላክቷል።

የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዳስታወቁት፤ የጥሬ ገንዘብ አልባ ግብይትን ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ለማድረስ የሲቢኢ ብር አገልግሎት ከፍተኛ ሚና መጫወት ባንኩ በጽኑ ያምናል። በአሁኑ ወቅትም የደንበኞችን ፍላጎት በማጥናት እርካታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ሊያደርስ የሚችል የአገልግሎት ማሻሻያን ይዞ ቀርቧል። ይህ የአገልግሎት ማሻሻያም ከUSSD በተጨማሪ በሞባይል መተግበሪያ አማካኝነት የሲቢኢ ብር አገልግሎት የሚሰጥበት ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ይሰጡ የነበሩ የክፍያ የገንዘብ ዝውውር አማራጮችን በማስፋት የተዘጋጀ ነው። በመሆኑም ሲቢኢ ፕላስ ብር ይዟቸው የመጣቸው አማራጮች ከነባር ደንበኞች በተጨማሪ አዳዲስ ደንበኞች ጭምር እንዲጠቀሙ የሚጋብዝ ቀላል፣ ፈጣንና ምቹ አገልግሎት ነው።

ባንኩ ሲቢኢ ፕላስን ይፋ ባደረገበት ወቅት ከተገኙ የሥራ ኃላፊዎች መካከል የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር /ኢንሳ/ ዋና ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ወይዘሪት ትዕግስት ሀሚድ አንዷ ናቸው። እሳቸው እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል ባንኪንግ ሥርዓትን በመሪነት የያዘና የተለያዩ ማሻሻያዎችን አድርጓል፤ መተግበሪያዎችን ሲያስተዋውቅ ቆይቶ፣ በዚህም ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።

ዋና ዳይሬክተሯ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁንም በርካታ አገልግሎቶችን በሲቢኢ ብር ፕላስ ለደንበኞቹ ይዞ ቀርቧል። ይህም በዲጂታል ቴክኖሎጂው ያለና በየጊዜው ማሻሻልን የሚፈልግ ዘርፍ በመሆኑ ነው። ለዚህም ነው ባንኩ በተቋሙ ውስጥ በሚያደርጋቸው ዘመናዊ የትራንስፎርሜሽን ሥራዎቹ ጭምር አንጋፋና ግንባር ቀደም ተቋም ሲሆን፣ ይህንንም በአዳዲስ አገልግሎቶቹ እያስመሰከረ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም የትራንስፎርሜሽኑ አካል የሆነውን የዲጂታል አክሰሰቢሊቲ ስኬት ጉዞውን እያስቀጠለ ለመሄዱ ወደ ሥራ ያስገባው የሲቢኢ ብር ፕላስ ማሻሻያ አንዱ ማሳያ ነው።

ባንኩ እንደ አንድ የፋይናንስ ተቋም የዲጂታል አገልግሎትን ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ ማድረግ የሚጠበቅበት በመሆኑ የሚያቀርበውን ዲጂታል አገልግሎት በየጊዜው በማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። ባንኩ አዲስ ያቀረበው የሲቢኢ ብር ፕላስ መተግበሪያም በሚገባ በባለሙያ ተፈትሾ ደህንነቱና አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ መተግበሪያው በውስጥ አቅም የተሠራ ነው። ይህን የተቋሙን ጥረት አድንቀው፣ በሥራው ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና በማቅረብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

አዲስ የተሻሻለው የሲቢኢ ብር ፕላስ (CBE­Birr Plus) መተግበሪያ ነባሮቹን አገልግሎቶች በማሻሻል እና አዳዲስ አገልግሎቶችን በመጨመር ለአጠቃቀም ቀላል እና ምቹ ሆኖ የቀረበ ሲሆን፤ ደንበኞች አገልግሎቱን ለማግኘት በራሳቸው መመዝገብ የሚያስችላቸው እንደሆነ በወቅቱ ተመላክቷል።

ደንበኞች ተጨማሪ የሲቢኢ ብር ፕላስ አገልግሎቶችን ለመጠቀም ከመደበኛው ሂሳብ ጋር በማስተሳሰር አገልግሎቶቹን ማግኘት እንደሚችሉም በመድረኩ ተጠቁሟል። አገልግሎቱም ደንበኛው ቅርንጫፍ መሄድ ሳያስፈልገው ሲቢኢ ብርን ከመደበኛ ሂሳቡ ጋር በማስተሳሰር ገንዘብ ለመሳብ፣ ነዳጅ ለመክፈል፣ ገንዘብ ለመላክ፣ የተለያዩ የቢል ክፍያዎችን ለመፈጸምና የኮንዶሚኒየም ብድር ለመክፈል፣ እንዲሁም ወደሌሎች ባንኮች ብር መላክ ለመክፈል የሚያስችል ቀላል ቀልጣፋና ምቹ ሆኖ የቀረበ መሆኑም ተጠቁሟል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You