መካከለኛው መደብ ጭቁን ወይስ ሥልጡን?

አንዳንድ ሰዎች የአንድን ሰው አለመሰልጠን ለመግለጽ ‹‹ዝግመተ ለውጡን ያልጨረሰ›› እያሉ ሲሳደቡ እንሰማለን። ስድቡ ነውር መሆኑ እንዳለ ሆኖ ልብ ያልተባለው ነገር ግን የተጠየቅ ስህተት ያለበት መሆኑ ነው። ዝግመተ ለውጥ አያልቅም። የአሁኑ ሆሞ ሳፒያንስ ከአንድ ሺህ፣ ሁለት ሺህ፣ ሦስት ሺህ…. አሥራ ምናምን ሺህ ዓመታት በኋላ ሆሞ ሀቢለስ፣ ሆሞ ኢሬክተስ እንደምንለው የቀደሙ ዝግመተ ለውጥ አይነቶች ይሆናል። ይህ አሁን የምንኖረው ሕይወት (የአውሮፓዎችን ጨምሮ) ‹‹የሰው ልጅ እንዲህም ይኖር ነበር?›› እየተባለ እንደ ኋላቀር የሚታይ ይሆናል።

ይሄ ማለት አሁን ያለነው የሰው ልጆች ሆሞ ሀቢለስን እና ሆሞ ኢሬክተስን እያየን ‹‹እንዴት የሰው ልጅ ከዚህ ደረጃ ተነስቶ እዚህ ላይ ደረሰ?›› እያልን እንደምንገረመው ሁሉ ከአሥራ ምናምን ሺህ ዘመናት በኋላ የሚኖረው የሰው ልጅ ይህን አሁን የተገረምንበትን ቴክኖሎጂ ምናልባትም እኛ የድንጋይ ዘመንን እንደምናየው ሊያየው ይችላል። አስባችሁታል ‹‹ድሮ የሰው ልጅ አውሮፕላን በሚባል ነገር በሰማይ ላይ ይሄድ ነበር›› እያሉ እንደ ኋላቀር ሲያዩት?

በፈረንሳይ ፓሪስ እየተካሄደ ያለው የኦሊምፒክ ውድድር ከመክፈቻው ጀምሮ ብዙ አስገራሚ ነገሮችን አሳይቶናል። በተለይም መክፈቻው ላይ ብዙ ነውር እና ፀያፍ ነገሮች ታይተዋል። የሥልጣኔ ጣሪያ ላይ ናቸው በሚባሉ ሀገራት እንዲህ አይነት ነገሮች በተደጋጋሚ እየታዩ ነው። ለመሆኑ መሠልጠን ማለት ምን ማለት ይሆን? በልማድ በተሰጠው የሰለጠኑ እና ያልሰለጠኑ ብያኔ መሰረት እስኪ ልዩነታቸውን እናነፃፅር።

ከመሰልጠን አንፃር የሰው ልጅ መደብ አለው። አንድ የሚገርመኝ ነገር ግን እጅግ በጣም የሰለጠኑ እና እጅግ በጣም ኋላቀር ናቸው የሚባሉት ወገኖች ሕይወት የሚመሳሰለው ነገር ነው። ጫፍ እና ጫፍ ያሉት እንደገና ይመሳሰላሉ። ከሁለቱ የሚርቀው የመካከለኛው መደብ ነው፤ የመካከለኛው መደብ በሁለቱም አኗኗርና ድርጊት ይገረማል። ሲጀመር ኋላቀርና የሰለጠነ ብሎ የፈረጀውም የመካከለኛው መደብ ሳይሆን አይቀርም። በእርግጥ በጣም የሰለጠኑትም እንደ አፍሪካ ሀገራት ያሉትን በኋላቀርነት ይፈርጃሉ። ልብ ብለን ካየነው ግን መሰልጠን የቱ ነው? ኋላቀርነትስ የቱ ነው? የሚለው ማለቂያ የለሽ ጥያቄ ያስነሳል።

በተለምዶ የተሰጠውን ብያኔ ይዘን የላይኛው መደብ እና የታችኛው መደብ ያላቸውን መመሳሰል ልብ እንበል። ለምሳሌ፤ ከሥልጣኔ የራቁ ናቸው፣ እጅግ በጣም ኋላቀር ናቸው የሚባሉት አካባቢዎች ራቁታቸውን የሚሄዱ ናቸው። ምንም ልብስ የሚባል ነገር ሰውነታቸውን የማይነካው ሀገራትና አካባቢዎች (ለምሳሌ ታንዛኒያ ውስጥ እና አማዞኒያ አካባቢ) አሉ። እነዚህ የተጠቀሱት ጭራሹንም ምንም አይነት ልብስ የማይነካቸው ናቸው። የእነዚህ ወገኖች ሕይወት የሚገለጸው ገና ልብስ የመልበስ ደረጃ ላይ ስላልደረሱ ነው በሚል ነው። አኗኗራቸውም የዘመኑ መለያ የሆኑ መገልገያዎች የሌሉበት ስለሆነ በኋላቀርነት ተይዟል።

በተቃራኒው ደግሞ የሥልጣኔ ጣሪያ ላይ ናቸው በሚባሉት ሀገራት እየሆነ ያለውን ነገር ልብ እንበል። ራቁት መሆን በድጋሚ ፋሽን እየሆነ ነው። ለምሳሌ እንደ ኒዮርክ ባሉ ሀገራት ሙሉ ራቁት የሚኮንባቸው ሪዞርቶች አሉ። ራቁት ማለት ሀፍረተ ሥጋቸውን እንኳን የምትሸፍን እራፊ ጨርቅ ሳይኖር ሙሉ ራቁት ማለት ነው። በመዲናችን አዲስ አበባም ከሰለጠኑት ሀገራት የተኮረጀ የሥልጣኔ መገለጫ ነው ተብሎ የራቁት ጭፈራ ቤቶች ተስፋፍተዋል። የፈረንሳዩ ቴሌቪዥን ፍራንስ 24 ሀፍረተ ሥጋቸው እንዳይታይ በማድረግ ሪዞርቶች ውስጥ ስለሚደረገው የሙሉ ራቁት መዝናናት ዘገባ ሰርቶ ነበር። አስተያየት ሰጪዎች ልብስ እንደማያስፈልግ ሲናገሩ ነበር። የሰጡት አስተያየት ሲጠቃለል፤ ሰውን ከሰው ያበላልጣል፣ ደረጃ ይፈጥራል፣ የሰው ልጅ የተፈጠረው ራቁቱን ነውና ነፃ መሆን አለበት…. የሚሉ ናቸው። ይህ እብደታቸው በራሳቸው ሀገርም ቢሆን አልተወደደም። የሁለቱ (የሰለጠኑ የተባሉትና ያልሰለጠኑ የተባሉት) ራቁትነት ግን የሚታይበት አተያይ ይለያያል። ግን ምን ልዩነት ነበረው?

ሌላው መለያ ደግሞ ሃይማኖት ነው። እጅግ ኋላቀር ናቸው፣ አልሰለጠኑም የሚባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች (ጎሳዎች) የተደራጀና የሚታወቅ ተቋማዊ ሃይማኖት የላቸውም። የሚኖሩት በደመ ነፍስ ነው። በተመሳሳይ እጅግ በጣም የሰለጠኑ ናቸው የሚባሉትም ሃይማኖት የላቸውም፤ እነርሱም የሚኖሩት የዕለት የዕለቱን ነው። ተመራምረው ተመራምረው የፍልስፍና ጥግ ላይ ደረሱ የሚባሉ ሰዎች ልክ አልሰለጠኑም እንደሚባሉት አካባቢዎች ሁሉ ውስብስብ ነገር አያበዙም። የእነርሱ ሲሆን ግን እንደ ፍልስፍና ይቆጠራል።

ባህልና ወግን ከተመለከትንም ተመሳሳይ ነው። እጅግ ኋላቀር ናቸው የሚባሉ ወገኖች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ‹‹ይህ አይደረግም፣ ይህ ነውር ነው…›› የሚባል ነገር ብዙም የለም። በአብዛኞቹ የዓለም ሀገራት ባህል እንደ ነውር የሚታየው ወሲብ ራሱ እንደ ነውር የማይታይባቸው ጎሳዎች አሉ። እንዲያውም በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ወሲብ ነውር የሆነው ከአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት በኋላ ነው የሚሉ መረጃዎችም አሉ። አውሮፓውያን ቀድመው ሰልጥነው እንደ ነውር ማየት ጀምረው ነበር ማለት ነው። በኋላ ደግሞ እንደገና ወደኋላ ተመልሰው በግልጽ ውይይት እንዲደረግበት የሚያስተምሩም እነርሱ ሆኑ።

ልክ እንደዚህ ሁሉ በጣም የሰለጠኑ ናቸው በሚባሉት ሀገራትም ‹‹ይህ አይደረግም፣ ይህ ነውር ነው….›› የሚባል ነገር የለም። በባህልና ወግ በግልጽ የማይነገሩ ነገሮችን ሕጋዊ እስከማድረግ ደረሱ። ሃይማኖትና ባህል የሚባሉ ነገሮች ብዙም ቦታ የማይሰጣቸው ሆኑ። ጭራሽ ይባስ ብለው እንስሳዊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ማስተዋወቅ ጀመሩ። ነፃ አስተሳሰብ፣ ነፃ ሕይወት፣ ነፃ እንቅስቃሴ የሚባሉ ነገሮችን እንደ ዘመናዊነት ማየት የተጀመረው የሰለጠኑ ናቸው በሚባሉት ሀገራት ነው። እነሆ ከእነርሱ በመኮረጅ ጥንት ነፃ የነበሩ ሰዎች እንደገና ደግሞ ወደ ነፃነት እየሄዱ ነው ማለት ነው።

በእነዚህ በሁለቱ መካከል ያለው መደብ ግን ብዙ የሚያነውራቸው ነገሮች አሉት። የሞራል ጥግ ላይ ነኝ ብሎ ያምናል። ያልሰለጠኑ ናቸው የሚባሉ ጎሳዎች ራቁታቸውን መሆናቸውን ከኋላቀርነት ጋር ያያይዘዋል። ሆኖም ግን እነርሱ ይሻሉታል። የሥልጣኔ ጣሪያ ላይ ያሉ ሀገራት የሚያደርጉትን ደግሞ ‹‹ሰይጣናዊ ድርጊት›› በማለት አምርሮ ያወግዘዋል። ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በራሳቸው በአሜሪካና አውሮፓ ሀገራትም አከራካሪ ነው፤ በራቁትና በልቅነት የሚያምኑት ሁሉም አይደሉም፤ በጣም ጥቂቶች ናቸው። መካከለኛው መደብ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ሞራል… የሚባሉ ነገሮች ይገዙታል።

እንግዲህ ሰሞኑን በፈረንሳይ ፓሪስ የኦሊምፒክ ውድድር እየተካሄደ ነው። ከመክፈቻው ጀምሮ ብዙ አስገራሚ ነገሮች ታይተዋል። ብዙ ነውር የሆኑ ነገሮች ታይተዋል። ብዙ የሀገራችን ሰዎች ‹‹መሰልጠን እንዲህ ከሆነ…›› እያሉ ነው። ያንን ድርጊት ‹‹ያልሰለጠኑ›› ናቸው የተባሉ ሀገራት አድርገውት ቢሆን ኖሮ ከኋላቀርነት ጋር ይያያዝ ነበር። ግን ያደረጉት የሥልጣኔ መዳቢዎች ናቸው። ስለዚህ እነርሱ ሲያደርጉት ለምን ኋላቀርነት አይባልም?

ለመሆኑ ግን የመካከለኛው መደብ ሥልጡን ነው ወይስ ጭቁን የሚባለው? የእነርሱ ልቅነት ነፃነት ከተባለ የመካከለኛው መደብ ሥነ ሥርዓት ጭቆና ሊባል ነው? ቅጥ ያጣ ሥልጣኔ ወደ ድንጋይ ዘመን የሚመልስ ከሆነ ይህ አይነት ሥልጣኔ ይቅርብን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You