በ2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ ተጠባቂው የወንዶች 3 ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር ዛሬ ምሽት ይካሄዳል። ኢትዮጵያ በሶስት ጠንካራ የርቀቱ አትሌቶች ትወከላለች። የወርቅ ሜዳሊያውን ለመወሰድም ከሞሮኮና ኬንያዊያን አትሌቶች ጋር የሚያደርጉት ፉክክር በጉጉት የሚጠበቅ ነው።
የማጣሪያ ውድድራቸውን በጥሩ ብቃት በማለፍ ለፍፃሜ የደረሱት አትሌት ለሜቻ ግርማ፣ ሳሙኤል ፍሬው እና ጌትነት ዋለ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳሊያ ለማስመዝገብ ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። በርቀቱ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ለማስመዝገብ በቡድን ሥራ እና በቴክኒክ ከተፎካካሪያቸው የኬንያ እና የሞሮኮ አትሌቶች ጋር ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉም ተብሎ ይጠበቃል።
የወርቅ ሜዳሊያውን ለማስመዝገብ እድል ያለውና ተስፋ የተጣለበት አትሌት ለሜቻ ግርማ ዘንድሮም ከሞሮኳዊው አትሌት ሶፊያን ኤል ባካሊ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል። ወጣቱ አትሌት ለሜቻ በርቀቱ በልምድም ይሁን በቴክኒክ መጎልበቱ እንዳለፉት ዓመታት ለሞሮኮው አትሌት በቀላሉ እጅ ይሰጣል ተብሎ እንዳይጠበቅ አድርጓል። ለሜቻ ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም በኦሊምፒክና በዓለም ቻምፒዮና በዛሬው የትራክ ላይ ባላንጣው ቢሸነፍም የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን በእጁ ይገኛል። ኤል ባካሊ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ድልን ለመድገም የሚሮጥ ሲሆን ለሜቻ ለራሱም ሆነ ለሀገሩ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ የመጀመሪያ የመሆን ጉጉት አለው። የ23 ዓመቱ አትሌት በእድሜና በልምድ ከሚበልጠው ሞሮኮዊ አትሌት የሚገጥመውን ፈተና ባዳበረው ልምድ ታግዞ ወርቁን ለኢትዮጵያ ሊያስገኝ እንደሚችልም ወቅታዊ አቋሙና የከዚህ ቀደም ውጤቶቹ ይናገራሉ።
ሶፊያን ኤል ባካሊ በዚህ ዓመት በጉዳት ምክንያት ሁለት ውድድሮች ብቻ ነው ማድረግ የቻለው። እነሱም በግንቦት ወር በተካሄደው የማራካሽ ዳይመንድ ሊግና በስፔን በተካሄደው የዓለም አቀፍ ሀገር አቋራጭ ውድድር ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀበት ነው። ለሜቻ በበኩሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት በውድድሮች ተወጥሮ በ1500፣ 2000፣ 3000 መሰናክልና በ5000 ሜትር ውድድሮችን በማካሄድ እድገቱን አስመልክቷ። ቶኪዮ ላይ ከኤል ባካሊ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ በመጨረሻም ለጥቂት ተቀደሞ የወርቅ ሜዳሊያውን ቢነጠቅም ብሩን ማሳካቱ አልቀረም።
ለሜቻ በዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ለ25 ዓመታት ማንም ያልደፈረውን ክብረወሰን ከአንድ ደቂቃ በላይ በማሻሻል በእጁ አስገብቷል። በዚህ ርቀት ደግሞ ለ19 ዓመት የቆየውን ክብረወሰንም የግሉ ማድረግ የቻለበትን ታሪክ ሰርተል። በቶኪዮ ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያውን ለመውሰድ 8፡10፡38 የሆነ ሰዓት ፈጅቶበታል። ይህም ወርቁን የወሰደው ኤል ባካሊ ከገባበት ሰዓት 2 ሴኮንድ ከ30 ማይክሮ ሴኮንዶችን ብቻ የዘገየ ሰዓት ነው።
አትሌት ጌትነት ዋለ እና ሳሙኤል ፍሬውም በተጠባቂው ውድድር ጠንካራ ፉክክር ለማድረግ ይሰለፋሉ። ማጣሪያውን በድንቅ ብቃት ካለፈ በኋላ ጉዳት የደረሰበት ሳሙኤል ፍሬው ግን የመወዳደሩ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። ያም ሆኖ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በውድድሩ ሜዳሊያ ለማስመዝገብ ከሚያደርጉት ጥረት ባለፈ ኤል ባካሊን የማዳከም የቤት ሥራ ይኖርባቸዋል። በውድድሩ ብዙ ልምድ ያካበተው ጌትነት ዋለ ባለፈው ቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎው 4ኛ ደረጃን ይዞ ነው ያጠናቀቀው። ሌላኛው የ3 ሺ ሜትር ተወዳዳሪ ወጣቱ አትሌት ሳሙኤል ፍሬው የመጀመሪያው ኦሊምፒክ ውድድሩን የሚያደርግ ሲሆን በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አስመዝግቧል። ሶስቱ አትሌቶች በቅንጅት ሰርተው ከሞሮኮና ኬንያ አትሌቶች የሚገጥማቸውን ፉክክር አሸንፈው ተናፋቂውን የወርቅ ሜዳሊያ እንደሚያስመዘግቡም ይጠበቃል።
የወንዶች 3 ሺ ሜትር መሰናክል በኦሊምፒክ መካሄድ የጀመረው እአአ በ1920 ሲሆን ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ያገኘቸው በ1980ው የሞስኮ ኦሊምፒክ በሻምባል እሸቱ ቱራ አማካኝነት ነው። ለሜቻ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ቶኪዮ ካስመዘገበው የብር ሜዳሊያ ጋር ኢትዮጵያ ሁለት በርቀቱ የኦሊምፒክ ታሪክ በወንዶች ከዓለም 11ኛ ደረጃን ይዛ ትገኛለች።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም