የድንቅነሽ (ሉሲ) ቅሪተ አካል ግኝት ታሪካዊና ለዘርፉ ተመራማሪዎች መነቃቃትን የፈጠረ ስለመሆኑም ይነገራል። የሰው ዘር መገኛ ስፍራን ያመላከተና ሳይንቲስቶችን ለተጨማሪ ምርምሮች ያነሳሳ ነው።
ሳይንስ የዝግመታዊ ለውጥ አመጣጥን ለማጥናት የጥንት ቅሪተ አካላትን በምርምር በማካተት ለማስረጃነት ያውላል። የምስራቅ አፍሪካዋ ኢትዮጵያ ደግሞ ለዚሁ የቅሪተ አካል ጥናት ከሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ተመራጭ ሆናለች። የሉሲ ግኝትም በዚህች ‹‹ምድረ ቀደምት›› ተብላ በምትጠራ ሀገር ውስጥ ከግማሽ ምእተ ዓመት በፊት ተገኝቷል፡፡ ሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠረው ቅሪተ አካል፣ ታላቅ የምርምር ውጤት ከመሆኑም በተጨማሪ ፈር ቀዳጅና የሳይንሱ ዘርፍ ከመላ ምት በዘለለ ርግጠኝነት ላይ እንዲያርፍ ፍንጭ ያስያዘ ተደርጎ የሚቆጠር ነው።
ይህ የተመራማሪዎች ግኝት ኢትዮጵያን ምድረ ቀደምት የሚል ስያሜን ከማሰጠቱም ባሻገር ከመላው ዓለም የሚመጣው ጎብኚ በብሔራዊ ሙዚየም የሚገኘውን ይህን ቅሪተ አካል ለመጎብኘት እንዲመጣ፤ የቱሪስት ፍሰቱም እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ከዚህ ባሻገር ለበርካታ አስርት ዓመታት ተጨማሪ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ለማድረግና ሌሎች መሰል ማስረጃዎችን ይፋ ለማድረግ ታላላቅ የአርኪዮሎጂ ተመራማሪዎች የኢትዮጵያን ምድር እንዲረግጡም አድርጓቸዋል። ይህም የኢትዮጵያን መልካም ስም የገነባ እና የዓለም ትኩረት ወደ ኢትዮጵያ እንዲሆን ያስቻለ ነው።
ተመራማሪዎች ለሰው ዘር አመጣጥ መሠረት የጣለ መሆኑን የመሰከሩለት የድንቅነሽ ግኝት ይፋ ከሆነ እነሆ 50 ዓመታትን (ግማሽ ምዓተ ዓመት) አስቆጥሯል። ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ተመራማሪዎች፣ ልዩ ልዩ የዓለማችን ተቋማት ይህንን አስመልክተው የእዮቤልዩ በዓል ለማክበር በኢትዮጵያ ተሰባስበዋል። ይህን መታሰቢያ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት የሚያስረዱ በርካታ ግኝቶች ስለመኖራቸው በማስረጃ አስደግፎ ለዓለም ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አሳውቋል።
በዓሉ ካሳለፍነው ሳምንት አንስቶ በተለያዩ መርሀ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል። ከእነዚህ ዝግጅቶች መካከል “የድንቅ ግኝት ግማሽ ምዕት ዓመት” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው የድንቅነሽ ቅሪተ አካል የተገኘበት 50ኛ ዓመት የወርቅ እዮቤልዩ ክብረ በዓል ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ይገኝበታል። በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በተካሄደው በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተገኝተውበታል፡፡
ከመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ባሻገር ይህን መታሰቢያ በማስመልከት የምስራቅ አፍሪካ ፖለንትሮፖሎጂስት ማህበር ዓመታዊ ጉባኤውን በአዲስ አበባ አድርጓል። የሉሲ መገኘት የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት ለዓለም ያበሰረና የሰው ልጅ አመጣጥ ጥናትን የትኩረት መስክ ወደ ኢትዮጵያ ያደረገ ክስተት መሆኑንም አመላክቷል።
በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በተጀመረው የኢዮቤልዩ በዓል ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሉሲ (ድንቅነሽ) ግኝት የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነትነት ያረጋገጠ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ድንቅነሽ ድንቅ ናት፤ ከድንቅ ሀገር የተገኘች›› በማለትም የሉሲ መገኘት የሳይንሱን ማኅበረሰብ ብሎም መላውን ዓለም ስለምድራችን እና ስላሳለፈችው የሕይወት መልክ ለማወቅ ያስቻለ መስራች ሁነት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ግኝቱ ብዙ ጥያቄዎችን የመለሰ፣ ብዙ አዳዲስ ጥያቄዎችን ያነሳሳ ሲሆን በጥያቄዎቹም ለብዙ ምርምሮች መነሻ መሆኑ እንደቀጠለ ተናግረዋል።
‹‹ቀደምት የሰው ልጆች መገኛ የሆነችውን ድንቅ ሀገር እንድትጎበኙ ጥሪ አቀርባለሁ›› በማለት ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመላው ዓለም የሚገኙ ሁሉ ቀደምት የሰው ልጆች መገኛ የሆነችውን ድንቅ ሀገር ኢትዮጵያን ሊጎበኙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንቅ ሀገር በሆነችው ኢትዮጵያ በርካታ የዓለም ቅርሶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ይህን መጥቶ መጎብኘት እንደሚያስፈልግ ነው ያመለከቱት።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የተመዘገቡና በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ መስህቦች አሏት፤ ባለፉት 5 ዓመታት በቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ኢንቨስትመንቶችን አከናውነናል ሲሉም ተናግረዋል። ድንቅነሽ የተገኘችበት 50ኛ ዓመት ሲከበርም ኢትዮጵያ እንደ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ያሉ በዓለም ምርጥ የተባሉ የቅሪተ አካላት ግኝት ያላቸው ተመራማሪዎችን የያዘች ሀገር በመሆኗ በቀጣይም በዘርፉ ብዙ ምርምር ይደረጋል ብለዋል።
በመድረኩ የሉሲ ቅሪተ አካልን ያገኙት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆንሰን ክብረ በዓሉን አስመልክቶ ንግግር ካደረጉት መካከል ይገኙበታል። እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ኢትዮጵያ በዓለማችን በበርካታ ጉዳዮች የምትወሳና የምትደነቅ ሀገር ነች። በተለይ ደግሞ የሰው ልጆች አመጣጥ ምን እንደሚመስል በሚያመላክተው የቅሪተ አካል ግኝት ባበረከተችው ታላቅ አስተዋጽኦ በቀዳሚነት እንደምትታወቅም ይናገራሉ። በዚህ ታላቅ ግኝት ላይ ኢትዮጵያ ባላት ግዙፍ አስተዋጽኦ ሁሉም የሰው ልጅ ሊኮራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ድንቅነሽ (ሉሲ) በዓለም በአርኪዮሎጂካል የሰው ልጆች ቅሪት አካል ምርምር ላይ ልዩ ፍላጎት እንዲያደር ተምሳሌት መሆን ችላለች ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ለበርካታ ተጨማሪ ግኝቶች መሰረትና መነቃቃት በመፍጠር ምልክትና መነሻ እንደሆነች ተናግረዋል። ለሳይንስና ፓሊዮ አንትሮፖሎጂ (በሰው ልጅ አመጣጥ የሚያተኩር) ጥናት ላይ ለተሰማሩ ተመራማሪዎችም ድንቅነሽ መነሻ እንደሆነች ይገልፃሉ። በዚህም ተመራማሪዎች በቤተ ሙከራና በመስክ ለሚያደርጓቸው ተደጋጋሚ ምርምሮች እና ይፋ ለሚያደርጓቸው አዳዲስ የሰው ልጅን አመጣጥ የሚጠቁሙ ቅሪተ አካል ግኝቶች ድንቅነሽ ተምሳሌት መሆኗን አስታውቀዋል፡፡
በምድራችን በየትኛውም ቦታና በማንኛውም የአኗኗር ሁኔታ ውስጥ ብንገኝ፣ መልካችን እና ባህሪያችን ቢለያይ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የተገኘችው ሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠረችው የድንቅነሽ ቅሪተ አካል ሁሉም የሰው ልጅ የመጣው ከአንድ የዘር ግንድ መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ይገልፃሉ። ይህ የዘር ግንድም በዚሁ በአፍሪካ (በኢትዮጵያ) ምድር እንደሆነም ያስረዳሉ። በመሆኑም ቅሬተ አካሉ ሁሉም የሰው ልጆች ባለፈው ዘመን የተሳሰሩ፣ በተፈጥሮም አንድ ዓይነት መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ፕሮፌሰር ዶናልድ ገለፃ ፤ ሉሲ ከተገኘች ከ50 ዓመተ በኋላም አስደናቂ ምርምሮችና ግኝቶች ቀጥለዋል። የአሁኑ ለየት የሚያደርገው ደግሞ እራሳቸውና ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች የሚመሩትና የሚሳተፉባቸው ግኝቶች መኖራቸውን ነው። ይህም የሰው ዘር አመጣጥን የሚጠቁም ታላቅ ግኝት መጪው ትውልድ ጥንታዊው የሰው ዘር የነበረበትን ሁኔታ በግልጽ እንዲያውቅ ይረዳዋል። በተጨማሪም ለዚህ ግኝት እውን መሆን አስተዋጽኦ ያበረከተውን ይሄኛውን ትውልድ የሚያመሰግኑበትና የሚኮሩበት እንደሚሆን ተስፋቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ምድረ ቀደምት ካሰኟት ምክንያቶች አንደኛው የሰው ዘር መገኛ መሆኗ ነው ያሉት ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳር ናሲሴ ጫሊ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት፤ ሀገሪቱ ከሰባት ሚሊዮን ዓመት ጀምሮ እስከ 200 ሺህ ዓመታት የተለያዩ የሰው ልጅ ዝርያዎች ሳይቆራረጡ የተገኙባት ብቸኛ ሀገር ነች። በዋናነት ግን የሰው ልጅ አመጣጥ ጥናትን አዲስ መስመር ካስያዙ ግኝቶች መካከል ድንቅነሽ (ሉሲ) ዋነኛዋ ነች።
‹‹የድንቅነሽን 50 ዓመት ግኝት ክብረ በዓል ማክበር ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ እውነተኛዋ የሰው ዘር መገኛ ምድረ ቀደምት ሀገር መሆኗን ለማስገንዘብ ነው›› የሚሉት ሚኒስትሯ፤ የቱሪዝም ብራንዷም ይህንን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህንን ለማስረዳት ከድንቅነሽ /ሉሲ/ ባሻገር በርካታ ግኝቶች እንዳሏትም ይገልፃሉ። ይህንን እውነታም በመሰል መሰናዶዎች ለዓለም ማስገንዘብ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።
ግኝቶቹን በተገቢው መንገድ ሰንዶ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በሙዚየም ውስጥ በማኖር እንዲጎበኝ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት ሚኒስትሯ፣ ይህን መሰል ሁነት በየጊዜው በመፍጠር የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነትን ማስታወስ አስፈላጊ እንደሆነም ያነሳሉ። የድንቅነሽ ቅሪተ አካል የተገኘበት የ50ኛ ዓመት ክብረ በዓልም በቀጣዮቹ ወራት በልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶች እየተከበረ እንደሚቆይ ገልጸዋል።
እንደ መውጫ
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ከተገኘችው ድንቅነሽ (ሉሲ) ባሻገር፣ ኢትዮጵያ እውነተኛዋ የሰው ዘር መገኛ ምድረ ቀደምት መሆኗን የሚያስረዱ በፓሊዮአንትሮፖሎጂ ምርምር የተገኙ ቅሪተ አካሎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የዝግጅት ክፍላችን የሚከተሉትን በአስረጂነት አቅርቧቸዋል።
አርዲፒቴከስ ካዳባ: ከ5.8 – 5.2 ሚሊዮን ዓመት
አርዲፒቴከስ ካዳባ በኢትዮጵያ የመካከለኛው አዋሽ የጥናት ቦታ በ1990 እና 1996 ዓ.ም መካከል ተገኘ። ካዳባ በቻድና ኬንያ ከተገኙት ቅሬቶች ጋር በዓለማችን እጅግ ጥንታዊ የሰው ዘር አውራሽ ቅሬተ አካል በመሆን ይታወቃል። የአርዲፒቴከስ ካዳባ የክራንቻ ጥርሶች በቅርፃቸው ከአርዲፒቴከስ ራሚደስ ይልቅ የቺምፓንዚን ይመስላሉ። አርዲፒቴክስ ካዳባ እና አርዲፒቴከስ ራሚደስ ይኖሩባቸው የነበሩት አካባቢዎች ጫካማ እንደነበሩ አብረዋቸው ከተገኙ የእንስሳት ቅሬቶች በመነሳት ማወቅ ተችሏል። በአፋርኛ ቋንቋ ካዳባ ማለት “ታላቅ አባት” ወይም “የቤተሰብ መሠረታዊ አባል” ማለት ነው።
አውስትራሎፒቴከስ ዴይረሜዳ: ከ3.3 – 3.5 ሚሊዮን ዓመት
ይህ ቅሪተ አካል የፊዚካል አንትሮፖሎጂ ተመራማሪ በሆኑት ዶክተር ዮሐንስ ኃይለ ሥላሴ የሚመራው ዓለም አቀፍ የሳይንስ ተመራማሪዎች ቡድን በጥር 27/2003 ዓ.ም የተገኘ አዲስ የሰው ዘር ዝርያ ነው፡፡ በአፋር ከልል ዋራንሶ-ሚሌ በተባለ መካነ ቅርስ የተገኙት የላይኛው እና የታችኛው መንገጭላ ቅሪተ አካላት አውስትራሎፒተከስ ዴይርሜዳ ተብለው በአዲስ ዝርያነት ተመድበዋል፡፡ ይህ የሰው ዘር ከታዋቂዋ “ሉሲ” ዝርያ አውስትራሎፒቴከስ አፋረንሲስ ጋር አብሮ ይኖር እንደነበር መረዳት ተችሏል። ዝርያው በግንቦት 20 ቀን 2007 ዓ.ም ኔቸር በተሰኘው ዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ መጽሔት እትም ላይ ታትሞ ይገኛል።
አውስትራሎፒቴከስ አናመንሲስ: ከ4.2 – 3.8 ሚሊዮን ዓመት
ዝርያው በኢትዮጵያ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ፈጀጅ በመካከለኛው አዋሽ በ1987 እና 1998 ዓ.ም ተገኝቷል፡፡ አናመንሲስ ከአውስትራሎፒቴከስ ዝርያዎች የመጀመሪያው ነው፡፡ የእግር አጥንቶቹ ከሉሲ ዝርያዎች ከአወስትራሎፒቴከስ አፋረንሰስ ጋር ሲመሳሰሉ የጥርሶቹና መንገጭላው ቅርጽ ከአርዲፒቴከስ ጋር ይመሳሰላል። ይህ የሚያመለከተው አርዲፒቴከስ ራሚደስ በፈጣን ዝግመተ ለውጥ ትላልቅ ጥርሶች እና ወፍራም መንጋጭላ ወዳለው የአውስትራሎፒቴከስ ዝርያ መሸጋገሩን ነው፡፡
ሆሞ ሃቢሊስ: 2.8 – 1.8 ሚሊዮን ዓመት
አሁን ያለውን ዘመናዊ የሰው ዘር ጭምር የሚያጠቃልለው የዚህ ጅነስ ጥንታዊ ዝርያዎች በምስራቅ አፍሪካ በኬንያ፣ በታንዛኒያና በደቡብ አፍሪካ ተገኝተዋል። ምንም እንኳን የተበጣጠሱ ቢሆኑም፣ ከፍተኛ እድሜ ያስቆጠረው “የሆሞ” ጅነስ አባል የተገኘው በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን እድሜውም ከ2.8 እስከ 2.3 ሚሊዮን ዓመት ይደርሳል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የተገኙት ቀደምት ጅነስ ዝርያዎች ሆሞ ሀቢለስ የተባለውን ዝርያ የሚወክሉ ናቸው፤ በአመዛኙም የተሟሉ የጭንቅላት ቅሎች ሲሆኑ፣ እድሜያቸውም በ2.0 እና በ1.8 ሚሊዮን ዓመታት መካከል ነው፡፡
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም