የንባብ ባሕላችን ከሀገር እድገት ጋር ያለው ትስስር

ማንበብ ለአንድ ሀገር ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ የማያውቅ አለ ብዬ አላስብም። ትውልድ ከሚገነባባቸው መልካም እሴቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ጠንካራ የንባብ ባህል ነው። የእያንዳንዳችን ነገ ለመጽሐፍ በሰጠነው ክብርና ዋጋ ልክ የሚመዘን ነው።

ከትላንት እስከዛሬ ስለመጽሐፍና ንባብ ብዙ ተብሏል። ዓለም በሚያነቡ ሰዎች እንደተለወጠችም የምናውቅም ብዙዎች ነን። ታዲያ ለምንድነው የማናነበው? ለብዙ ነገር ጊዜ ሲኖረን እንዴት ለማንበብ የሚሆን ጊዜ አጣን? ይሄን ጥያቄ ሁላችንም ልንመልሰው የሚገባ ነው።

አሁን ላይ ብዙዎቻችን ከእውቀት ሽሽት ላይ ነን። ለሕይወታችን ብሎም ለወጣትነታችን እሴት የሚጨምሩልን መልካም ነገሮች እያሉ በሚጎዱን ነገሮች ላይ የተጠመድን ነን። በሕይወት ውስጥ አብዛኞቹ አደጋዎች ከእውቀት ማነስ የሚመጡ ናቸው። በዛው ልክ በቁጥጥራችን ስር ያደረግናቸው ችግሮቻችን ሁሉ በእውቀታችን ታግለን የጣልናቸውም ስለመሆናቸው ተጠራጣሪ አይኖርም።

እኔን ጨምሮ አብዛኞቻችን ለብዙ ነገር ጊዜ ሲኖረን ለመልካም ነገር ግን ጊዜና ቦታ የሚጠበን ነን። በተለይ ለንባብና ከንባብ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ጸጋዎች ሩቅ ነን። ዛሬ ላይ በብዙ ነገር ጎለን የምንገኘው የሚጠቅመን እያለ በማይጠቅመን ላይ ስለምንለፋ ነው። እስኪ ሥልጣኔ ለእናንተ ምንድነው? የሀገርና የማህበረሰብ እድገትና ሥልጣኔ በምን ይለካል?

ሥልጣኔ ዘርፈ ብዙ መልክ ቢኖረውም አእምሮን በተገቢ መንገድ በመጠቀም የሚመጣ በጎ ውጤት እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። እንዲሁም እውቀትን መሠረት ያደረገ የድንቅ አስተሳሰብና የድንቅ ተግባር ውጤት ነው። ሥልጣኔ በእውቀት በሚመሩ፣ እውቀትን በሚናፍቁ፣ ለእውቀት በሚተጉ ማህበረሰብ የሚፈጠር የመልካም እሳቤ ነጸብራቅ ነው። በምክንያት የተጉ የንቁ ማህበረሰቦች ዐሻራ ነው።

ከጥንት እስከዛሬ ዓለም ሰንኮፏን ጥላ ዛሬ ላይ ተውባ የቆመችው በእውቀት ተመርታ ነው። በሌላ አገላለጽ የትኛውም ሥልጣኔ እውቀትን መሠረት ያደረገ ነው። ራሳችንን የምንፈልግበት ፈልገንም የምናገኝበት አንድ ጥበብ ቢኖር ብስለት ነው። ለራሳችንም ሆነ ለሀገራችን መልካም የምንሆንበት፣ ትውልዱን በአስታራቂ ትርክት የምናስተቃቅፍበት ብዙኀን መር የትስስር ገመድ ሆኖ የሚጠራ ነው።

ሀገርና ማህበረሰብ የግለሰቦች ጥርቅም እንደመሆኑ መጠን የሀገርና ሕዝብ ሥልጣኔ ከግለሰብ ሥልጣኔ የሚጀምር ነው። ግለሰብ ሳይሰለጥን የሚሰለጥን ሀገርና ሕዝብ የለም። እኔና እናንተ ለእውቀትና ለሥልጣኔ ባለን ጉጉት ልክ የሀገራችን እድገትና ሥልጣኔ ይለካል። የዜጎች የንባብ ቅርበት ባለውና በሚመጣው ትውልድ ላይ ያለው አዎንታዊ ዐሻራ በግዝፈት የሚለካ ነው። ሀገር ስትሰለጥን ሳይሆን እኛ ስንሰለጥን ነው ሀገር ፊተኝነት የሚጎበኛት። ለዛ በቀዳሚነት የሚነሳው የዜጎች የእውቀት ትስስር ነው።

የሀገር ሥልጣኔ ከግለሰብ ሥልጣኔ የሚነሳ ነው። የትውልድ ሥልጣኔ ከማህበረሰብ ሥልጣኔ የሚቀዳ ነው። ይሄን እውነት በመሳት የምንማረው ለራሳችን ብቻ የሚመስለን ብዙዎች ነን። የእውቀት አፍ እንደወረርሽኝ ወደሌላው የሚተላለፍ ነው። ማወቅና መረዳት ሀገርን ከድህነት ማህበረሰብንም ከተረጂነት የሚያላቅቅ የእድገትና የመፍትሔ መላ ነው።

ሀገራችንን እየጎዳት ያለው የእያንዳንዳችን እንቢተኝነት ነው። የእኔና የእናንተ እውቀትን ያለ መሻት ችግር ነው ሀገራችንንም ሆነ ሕዝባችንን ወደኋላ እያስቀረው ያለው። በየትኛውም እውቀትና መመዘኛ እዩት የምንፈልገው ነገር ሁሉ በእውቀታችን ውስጥ የሚገኝ ነው።

እውቀት ከተለያዩ ቦታዎች ሊገኝ ይችላል። ቤተሰብ፣ አካባቢ፣ ጓደኛ፣ ትምህርት ቤት እውቀት የምናገኝባቸው ቦታዎች ሲሆኑ በጥረትና በተፈጥሮም የምናገኘው እውቀት አለ። ከዚህ በተጨማሪም በእያንዳንዱ የሕይወት እንቅስቃሴያችን ከምናየው፣ ከምንሰማው፣ ከደረሰብን አጋጣሚ የምንማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ።

ዓለም ራሷ ትምህርት ቤት ናት። ተፈጥሮ ራሱ መምህር ነው። ራሳችንን ለመማር ካዘጋጀን እውቀት የትም አለ። የእውቀት ምንጭ ናቸው ተብለው በብዙዎች ዘንድ ከታመነባቸው ውስጥ አንዱና ዋነኛው ማንበብ ነው። ብዙዎቻችን ማንበብ ትልቅ ሰው ያደርጋል፣ አንባቢዎች መሪዎቻችን ናቸው እየተባልን ያደግን ቢሆንም ጆሮ ዳባ ብለን ከንባብ ተኳርፈን የምንኖር ነን። ለምን የሚለው መጠየቅ ብዙ ምክንያቶችን ቢያስነሳም በዋናነት ግን የተነሳሽነትና የአስተዳደግ ውስንነት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።

አብዛኞቻችን ለመቃም ለማጨስ፣ አልባሌ ነገሮችን ለማድረግ ጊዜ ሲኖረን የእውቀት ሁሉ መሠረት የሆነውን መጽሐፍ ለማንበብ ግን ጊዜ የምናጣ ነን። የሚጠቅመን ነገር እያለ፣ ሕይወታችንን የሚቀይር መልካም አጋጣሚ እያለ ለማይጠቅመንና በሚጎዳን ነገር ላይ የተጠመድን ነን። እያወቁ መሳሳት ሳያውቁ ከመሳሳት በላይ ለሕይወት አደገኛው ነገር ነው። የምንፈልገው ማንኛውም ነገር እውቀታችን ውስጥ ያለ ነው። ሳናነብና ራሳችንን ለእውቀት ሳናዘጋጅ የምንለውጠው አንዳች ነገር የለም።

እውቀት ሕይወትን ቀላል ማድረግ እና ለችግሮቻችን መፍትሔ የምንሰጥበት ነው። እውቀት ነገን የተሻለ ማድረግ ነው። ማንበብ ራስን ማሳደግ፣ አእምሮን ማበልጸግ ነው። ይሄ ሁሉ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ የሚኖረን መልካም ነገር የለም። አንብበን እስካልተለወጥንና ትውልዱ ከመጽሐፍ ጋር ቁርኝትን እስካልፈጠረ ድረስ የእርስ በርስ ትግሎቻችን ማብቂያ አይኖራቸውም። አንባቢ ትውልድ ሰይፍ አያነሳም። በእውቀትና በምክንያት የሚመራ ማህበረሰብ ለእርቅ ካልሆነ ለመለያየት መንገድ አይከፍትም።

ዓለምን የለወጧት የትላንትናዎቹ ጠበብቶች አንባቢዎች ነበሩ። የዛሬዎቹ የእኔና የእናንተ ትውልድም የዓለምን አዳፋ መልክ በንባባቸው የቀየሩ ናቸው። ፍላጎታችን ምንም ይሁን እውቀት ያስፈልገናል። እውቀት ሃሳባችንን የምናክምበት፣ አእምሯችንን የምናጸናበት፣ አለማወቅን የምንገራበት ፍቱን መድኃኒታችን ነው። ውስጣችን ያለው ጽኑ ፍላጎት ይቀጣጠል ዘንድ እውቀት ግድ ይለናል። በተለይ አብሮነት አጥታ በብሔርና በዘር ለምትባላው ሀገራችን በእውቀትና በመረዳት የሚኖር ትውልድ ግድ ይላታል። ሀገራዊ ችግሮች በዘልማድ ሳይሆነው ባወቀና በተረዳ፣ ሁሉን አሰላሳይ በሆነ ማህበረሰብ በኩል አዳፋ ጥብቆዋን የምትቀይር ናት።

ካለእውቀት የምንሄድበት ጎዳና በእንቅፋት የተሞላ ነው። አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ለመገንባት ያለ ጥርጥር እውቀትና መልካም አስተሳሰብ ያስፈልገናል። እውቀትና መልካም አስተሳሰብ የሚገኘው ደግሞ ከማንበብና ራስን ለእውቀት ዝግጁ በማድረግ ነው። ዛሬ ላይ ብዙ ነገሮች እየተበላሹብንና እየፈረሱብን ያሉት ካለ እውቀት በዘልማድ ስለምናደርጋቸው ነው።

የእውቀት ሽግግር የዘልማድ ሽግግርን የሚሽር የአዲስ አተያይ መነሻ ነው። አዲስ አተያይ ደግሞ የተሃድሶና የነፃ መውጫ ሰርጣችን ነው። ከድህነት ነፃ መውጣት እንፈልጋለን። ከጥላቻና ከዘረኝነት መራቅ ህልማችን ነው። በአንድነት ያበረ ኢትዮጵያዊነትን እንሻለን፣ ዘመናዊነትና ሥልጣኔ የቀጣዩ ጊዜ ስማችን እንዲሆን ብርቱ መሻት አለን። እኚህ ሁሉ አሮጌውን ትተን ለአዲሱ ራሳችንን ስንሰናዳ የሚሆኑ ናቸው።

ካለ እውቀት የሚሳካ ግለሰባዊም ሆነ ሀገራዊ ትልም የለንም። ይሄን እውነት በመረዳት ራሳችንን በእውቀት መክበብና ለንባብ ግድ የሚሰጠን ልንሆን ይገባል። ማንበብ ባሕላችን፣ ከባሕልም የትውልዱ መገለጫ እንዲሆን አበክረን መሥራት ይጠበቅብናል። በመቃምና በማጨስ ከመክሰር ባለፈ የምናተርፈው ትርፍ የለም።

በመስከርና በየምሽት ቤቱ በመዞር ህልማችን ይጨልማል እንጂ አይሳካም። አሁን ላይ በብዙ ነገራቸው ስኬታማ የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን በእውቀት የከበቡ ናቸው። ዓለምን በቢሊየነርነት የሚመሯት የምድራችን ባለጸጋዎች ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ አንባቢዎች መሆናቸው የንባብን ዋጋ እንድንረዳ እድል የሚሰጠን ነው።

ሁሉም ባለጸጋና ግለሰቦች ራሳቸውንም ቢዝነሳቸውን ለማሳደግ በወር ሁለትና ከዚያ በላይ መጻሕፍት የሚያነቡ ናቸው። ለምሳሌ ብነግራችሁ በሀብት መጠኑ ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የሚሰለፈው ሽማግሌው ዋሬት ቡፌት የእድሜውን ሰማኒያ ፐርሰንት ያህሉን ያሳለፈው በማንበብ ነበር። በጣም የሚገርመው ደግሞ የመጨረሻው የስኬት ጥግ ላይ ደርሶ ዛሬም ድረስ ማንበቡ ነበር። ‹ሀብታም እንደምሆን ቀድሜ አውቅ ነበር፣ መቼም ቢሆን ለደቂቃ እንኳን ስኬታማ እንደምሆን ተጠራጥሬ አላውቅም የሚለው ሽማግሌው ቡፌት መጽሐፍ ማንበቤ የዛሬውን በሁሉ ነገሩ የተሳካለትን እኔን ፈጥሮኛል ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።

የብልጌትና የቱጃሩን ቤዞስ እንዲሁም የምድራችንን ቁጥር አንድ ባለጸጋ የአለን መስክን ጀርባ ብታጠኑ የስኬታቸው ምስጢር ማንበብ ነው። ሌላው ከታዋቂ ሰዎች የሳምንቱን መጨረሻ በንባብ ለማሳለፍ የማንበቢያ ክፍሉን በላዩ ላይ የሚቆልፈው የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ነው። ያለማመንታት ዓለም ላይ የሁሉም ስኬታማ ሰዎች የስኬት መነሻ እውቀት ነው። ንባብ ነው። ለሚጠቅማቸው ነገር መለፋታቸው ነው። ስኬታማ ሆኖ እውቀት የሌለውና ማንበብን ባህል ያላደረገ ግለሰብ አይገኝም።

በግልጽ አማርኛ አለማንበብ ከስልጣኔ መራቅ ነው። ህልምንና ራዕይን ማጨንገፍ ነው። ይሄ ደግሞ የመጨረሻው የሰውነት ዝቅጠት ነው። አለማንበብ አለማወቅን መምረጥ ነው። አለማወቅ መነሻውም መድረሻውም ደግሞ ድህነት ነው። ከዚህ ዓይነቱ አስከፊ ገመና ራሳችንን ለመጠበቅ ማወቅ፣ መማር፣ ማንበብ፣ መብሰል ማምለጫ መንገዳችን ናቸው።

በእውቀታችን ልናሸንፋቸው እየተገባን ግን ደግሞ ባለማወቅ ተላምደናቸው እየጎዱን ያሉ ብዙ ነገሮች አሉ።

ከነጉድፋቸው በጉያችን ውስጥ የታቀፍናቸው፣ ከመጸየፍ አልፈን ያከበርናቸው፣ ከመናቅም እውቅና የሰጠናቸው ብዙ ነውሮች አሉብን። የማንም ያልሆኑ የእኛ የኢትዮጵያዊያን ብቻ የሆኑ የእልፍ ጉድፎች ሰለባዎች ነን። ይሄ ሁሉ ነውራችን የሚስተካከለው ደግሞ በእውቀት ነው። ይሄ ሁሉ ጉድፋችን የሚጠራው ደግሞ አንባቢ ትውልድ ስንፈጥር ነው። ይሄ ሁሉ መደነቃቀፋችን እልባት የሚያገኘው በእኔና በእናንተ ምክንያታዊ እሳቤ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ትዝብቴን ላንሳ… በየሰፈሩ፣ በየቤቱ በረንዳ ላይ ግሮሰሪና መቃሚያ ቤት ያልሰራ ማን አለ? በየመንገዱና በየጎዳናው ጭፈራ ቤት እና ማሳጅ ቤት ስንሰራ ለአንድ ላይብረሪ ሲሆን ቦታ የምናጣ ነን። በክልልና በዋና ከተማ ጎዳናዎች ላይ ምንም የማይሰሩ ባለቤትነታቸው የማይታወቅ ተጀምረው ሳይጠናቀቁ አስርና አስራ አምስት ዓመት የቆዩ ትላልቅ ፎቆችን ስንገነባ ለሕዝብ ላይብረሪ ሲሆን አሻፈረኝ የምንል ነን። በየቤታችን መደርደሪያ ላይ ብዙ ዓይነት ውስኪና ሻፓኝ ስናስቀምጥ አንድ መጽሐፍ ግን የለም..ለምን?

ሰኔ ሰላሳን ለሀገር አቀፍ የንባብ ቀን መርጠነው ከስም ባለፈ ምንም አላደረግንም። ይሄ ሁሉ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ ትውልድ ለመፍጠርም ሆነ ሀገር ለመገንባት የምንሮጠው ሩጫ አያዋጣንም። ከሁሉ በፊት እውቀት ያለው፣ ምክንያታዊ ትውልድ መፍጠር አለብን። በእኛና ባደጉት ሀገራት መካከል የተፈጠረው የኢኮኖሚና የሥልጣኔ ልዩነት በእውቀት እንጂ በሌላ በምንም የመጣ አይደለም። እውቀት እኔነት የሌለበት ሁሌም ሀገርን የሚያስቀድም የብዙኅነት አጽናፍ ነው። ለሕዝብ ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ለእርቅና ለተግባቦት መንገድ የሚከፍት፣ ለአንድነትና ለአብሮነት የሚተጋ የሥልጣኔ መነሻ ነው።

ብዙሃነት የሌለበት እኔነት አውዳሚ ነው። አጥፊ ነው። እውቀት ይሄን ጽንፍ የረገጠ አስተሳሰብ የሚያስተካክል ነው። እውቀት በእኚህ ሁለት የተለያዩ አመለካከቶች መካከል የቆመ የዳኝነት መስመር ነው። ከሀገርና ከሕዝብ ልቆ ራሱን ያስቀደመ እውቀት የለም። እውቀት ሀገርና ሕዝብን መሠረት ያደረገ የትብብርና የአብሮ መቆም ጽንሰ ሃሳብ ነው። በተቃራኒው አለማወቅና አለማንበብ የእዳና የጥላቻ መንፈስ መፈንጫ ነው።

በእውቀታችን ድህነታችንን ማሸነፍ አለብን። በእውቀታችን ሀገርና ሕዝብን አስቀምጠን ስር በሰደደ ራስ ወዳድነት እኔ የምንለውን ራስ ተኮር አሳቤ ማከም አለብን። ባለማንበብ ያጣናቸውን፣ በእውቀት ማነስ ያሸሸናቸውን ጸዳሎቻችንን መመለስ አለብን። ከግሮሰሪ ይልቅ ላይብረሪ በመክፈት፣ ቤታችን መደርደሪያ ላይ ውስኪ ሳይሆን መጽሐፍ በማስቀመጥ፣ አጉል ልማዳችንን ማስተካከል አለብን።

እናብብ.። ለውጥ ያለው በማንበብ ውስጥ ነው። ሥልጣኔ ፎቅና መንገድ መገንባት አይደለም። ሥልጣኔ ስማርት ስልክና በስማርት ጫማና ልብስ መዘነጥ አይደለም። ሥልጣኔ በእስማርት አስተሳሰብ መዘነጥ ነው። ሥልጣኔ ምክንያታዊ ትውልድ መፍጠር ነው። ዘመናዊነት ሁሉን አቃፊ ሃሳብ ነጸብራቅ ነው። ሥልጣኔ በእውቀት የዳበረ ሚዛናዊ እይታ ነው።

ብዙዎቻችን ከማይጠቅሙን ነገሮች ጋር ተዋደንና ተፋቅረን የምንኖር ነን። ከሚጎዱንና ሕይወታችንን ሊያሳጡን ከሚችሉ መጥፎ ነገሮች ጋር ተቃቅፈን ያለን ነን። በእድሜያችን፣ በወጣትነታችን ብዙ ነገር መሥራት ሲገባን ባለማወቅ ወይም ደግሞ አውቆ ባለመንቃት ጊዜያችንን በከንቱ የምናባክን ነን። ያለማንበብ ልክፍት፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን ያለመሻት፣ እውነትን ያለመፈለግ ታማሚ ነን። ሕይወትን በመረዳት በእውቀትና በምክንያት ከመኖር ይልቅ እንዳው ዝም ብሎ መሽቶ የሚነጋልን ብዙዎች ነን።

ለውጥና ልቀትን፣ ከፍታና ተሃድሶን፣ ብስለትንና ምጥቀትን እንዲሁም ክብርን በማይጨምሩልን ነገሮች ተከበን መኖራችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። በሕይወታችን ያላፈራነው፣ በቅለን ፍሬ አልባ ዛፍ የሆነው ከእውቀት በመኳረፋችን ነው። አድገንና ጎልምሰን ከነህልማችን የተቀበርነው ከእኛ የራቀ የሕይወት ብርሃንን ስላረጨን ነው። እጆቻችን ለልማት፣ አእምሯችን ለለውጥ የሰነፈው በአጉል አመለካከት ነው። ለምንም ነገር እውቀት ያስፈልገናል። ትውልድ እየገደልን የምንፈጥረው ሌላ ትውልድ። ትውልድ የሚፈጠረው በእውቀት ብቻ ነው። እናንብብ።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You