ከዋክብቶች የተፋጠጡበት አጓጊ ፍልሚያ

የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷን አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ከኦሊምፒክ እና ከዓለም ሻምፒዮናዎቹ ፌይዝ ኪፕየጎን እንዲሁም ሲፈን ሀሰን ጋር የሚያገናኘው የሴቶች 5ሺ ሜትር ሴቶች ፍጻሜ፤ በፓሪስ ኦሊምፒክ በጉጉት ከሚጠበቁ ፍልሚያዎች አንዱ ነው። ነገ ምሽት የሚካሄደው ይህ ውድድር በሦስት አትሌቶች መካከል ብቻ የሚካሄድ እስኪመስል ድረስ የዓለም አትሌቲክስ ቤተሰብ ሊመለከተው ጓጉቷል።

ከ5ሺ ሜትር በተጨማሪ በተለያዩ ርቀቶች ለመወዳደር ያለሙት እነዚህ የዓለም ድንቅ አትሌቶች ቀዝቀዝ ብሎ ለጀመረው 33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ ድምቀት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሦስቱ ከዋክብት በሌሎች ርቀቶችም ተጠባቂ ፍልሚያ ቢኖራቸውም፣ የኦሊምፒኩ የመጀመሪያ ውድድራቸው 5ሺ ሜትር ነው። በመሆኑም ከሚገኙበት አስደናቂ ወቅታዊ አቋም ባለፈ በአዲስ ጉልበትና ሞራል እርስ በእርስ በሚገናኙት በዚህ ሩጫ ላይ የሚኖራቸው የእርስ በእርስ ፉክክር እጅግ ፈታኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ባለፉት 12 ወራት አዳዲስና አስደናቂ ውጤቶች ሲመዘገቡባቸው ከቆዩ ርቀቶች መካከል አንዱ የሆነው የ5ሺ ሜትር ሴቶች የርቀቱን የወቅቱን ከዋክብት በታላቁ ኦሊምፒክ ማገናኘቱ አሸናፊውን ለመገመት አዳጋች አድርጋል። የርቀቱ የበላይ በመሆን ለ18 ዓመታት ያህል የዓለም ክብረወሰኑን እየተፈራረቁ የያዙት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው። ባለፈው ዓመት ኬንያዊቷ አትሌት ፌይዝ ኪፕዬጎን በአንድ ሰከንድ አሻሽላ የታሪኩ አካል ለመሆን ብትሞክርም ከሦስት ወራት በላይ ልታቆየው ግን አልቻለችም። የርቀቱ ፈርጥ በሆነችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ክብረወሰኑ ዳግም ወደቤቱ ሊመለስ ችሏል። በአንጻሩ ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሃሰን በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተቀዳጀችውን አሸናፊነት ፓሪስ ላይም ማስጠበቅ ትፈልጋለች። በመሆኑም የነገው ውድድር የኦሊምፒክ ክብር ብቻም ሳይሆን የርቀቱ የበላይነት ፍልሚያም ጭምር እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሦስቱን አትሌቶች ያገናኘው የቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኬንያዊቷ አትሌት የበላይነት ሲጠናቀቅ፤ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰን ደግሞ ተከትላት ነበር የገባችው። እጅግ ጠንካራ ፉክክር በተስተናገደበት በዚህ ውድድር ላይ የ10ሺ ሜትር ቻምፒዮናዋ ጉዳፍም እግሯ ላይ ባጋጠማት ጉዳት ምክንያት 13ኛ ሆና ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። በሻምፒዮናው ላይ ሁለት ሜዳሊያዎችን የማጥለቅ ዓላማ የነበራት ጉዳፍ ባይሳካላትም፤ ፓሪስ ላይ ግን ይህንኑ እውን ለማድረግ ጠንካራ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች። የቶኪዮ ኦሊምፒክ የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው ጉዳፍ በአንጋፋዋ አትሌት መሠረት ደፋር ለንደን ኦሊምፒክ ላይ እአአ በ2012 ከተመዘገበ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ያልተመለሰውን የወርቅ ሜዳሊያ ለመመለስ ተስፋ ተጥሎባታል።

በረጅም ርቀት አትሌቲክስ በተደጋጋሚ ስሟን በክብር ማስነሳት ሰንደቋንም በቀዳሚነት ማውለብለብ የቻለችው ኢትዮጵያ፤ በኦሊምፒክ መድረክ በዚህ ርቀት የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ያገኘችው እአአ 2000 ላይ በሲድኒ ኦሊምፒክ ነው። የአትሌት ጌጤ ዋሚን የነሐስ ሜዳሊያ ተከትሎም አቴንስ ላይ በመሠረት ደፋር የወርቅ እንዲሁም በጥሩነሽ ዲባባ የነሐስ ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል። በቀጣዩ የቤጂንግ ኦሊምፒክ ጥሩነሽ እና መሠረት ተከታትለው ሲገቡ፤ በለንደን ኦሊምፒክ ደግሞ መሠረት የወርቅ፣ ጥሩነሽ የነሐስ ሜዳሊያዎችን አጥልቀዋል። ሪዮ ላይ የኬንያ አትሌቶች የበላይነቱን ሲይዙ አትሌት አልማዝ አያና ነሐሱን ወደሃገሯ ልታመጣ ችላለች። በቶኪዮ እና በፓሪስ ተከታታይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የምትገኘው ጉዳፍም ከቡድን አጋሮቿ መዲና ኢሳ እና እጅጋየሁ ታዬ ጋር በመሆን ለወርቅ ሜዳሊያው ትፎካከራለች።

በጋና የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ሻምፒዮን የሆነችውና የራባት ዳይመንድ ሊግ አሸናፊዋ አትሌት መዲና ኢሳም በመጀመሪያው የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ አዲስ ነገርን ሊያስመለክቱ ይችላሉ ተብለው ከሚጠበቁ ወጣት አትሌቶች መካከል አንዷ ናት። በቡድን ሥራ የምትታወቀው የ10ሺ ሜትር የዓለም ቻምፒዮና ነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቷ እጅጋየሁ ታዬ በበኩሏ፣ ቶኪዮ ላይ አስደማሚ ፉክክር በማድረግ 5ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። በመሆኑም አትሌቷ በዚህ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ሜዳሊያውን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣትና ጠንካራ ፍልሚያ ታደርጋለች።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You