የመስኖ ልማትና የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት

ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በብዙ እየታተረች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት የክረምት ዝናብ ጠብቆ ማምረት ላይ ከመንጠልጠል ይልቅ ትኩረቷን በበጋ መስኖ ስንዴ ላይ በማድረግ ላይም ናት። በተለይ በመስኖ ሥራ ላይ አተኩራ መንቀሳቀስን በመምረጧ ለውጥ ማየት ጀምራለች። ይሁንና ይህ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረግ ጉዞ በአንድ ግለሰብ ወይም በጥቂቶች ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ መቅረት እንደሌለበት የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።

ዛሬ የተለያዩ ሀገራት ሕዝባቸውን ለመቀለብ ሲደክሙ ይስተዋላል። ጥቂት የማይባሉ ሀገራትም ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችን በጥራትና በስፋት ለማምረት የማይጠቀሙት የቴክኖሎጂ አይነት የለም። ይህንን ለማረጋገጥ በሀገራቸው ምንም አይነት ምርት ለማምረት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ሳይኖር በጥቂት መሬትና እጅግ በጣም አነስተኛ በሆነ ውሃ፤ በብዛትና በጥራት በማምረታቸው ሕዝባቸውን ሲቀልቡ ይስተዋላሉ። ከራሳቸውም አልፈው ለሌላው ሀገር የሚተርፉ ሀገራት ስለመሆናቸው በየጊዜው ከሚነገረው መረጃ መረዳት ይቻላል። ከዚህም የተነሳ ጥቂት በማይባሉ ሀገራት ውስጥ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ይበልጥ በመራቀቅ አዳዲስ ጉዳዮችን ለማፍለቅ ደፋ ቀና ማለት እንጂ የበልቶ ማደር ጥያቄ የማይነሳ ጉዳይ መሆን ከጀመረ ከራርሟል።

ታዲያ በኢትዮጵያም ይህን ለማድረግ ችግሩ ምንድን ነው? ኢትዮጵያ የሰፊ መሬት፣ ዓመቱን ሙሉ ያለማቋረጥ የሚወርድ ወንዝ እና የመልካም አየር ንብረት ባለቤት መሆኗ የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህን ጸጋ በመጠቀም ራስን በምግብ ለመቻል የሚያግድ ነገር እንደማይኖርም ይነገራል። በተለይ አሁን የተጀመረው የመስኖ ሥራ ትክክለኛው መንገድ እንደሆነም የሚያመላክቱ አሉ፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ በመስኖ ማልማት የሚያስችላት ምን ምቹ ሁኔታ አለ? ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች ጠይቀናል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህርና የመስኖ ኤክስፐርት በለጠ ብርሃኑ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት አበክራ ካልሠራች በስተቀር ሕዝቧን በትክክል መመገብም አትችልም። መሠረታዊ ከሚባሉት ከየትኞቹም ሀገሮች ከሠሩትና ካደጉት አንጻር የመጀመሪያ ትኩረታቸው የምግብ ሰብል ማምረት ነው። ለዚያ ደግሞ መስኖ ወሳኝ ነው።

እስከ ዛሬ ድረስ ግብርናችን እንደ ሀገር ሲከተል የነበረው በዝናብ ማብቀልን ነው። አሁን ያለው የአየር ንብረት መለዋወጥ ደግሞ በዚያ መልኩ ለመቀጠል የሚያስችል ካለመሆኑም በላይ በዝናብ በማምረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚታሰብ አይደለም። ስለዚህ በተለዋዋጭ የአየር ንብረትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች በዝናቡ ብቻ በዓመት አንድ ጊዜ እያረስን መኖር ወደማንችልበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል። ለዚህ አንደኛው ምክንያት ሕዝባችንም በቁጥር ማደጉ ተጠቃሽ ነው። በዝናብ የሚመረተው ምርታማነትም ቀንሷል። ስለዚህ የግድ ወደመስኖ ልማት መምጣት ያስፈልጋል ሲሉም በለጠ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

እርሳቸው፤ “ወደመስኖ ልማት እንምጣ ሲባል መታየት ያለበት አንዱና ዋናው ነገር ምቹ ሁኔታው ነው” ይላሉ። የመጀመሪው ምቹ ሁኔታ መሬት ነው። ምክንያቱም መስኖ እናልማ ሲባል የሚለማበት መሬት የግድ ነው። በብዙዎች ዘንድ ይነገር የነበረው ኢትዮጵያ ለመስኖ ብዙ ጊዜ የሚመች ቦታ የላትም የሚል ነው። ይህ ግን የተሳሳተ ግንዛቤ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

በለጠ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ከዚህ አንጻር ሲወሰድ ተዳፋቱ፣ ጉብታው፣ ሜዳው እየተባለ ይለያያል እንጂ የግብርና ሚኒስቴር የሚያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በአጠቃላይ ገጸ ምድራችን ወደ 112 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ነው። ከዚያ ውስጥ 74 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ወይም ደግሞ 70 በመቶ አካባቢ የሚለማና ለእርሻ የሚሆን መሬት ነው። ይህንን ያህል መሬት እስካሁን በመጣንበት ዝናብን ብቻ ጠብቆ በማረስ ሊመጣ የሚችል ለውጥ አይኖርም። ይህ ሁሉ መሬት ያላረስነው ሀብታችን ነው፡፡

“የየዓመቱ ሪፖርቶች መለያየት እንደ ተጠበቀ ሆኖ ግን እስከ ዛሬ ያሉት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከ16 እስከ 20 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ማልማታችንን ነው” የሚሉት የመሰኖ ኤክስፐርቱ በለጠ (ዶ/ር)፣ ይህ ማለት ከ74 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ ነው በማለት ይገልጻሉ። ይህ ደግሞ ገና ብዙ ያላለማነው መሬት እንዳለ የሚሳይ ነው ብለዋል።

ስለዚህ ከመስኖ ልማት አንጻር ስንመለከት ይህ መሬት ምንም የተወሳሰበ ቴክኖሎጂ ሳንጠቀም ማልማት የሚያስችለን እንደሆነ ጠቅሰው፤ ቀለል ያለ ቴክኖሎጂ ብቻ በመጠቀም በቀጥታ ሊለማ የሚችለው እንደሆነም አመልክተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት የገመትነው እስከ 20 እና 21 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ብለን ነው። በዚህ መልኩ የተለያዩ ጥናቶችም የየራሳቸውን ግምት አስቀምጠዋል። ይህ ከመሬት አንጻር በመደበኛ የውሃ ፍሰት ሊለማ የሚችል መሬት ማለት ነው። በዚህ መልኩ እስከ ሃያ ሚሊዮን ሔክታር መሬት ማልማት እንችላለን። ይህ ከመሬት አንጻር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ በለጠ (ዶ/ር) ገለጻ፤ በመሠረቱ ሁልጊዜ የመስኖ ልማት ሲነሳ ምቹ ሁኔታዎች ናቸው የሚባሉት መሬትና ውሃ ናቸው። ከዚህ አንጻር ለመስኖ ልማት ሁለተኛ ምቹ ሁኔታ ውሃ ነው። ኢትዮጵያ በተለያየ መልኩ የሚገለጽ የውሃ ሀብት አላት።

አሁን ባለው ሁኔታ ከሆነ ግን ያለው አተያይ ኢትዮጵያ ያላት የውሃ ምንጭ እንጂ የውሃ ሀብት አይደለም። እንዲህ የተባለበት ምክንያት ደግሞ ስላላጠራቀምነው፣ ስላልያዘነውና ስላልተቆጣጠርነው ነው። በአብዛኛው ውሃችን የሚፈሰው በክረምት ወቅት ነው። ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የውሃ ምንጭ በክረምት ወቅት የሚገኝ ነው። በበጋ ወቅት የምናገኘው አነስተኛ ውሃ ነው። ስለዚህ በየጊዜው መጠቀም አንችልም ማለት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛዎቹ ወንዞቻችን ድንበር ተሻጋሪዎች ናቸው። ስለዚህ ውሃን ካላቆርን፣ ካልያዝን እና በግድ ካልተቆጣጠርን በስተቀር ውሃችን የውሃ ሀብት አይሆንም። ውሃ ሀብት እንዲሆን በግድብ መያዝ ይግድ ይላል። በግድብ ከያዝነው አንጻር ሲታይ በጣም አናሳ ነው። አሁን ባለን (በየዓመቱ ታዳሽ የሚሆነው) አነስተኛና መለስተኛ ግድቦች የያዝነው ውሃ ወደ 40 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ብቻ ነው፡፡

በአጠቃላይ በገጸ ምድር ወደ 122 ወይም 134 ቢሊዮን ሜትር ኪየብ ውሃ አለን የሚሉ መረጃዎችና ማስረጃዎች እንዳሉ የሚናገሩት የመስኖ ኤክስፐርቱ፣ አነስተኛውን ማለትም 122 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የተባለውን ቁጥር ወስደን ብንፈትሽ ከዚህ ውስጥ እኛ በፈለግነው መንገድና በፈለግነው ሰዓት ልንጠቀምበት የምንችለው ብለን ያስቀመጥነው ውሃ 40 ሚሊዮኑን ብቻ ነው ይላሉ። ስለዚህ ከዚህ አንጻር በብቃት ሀብት አለን ማለት አያሰኝም። ነገር ግን ሀብታችንን ማደራጀት፣ ማጠራቀምና መቆጣጠር ከቻልን የመስኖ ልማታችንን ለማሳደግ የሚያስችለን የውሃ ሀብት አለን። ስለዚህ ውሃ እና መሬት ካለ መስኖ አለ ማለት ይቻላል።

ከሰሞኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በፓርላማው አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ዘንድሮ ከሃያ አራት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለማረስ እቅድ ተይዟል። ለወጡ እንደመጣ ኢትዮጵያ የምታርስ የነበረው 14 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ነው።

“ዘንድሮ ከተሳካልን በዚህ ላይ 10 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንጨምራለን፡፡” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ከ 35- 40 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማረስ እንደምትችል ተናግረዋል። በኖራ መሬቷን ማከም ከቻለች፣ ውሃ የሌለባቸውን ቦታዎች ውሃ እንዲያገኙ ማድረግ ከቻለች፣ ገና ትልቅ አቅም አላት። ነገር ግን 24- 25 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማረስ ትልቅ እምርታ ስለሆነ የምክር ቤቱ አባላትም ሚናቸውን ከተወጡ በኑሮ ውድነትም በኢኮኖሚ እድገት ላይም ከፍተኛ ለውጥ ልናመጣ እንችላለን፡፡” ብለዋል።

ለመስኖ ልማት በዋነኝነት ምቹ ሁኔታዎች ናቸው የሚባሉት መሬትና ውሃ ናቸው፤ ይህ ደግሞ ትልቁ ጉዳይ ነው ሲሉ የጠቀሱት ደግሞ የመስኖ ባለሙያዎች ናቸው። ከዚህ ወጣ ተብሎ ሲታይ ደግሞ ሌላው የሚያስፈልገው ምቹ ሁኔታ የሰው ሃይል ነው ሲሉ ገልጸዋል። ኢትዮጵ ደግሞ የሰው ሃይል አላት። የእርሻ ልማት ስራዋን በተለይ በመስኖ ስታደርገው በጣም በርካታ ሠራተኞችን መያዝ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አንድ አነስተኛ ምናልባትም እስከ አምስት ሔክታር መሬት ላይ ሊለማ የሚችል የግለሰብን የመስኖ ቦታ ብንወስድ በርካታ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ነው። መሬቱን ከሚያለማው ጀምሮ ዘር እስከሚመርጠው የአግሮኖሚ ባለሙያ፣ ስለአፈር የሚያጠናው ባለሙያ፣ የውሃውን ፍሰት የሚቆጣጠረው ባለሙያ፣ ከዚያ ደግሞ ወደገበያ የሚወስደው የገበያ ባለሙያን ጨምሮ በርከት ያሉ አካላትን የሚያሳትፍ በመሆኑ ሰፊ የሥራ እድል ያለው መስክ ነው ብለዋል። ይህ ሁሉ የሰው ሀብት ደግሞ ኢትዮጵያ አላት። እነዚህን ባለሙያዎች ዩኒቨርሲቲዎቻችን በስፋት እያመረቱ ይገኛሉ። በብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች የመስኖና ተያያዥነት ያለውን ባለሙያ ያስመርቃሉ። ስለዚህ ሌላው ምቹ ሁኔታ የሰው ኃይል ነው። ነገር ግን ትልቁ ችግር የሚባለው በአግባቡ ያለውን የሰው ኃየል ማሰማራቱ ላይ ነው ሲሉ ያብራራሉ።

እንደ ዶክተር በለጠ ገለጻ፤ በሕዝብ ስርጭት አንጻር ሲታይ አበብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወጣት እና ገና በጉልምስና የእድሜ ክልል ውስጥ ያለ ነው። አሁን ያለንበት አማካይ እድሜ ስታቲስቲክ እንደሚያመለክተው ወደ 18 ዓመት ነው። ይም ማለት ደግሞ አብዛኞቹ ልጆች ናቸው ማለት ነው፡። ብዙ ወጣቶች አሉ ማለት ደግሞ በብዙ ማምረት እንችላለን ማለት ነው። ይህ አንዱ መታየት የሚችል ምቹ ሁኔታ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ሊያሠራ የሚችሉ ፖሊሲዎች አሏት። ከሕገ መንግሥቱ ጀምረን እየወረድን ብንሄድ እንድናለማና በምግብ ራሳችንን እንድንችል የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች ናቸው። የበጀት ቀመር ሲደለደል ሁሉ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መካከል አንዱ ነው። ብዙ ጊዜ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ከጤና ቀጥሎ የምግብ ሰብል ማምረት ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ ይህን ሁሉ ሲታይ ምቹ ሁኔታዎች ብዙ ናቸው ያስብለናል ሲሉ አመልክተዋል።

የመስኖና እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር፣ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፎ የመስኖ ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት እንስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን የሚናገሩት ደግሞ በሚኒስቴሩ የመስኖ ምርምር ዴስክ ኃላፊ አቶ ያሬድ ሙላቱ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ አስር ሚሊዮን ሄክታር መሬት ያህል አቅም ቢኖርም በዚህ ዓመት በተደረሰበት ደረጃ በመስኖ ማልማት የተቻለው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሔክታር ያህል መሬት ብቻ ነው፡፡

ከመስኖ ልማት አኳያ ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በመረዳት አንፃር ክፍተቶች አሉ የሚሉት ኃላፊው፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የገፀ ምድር የውሃ ሀብት ቢኖራትም በመስኖ መሠረተ ልማቱ ላይ ሰፊ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ያመለክታሉ። ከእነዚህም መካከል ለአብነት ያህል በአብዛኛው የሀገራችን አካባቢዎች ክረምቱን ተከትሎ ለሶስት ወራት ያህል የሚገኘው የውሃ መጠን ከፍተኛው ሲሆን፣ ይኸውም 70 በመቶውን የሚይዝ ነው። ቀሪዎቹ ዘጠኝ ወራት ደግሞ የውሃ እጥረት የሚከሰትበት ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ከፍ ያለ ስለሆነም የሚገኘው ውሃ 96 በመቶ ያህል ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚፈስ ነው። ትልቁ ተግዳሮት የሆነው አንዱ ይህ ነው ይላሉ። በመሆኑም በመስኖ ዘርፉ የጎረቤት ሀገራትን ተጠቃሚነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሀገራችን መጠቀም ያለባትን መጠቀም ይኖርባታል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ያሬድ እንደሚሉት፤ መስኖ እንደ ሀገር የህልውና ጉዳይ ነው። መስኖ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የግድ አስፈላጊ ነው፤ ይሁንና ይህን የመረዳት ጉዳይ ላይ ዛሬም ቢሆን ያልተፈታ ችግር ነው። ዛሬም የግንዛቤ እጥረት ትልቁ ተግዳሮት ነው። መስኖ ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፤ የህልውና ጉዳይ ነው የሚል ግንዛቤ ሊዳብር የግድ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ተቋማት እና በባለድርሻ አካላት ዘንድ የአቅም እጥረት አለ። ከመንግሥት ተቋማት ጀምሮ መስኖ ላይ እየሠሩ የሚገኙ የልማት ድርጅት ላይ የአቅም እጥረት ይታያል። የግል ዘርፉ ተሳትፎ አነስተኛ ነው። የግል ዘርፉ እንዲያድግ በሚያስችል ደረጃ ባለመደረሱ እስካሁን መስኖ ላይ የግሉ ዘርፍ አቅም በሚፈለገው ልክ መምጣት አልቻለም። እሱን ችግር ለመፍታት ፕሮግራም ተነድፎ፣ ፍኖተ ካርታ ተቀርጾ የመስኖ አቅም ለማሻሻል ጥረት ያስፈልጋል። የሙያ ብቃት እጥረትም ስለሚታይ ተግባር ተኮር እውቀትና ክህሎት እንዲኖር ለማድረግ ሥራ በመሠራት ላይ ይገኛል።

ትልቁ ተግዳሮት ያለንን የመስኖ ሀብት በቁጥር አለማወቅ ነው። እስካሁንም በመንግሥት ተቋምም ሆነ በተለያዩ አካላት የተደረጉ ጥናቶች የተለያዩ ናቸው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ይህንን ችግር ለመፍታተ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው ብለዋል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ መስኖን ለማልማት የሚያስችል የመሬት፣ የውሃ፣ የሰው ኃይልና ማምረት የሚችል አቅም እያላት ራስን በምግብ ለመቻል መታተር የግድ እንደሚላት የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል። ያሉት ምቹ ሁኔታዎች ሁሉ ተደምረው ውጤት በመሆን በምግብ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጉዞ ከፍተኛውን ሚና መወጣት እንዳለበትም አመልክተዋል። ለዚህ ሁሉ ስኬት ግን ግንዛቤው ዳብሮ ትብብሩም ጎልብቶ መታየት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 /2016 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You