
አዲስ አበባ፡– በአዕምሮና በአካል የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር ማይክሮ አልጌን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና የማይክሮ አልጌ ተመራማሪ ዶክተር ሀብቴ ጀቤሳ አስታወቁ፡፡
የማይክሮ አልጌ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሀብቴ ጀቤሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የማይክሮ አልጌ (ስፓይሩሊና) ምርምርና ማምረቻ ማዕከል በባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አማካኝነት ባለፉት ሶስት ዓመታት የምርምርና የማምረቻ ሥራው ሲጠና ቆይቶ ስኬታማነቱ ተረጋግጦ በአዳሚ ቱሉ የግብርና ምርምር ማዕከል ውስጥ ስራው ተጀምሯል፡፡ የዚህ ደቂቅ ህዋስ ሳይንሳዊ አጠራር ስፓይሩሊና የተሰኘ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ተፈላጊና የአዕምሮና አካል መቀንጨርን በከፍተኛ ደረጃ የሚከላከል መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡
የሕፃናትን መቀንጨር ለመቀነስ በተለያዩ ፕሮቲኖች የበለጸገውን ማይክሮ አልጌ በምግብ ውስጥ ጨምሮ መመገብ አስፈላጊ ነው የሚሉት ተመራማሪው፤ ኢትዮጵያ ለማይክሮ አልጌ ምርት ምቹ በመሆኗ በስፋት ማምረት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር የሚረዳ ሲሆን፤ ሕፃናት ከተጸነሱ እስከ አንድ ሺህ ቀናት ውስጥ የተመጣጠነ ምግብ የማያገኙ ከሆነና በተለያዩ ተዋሲያን ስለሚጠቁ የመቀንጨር ችግር እንደሚገጥማቸው አስረድተዋል፡፡ ይህም እንደ ሀገር የአምራች ቁጥር በመቀነስ ሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ የማይክሮ አልጌ ዘርን በማልማት በሀገሪቱ የሚታየውን የመቀንጨር ችግር ለመከላከል ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል፡፡ በምርምር ማዕከሉ የሕፃናት አልሚ ምግቦችን ለማምረት የሚረዳ የማይክሮ አልጌ ዘር እየወጣ ይገኛል፡፡
ከየትኛውም በመሬት ላይ ካለ እህል በላይ በባህር ውስጥ ያሉ ማይክሮ አልጌዎች የበለጠ ንጥረ ነገር አላቸው የሚሉት ተመራማሪው፤መሬት ለበርካታ ሚሊዮን ዓመት በጎርፍ ሲሸረሸርና ሲታጠብ ንጥረ ነገሩ ወደ ሀይቆችና ባህሮች እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ይህም የበርካታ ንጥረ ነገሮች መኖሪያ በሀይቆች ውስጥ በመሆኑ ለማይክሮ አልጌዎች ምግብነት እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
እንደ ተመራማሪው አባባል፤ ማይክሮ አልጌዎች ከ90 በመቶ በላይ ለሰው ልጅ የሚያስፈልገውን የምግብ ንጥረ ነገሮችን በነጠላ ህዋስ የያዘ ብቸኛው ማይክሮ አልጌ ነው፡፡ እንዲሁም በዓለም ላይ አምስቱንም ንጥረ ነገሮች ካርቦሀይድሬት፣ፕሮቲን፣ ሚኒራል፣ፋትና ቫይታሚን የያዘ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ ከ40 ዓመት በፊት ስለ ማይክሮ አልጌ ግንዛቤ ነበር ያሉት ተመራማሪው፤ ይህ እንደ ሀገር ትኩረት በመነፈጉ የዘርፉ ምሁራን ሀገር ለቀው እንዲወጡ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ አሁን ላይ መንግሥት ዘርፉን እየደገፈው በመሆኑ ኢትዮጵያ የማይክሮ አልጌ (ስፓይሩሊና) ምርት ዓለምን በመቀላቀል ላይ እንደምትገኝ ጠቁመዋል፡፡ ይህን ለማስፋትና ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ እንዲሆኑ የግል አልሚዎች በዘርፉ ሊሰማሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30 /2016 ዓ.ም