የአሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ኬንያ አትሌቶች ስኬታማ የሆኑበት የሴቶች 800 ሜትር ውድድር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ ተፎካካሪ አግኝቷል። በተያዘው የውድድር ዓመት ግላስኮው ላይ በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ባልተጠበቀ ሁኔታ የወርቅ ሜዳሊያውን ያጠለቀችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት በፓሪስ ኦሊምፒክም ክስተት ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል። ጥቁሯ እንቁ አትሌት ጽጌ ድጉማ ዛሬ ምሽት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ በርቀቱ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ለማስመዝገብ ትሮጣለች።
በመካከለኛና ረጅም ርቀት ውድድሮች ስኬታማ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በ800 ሜትር እአአ በ2013 በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መድረክ በአትሌት መሐመድ አማን የተገኘው የወርቅ ሜዳሊያ በታሪክ ቀዳሚው መሆኑ ይታወቃል። ተመሳሳይ ድል ለዓመታት ሳይደገም ቢቆይም በርቀቱ ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ ሻምፒዮናዎች ላይ ተፎካካሪ በሆኑ አትሌቶች የዲፕሎማ ደረጃዎች ግን ተመዝግበዋል። በተያዘው የውድድር ዓመት መጀመሪያ ላይ በርቀቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁለተኛው ድል በወጣቷ አትሌት ጽጌ ድጉማ ግላስኮው ላይ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ሲመዘገብ ማንም አልጠበቀም ነበር። ዛሬ ምሽትም በፓሪሱ ኦሊምፒክ 800 ሜትር የኢትዮጵያ በዚህች ወጣት አትሌት ሜዳሊያ ታገኛለች ተብሎ ግምት ተሰጥቷታል።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገኘችው የ23 ዓመቷ ወጣት አትሌት ጽጌ ድጉማ የጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ተቋም ፍሬ እንዲሁም የንግድ ባንክ ክለብ አትሌት ናት። ሃገሯን እአአ በ2017 በአልጄሪያ አዘጋጅነት በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመወከል በ200 ሜትር የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች። በ400 ሜትር ደግሞ ከ2019 እስከ 2022 በተከታታይ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና የሜዳሊያ ባለቤት በመሆን ቆይታለች። በ800 ሜትር ቀዳሚ ውድድሯን በቤልጂየም አድርጋ በአሸናፊነት ስታጠናቅቅ በቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድር 1ደቂቃ ከ59 ሰከንድ ከ66 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ፈጣን ሰዓት በመግባት ቀዳሚ እንደነበረች ይታወሳል። ልቃ በታየችበት የግላስኮው የቤት ውስጥ ዓለም ሻምፒዮናም ውድድሩን ተቆጣጥራ በመሮጥና የመጨረሻውን ዙር በፈጣን አሯሯጧ ልዩነት በመፍጠር 2:01.90 በመሆነ ሰዓት በማሸነፍም ነው የወርቅ ሜዳሊያውን ያጠለቀችው።
የጽጌ ስኬት ከቤት ውጪ በተካሄዱ ውድድሮችም የተመሰከረ ሲሆን ጋና ላይ በተካሄደው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ለሃገሯ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች። ሎስ አንጀለስ ላይ በተካሄደ ሌላ ውድድር ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ብታጠናቅቅም የገባችበት 1:57.56 የሆነ ሰዓት ደግሞ በፍጥነቱ በቀዳሚነት ተመዝግቦላታል። አትሌቷ በኦስሎ እና ዩጂን ዳይመንድ ሊጎች በመሮጥም በውድድር ዓመቱ ከስኬት አልራቀችም። በወጣቱ አሠልጣኝ ዓለሙ ዋቅጅራ የምትሠለጥነው አዲስ ኮከብ ፓሪስ ላይ አንድ ነገር ትፈጥራለች የሚሉ ግምቶች ተበራክተዋል።
በትናንት ምሽቱ ግማሽ ፍፃሜ ማጣሪያ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ የግሏን ፈጣን ሰዓት በ1:58:06 ማስመዝገብ ለዛሬው ፍፃሜ የደረሰችው ወርቅነሽ መለሰ ከተጠባቂ አትሌቶች አንዷ ስትሆን፣ ከፅጌ ዱጉማ ጋር በርቀቱ ታሪክ ለኢትዮጵያ ፍፃሜ መድረሳቸው በራሱ የተለዩ አድርጓቸዋል።
ከአራት ዓመት በፊት ቶኪዮ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችውና በሌሎች ሻምፒዮናዎች ላይም በአስደናቂ አሯሯጧ የምትታወቀው የአሜሪካ ዜግነት ያላት ደቡብ ሱዳናዊቷ አቲንግ ሙ ፓሪስ ላይ አትሮጥም። ይህም ለተፎካካሪዎቿ መልካም ዜና ሲሆን፤ የአሸናፊነት ፍልሚያውም በእንግሊዝ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያዊቷ አትሌቶች መካከል እንደሚሆን ይጠበቃል።
እንግሊዛዊቷ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ኬሊ ሆኪንሰን፤ በዩጂን እና ቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮናዎች ላይም የብር ሜዳሊያ ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው። ኬኒያዊቷ ሜሪ ሞራ ደግሞ በዩጂን የነሐስ ሜዳሊያ ብታጠልቅም በቡዳፔስት ደግሞ የዓለም ሻምፒዮን መሆን ችላለች። ታዲያ ሦስቱ አትሌቶች በተመሳሳይ የእድሜ ክልል ውስጥ ከመገኘታቸውም ባለፈ ያላቸው ፈጣን ሰዓትም እጅግ ተቀራራቢ መሆኑ በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ የወርቅ ሜዳሊያውን አጥልቆ የክብር ባለቤት ለመሆን በመካከላቸው ሊኖር የሚችለው ፍልሚያ ከምሽቱ ተጠባቂ ሁነቶች መካከል አንዱ ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም