አበው ሲተርቱ ‹‹ክፉ ቀን አይምጣ›› ይላሉ፡፡ይህን ያሉት ደግሞ ያለምክንያት አይደለም፡፡በክፉ ቀናት ክፉ የሚባሉ ሰዎች ቢገጥሟቸው እንጂ፡፡ አንዳንዴ በገጠመኝ የሚከሰቱ እውነታዎች ይህን ተረት ደጋግመን እንድናስታውሰው ያስገድዱናል፡፡ አጋጣሚዎቹ እንደ ቃሉ ይዘት ክፉ የሚባል ደረጃ ባያሰጣቸውም ሁኔታዎች ግን ከእዚሁ ሀቅ እንዳንርቅ ያደርጉናል፡፡
የሰሞኑ እውነታ ደግሞ ለዚህ የአበው አባባል ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ እንደሚታወቀው አሁን ላይ በሀገራችን የዶላር ምንዛሪ ዋጋ መጨመሩ ይታወቃል፡፡ እንዲህ መሆኑ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ላይ የራሱ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ግልፅ ነው፡፡
አጋጣሚው ሰበብ የሆነላቸው አንዳንዶች ደግሞ ድርጊታቸው ከታሰበው በላይ ሆኗል፡፡ ከሰሞኑ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀናት ‹‹ሽው›› ማለት የጀመረው መረጃ እንደተራ ነገር የናኘ አልነበረም፡፡ እንዲህ መሰሉን ወዝ ያለው ወሬ ነቅተው የሚጠብቁ ስግብግቦች አጋጣሚውን በደስታ ተጠቅመውበታል፡፡አሁን ላይ በበርካታ አካባቢዎች የሸቀጦች ዋጋ ሰማይ መንካት ጀምሯል፡ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች ሱቆቻቸው ከመሸጫነት ተሻግረው የማከማቻ መደብሮች እየሆኑ ነው፡፡
ትናንት ከሚታወቀው ዋጋ በተጋነነ መልኩ የሚጨምሩ ሸቃጮች ባሉበት ብቻ የሚቆዩ አልሆኑም፡፡ ማግስቱን ሌላ ዋጋ ጨምረው በአዲስ ሂሳብ ይደራደራሉ፡፡ በጉዳዩ ተገርሞ ስለምን የሚል ከተገኘ ደግሞ ማብራሪያ አያጡም፡፡ሰበባቸው ሁሉ የሰሞኑ የዶላር ምንዛሪ ጉዳይ ይሆናል፡፡
ብዙ ነዋሪዎች በሁኔታዎች ተማረዋል፡፡ ደንግጠዋልም፡፡ ዛሬ ያለአንዳች መነሻ አንዷ እንቁላል በአስራአምስት ብር ከተሸጠች ነገ ህይወት በምን መልኩ ሊቀጥል እንደሚችል መገመት አያቅታቸውምና፡፡
መሰረታዊ በሚባሉ የምግብ ፍጆታዎች ላይ የተጋነነ ዋጋ ለመጨመር የተዘጋጁ ስግብግቦች ከሰሞኑ ስራ በዝቶባቸዋል፡፡ ሱቆቻቸውን እያሰፉ፣ቦታ እያደላደሉ ነው፡፡ቀድሞ በተገቢው ዋጋ የገዙትን ዕቃ ደብቀው ለማቆየት እንቅልፍ ካጡ ከራርመዋል፡፡ተፈላጊ ዕቃዎችን በተጠየቁ ጊዜም አንደበታቸው ‹‹የለም›› ለማለት የፈጠነ ነው ፡፡አያገባቸው ገብተው የየዕለቱን የባንኮች የዶላር ዝውውር ማየት የጀመሩም አልታጡም፡፡ በአንድ ኪሎ ምስርና ሩዝ ላይ ዋጋ ለማከል የዶላር ዋጋውን ከፍታ ለማየት ሲሽቀዳደሙ ሀፍረት ይሉትን አያውቁም፡፡
ከሰሞኑ የዘይት፣የምስር የሩዝ ፣ፓስታና ማካሮኒ ዋጋ ከወትሮው ማሻቀብ በተለየ ምክንያት አይደለም፡፡እነዚህን ምርቶች ጨምሮ ሌሎች ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች ሰበባቸው የዶላር ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ይህ ክፋት የሞላበት የግብይት ልማድም በየአጋጣሚው ሲከሰት ተስተውሏል፡፡
ዋጋ ባሻቀበ ነውርነት በሰፋ ቁጥር እንዲህ እንደ አሁኑ የሚመለከታቸው አካላት የነጋዴዎቹን ሱቅ ከጥብቅ ማሳሰቢያ ጋር እያሸጉ፣ ያሳዩናል፡፡ ወቅቱን የመጠነ ዜና ተሰርቶም ወሬው ሲናፈስ ይቆያል፡፡ከጥቂት ጊዚያት በኋላ ግን እሽግ ሱቆች ተከፍተው መደበኛ ስራቸው ይቀጥላል፡፡
አስገራሚው ጉዳይ ይህ መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ነጋዴዎቹ በራሳቸው ይሁንታ ሰማይ ያጎኑት የገበያ ዋጋ አንዳች ለውጥ ሳይኖረው በጅምሩ ይቀጥላል፡፡አሸገናል፣ አስጠንቅቀናል የሚሉ አካላት ሳይቀር በግብይቱ ያመኑበት ይመስል ጣልቃ ገብነታቸው ከስሞ እንጂ ጎልቶ አይታይም፡፡በዚህ ሁሉ መሀል ተጎጂ ሀኖ የሚቀረው ታዲያ ሸማቹ ህብረተሰብ ብቻ ይሆናል፡፡ተጠቃሚው በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚደርስበት የኑሮ ውድነት አቅሙ ይዳከማል፡፡ የኢኮኖሚው ጫና ቀና ብሎ እንዳይሄድ ሰበብ ነውና ለድህነት እጁን ሲሰጥ አይዘገይም፡፡
አብዛኛው ነዋሪ አሁን ላይ በፈታኝ የኑሮ ስጋት ተሸብቧል፡፡ ገና ከጅማሬው ይህ ምልክት መስተዋሉም የነገውን ችግር አስቀድሞ እንዲተነብይ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እንዳሻቸው በሚሆኑ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ መላላቱ ድርጊቱን በስፋት እንዲደጋግሙት ድፍረት ሆኗቸዋል፡፡
እርግጥ ነው ከሰሞኑም በተስተዋለው ሙከራ የአንዳንዶች ሱቅ መታሸጉን ሰምተናል፡፡የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በሰጠው መግለጫም ዶላር ጨመረ በሚል ሰበብ የዋጋ ንረት በታየባቸው 77 የንግድ ድርጅቶች ላይ ሕጋዊ ርምጃ ተወስዷል፡፡ ይህ ብቻውን ግን ስር ለሰደደው አሳሳቢ ችግር በቂ ሆኖ አይገኝም፡፡ ቀጥሎ በሚሆነው ፈጣን መፍትሄ ላይ ተጠቃሚው መልስን ይሻል፡፡
ምንጊዜም ቢሆን ሸማቹ ከኑሮው ጋር የሚመጥን የዋጋ አቅርቦት ያስፈልገዋል፡፡ ጊዜና አጋጣሚን አሳበው ህይወቱን የሚያከብዱበት ስግብግቦችም በሕግ ቢጠየቁለት አይጠላም፡፡ ይህ እውነታ በአግባቡ ያለመተርጎሙ በቀጥታ ተጠቃሚውን ሲጎዳው ቆይቷል፡፡
እስካሁን የነበረው የአገም ጠቀም ርምጃ ለሕገወጦች መበራከት ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ተጠቃሚው ስጋት ቢያድርበት አይፈረድም፡፡ እውነቱን ለመነጋገር አጋጣሚና ሰበብ እየፈለጉ ነዋሪውን በኑሮ ውድነት የሚፈትኑ ስግብግቦች አስተማሪ የሚባል ርምጃ ሲያገኛቸው አይስተዋልም፡፡እንዲያ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ብድግ ብለው በማን አለብኝነት ገበያውን አይዳፈሩም፤ በነዋሪው አቅም አይቀልዱም ነበር፡፡
ማንም እንደሚረዳው ያለአንዳች በቂ አቅርቦት የነጋዴዎች ጎተራ አይሞላም፡፡ተጠቃሚው በሌለበት አግባብም የሻጭ ለዋጩ ህልውና አይቀጥልም፡፡ይህ እውነት ግልጽ ቢሆንም አንዳች አጋጣሚ በተፈጠረ ቁጥር ስግብግቦቹ ነጋዴዎች ትስስሩን ይዘነጉታል፡፡ ታምኖ የሚገዛቸውን ተጠቃሚ ገሸሽ አድርገውም ለራስ ጥቅም ብቻ ይሮጣሉ፡፡አሁንም መንግሥት ሱቆችን ከማሸግና ማስጠንቀቂያ ከመስጠት የዘለለ ርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ እንደዋዛ ተሰቅሎ የሚቀረውን የገበያ ዋጋ በነበረበት ከቀጠለ ግን ሀገር ትጎዳለች፡፡ ኢኮኖሚው ለአንድ ወገን አመዝኖም ኑሮ ፍትሀዊነትን ይነጠቃል፡፡
ብዙዎች እንደሚሉት ዛሬ ላይ እየተስተዋለ ላለው የኑሮ ውድነት መንግሥት የራሱን አማራጭ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ገበያውን በሚደጉሙና ኑሮን በሚያረጋጉ ስልቶች መንቀሳቀስ ካልተቻለ የኑሮ ክብደት ጫናው አይቀልም፡፡አጋጣሚን እየጠበቁ ከሕግ በላይ የሚሆኑ ሕገወጦች በአግባቡ ካልተዳኙ ህይወት ሚዛናዊ አይሆንም፡፡
አሳሳቢውን የምግብ ፍጆታ ጉዳይ እንደመነሻ አወሳነው እንጂ ችግሩ በዚህ ብቻ የሚበቃ አይደለም፡፡ አሁን ላይ ዶላርን አሳበው ንግድን የሚከውኑ አካላት በእጆቻቸው የሚገኙ ማናቸውንም ዕቃዎች በእጥፍ ለመጨመር የሚያግዳቸው አይኖርም፡፡ በተለይ ዕቃዎችን ከውጭ ሀገራት እናስገባለን የሚሉ ወገኖች አፋቸውን ሞልተው ለመናገር አጋጣሚው የሚያግዛቸው ይሆናል፡፡
እነሱን እንደ መነሻ ተከተልን የሚሉ አንዳንዶች ደግሞ የጉልት ፍጆታዎችን ዋጋ ጭምር ከዶላር ጋር ሊያዛምዱ የፈጠኑ ናቸው፡፡ ጉዳዩ በወጉ ያልገባቸው ወገኖች ሳይቀሩ በአጋጣሚ ራስን ለማክበር የሚያደርጉት ሩጫም ከመተዛዘብ ያለፈ ነው፡፡
አግባብነት ያለው የንግድ ሥርዓት ሰፍኖ ሁሉም እንደአቅሙና እንደፍላጎቱ ያድር ዘንድ ሕጋዊነት በወጉ ሊተገበር ይገባል፡፡ኮሽ ባለ ቁጥር ሰበብና አጋጣሚን አስልተው ለመቅደም የሚሮጡ ራስ ወዳዶችም ትርጉም ባለው ሕግ ሊዳኙ ግድ ይላል፡፡
ሀገር የምታድገው፣ኢኮኖሚ የሚልቀው ጥቂቶች በራስ ወዳድነት በልጠው ስለሄዱ አይደለም፡፡ በመተሳሰብ፣በመግባባት የሚዘልቁት ህይወት ፍሬያማ ሲሆን ሁሉም በአቅሙ፣በልኩ የመኖር ዕድል ያገኛል፡፡ለእንደኛ አይነቷ ሀገር የሚበጀው ደግሞ በመተሳሰብ ማደር ሲቻል ብቻ ነው፡፡
አሁንም ጊዜና አጋጣሚን እየጠበቁ ኑሮን በሚያከብዱ ራስወዳዶች ላይ ትርጉም ያለው ሕጋዊ ርምጃ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለሕገወጦቹ ድርጊት ተባባሪ በመሆን ራሳቸውን በሙስና ድርጊት ዘፍቀው ያሉ አንዳንድ አካላት ጭምር በተለየ ዓይን ሊቃኙ ግድ ነው፡፡ ይህ እውነት በግልፅ የሚታይ ሀቅ ነውና፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም