የአፈር አሲዳማነትን የማከም ሥራዎችና የታየ ለውጥ

ለሰው ልጆች ከሚያስፈልጉት ዋና እና መሰረታዊ ነገሮች አንዱ አፈር ነው። የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚሉትም፤ አፈር የሰውም ሆነ የእንስሳት ምግብ የሚጀመርበት ከመሆኑም ባሻገር ያለአፈር ህልውናን ማስቀጠል አዳጋች ነው። ይህ የተፈጥሮ ሃብት በምድር ለሚበቅሉት አዝርዕት ሁሉ መብቀያ፣ ለፍጥረታት ምግብ መገኛ መሆኑን በሚገባ በመገንዘብ ዋጋ ሰጥቶ ደህንነቱን ማስጠበቅ ላይ የተከናወነው ተግባር እምብዛም እንደሆነ እሙን ነው።

አፈር በተለያዩ ምክንያቶች ደህንነቱ ለአደጋ ካለበት ሁኔታ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው። በመሬት መሸርሸር፣ በንፋስና በመሳሰሉት ተጠርጎ እየተወሰደ ያለበት ሁኔታም ለእዚህ ሌላው ማሳያ ነው።

የአፈር ኢሲዳማነት ደግሞ ሌላው ችግር ሆኗል። በሀገራችን አፈርን ከአሲዳማነት መታደግ ባለመቻሉ ሳቢያ ሊታረስ እና ሰብል ሊያበቅል የሚችለው ውስን የመሬት ክፍል ለከፍተኛ ጉዳት ሲዳረግ ይታያል።

ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየውም፤ ግማሽ የሚሆነው የዓለም ክፍል አፈር በአሲዳማነት የተጠቃ ነው። በተለይም እስያ፣ መካከለኛው አፍሪካ፣ ሰሜን አሜሪካና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም አውስትራሊያ በአፈር አሲዳማነት ተጠቅተዋል። በዚህ ችግር የተነሳ ሊታረስ የሚችለው 32 በመቶው መሬት ብቻ ሲሆን፣ የህዝብ ቁጥር እድገት በከፍተኛ ደረጃ በሚጨምርባቸው አካባቢዎች ላይ የአሲዳማነት መጠኑ የከፋ እየሆነ በመምጣቱ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል።

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንዳመለከተው፤ ወደ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር ወይንም አሁን ከሚታረሰው መሬት 43 ከመቶው በአሲዲቲ እየተጠቃ ነው። ሶስት ሚሊዮን ሄክታሩ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ በአሲዲቲ ተጠቅቷል። በዚህ መሬት ላይ ማዳበሪያም መጠቀም ቢቻል በቂ ምርት ሊገኝበት አይችልም።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምርምር ማዕከላት ዳይሬክተርና የአሲዳማ አፈር ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ገረመው ታዬ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያም የአፈር አሲዳማነት በስፋት የሚታየው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባለባቸውና የምግብ እጥረት በሚታይባቸው አካባቢዎች ነው። በሌላ መረጃ እንደተመለከተው ደግሞ ስርጭቱ ደግሞ ከሰሜን ምዕራብ፤ ከመካከለኛው ወደ ምዕራብና ከደቡብ ምዕራብ ወደ ምዕራብ ሲኬድ የአሲዳማ አፈር ጫና እየጨመረ ይሄዳል። የምስራቁ ክፍል የአፈር አሲዳማነት እምብዛም አይታይበትም።

‹‹ከመካከለኛው ወደ ምዕራቡ የሃገራችን ክፍል በተጓዝን ቁጥር የአሲዳማነት መጨመር በከፍተኛ ሁኔታ ይታያል፤ ከዚህ ውስጥ 28 በመቶው በጣም ጠንካራ አሲድ ያለበት ሲሆን፣ 13 ነጥብ ሁለት በመቶው ደግሞ በጣም በከፍተኛ ደረጃ አሲዳማ ሆኖ የኮምጣጣነት መጠኑም ወደ አራት ነጥብ አምስት የሚጠጋ ነው›› በማለት ዶክተር ገረመው ያብራራሉ።

አሲዳማነትን በኢትዮጵያ የከፋ የሚያደርገውም 88 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የሚኖርበት አካባቢ አፈር አሲዳማ መሆኑ ነው የሚሉት ዶክተር ገረመው፤ በተጨማሪም 86 በመቶ የሚሆነው የእንስሳት ሃብት የሚገኝበት አካባቢም በተመሳሳይ መልኩ ችግሩ ጎልቶ እንደሚታይበት ያመለክታሉ።

እንደ ከፍተኛ ተመራማሪው ማብራሪያ፤ አሲዳማነት ያለው አፈር በተለይ ለሰብሎች እድገት ጠንቅ ነው። አሲዳማነት እየተስፋፋ በመጣ ቁጥር ደግሞ ከዚህ ቀደም ይታረስ የነበረው መሬት ሳይቀር ምርታማነቱ እየቀጨጨ ይመጣል፤ አለፍ ሲልም ምንም አይነት ምርት እስካለመስጠት ሊደርስ ይችላል። በተለይም አሲዳማነት ባለባቸው አፈሮች ላይ የሃይድሮጂን ክምችት ከፍተኛ ነው፤ በዚህም ጎጂ የሆነ የአልሙኒየም ንጥረ ነገር በስፋት ይገኛል።

‹‹ይህ አልሙኒየም ደግሞ በአፈር ውስጥ ተከማችቶ መገኘት ለሰብሎች ስር እድገት አደገኛ ነው። እንደፀጉር የቀጠኑ ስሮችን ሳይቀር ያቃጥላል፤ ይገላል›› ሲሉ ያስረዳሉ። በእነዚህ አካባቢዎች ሰብሎች ውሃም ሆነ በቂ ምግብ ቢያገኙም በየጊዜው እየተዳከሙ እንደሚሄዱ ጠቁመው፤ በተቃራኒው ደግሞ አረሞች የሰብሎችን ምግብ በመሻማት የሚፋፉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ያመለክታሉ።

እንደ ዶክተር ገረመው ማብራሪያ፤ በተፈጥሮ ከሚከሰተው የአፈር አሲዳማነት በተጨማሪ የአካባቢው የዝናብና የአየር ሙቀትና ቅዝቃዜ መዛባት የራሱ አስተዋፅኦ አለው። በተለይም ከፍተኛ የዝናብ መጠን ያለባቸው አካባቢዎች የአሲዳማነት ችግር ጎልቶ ይታይባቸዋል። በቆላማና ደረቅ በሆኑ አካባቢዎች የአሲዳማነት ችግር የለም። በመሆኑም የአፈር ውስጥ የዝናብ መጠን መቆጠጠር አዳጋች በመሆኑ የበለጠ ተመራጭ የሚሆነው እንደየአካባቢው የአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ ሰብሎችን ማብቀል ነው።

ከዝናቡ ጋር ተያይዞም ሞቅ ያለ አየር በዝናብ ሲታጀብ ብረት የሆኑ ካልሺየም፣ ፖታሺየም፣ ማግኒዚየም የሚባሉት ንጥረ ምግቦች በቀላሉ በአፈር ውስጥ ሊገቡ ስለሚችሉ ዝናብ ሲጥል ወደ ውስጥ የመስረግና ከሰብሎች የስር እድገት በታች በጣም ርቀው ስለሚሄዱ ለመጠቀም እንደሚያስቸግር ያስረዳሉ። በተቃራኒው ደግሞ በአየር ሙቀትና ቅዝቃዜ እንዲሁም በዝናብ መብዛት ምክንያት እንደ ናይትሮጂን አዮን የሚባሉት መርዛማ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ወደላይኛው የመሬት ክፍል ስለሚቀሩ ለሰብሎች ስር እድገት አስቸጋሪ ይሆናል ሲሉ ያመለክታሉ።

የሰው ልጆችም ለአፈር አሲዳማነት መስፋፋት የራሳቸው አስተዋፅኦ እንዳላቸው ዶክተር ገረመው ይናገራሉ። አብነት አድርገውም ‹‹ብዙውን ጊዜ በምርት ስብሰባ ወቅት የምንመገባቸውን ለይተን ተረፈ ምርቱን ወይም ቃርሚያውን፣ የስንዴ፣ የበቆሎ፣ ገለባና ጭድ እዛው አፈር ላይ መተው ሲጠበቅብን ምንም ሳናስቀር የምናጭደው በመሆኑ የአፈሩን ለምነት የሚጨምሩ ነገሮች እንዲሟጠጡና አሲዳማነት እንዲስፋፋ እናደርጋለን›› ይላሉ። ተረፈ ምርቱ ተመልሶ በአፈሩ ለምነት ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ ሲገባው የሚሰበሰብ በመሆኑ የአፈርን ካርቦን ከመጨመር ይልቅ የሰብል ንጥረ ነገር የሚሳሳበት ሁኔታ ይከሰታል። በተጨማሪም የካርቦን ምጣኔ በአፈር ውስጥ ስለሚዛባ አሲዳማነት እየተስፋፋ ይሄዳል ሲሉ ያብራራሉ።

በመሆኑም አርሶአደሩ ሰብሉን ከነስሩ ነቅሎ ከመውሰድ ይልቅ የተወሰነውን ማሳ ላይ በመተውና ከአፈር ጋር በመደባለቅ የአፈርን ምርታማነት መጨመር እንደሚገባው ያስገነዝባሉ።

‹‹ብዙውን ጊዜ አርሶአደሮች መሬታቸው በአሲዳማነት ሲጠቃባቸው ማዳበሪያ አጥቶ ነው፤ መሬቴን በደንብ ስላላረስኩ ነው ብለው ያስባሉ። ማዳበሪያም ጨምረው፤ ምርጥ ዘርን ተጠቅመው ለምነቱን ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ምርት ከመቀነስ ውጪ ሲጨምር አይታይም›› ሲሉ ከፍተኛ ተመራማሪው ይናገራሉ። በዚህ ችግር ምክንያት ከዚህ ቀደም ምርታማ የሚባሉ አካበቢዎች የተለያዩ ሰብሎችን ማምረት እስከ ማቆም የደረሱበት ሁኔታ መኖሩን ያስረዳሉ።

ለአብነትም የደጋማው የሃገሪቱ ክፍልን ነው የጠቀሱት። ‹‹እነዚህ አካባቢዎች ላይ አሲዳማነት በመብዛቱ ምክንያት ከዚህ ቀደም ይመረትባቸው የነበሩት እንደ ባቄላ፣ አተርና የመሳሰሉ ጥራጥሬ ሰብሎችን ማምረት እየቆመ ነው›› ይላሉ። በተለይ አተር አሲዳማነት በከፋባቸው ቦታዎች ላይ እየተመረተ አለመሆኑን ይናገራሉ። አሲዳማነት ከምርት መቀነስ ባሻገር ሰራም እንዳይበቀል፤ በአፈር ውስጥ የሚኖሩ ነፍሳት ሳይቀሩ እንዲሞቱ በማድረግ ከፍተኛ ጫና እንደሚያስከትል ዶክተር ገረመው ያስረዳሉ።

በሌላ በኩልም የማምረቻ ወጪ፣ ገንዘብና ድካም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር እንደሚያደርግም ነው ያመለከቱት። ‹‹ከዚህ ቀደም ድሮ በተወሰነ የማዳበሪያ መጠን የሚገኘው ምርት አሁን ብዙ ማዳበሪያ መጨመርን ያስከትላል። ይህም የሚሆነው ንጥረ ነገር እጥረትን ስለሚያስከትል ነው›› ይላሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከውጭ የሚገባው የማዳበሪያ መጠን በአብዛኛው ስራ ላይ እንደማይውል ጥናቶችን መሰረት አድርገው ይናገራሉ።

‹‹ባለፉት አራት ዓመታት በአሲዳማ አፈር የምንጠቀመው የማዳበሪያ መጠን በአብዛኛው ስራ ላይ እንደማይውል ጥናቶች ያሳያሉ›› በማለት ይጠቅሳሉ። በእነዚህ ዓመታት በአሲዳማ አፈር ምክንያት አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚሆነው ማዳበሪያ ስራ ላይ አለመዋሉንም ነው ያስገነዘቡት።

ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የአፈር አሲዳማነት በተስፋፋባቸው የሃገሪቱ አካባቢዎች አሲዳማ አፈርን ለማልማት የተለያዩ ተግባሮች እየተከናወኑ ናቸው።

‹‹አሲዳማ አፈር ከታከመ ለስራ አመቺ ነው፤ ደግሞም በዝናብም ሆነ በደረቅ ጊዜ ሊታረስ የሚችል በመሆኑ ብዙ ጉልበት ሳይፈልግ በቀላሉ አልምቶ ማምረት ይቻላል›› ሲሉም ያመለክታሉ።

እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ አሲዳማነትን ከሚያባብሱ ነገሮች አንዱ ጥቅም ላይ የሚውሉ የማዳበሪያ አይነቶች ይጠቀሳሉ። በተለይ አሞኒካል ፈርትላይዘር የሚባሉ ማዳበሪያዎች አሲዳማነትን ስለሚያባብሱ የአፈርን ጤንነት ከመጠበቅ አኳያ የኬሚካል ማዳበሪያ አይደገፍም።

እሳቸው መፍትሄ ያሉትንም አስመልክቶው እንዳስታወቁትም፤ አርሶአደሩ ከኬሚካል ማዳበሪያ ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዞር አለበት። በአንድ ጊዜ ባይሆንም እንኳን በከፊል በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም የሰብል ተረፈ ምርቶችን አሟጦ ከማሳ ላይ ባለመውሰድ የአፈር አሲዳማነት እንዳይበዛ መከላከል ይቻላል። በተጨማሪም ካልሺየም ኦክሳይድን የያዘ ማዳበሪያ ከኖራው ጎን ለጎን መጠቀም ዘላቂነት ያለው ምርት ማምጣትና የአፈሩንም ጤንነት ይዞ መቆየት ያስችላል። ከዚህ ባሻገርም በየቦታው የሚጣለውን የእንሳሳት አጥንት በመፍጨት ለማዳበሪያት መጠቀም ጠቃሚ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎንም የአርሶአደሩን ግንዛቤ መጨመር ይገባል።

በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ላለፉት 12 ዓመታት የአፈር አሲዳማነት ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን በመገንዘብ ምርምሮችና ሙከራዎችን ማድረጉን ከፍተኛ ተመራማሪው ይጠቁማሉ። በዋነኝነትም የግብርና ኖራን ከአፈር ጋር ቀላቅሎ የአፈር አሲዳማነትን ማከም፤ ለሰብሎች ተስማሚ ሁኔታ እንዲፈጠር የማድረግ ስራዎች በሰፊው መሰራታቸውን ያስረዳሉ። ‹‹ይህንን በመስራታችን ለብዙ አርሶአደሮች ተደራሽ አድርገን የተጎዳ አፈር እንዲለማ፤ ምርታማነት እንዲጨምር በተለይ በገብስ በስንዴና በበቆሎ፤ በአኩሪ አተርና በባቄላ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፤እንደሃገር አሲዳማ አፈርን በኖራ የማከም ስራ ከተጀመረ ወዲህ የአርሶአደሩ የምርታማነት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል›› በማለትም ያብራራሉ።

እንደእርሳቸው ገለፃ፤ የግብርና ኖራ በዋነኝነት የሚጠቅመው ማዳበሪያን ለመተካት ሳይሆን የአፈሩን አሲዳማነት ለማከም ነው። በአሲድ ምክንያት ሰብሎችን የሚያቀጭጨውንና በአሲዳማ አፈር ውስጥ የሚገኘውን የአልሙኒየምና የናይትሮጂንአዮን የተባለውን ንጥረ ነገር እንዲቀንስ ያደርጋል። ኖራ የአልሙኒየሙን ወደ ሌላ ንጥረ ነገር ቀይሮ የአፈርን ምርታማነት ከፍ የማድረግ ስራም ይሰራል። ይሄ በመሆኑ የሰብሎች ስር ጎዳት ይቀንሳል፤ በአፈር ውስጥ የጠፋውን ማግኒዢየምና ካልሺየም ይመልሳል። ከዚህም ባሻገር ሰብሉ የተጨመረለትን ማዳበሪያ በአግባቡ ተጠቅሞ የራሱን እድገት የማፋጠን ስራ እንዲሰራ ሚና ይጫወታል።

‹‹የኢንስቲትዩቱ ዋነኛ ተልዕኮ ቴክኖሎጂ ማፍለቅ ነው፤ በዚህ መሰረት ባለፉት 12 ዓመታት የኖራ ቴክኖሎጂን በማፍለቅ በኢንስቲትዩቱ ስር ባሉ 11 ማዕከላት ላይ ለሚገኙ 11ሺ 105 አርሶአደሮች በኩታ ገጠምም ሆነ በሰርቶ ማሳያ በቀጥታ እንዲተዋወቅ ተደርጓል›› ይላሉ። በተጨማሪም በተከናወነው የምርምር ስራ 4ሺ 463 ሄክታር የአርሶአደሩ ማሳ አገግሞ ምርት መስጠት እንዲችል መደረጉን ይጠቁማሉ። ይህም በክልሎች፣ በክልል የግብርና ምርምር ተቋማት፣ ግብርና ቢሮዎች፤ በዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች ተቋማት የተሰራውን አይጨምርም።

አሁን ላይ የግብርና ሚኒስቴር ይህንን መነሻ በማድረግ አሲዳማ አፈርን በኖራ የማከም ተግባርን ከፍተኛ ስራ አድርጎ በክልል ግብርና ምርምር፤ በዞንና በወረዳዎች ላይ እስከ 200 ሺ ሄክታር እንዲታከም እቅድ ይዟል። ለዚህም አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦ እየተሰራ ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ ቅንጅታዊ አሰራር ተግባራዊ መደረጉን ይጠቅሳሉ፤ ‹‹የኖራና የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ተጠቅሞ የአፈርን ምርታማነት ለመጨመር በከፍተኛ ደረጃ እየሰራን ነው። ዘንድሮ በተወሰኑ ማሳዎች ላይ ሰፋ አድርገን በሰርቶ ማሳያ እየሰራን ነው›› ይላሉ። ይህም የተሻለ ምርት እንዲገኝ ከማድረጉም ባሻገር ወጪ ቆጣቢና አርሶአደሩ በቀላሉ ሊጠቀም በሚችለው መልኩ የሚከናወን መሆኑን ያስረዳሉ። በተጨማሪም አሲዳማነት የሚቋቋሙ ሰብሎች ላይ ትኩረት ያደረጉ የምርምር ስራዎች እየሰተሩ መሆናቸውን ያመለክታሉ።

‹‹አሲዳማነትን የሚቋቋሙ ሰብሎችን በመለየት ለአርሶአደሩ የማቅረብ ስራ ይሰራል። ከዚህ ቀደምም አራት አሲዳማነትን የሚቋቋሙ ሰብሎችን አውጥተናል፤ ከእነዚህም ውስጥ አንድ የስንዴ ዝርያና ጣፋጭ የሆነ የግብጦ ዘር አውጥተን አርሶአደሮች በስፋት እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ›› ሲሉ ይጠቅሳሉ። በተጨማሪም በ2016 ዓ.ም አንድ የተልባና አንድ የጎመን ዝርያ ማውጣቱን ይጠቁማሉ። በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ የዘር ማባዛቱን ስራ በመስራት ለገበሬዎች የማስተዋወቅ ስራ እንደሚጀምር ነው ያመለከቱት።

ከዚህ በተያያዘም አንድ የድንች ዝርያም በምርምር ሂደት ላይ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ገረመው፤ በቅርቡ ይወጣል ተብሎ እንደሚጠበቅና ለተጠቃሚዎች የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ኢንስቲትዩቱ በድምሩ ወደ ሰባት ዝርያዎችን ማውጣቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ምርታማነትን የሚያሳድጉና አርሶአደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምር ስራዎችን በማከናወን የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወጣ አስታውቀዋል። እንደሃገርም ዘላቂ የሆነ ምርታማነት እንዲመጣ ከተፈለገ የአፈርን ጤንነት ማስጠበቁ ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You