የሲዳማ ክልል መዲና ሀዋሳ የተሻለ ፕላን ይዘው ከተመሠረቱ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ስሟ ይጠራል፤ ከተማዋ ማራኪ እና ውብ ናት:: መንገዶቿ የተቀየሱበትና የለሙበት ሁኔታም በመንገድ መሠረተ ልማቷ ብዙም የማትታማ አድርጓታል::
የሀዋሳ ሀይቅ፣ የታቦር ተራራና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶቿ ደግሞ የከተማዋ ተጨማሪ ውብቶች ናቸው:: ከተማዋ ወደ ኬንያ የሚወሰደው ዋና አውራ ጎዳና የሚያቋርጣት፣ ግዙፉን የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በርካታ ኢንዱስትሪዎች፣ ትላልቅ ሆቴሎች የከተሙባት እና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መገኛም ናት:: ከሞጆ ሀዋሳ እየተገነባ ያለው የፍጥነት መንገድ፣ የአውሮፕላን ማረፊያዋ ሀዋሳን ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ምርጥ ከተማ ካደርጓት መካከል ይጠቀሳሉ::
የፍቅር ሐይቅ፣ የአሞራ ገደል የመሳሳሉ ቦታዎች ለመዝናኛነት ከሚመርጡ ምቹ ስፍራዎች መካከል ይጠቀሳሉ:: እነዚህን ጨምሮ በመንገድ ዳርቻዎቿና አካፋዮቿ፣ አደባባዮቿ፣ ሌሎች አረንጓዴ ስፍራዎቿ ያለማቻቸው ዛፎች፣ የአበባና የሳር ተክሎች ለነዋሪዎቿ፣ ለእንግዶቿ፣ ለቱሪስቿ እና ለአላፊ አግዳሚው ምቾት የሚሰጡ ተጨማሪ ውብቶቿ ናቸው። ሞቃታማ አየር ንብረቷም ቢሆን የሚወደድላት እንደሆነ ይነገራል::
ከተማዋ የነዋሪዎቿ ብቻም አይደለችም፤ ብዙ ትላልቅ ጉባኤዎችና ዝግጅቶች ይካሄዱባታል:: በሀገር ውስጥና በውጭ ቱሪስቶች በእጅጉ ከሚጎበኙ የሀገሪቱ ከተሞች አንዷ ናት::
ይህች ውብ ከተማ ግን ሙሉ ነኝ ብላ አልተቀመጠችም:: የሲዳማ ክልልና የሀዋሳ ከተማ መሪዎች በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለውን የኮሪደር ልማት ተሞክሮ ቀስመው ከተማዋን ይበልጥ ውብ ለማድረግ ወደ ሥራ ገብተዋል:: በዚህም ከተማዋን ለነዋሪዎቿ፣ ለእንግዶቿ፣ ለቱሪስቶቿ፣ ወዘተ ይበልጥ ምቹ ለሚያደርጋት የኮሪደር ልማት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ።
የሀዋሳ ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ ኢንጂነር ምህረቱ ገብሬ ዶያሞ እንዳሉት፤ የሀዋሳ ከተማ በከተማነት ከተመሰረተችበት ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ በተለይ መሃል ከተማ የሚባለው እና ከተማው የተቆረቆረበት አካባቢ መንገዶች ሰፋፊ እና በፕላን ላይ ተመስርተው የተገነቡ ናቸው::
ይሁንና በማስፋፊያ አካባቢዎች ያለው ህብረተሰብ የሚያቀርበውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ሰፋፊ መንገዶች መገንባት ብቻውን በቂ ሆኖ አልተገኘም:: በዚህ መነሻም ከተማዋን ለማስፋፋት ባለፉት አሥር ዓመታት የከተማ ማሻሻያ ፕላን መሰራቱን አስገንዘበዋል።
ጥናቶችን በማካሄድ፣ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት፣ ከተማዋን ይበልጥ ለነዋሪዎቿ፣ ለጎብኚዎችና ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት አማራጮችን እውን የማድረግ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠውን የኮሪደር ልማት ተሞክሮ በመውሰድ በሀዋሳም ተግባራዊ ወደ ማድረግ መገባቱን አስታውቀዋል።
ኢንጂነሩ እንዳብራሩት፤ የከተማዋ ኮሪደር ልማት ሥራ በማስፋፊያ አካባቢዎች መንገዶችን የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነበት ይገኛል፤ በመሀል የከተማዋ ክፍል ደግሞ ለእግረኞችና ለሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች የሚሆኑ መንገዶች፣ የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ግንባታዎችም እየተካሄዱ ናቸው::
ለከተማዋ ውበትን የሚጨምሩ የመብራት ዝርጋታዎች፣ የአጥር፣ የሕንፃ ከፍታ እና ጥራት ደረጃዎች ወጥተው ግንባታው እየተካሄደ ይገኛል። የኮሪደር ልማቱ ከከተማዋ መዋቅራዊ እቅድ ጋር ተያይዞ የሕንፃ ከፍታ ጉዳይ አብሮ ይከለሳል። የሕንፃ ቀለምም በተመሳሳይ በወጣለት ደረጃ መሠረት ይከናወናል።
የከተማዋ ኮሪደር ልማት ሥራ በሁለት ይከፈላል:: የመጀመሪያው በከተማዋ ውስጣዊ ክፍል ያሉ መንገዶችን በተወሰነ መልኩ የማስፋት ሥራ ይከናወናል። ከተማን በመገንባት ሂደትም እንዲሁ መሠረተ ልማቶች መሟላት አለባቸው። ልማቱ የብዙሃን ትራንስፖርትን ማስተዋወቅን፣ ለዚህም የአውቶብስ ፌርማታዎች፣ ከሞተር ነፃ ወይም ጪስ አልባ ትራንስፖርት መንገድ መገንባትና የትራንስፖርት አገልግሎቱን ማበረታታትንም ያካተተ ነው። ከተማዋ በብስክሌት ተጠቃሚዎች ብትታወቅም፣ ለዚያ ምቹ መንገድ አልነበራትም:: በመሆኑም ሰፋፊ የእግረኛና የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች መንገዶች እና የአረንጓዴ ስፍራዎች ልማትንም ያካትታል።
የአስፓልት መንገዶቹ በራሳቸውም ሰፋፊ ቢሆኑም የትራንስፖርት ሲስተሙ የተሳለጠ እንዲሆን የሚያደርግ ሥራ ግን ይሰራል። የትራፊክ መብራቶችና ሌሎች የትራንስፖርት መቆጣጠሪያ ሥርዓቶችና ሌሎች ዘዴዎች ይዘረጋሉ:: ይህም ከተማዋንም ስማርት ከተማ ለማድረግ የሚከናወነውን ተግባር ታሳቢ ያደረገ ነው።
እሳቸው እንዳሉት፤ ለኮሪደር ልማቱ በዋናው የከተማ ክፍል ወደ አራት መንገዶች ተመርጠዋል። የመጀመሪያው ደቡብ ስፕሪንግ ከሚባለው እስከ ሻፌታ አደባባይ ያለው መንገድ ነው። ሁለተኛው ከሻፌታ አደባባይ በተለምዶ ፍቅር ሀይቅ አካባቢ ያለው አደባባይ፤ ከዚህ አደባባይ እስከ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ያለው ሱሙዳ አደባባይ የሚደርስ ነው።
ሶስተኛው የኮሪደር ልማቱ የሚመለከተው መንገድ ከገብርኤል ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ወይም ከሱሙዳ አደባባይ በሳውዝ ስታር ሆቴል አድርጎ እስከ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚወስደውን መንገድ ነው። አራተኛው ደግሞ ፤ ከፒያሳ ዳሽን ባንክ ጀምሮ ከአዳሪ ሆስፒታል አጠገብ እስከ ሞቢል ይዘልቃል።
እነዚህ አራት በኮሪደር ልማቱ የተለዩ መንገዶች መስፋት አለባቸው ያሉት ኢንጂነር ምህረቱ፤ እነዚህ መሠረተ ልማቶች በኮሪደር ልማቱ ዲዛይን መካተት አለባቸው ተብሎ መለየታቸውን አመላክተዋል።
ኢንጂነር ምህረቱ፤ ሁለተኛው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ክፍል በከተማዋ የማስፋፊያ አካባቢዎች የሚካሄደው መሆኑን ጠቁመዋል:: በማስፋፊያ አካባቢዎች ያሉት መንገዶች ጠባብ ናቸው። ለምሳሌ ጨፌ በሚባልበት አካባቢ ከቱላ ክፍለ ከተማ እስከ 50 ሜትር ድረስ መሠረታዊ የከተማዋን ደረጃ የሚመጥኑ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉላቸው ተብለው አሥር መንገዶች ተለይተዋል። ከእነዚህም ቅድሚያ በመስጠት ሶስት መንገዶች እየተሠሩ ናቸው።
ከእኚህ መንገዶች አንደኛው ከዲ.ኤም.ሲ እስከ ጨፌ፣ ሁለተኛው በጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በቢጂአይ አድርጎ ጨፌ፣ ሶስተኛው ከሼል፣ በቴክኖሎጂ ካምፓስ አድርጎ እስከ ጨፌ የሚወስዱት ናቸው። በእነዚህ ሦስቱ መንገዶች የሚገኙ የልማት ተነሺዎችም ተለይተዋል። በአጠቃላይ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎች ተጠቅመው በሕግ እና በአዋጅ መሠረት እያንዳንዱ የልማት ተነሺ ተገቢውን የካሳ ክፍያ እና ምትክ መሬት እንዲሰጠው የውሳኔ ሃሳብ መቅረቡን አስታውቀዋል።
እንደ ኢንጂነር ማብራሪያ፤ የከተማዋ የኮሪደር ልማት ከሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ፕሬዚዳንት ይፋ ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል። ከመምቦ የትራፊከ መብራት መስቀለኛ መንገድ እስከ ሪፈራል ድረስ ያለው አንድ ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት 140 ሚሊዮን ብር በሚደርስ ወጪ የሚገነባ ይሆናል:: ሥራውም በተስፋዬ ጸጋዬ ጠቅላላ ተቋራጭ የሚካሄድ ሲሆን፣ ተቋራጩ የሚሰራው የመንገድ ዳርቻ ልማት ይሆናል።
ግንባታውም ቀን ከሌሊት በፍጥነትና በጥሩ ደረጃ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ግንባታውንም በሶስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸዋል። የዚህ ፕሮጀክት አጠቃላይ ስፋት 31 ሺህ ካሬ ሜትር ያህል ነው ብለዋል።
ሌላው በተመሳሳይ ቀን ሥራው ይፋ የተደረገው እና በህብረተሰብ ተሳትፎ የሚሰራው፤ ከዲኤምጂ እሰከ ሀዋሳ ጨርቃጨርቅ፣ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ፓርክ ፊት ለፊት እስከ ታቦር ሴራሚክ ድረስ ስድስት ነጥብ ሶስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ድረስ ያለው ነው። ይህም አጠቃላይ 330 ሺህ ካሬ ሜትር አካባቢ የሚደርስ ስፋት አለው:: የዚህም የዲዛይን ሥራ ተጠናቅቋል።
እያንዳንዱ በዚያ አካባቢ የሚገኝ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ፊት ለፊቱን እንዲያለማ ዲዛይን ተሰጥቶታል፤ እነሱም ዲዛይኑን ተቀብለው እያለሙ ይገኛሉ። ለሀዋሳ ኮሪደር ልማት የቴክኒክ ኮሚቴና አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ክትትል እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።
ኢንጂነር ምህረቱ እንዳሉት፤ በከተማዋ መሠረተ ልማቶች ሲገነቡ አንደኛው መሠረተ ልማት የሚገነባው አካል ሌላው የገነባውን መሠረተ ልማት የሚጎዳበት ሁኔታ ነበር። ለምሳሌ የውሃ መስመር ሲዘረጋ፤ አስቀድሞ የተዘረጋ የመብራት መስመርን የሚጎዳበት ሁኔታ ስለነበር በተለይ መንገድ ላይ ብዙ ጉዳቶች ሲደርሱ ቆይቷል።
በዚህ በኮሪደር ልማቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ የሚመሩት አብይ ኮሚቴ በተለይ ቴሌ፣ መብራት ኃይል እና ውሃ የመሠረተ ልማት ዘርፎች በተገኙበት እየተናበቡ ከመሥራት አኳያ አቅጣጫ ተቀምጦ እና ከስምምነት ላይ ተደርሶ በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል። ለምሳሌም ከመምቦ እስከ ሪፈራል ባለው የኮሪደር ልማት ሥራ የመንገድ ዳርቻ ሥራ ላይ ተቋማት ቅንጅታዊ ሥራቸውን በተግባር አሳይተዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በእግረኛ እና የብስክሌት መሄጃ መንገዶች ላይ የሚገኙ ምሰሶዎችን አንስቶ በዲዛይኑ መሠረት አዳዲስ ምሰሶዎችን እየተከለ ይገኛል። ኢትዮ-ቴሌኮም እንዲሁም የውሃ ዘርፍ ተቋም ባለሙያ መድበዋል:: በሥራ አጋጣሚ የሚከሰት ችግር ካለም ርምጃ እንዲወስዱ እና እንዲያርሙ በማድረግ በተናበበ መልኩ እየተሰራ ነው።
ህብረተሰቡም በአዲስ አበባ የተደረገውን የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ በሚዲያ በተመለከተ ጊዜ ልማቱ በሀዋሳም እንዲከናወነ ሲጠይቅ መቆየቱን አስታውሰው፣ የኮሪደር ልማቱ በሀዋሳ ከተጀመረ በኋላም በቁሳቁስ፣ በገንዘብ ለመደገፍ እንዲሁም ከከተማዋ ከንቲባ ጋር የከተማዋ የልማት ምክር ቤት እስከ ማቋቋም ድጋፍ አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል:: የከተማዋ ነዋሪ ከመንግሥት በጀት በተጨማሪ በገንዘቡ፣ በእውቀቱ፣ በቁሳቁሱ ጭምር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከከተማዋ የኮሪደር ልማት በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ እንዳለም ጠቅሰው፣ 24 ሰዓት ሲሰራ የቆየው ከማምቦ የትራፊክ ማሳለጫ እሰከ ሪፈራል ሆስፒታል ድረስ ያለው ሥራ በእቅዱ መሠረት እየተከናወነ መሆኑን ኢንጂነር ምህረቱ አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የኮሪደር ልማቱ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች አሉት። የመንገዶች መስፋት የትራንስፖርት አቅርቦት እንዲጨምር ያደርጋል። የትራፊክ መጨናነቅን በመቀነስ ለመጓጓዝ የሚፈጀውን ጊዜ ይቀንሳል። ይህ መሆኑ ኢኮኖሚውን የማንቀሳቀስ እድሎችን ይዞ ይመጣል።
ሰዎች በቀላሉ በእግራቸው እንዲንቀሳቀሱ፣ ብስክሌት እንዲጠቀሙ ያስችላል። በከተማዋ ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ላይም የራሱ አዎንታዊ አስተዋፅኦ አለው። የከተማዋን የንግድ አካባቢዎች ለምሳሌ ፒያሳ፣ አቶቴ፣ የአሮጌ መናኸሪያ አካባቢ እና በተመሳሳይ የሚታወቁ የኢኮኖሚ እና የንግድ አካባቢዎች አሉ። ኮሪደሩ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፉ የራሱ ፋይዳ ይኖረዋል:: በከተማዋ መሠረተ ልማት ሲማሏ ማዘጋጃ ቤቱም ከአገልግሎት እና ከግብር የሚያገኘው ገቢ ያድጋል። ተጨማሪ መሠረተ ልማቶች ባልተዳረሱባቸው አካባቢዎች ላይ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ እድል ይፈጥራል:: የኮሪደር ልማቱ ለቱሪዝም ዘርፍ፣ ለከተማዋም ሆነ ለነዋሪው በአጠቃላይ ለኢኮኖሚው በጎ ትሩፋት አለው።
የሀዋሳ ከተማ የአረንጓዴ ስፍራ ልማትን በተመለከተም ኢንጂነሩ ሲያስረዱ፤ በኢትዮጵያ የከተሞች ደረጃ 30 በመቶ አረንጓዴ፤ 30 በመቶ መንገድ እንዲሁም 40 በመቶ በቤቶች የተሸፈን መሆን አለበት። አሁን ባለው ደረጃ መሠረት በከተማዋ ሰፋፊ የአረንጓዴ ስፍራዎች ሽፋን 27 በመቶ ላይ ደርሷል ሲሉ አስታውቀዋል።
የኮሪደር ልማቱ እንዳለ ሆኖ የሀዋሳ ሀይቅ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ለማልማት ዲዛይን ተከልሶ የማስተካከል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ይገልጻሉ። ይህ እውን ሲሆንም ከከተማዋ ወደ ሀይቅ የሚሄደው ጎርፍ ንጹህ ሆኖ እንዲገባ ማድረግ የሚያስችሉ የዲዛይን ሥራዎች ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር መዘጋጀቱን ጠቁመው፣ የግንባታ ሥራው ብቻ መቅረቱን አመላክተዋል።
የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በበኩላቸው በሀዋሳ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ይቀይራል። የመንገድ ማስዋብ ሥራዎች፣ የሳይክል እና የእግረኛ መንገዶችን የለየ እና አካል ጉዳተኞችን ከግምት ባስገባ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ ግንባታው ሲጠናቀቅ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት እንደሚያጎናጽፋት አስታውቀዋል።
በከተማዋ በኮሪደር ልማት በማስፋፊያ አካባቢ እና በመሀል ከተማ የሚከናወኑ በሚል ሦስት መሠረታዊ መንገዶችን ያካተቱ ሥራዎች እንደሚሰሩ ይገልጻሉ:: ሥራው 34 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና አስር ትልልቅ መንገዶችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰው፣ በግንባታው የመጀመሪያ ዙር ለ813 ተነሺዎች ካሣ ከፍሎ የማንሳት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመላክተዋል።
በመሀል ከተማ የሚሠሩት ሰባት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ሶስት መሠረታዊ መንገዶች በቅድሚያ ተለይተው የመንገዶቹን ደረጃ የማሻሻል ሥራዎች ይከናወናሉ። ከዲኤምሲ እስከ ሀዋሳ ሴራሚክስ ፋብሪካ ያለው የመንገድ ልማት በአካባቢው ባሉ ተቋማት እንደሚለማ አመላክተው፣ ተቋማቱ መንገዱን ለማልማት በግምት እስከ አንድ ቢሊየን ብር ወጪ እንደሚያደርጉ አቶ መኩሪያ አስታውቀዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም