ቦንዳ ከፍርሃት ወደ ኩራት

ቦንዳ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የማውቀው ልጅ እያለሁ በአካባቢያችን ልብስ የሚሰፉ ሰዎች የሚሸጡት ብትን ጨርቅ ነበር:: ልብስ የሚያሰፉ ሰዎች ተለክተው ከብትን ጨርቁ የመረጡትን አይነትና ቀለም አዝዘው ይሄዳሉ:: ይሄው ብትን ጨርቅ የጣውላ ቅርጽ ባላት ስስ መጠቅለያ ተጠቅልሎ ገበያ ላይ ይሸጣል:: የሚሸጡትም በብዛት በልብስ ስፌት ሥራ ላይ ያሉ ሰዎች ናቸው:: ወንድሜ ከእነዚህ አንዱ ስለነበር የብትን ጨርቁ መጠቅለያዋን ስስ ጣውላ በእርሳስ እየጻፍኩ እለማመድባት ነበር:: ይህ የተጠቀለለ ብትን ጨርቅ ቦንዳ ይባል ነበር::

ከዓመታት በኋላ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም ሆነ በዙሪያዬ ባሉ ሰዎች ‹‹ቦንዳ›› ሲባል መስማት ጀመርኩ:: ደግሞ ከተማ ቦታ ቦንዳ ምን ይሠራል? እያልኩ ብዙም ትኩረት ሳልሰጠው ቆየ:: በኋላ ነገሩን ስረዳ ቦንዳ ማለት ለካ የሰልባጅ ስም ተሽሞንሙኖ ማለት ነው:: እዚች ላይ አንድ የአካባቢያችን ገበሬ ከተማ ቦታ ሄዶ የተናገራትን አስቂኝ ገጠመኝ ላካፍላችሁ:: ያደረ እንጀራ (ደረቅ ማለት የጀመረ ማለት ነው) ጠዋት በድስት ቁሌት ነገር ተሠርቶ ይፈተፈታል:: ይህም በአካባቢያችን ግፍልፍል ተብሎ ይጠራል:: በሥራ ተወጥረው ወይም በሆነ አጋጣሚ ምግብ ማዘጋጀት የማይቻል ሲሆን ለመቆያ ተብሎ የሚደረግ ስለሆነ ብዙም ተመራጭ አይደለም:: እንዲያውም ሙያ የሌላትን ሴት ሲሳደቡ ‹‹ይቺ ግፍልፍላም!›› ይባላል::

እና ይህ የአካባቢያችን ገበሬ ከተማ ቦታ ይሄድና ምግብ ቤት ይገባል:: ምን ምን እንዳለ ሲጠይቅ ‹‹ፍርፍር›› የሚል ቃል ይሰማል:: የሆነ የተለየ ነገር መስሎት ፍርፍር አዘዘ:: ተሠርቶ መጣ፡፤ ሲያየው ያው ከቤቱ የሚያውቀው ነው:: ‹‹አይ! ግፍልፍል ስምሽን ቀይረሽ መጣሽ?›› አለ እየተባለ ሲቀለድ እሰማ ነበር::

ቦንዳ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ስሰማ ልክ እንደ ገበሬው ‹‹ሰልባጅ ስምሽን ቀይረሽ መጣሽ?›› የሚለው ነው ትዝ አለኝ:: ሰልባጅ ማለት ከዚህ በፊት የተለበሰ እና ታጥቦ የሚሸጥ ማለት ነው:: ይህ ቃል ከመለመዱ የተነሳ ለስድብነት ሁሉ ያገለግል ነበር:: የአለቃ ዕቃ ማለት ነው:: የማይረባ፣ በቀላሉ የሚበላሽ ማለት ነው::

ቦንዳ ግን ትንሽ ለየት የሚያደርገው ነገር አለ:: በአጭሩ ቦንዳ ማለት ብራንድ ልብስ ሆኖ በሀብታም ሃገራት የተለበሰ ማለት ነው:: በሀብታም ሀገራት ተለብሶ ወደ ድሃ ሃገራት የሚሸጥ ማለት ነው:: ለባሾቹ ድሃ ስላልሆኑ ምናልባትም ከአንድና ሁለት ቀን፣ ቢበዛ ከሳምንት ዕድሜ በላይ አይለብሱትም ተብሎ ይገመታል:: ያው ይገመታል ነው እንግዲህ!

ይህ የቦንዳ ልብስ ከዓመታት በፊት በድብቅ የሚሸጥ ነበር:: በድብቅ ማለት ሻጮቹ ቦንዳ መሆኑን ሳይናገሩ ማለት ነው:: ገዥዎቹም ቦንዳ መግዛታቸውን ሳይናገሩ ማለት ነው:: ከአንድ ዓመት በፊት ራሱ ቦንዳ እንዲህ እንደዛሬው በኩራት የሚሸጥ አልነበረም:: ‹‹ከቦንዳ ገዝቼ፣ ከቦንዳ ልግዛ›› የሚባልም አልነበረም:: ገዥዎችም ቦንዳ ቤት ሲገቡ ተደብቀውና ግራ ቀኙን አይተው ነው እየተባለ በማኅበራዊ ገጾች ይቀለድ ነበር:: ቦንዳ መልበስ ያስፈራ ነበር፤ ትንሽ እንደማሳፈር ይል ነበር::

ዛሬስ? ዛሬማ ‹‹ቦንዳ›› የሚለው ቃል በትልቅ ባነር በኩራት የሚለጠፍ ነው:: ገዥዎችም ጥንድ ጥንድ ሆነው (ፍቅረኛሞችም ሊሆኑ ይችላሉ) ሲለኩና ሲመርጡ እናያለን:: ቦንዳ ቤቶች ከመደበኞቹ ልብስ ቤቶች በላይ በወረፋ ተጥለቅልቀው ይታያሉ:: ሰው ብልጥ የሆነ ይመስላል፤ በእርግጥ ኑሮ አስገድዶት ነው:: ዋጋውን እንጂ የግል ክብር በሚባለው ነገር መንጠራራት እየቀረ ነው::

ኧረ እንዲያውም አሁን አሁን በተቃራኒው እየሆነ ነው:: ቦንዳ በሀብታም ሃገራት ያሉ ዜጎች የለበሱት ነው ተብሎ ስለሚታሰብ የተሻለ አድርጎ የማየት አመለካከት እየሰረጸ ነው:: ቦንዳ መልበስ ያሳፍር የነበረው ቀርቶ የሚያኮራ ሊሆን ነው:: ‹‹ቦንዳም!›› ብሎ ከመሳደብ ወደ ‹‹ዋው! ቦንዳ ነው እኮ የገዛ›› አድናቆት ልንሄድ ነው ማለት ነው::

እዚህ ላይ ግን አንድ ትልቅ ሐሜት አለ:: መደበኛዎቹ ልብስ ቤቶች ከቦንዳ እየገዙ ይሸጣሉ ይባላል:: በእርግጥ ብልጥ ለሆነ ሰው የሚለይበት ዘዴ ይኖረዋል:: ሆኖም ግን ብዙ ሰው ያጭበረብሩበታል:: በመደበኛ ልብስ ቤት ዋጋ ሰልባጅ ይሸጣሉ ማለት ነው:: እንዲያ ከሆነ ደግሞ ከራሱ ከቦንዳ ቤቱ መግዛት ይሻላል ማለት ነው:: ይህ አሠራር ገበያቸውን ይዘጋባቸዋል:: እንዲያውም ከወራት በፊት በወጣ መረጃ በቦንዳ ምክንያት መደበኛዎቹ ልብስ ቤቶች እየከሰሩ እንደሆነ መነገሩን እናስታውሳለን::

ሌላው ችግር ደግሞ ከሃገር ውስጥ ልብስ ይልቅ ቦንዳ መመረጡ ነው:: ‹‹ቦንዳ ቤት›› ብለው በሚሸጡ ቤቶች ውስጥ ያለው ክርክር ‹‹የምር ግን ቦንዳ ነው?›› የሚል ነው:: ከሃገር ውስጥ ዋና (አዲስ) ይልቅ ቦንዳው የተሻለ ተደርጎ ይታሰባል ማለት ነው:: የዚህ ችግሩ ግን የአመለካከት ብቻ አይደለም፤ የምርም ቦንዳው (ሰልባጅ ማለት እኮ ነው!) የተሻለ ጥንካሬም ሆነ ጥራት ስለኖረው ነው:: በዚያ ላይ አመለካከታችንም ቀላል ሚና የለውም:: ምንም ቢሆን ፈረንጅ የሠራው ይሻላል የሚል አመለካከት የሰረፀብን ነን:: የሃገር ውስጥ ምርቶቻችን ግን ይህ ሊቆጫቸው ይገባል፤ መንግሥትም ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ ይገባል::

መደበኞቹ ልብስ ቤቶች ላይ ግን ቁጥጥርና ክትትል መደረግ አለበት:: በመደበኛ ልብስ ዋጋ የቦንዳ ልብስ ሊሸጡ አይገባም:: ይህ ማለት ብዙዎች ያደርጋሉ ማለት አይደለም:: ትልልቅ የገበያ አዳራሾች (ሞል) ይህን ላያደርጉ ይችላሉ:: ዳሩ ግን ብዙ ሰው ደግሞ ከእነርሱ የመግዛት አቅም አይኖረውም:: የቀበቶ ዋጋቸው ብቻ እኮ ከመደበኛ ልብስ ቤት ሦስት ሱሪ ሊገዛ ይችላል:: ስለዚህ ከእነርሱ በታች ያሉት መደበኛዎቹ ልብስ ቤቶች እርስ በእርሳቸው ሊገማገሙ ይገባል:: ምክንያቱም አንዱ የሚሠራው ስህተት የብዙዎችን ገበያ ያበላሻል::

‹‹ለመሆኑ ግን ቦንዳ ለምን ተስፋፋ? ሰዎችስ ለምን መረጡት?›› የሚለውን ግን እንደ መንግሥትም እንደ ግለሰብም ሊያሳስበን ይገባል:: ኑሮ ውድነት ነው:: ሰዎች በውድ ዋጋ ‹‹ኦርጂናል›› ነገር መግዛት ስላልቻሉ ነው:: በሃገራቸው ምርት ቢኮሩም በሚቀንስ ዋጋ የተሻለ ጥራት ያለው ነገር ይሻለናል ብለው በማመን ነው::

ሁለት ነገሮች ግን ልብ ይባሉ:: መደበኛዎቹ ልብስ ቤቶች ቦንዳ እንዳይቀላቅሉ ክትትል ሊደረግ ይገባል፤ የሃገር ውስጥ አልባሳት ላይ መንግሥት ትኩረት አድርጎ ተፈላጊ እንዲሆኑ ይደረግ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You