
ሃዋሳ፦ በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 360 ሺህ ሕዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የሲዳማ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ። የክልሉ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን 60 በመቶ መድረሱም ተነግሯል፡፡
የሲዳማ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ከበደ ጋኖሌ (ኢንጅነር) እንደገለጹት፤ በክልሉ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ብቻ 360 ሺህ ሕዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
ሲዳማ ክልል እንደክልል ሲቋቋም ንጹህ የመጠጥ ውሃ ሽፋኑ 38 ነጥብ 2 በመቶ እንደነበር የገለጹት ቢሮ ኃላፊው፤ ክልሉ እንደ ክልል ከተቋቋመ ወዲህ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ሽፋኑን በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ዘንድሮን ጨምሮ በአራት ዓመታት ውስጥ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ሽፋኑን ከ38 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 60 በመቶ አድጓል ብለዋል።
ከክልልነት በኋላ በተፈጠረው ምቹ አስተዳደራዊ መዋቅር በከፍተኛ ትኩረት ከተሠሩ መሠረተ ልማቶች ውስጥ አንደኛው ንጹህ የመጠጥ ውሃ የማስፋፋትና ተደራሽ የማድረግ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ በርካታ ተዋናዮች መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፤ እነዚህን አካላት በማቀናጀትና በማስተባበር ቅድሚያ ችግሩ በጥልቀት የሚስተዋልባቸው ቦታዎች ላይ የውሃ ፕሮጀክቶች በስፋት መሠራቱን አብራርተዋል።
875 መካከለኛ፣ አነስተኛ እና ጥቃቅን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ዘንድሮን ጨምሮ በአራት ዓመት ውስጥ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 38 አንኳር ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አመላክተዋል።
38ቱ ፕሮጀክቶች እያንዳንዳቸው ከ376 ሺህ እስከ 25 ሚሊዮን ብር ድረስ የግንባታ ወጪ የሚጠይቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በድምሩ የ38ቱ ፕሮጀክቶች የግንባታ ውል ሁለት ቢሊዮን ብር መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ግንባታውን ለሚያከናውኑ ተቋራጮች የተከፈለ ሲሆን፤ ቀሪው ፕሮጀክቶቹ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቁ ድረስ ይፈጸማል ብለዋል።
ከ38ቱ አንኳር ፕሮጀክቶች ውስጥ 28ቱ ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ኃላፊው ገልጸው፤ እነዚህ አንኳርና ሌሎች ጥቃቅን ፕሮጀክቶች በከፊልና ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት በመስጠታቸው 650 ሺህ 840 የማህበረሰብ ክፍል ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ክልል እንደ ክልል ከተዋቀረ በኋላ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሕዝብ ቁጥሩን ወደ ሦስት ሚሊዮን ገደማ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 /2016 ዓ.ም