
አዲስ አበባ፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጡን በቁንጽል ሳይሆን በምልዐት መመልከት ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የነበራቸውን መድረክ አስመልክቶ ትናንት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጡን በቁንጽል ሳይሆን በምልዐት መመልከት ይገባል። በመደመር ዕሳቤያችን ለሀገር ልማት ምን መደረግ እንዳለበት በጥልቀት መዝነን አስቀምጠናል ብለዋል።
ዓላማችን የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አካሄዳችን ድሃ ተኮር ነው። ትኩረታችን ለችግር በመጠቃት ተጋላጭ የሆኑ ደካሞችን መደገፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የለውጥ ሥራዎች ሁሉ ስኬት በባለድርሻ አካላት የተባበረ ጥረት ላይ እንደሚመሠረት ገልጸው፤ ይህም ምርታማነትን፣ የውጭ ንግድን እና ገቢን ተባብሮ ማሳደግ ማለት ነው ብለዋል።
የሕግ አስፈጻሚ አካላት የለውጥ ሥራውን ባልተገባ ሕገ ወጥ መንገድ ለመጠቀም በሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ እንዲወስዱ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሀምሌ 26 /2016 ዓ.ም